September 28, 2017

እስራኤል ዳንሳ የሚባል በተለምዶ አጠራር ‹ጴንጤ› በሚል ስያሜ ከሚታወቁ ወገኖች አንዱ የሆነና በፓስተርነት የሚያገለግል አባይ ጠንቋይ አለ – እርሱ ብቻም ሳይሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሥራ ፈት ወጣት ፓስተሮች የሳተላይት ቴሌቪዥን መስኮቶችን በፉክክር በሚመስል አኳኋን  በየቀኑ በማጨናነቅ ላይ ናቸው፡፡  እነዚህ የዲያብሎስ ቡችሎች ክርስትና እንዲያስጠላ እያደረጉ ናቸው፡፡ ከአለባበስና ከፀጉር አቆራረጥ ጀምሮ የለየላቸው ዱርዬ የሚመስሉት እነዚህ ወሮበሎች ሕዝቡን መድረሻ እያሳጡት ይገኛሉ፤ የመምሬ እንደሻውን የአቡነ ሐጎስን ገመና የተረዳ ምዕመን የተሸለ ነገር ይገጥመኛል በሚል ተስፋ ወደነዚህ የአጋንንት ልጆች እየነጎደ መከራውን ይበላል – ግን ሁሉም የጨለማው ንጉሥ ደቀ መዛሙርት ስለሆኑ ዝውውሩ ከጨለማ ቁጥር አንድ ወደ ጨለማ ቁጥር ሁለት የመገለባበጥ ያህል ነው፡፡ እንደመረገም ሆኖ  ይህ ዘመን የማያሳየን የጠንቋይና የአበጋር ዓይነት የለም፡፡  ዘመኑ የጭንቅና የጥበት እንደመሆኑ ሥራ ያጣ ቀጣፊና ወለፈንዴ ሁሉ በነዚህ ብዙም ባልተበላባቸው የጥንቆላና የፓስተርነት ‹የሙያ መስኮች› እየገባ ሕዝብን መንጨትና ትዳሩን ማስፈታት ሥራየ ብሎ ተያይዞታል፡፡ ለአብነት ያህል በኛ ሠፈር አንዱ ፓስተር ሰሞኑን አንድ ትዳር በትኗል፡፡ ሚስትን ከባሏ ቀምቶ ልጆችን ሜዳ አስጥሎ ይሄውና ቤታቸውን አፈረሰው – እግዜር ይይለት፤ ይህ ደግሞ የብዙዎቹ የፕሮቴስታንት ፓስተሮችና የኦርቶዶክስ ቀሳውስት የየለት ተግባር ነው – ለምን ይዋሻል? ዱሮም ከአጋንንት “ቤተ ክርስቲያን” ከዚህ በላይ አይጠበቅም፡፡ የነዚህ አጋንንት ፖስተሮች ማለትም ፓስተሮች ዕኩይ ተግባር በቴሌቪዥን የውሸት የፈውስ ቅንብር – በሰለጠኑና በሚከፈላቸው ተፈዋሾችና ፈዋሾች ትርዒት – እየታገዘ ብዙውን ሕዝብ ገደል እየከተተው ነው፤ ሰውን ምን እንደነካው አይገባኝም በተራ ቁጭ በሉዎች በቀላሉ ሲታለል ይታያል፡፡ ብንጮህ ብንጮህ ደግሞ  የሚሰማን አጣን፡፡ ሰይጣን አደግድጎ እየጠበቃቸው በመሆኑ ከነዚህ ጉዶች አደገኛና አጥፊ አካሄድ የሚድን ሰው በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በየመንደሩ “ቸርች” እንደኪዮስክና እንደጉሊት እየከፈቱ በባዶ ጩኸት ሀገር ምድሩን እያናጉት ናቸው፡፡ ተረቱ “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ” ነውና ማንም ቢሆን ወደነዚህ የአደንዛዦች መንደር ወዶ ከገባ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ምድረ ፓስተር ነኝ ባይ አዳሜን እያጭበረበረ ምድራዊ ሰይጣናዊ እንጀራውን በመጋገር ላይ ይገኛል፤ ወያኔን ምሥጋን ይንሳውና በቁሟ የጠፋችው የኦርቶዶክስ ሃይማኖትም በዲያቢሎሶች ተወርራ ፓትርያርኩም፣ ጳጳሱም፣ ካህናቱም፣ ደባትሩም፣ ዲያቆናቱም በአብዛኛው የአጋንንት መፈንጫ በመሆናቸው ሕዝቡ አንድ ባንድ በተኩላ እየተመነተፈ ቤተ ክርስቲያኗ ራቁቷን በመቅረት ላይ ነች፡፡ እግዚአብሔርም እንደፍጥርጥራችሁ ብሎ ሳይተወን አይቀርም ቤተ ክርስቲያን በዘረኝነትና በምንፍቅና እንዲሁም በሰይጣናዊ ኃጢኣቶች ስትበክት የመታደግ ሥራውን እርግፍ አድርጎ ትቶታል፡፡ ሁኔታዎችን በትኩረት ስንታዘብ ከዚህ በላይ የመጨረሻ ዘመን ሊኖር አይችልም፡፡ ይሄን በአነጋገሩ ከተራ ዱርዬም ያነሰ እስራኤል የሚባል ፓስተር ተብዬ በቲቪ እንዳየሁት ማይም ቢጤ ነው – (በእንጀራው ገብቼ እንዲህ የምተቸውን ሰው ለአባቱ ለዲያብሎስ ማሳጣትና አንዳች ነገር እንዲደርስብኝ ማድረግ ከፈለገ ይችላል፡፡ በርሱ ውስጥ መንፈስ ካለ የሰይጣን እንጂ የክርስቶስ እንደማይሆን አንድ ሺህ በመቶ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የሚገርመኝ ይልቁንስ በዚህ መናኛ ሰው የሚጃጃለው ሰው ብዛት ነው፡፡) ይህን መሰሉ ማይም ዱርዬ ብዙ የተማረ ኃይልን ሳይቀር እንደበግ እየነዳና በ “ቸርቹ” ውስጥ እያስለቀሰ ሲታይ “ምን ያለ ዘመን መጣብን?” በሚል እጅግ ማሳዘኑ አይቀርም፡፡ በመሠረቱ ማይም – ብዙው ማይም ማለት ይቻላል – ደፋር ነው፤ ማይምነት ሰውን ከዕውቀትና ከጥበብ ማዕድ በብዙ ማይሎች ያርቃል፡፡ ማይምነት የደደብነት አባትም ነው፡፡ ማይምነትና ድፍረት ከተገናኙ የሚፈሩት ነገር ስለማይኖር ትልቅ አደጋ ማስከተሉ አይቀርም – የሕወሓትን ሰዎች ለአብነት እዚህ ላይ መጥቀሱ ለዚህ አባባል ዋና አስረጅ ነው፡፡ ይሄ እስራኤል የሚባል የማይም ጨላጣ አራዳ የሚሠራውን ስታዩ ሀገር ላይ ምን ዓይነት መዓት እየወረደ እንደሚገኝ ይገባችኋል፡፡ እኔ ከልብ አዘንኩ፡፡ ያ ሁሉ ሰው ተሰብስቦ በዚህ ቁጭ በሉ ሲታለል ሕዝቡን የቀፈደደው አንዳች ነገር እንዳለ ገባኝ፡፡ ወዴት እየሄድን ይሆን ግን?ታምራት ገለታ የተባለ – አሁን በእስር ላይ የሚገኝ ይመስለኛል – የአራተኛ ክፍል ምሩቅ ማይም ሕዘበ ክርስቲያንን እንዴት ያጭበረብር እንደነበረ አስታውሳለሁ – ስንቱን አትሌት፣ ስንቱን አርቲስት፣ ስንቱን ድምፃዊ፣ ስንቱን ፖለቲከኛ፣ ስንቱን ኢንቬስተር ጉድ እንደሠራው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው – እሱን መሰሎች አሁንም በብዛት አሉ – ሕዝበ አዳምን እያታለሉ፡፡ በዚህን ዓይነት ትናንሽ ሰዎች የሚወናበድ ሕዝብ ይዘህ ወደየትኛው የሥልጣኔ ማማ እንደምትጓዝ አስበውና የሀገርህን የቁልቁለት መንገድ አስተውል፡፡ ወያኔ ሳያንሰን እነዚህን መሰል ማጅራት መቺዎች የተላኩብን በምን አበሳችን ይሆን? አንድ ሕዝብና አንዲት ሀገር ወደዚህ ዓይነት የለዬለት ምድራዊ እንጦርጦስ የሚወርዱትና ታሪክ የሚቆሽሸው ምን ሲሆን ነውእስኪ እንጠናና ጉዳችንን እንወቅ፡፡ በቁም ሞተናል እኮ!አንዲት ሴት ደግሞ  የትም የደቀለቻቸውን አምስት ልጆቿን ደርድራ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ወለድኳቸው” እያለች ሕዝብን ታታልል እንደነበረ በዚያን ቆየት ባለ ዘመን ሰምተናል፤ እርሷም በእስር ላይ የምትገኝ ይመስለኛል፡፡ በዚህ መንገድ ጥቂት ብጓዝ የሕዝባችንን የንቃት ደረጃ አሳሳቢነት እንዲሁም የአጭበርባሪዎችን ብዛትና ስኬታማ ጉዞ ማየት በቻልን፡፡ አብዛኛው በሚባል ደረጃ ሕዝቡ በተኩላዎችና በቀበሮዎች የማታለልና የማስመሰል ሸርና ተንኮል እየተወሰደ የዲያብሎስን ጎራ እያጨናነቀ ይገኛል፡፡ ምድረ ጠንቋይና ደብተራ ግቢው በሰው ይርመሰመሳል፡፡ አብያተ ክርስቲያን ደግሞ በሰው መሳይ በሸንጎ የሁለት ዓለማት ሰዎች በተለይ ጧት ጧት ይጨናነቃሉ፡፡ ጧት ነጫጭ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን፤ ማታ ፊትን ሸፋፍኖ ጠንቋይ ቤት የሚመላለሰው የሕዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ሀገረ ማርያም ኢትዮጵያ ጠፍታለች፡፡ ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ የወያኔና የአባቱ ዲያብሎስ መጫወቻ ሆናለች፡፡ ከዚህ በላይ እግዚኦ የሚያሰኝ ዘመንና ክፉ ዕጣ ደርሶብን አያውቅም፡፡ እግዚኦ እንበል፡፡ በነገራችን ላይ በሃይማኖቶች መለያየት ላይ አስተያየት እየሰጠሁ እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ “ጣፋጭ ፍሬ ከዛፉ ላይ ይታወቃል” እንዲሉ እየተቸሁ ያለሁት ሰዎቹ በሚያደርጉት ዕኩይ ተግባር እንጂ የሃይማኖቱ ግንድም በሉት ቅርንጫፍ ላይ እንዳልሆነ ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ ለጊዜው ያ የተነሳሁበት ጉዳይ አይደለም፡፡ የሚያድነውንና የሚያጠፋውን መንገድ ከአንድዬ በቀር የሚያውቀው አለመኖሩን ግን ከግርድፍ ሃይማኖታዊ ግንዛቤየ ተነስቼ ሳልጠቁም ማለፍን አልወደድኩም፡፡ ስለሆነም “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ” እንዳለችው ብልጥ ሴትዮ አጓጉል ነገር በመዘባረቅ ትዝብት ውስጥ መግባትን – ቢያንስ አሁን – አልፈልግም፡፡ አንተ ግን መልካም ሥራን ሥራ፣ ሰዎችን እንደራስህ ውደድ፣ ቂም በቀልን አስወግድ፣ የእውነተኛና የትክክለኛ ፍትህ ባለቤት ሁን … ሰውን በዘሩና በሀፍቱ ወይም በትምህርቱና በሌላ ሰው ሠራሽ ደረጃው ሣይሆን በሰውነቱ ብቻ አክብረው፤ ውደደውም፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ጤናማ የማኅበረሰብ አባል እንደሆንክ የምታምን ከሆነ የፈላስፋውን የኮንፊውሸስን አባባል ለመተግበር ሞክር – “ሰዎች ባንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን ነገር አንተም በነሱ ላይ አታድርግ፡፡” ለሚገባው ይህ ትልቅ የሕይወት መርኅ ነው፡፡ አዲስ የሕይወት ደቀ መዝሙር ከሆንክ ለጊዜው በነዚህ ጀምርና ለሌላው የመዳንና ያለመዳን የወዲያኛው ዓለም ጣጣ መንፈሣዊ ዐይንህ እንዲገለጥልህ ለምታምነው በርትተህ ጸልይ፡፡ መጽሐፉም እኮ “እሹ – ታገኛላችሁ” ነው የሚል፡፡ዓለምም የዚሁ በኛ የደረሰው ክፉ ዕጣ ተቋዳሽ ናት፡፡ ያልጠፋ ሀገርና ያልማሰነ የሃይማኖት ጎራ ለማግኘት ይቸግራል፡፡ ዛሬ ጠዋት አንድ ድረገጽ ሳነብ ደግሞ የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ከመሰመር እየወጡ እንደሆነና ከካርዲናሎቻቸውም ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው ሰማሁ፡፡ ይህ ፍራንሲስ የተባለ ሊቀ ጳጳስ የሚሾማቸው ጳጳሳት ግብረ ሰዶማዊነትን የሚደግፉና ኃጢኣትን እንደጽድቅ የሚቆጥሩ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ የዘመን ሙጣጭ ውስጥ ኦርቶዶክሱም፤ ካቶሊኩም፣ ሂንዱውም፣ ቡድሃውም፣ አይሁዱም፤ ሙስሊሙም … በከፍተኛ የጥፋት ማዕበል ውስጥ ሲናጡ የማየታችን ምሥጢር ከዘመናት በፊት የተነገረለት የዘመን ፍጻሜ መቃረቡን ብቻ ሳይሆን በራችንን እያንኳኳ መሆኑን ነው፤ ስንቶቻችን ይህ ነገር እንደገባን ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የብዙዎቻችን ልብ እንደ አለት እንደጠነከረ ነውና፡፡   የናቡከደነፆርና የፈርዖናውያን ልብ ድንጋይ እንደነበረ ሁሉ በአሁን ዘመንም ዓለማችን ውስጥ ዳግማዊያን ሶዶምና ገሞራ ተከስተው ባይናችን በብረቱ እያየን ልባችን ታውሯል፤ እናም በሰይጣናዊ የአሥረሽ ምቺው ደስታና ፈንጠዝያ ተጥበርብረን ወደ ዕልቂት እየተጣደፍን እንገኛለን፡፡ ሁሉም በየጓዳው ጠበንጃውን ሲወለውል፣ ጦሩን ሲሰብቅ፣ ጎራዴውን ሲስል ይስተዋላል፡፡ ጎበዝ አለ ነገር! ይህ ሁሉ የሚጠቁመን ታዲያ ዓለማችን ያበቃላት መሆኑን ነው – ከሩብ ሐሙስ ያነሰ ጊዜ ያላት ትመስላለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተተነበየው የመጨረሻው ዘመን ምልክት ሁሉ አንድ ባንድ እየታዬ በመሆኑ ጥቂት ቢሆኑም ሩቅ ተመልካቾች አይጠፉምና ዛሬ አልፋ ነገ እስክትመጣ በፍርሀት መጠባበቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ ክቡር አንባቢስ?

ለማንኛውም በዙሪያው በሚታይ መጥፎ ነገር ሳይወናበድና አቋሙን በሞተ እህል ውኃ ሳይለውጥ እስከመጨረሻው በአንድ አምላክ የጸና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወርሳል፡፡ ብዙ ሀተታ አያስፈልግም፡፡ ሁሉም አለቀ!!! የሚቀረው የመጨረሻው እምቢልታ ነው፡፡ ግን ከመጨረሻው መጨረሻ በፊት ኢትዮጵያ እንደምትድንና ዳግም እንደገና የዓለም መሪ እንደምትሆን ቀደም ሲል ተነግሯልና ያንንም የተስፋ ቃል በጉጉት እንጠብቃለን – “ማምሻም ዕድሜ ነው” ወንድሜ፡፡ የአሁኑ ግን አይነሣ! ለመጪው ትውልድ ምን ብለን እንደምናወራ ራሱ በጣም የሚጨንቅ ነው፡፡ ተያይዞ መጥፋት በስኬት የተከናወነበት ከሀገራችን ኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ሀገር የሚኖር አይመስለኝም፡፡

ሰውነት ቢያብጥ በምላጭ ይበጣል – ምላጭ ራሱ ቢያብጥስ በምን ይበጣል? እህል ቢያንቅ በውኃ ይዋጣል –  ውኃ ራሱ ቢያንቅስ በምን ይዋጣል? አያድርስ ነው ወገኖቼ፡፡ የነፍስን ድኅነት ሊያስገኝ የተሾመ የሃይማኖት አባት ዘረኝነትንና ፍቅረ ንዋይን ዋና ባሕርያቱ ላደረገ የሰይጣን መንፈስ እጅ ሰጥቶ ነፍስህን ቢያስነጥቅ፣ ሀገርህን ሊያሳድግና አንተን ሊያበለጽግ የተሾመ ወይም ሥልጣንን የተቆጣጠረ የፖለቲካ መሪ ሕዝቡን በዘርና በጎሣ እየከፋፈለ አንዱን የእንጀራ ልጅ ሌላውን የወለዱት ልጅ በማድረግ  የጎሣውን አባላት ቢጠቅም ሌሎችን ግን ቢጎዳና ቢያሰቃይ የማን ያለህ ይባላል? አንተ እናቴ የምትላትን ሀገርህን እንደዋና ጠላቱ ቆጥሮ ሲያጠፋትና ለባዕዳን ባወጣች ሲቸበችባት ስታይ፣ “ኢትዮጵያ” ብለህ በፍቅር መጥራትህን እንደወንጀል ቆጥሮ አንተኑ መልሶ ድባቅ የሚመታህ አስመሳይ ዜጋ ትልቁን የሥልጣንና የሀብት ቦታ በመቆጣጠር እውነተኛ ልጆችን ሲያሳድድና ሲገድል ቢገኝ ለማን አቤት ይባላል? አሁንም አያድርስ ነው፡፡ ማን ነበር – “ጉድ ነሽ ያንኮበር ቅጠል….” ያለው? ወይ ኢትዮጵያ!! ከቶ ስንቱን ነው የምታሳይን?

ምንጮች ፡ http://habeshacults.com/pages/tamerat.htmlhttp://shoebat.com/2017/09/25/major-division-not-seen-in-catholic-church-for-centuries-erupts-as-60-major-

catholic-cardinals-priests-bishops-and-laity-issue-declaration-of-heresy-to-pope-francis/