የኢትዮጵያ መንግሥት በጎረቤት ሃገራት ያሉ ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ቤት አላስመጣሁም ሲል አስተባበለ

ሂውማን ራይትስ ዋችየተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ኬንያ ባሉ ጎረቤት ሃገራት ተጠልለው የሚገኙ ስደተኛ ዜጎቹን የዓለም አቀፉን ሕግ በመጣስ ወደ ሀገር ቤት አስመጥቷል ሲል ይወቅሳል።

ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኛ ዜጎቹን ወደ ሀገር ቤት በማስመጣት አሰቃይቷል ሲልም ይከሳል።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ በኬንያ ተጠልሎ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ ለቢቢሲ እንደተናገረው የኢትዮጵያ መንግሥት የደህንነት ሰዎች ባለፈው ሰኔ አፍነው ሊወስዱት እንደሞከሩ ይናገራል።

ከስምንት ዓመት በፊት በፖለቲካ አቋሙና በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነቱ እንደታሰረ እና እንደተሰቃየም ይናገራል። በኬንያ ቆይታው ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ሙከራዎች ተደርገውበት እንዳመለጠ ገልጿል።

በሬስቶራንት አስተዳዳሪነት እየሰራሁ ሳለ አንድ የኬንያ ፖሊስ ከኢትዮጵያዊ የደህንነት ሰው ጋር በመሆን ሊይዙኝ ሞከሩ። ምን እየተካሄደ እንዳለ ሊገባኝ አልቻለም። ሰውን ለማሰር ስትመጣ ምክንያት ሊኖርህ ይገባልሲል ያጋጠመውን ይተርካል።

እኛ ኬንያ መጥተን የተጠለልነው የኬንያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ሕግን አክብሮ እንዲጠብቀን ነው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ቡድን ሂውማን ራይትስ ዋችመሰል ኢትዮጵያውንን ከተጠለሉበት አፍኖ ለመውሰድ የተካሄዱ ድርጊቶች መኖራቸውን ይጠቅሳል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነው እንግሊዛዊው አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን እና አሁን በእስር ላይ እንደሚገኝ ቡድኑ አስታውሷል።

ንዳርጋቸው ጽጌ

ባለፈው ወርም የሶማሊያ መንግሥት አንድ ግለሰብን ለኢትዮጵያ አሳልፎ መሰጠቱ ይታወሳል። ሌሎችም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ እንደተደረገ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኛ ዜጎችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ቤት አላመጣሁምሲል እያስተባበለ ይገኛል።

እኛ ማንንም ወደ ኬንያ ወይም ከኬንያ ወደ ሃገር ቤት የመውሰድ እና የማምጣት ተግባር ላይ አይደለንምይላሉ፤ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ። አጠቃላይ ውንጀላው ልብወለድ ነውሲሉም ያስተባብላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት መሰል ወቀሳዎች እና ክሶች ሲቀርቡበት ይህ የመጀምሪያው አይደለም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ስደተኛ ዜጎችን ከሌላ ሃገር ማስመጣት የዓለም አቀፉን የስደተኞች ሕግ መጣስ ነው ሲሉ ይከሳሉ።