ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለ36 ቀናት ያህል ኢንተርኔትን (በይነመረብ) በዘጋችበት ጊዜ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጥታለች ሲል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የመረጃ ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ትብብር የተሰኘው ተቋም ገለፀ። የተቋሙ ጥናት የኢንተርኔን መዘጋት በሃገራት ምጣኔ ሐብት ላይ ያደረሰውን ጉዳት በተለያዩ መለኪያዎች የገመተ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ለ36 ቀናት ያህል ኢንተርኔትን በዘጋችበት እንዲሁም ለሰባት ቀናት ያህል በነበረው የማኅበራዊ ሚዲያ መናወጥ ወቅት በጥቅሉ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጥታለች ይላል።ኢንተርኔት በተዘጋበት እያንዳንዱ ቀን ከ3.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የመልክዕት ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች (አፕ) በታወኩበት አንድ ቀን ደግሞ ከ870 ሺህ ዶላር በላይ አገሪቷ ታጣለች ሲል ጥናቱ ይገምታል። ..አ ከ2015 ጀምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት በተለያየ ምክንያት ኢንተርኔትን መዝጋታቸው ንፍቀ አህጉሩን ከ237 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስጥቶቷል። ተቋሙ ባጠናቀረውና ይፋ በሆነ ጥናት እንደተመላከተው ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢንተርኔት ለቀናት እንዲዘጋ ባደረጉ የአፍሪካ ሃገራት የእርምጃው ምጣኔ ሐብታዊ ጠባሳ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ነው።

ጥናቱ ቢያንስ በአስራ ሁለት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ኢንተርኔትን የመዝጋት መንግሥታዊ እርምጃ መወሰዱን ያወሳ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አስሩን መርምሯል። እርምጃው በተለያዩ ምክንያቶች መነሻነት የተወሰደ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በብሔራዊ ፈተና ወቅት የፈተናን ሾልኮ መውጣት ለመከላከል በሚል ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ነበር። ቻድ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ኡጋንዳ ደግሞ ምርጫን አስታክከው ኢንተርኔትን የዘጉ ሃገራት ናቸው። ሕዝባዊ ፀረመንግሥት ተቃውሞዎች ለኢንተርኔት በመንግሥት መዘጋት ምክንያት ከሆኑባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ በድጋሚ የምትገኝ ሲሆን፤ ተመሳሳዩን እርምጃ የወሰዱ ሌሎች ሃገራት ብሩንዲ፣ መካከለኛው የአፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ካሜሩን፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ማሊ፣ ኒጀር እንዲሁም ቶጎ ናቸው። ካሜሩን እ..አ ከ2015 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ለ93 ቀናት ኢንተርኔትን ስትዘጋ ኢትዮጵያ ደግሞ ለ36 ቀናት ያህል ኢንተርኔን ዘግታለች።ኢንተርኔትን መዝጋት የመረጃ ተደራሽነትን እና የመናገር ነፃነትን በማወክ የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች ይጥሳል ያለው ተቋሙ፤ ቁርጥ ያለ መረጃ እንደልብ የማይገኝ መሆኑ የእርምጃውን ምጣኔ ሐብታዊ ዋጋ ማስላትን አዳጋች እንደሚያደርገው ያምናል።

ይሁንና የቱንም ያህል ለአጭር ቀናትም ቢሆን የኢንተርኔት መዘጋት የምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴዎችን ውጤታማነት ያስተጓጉላል፣ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያለ መተማመንን ይቀንሳል፣ እርምጃውን የወሰደችውን አገር የአደጋ ተጋላጭነቷ ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያስገምት ገፅታንም ይሰጣል።እንዲሁም የዜጎችን የዕለት ተዕለት አኗኗርን ያውካል ይላል ተቋሙ።ጥናቱን ያከናወነው የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የመረጃ ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ትብብር የተሰኘው ተቋም ልማትን እና ድህነት ቅነሳን ለማሳለጥ የመረጃ እና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን መጠቀም ላይ የሚሰራ ነው።

BBC