ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ

ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ ጥርት ያለ ህዝባዊና ብሄራዊ ዓላማ ይዞ የተመሰረተና እየታገለ ያለ ድርጅት ነው።አላማችን በአማራ ህዝብ ላይ የታወጀውን ሁሉን አቀፍ የእልቂት፣ የመከራና የግዞት አዋጅ በመቀልበስ የአማራን ህዝብ ከፈጽሞ ጥፋት ለማዳንና አንድነቷ በተጠበቀች ሀገር ውስጥ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በእኩልነት የሚኖርበትን ዘመን ለመፍጠር የህይወት መሰዋዕትነት እየከፈለ ነው። ይህን የተቀደሰ ዓላማችንን ደግሞ ለበቀልንበት ማህበረሰብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ አጽኖት ሰጥተን ስንገልጽ ቆይተናል።በዚህ አማራን እንደ ህዝብ ኢትዮጵያንም እንደ ሀገር ለማኖር በሚደረግ ትንቅንቅ ውስጥ በደማችን ፍሳሽ በአጥንታችን ክስካሽ ህዝባችንንና ሀገራችንን እንታደጋለን ያልን የአማራ ልጆች የመከራው ዘመን ያጥር ዘንድ ሌት ከቀን ከሞት ጋር ግብ ግብ ገጥመን እንገኛለን።

በወያኔ መቃብር ላይ በምትገነባዋ ኢትዮጵያ አማራው እንደ ህዝብ በነጻነትና በእኩልነት የሚኖሩበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ጥርጥር የለንም። ህዋሃትን ለማስወገድ እዚህም እዚያም የሚደረጉ ጥረቶችን እናውቃለን፣እናከብራለንም። ከህዋሃት በቀር የትኛውንም ድርጅት በጥላቻ የሚያይ ዓይን ለየትኛውም ድርጅት እንቅፋት የሚሆን ድርጅታዊ ባህል የለንም።እንደዚህ ዓይነቱን ተግባርም በጽኑ እንኮንናለን።ለምን ቢባል የጥሎ ማለፍ ፖለቲካ ባለፉት ሃምሳ አመታት ምን አይነት ዋጋ እንዳስከፈለና እያስከፈለ እንዳለ ጠንቅቀን ስለምናውቅ።ይሁንና ይህ በሽታ የተጣባቸው ግለሰቦችና በሽታው የሚታይባቸው አንዳንድ ድርጅቶች ትላንትና ከትላንት ወዲያ አዳልጦ በጣለን ጭቃ ውስጥ ከልብ ለመሮጥ ሲሞክሩ በማየት እየታዘብን ነው። ከእነዚህም ድርጅቶች ዋናው አርበኞች ግንቦት ሰባት ነው።

በእኛ በኩል አርበኞች ግንቦት ሰባት የሚባል ድርጅት ለምን ተፈጠረ ወይም ለምን በጸረ ወያኔ ትግሉ ውስጥ ኖረ አላልንም፤ ብለንም አናውቅም። ለድርጅቱ የተለየ ጥላቻም የለንም። የእኛ እምነት ይህ ሆኖ እያለ በአርበኞች ግንቦት ሰባት በኩል ግን በተለይ ከሰሞኑ የተጠናከረ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብናል። ከሰሞኑ በተካሄደው ጉባኤ ለመሳተፍ ከውጭ ሀገር ለመጡ የድርጅቱ አባላት በአዴሃን ላይ መጥፎ ስዕል እንዲኖራቸው ለማድርግ በዘዴ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲያደርጉ መሰንበታቸውን በማያሻማ ሁኔታ ለማወቅ ችለናል።

በእርግጥ አርበኞች ግንቦት ሰባት በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ ላይ እንድንገኝ ጥሪ ልኮልናል።ሆኖም ግን ድርጅታችን በእራሱ ምክንያት በጉባኤው ላይ መገኘት አልፈለገም ነበር። በዚህ መነሻ በእጅጉ የተበሳጩ የሚመሰሉት አርበኞች ግንቦት ሰባቶች አዴሃን የሚባል ድርጅት የለም ከማለት ጀምሮ ወዲያው ነበር የበቀል ጀራፋቸውን መግረፍ የጀመሩት።

የእኛን መኖር አለመኖር የሚያውቅ ስለሚያውቀውና ጊዜም የሚያረጋግጠው ስለሆነ ብዙም ትኩረት አልሰጠነውም ነበር።ማጠልሸቱ በዚህ ብቻ የቆመ እንዳልነበር ለማረጋገጥ ግን ሁለትና ሶስት ቀናት ብቻ መጠበቅ በቂ ነበር።
በቀጣይ ጉባኤውን ተካፍለውና የእኛን ስም ለማጠልሽት ግዳጅ ተቀብለው በተመለሱ አባሎቻቸው አማካኝነት በደንብ የታሰበበት የሚመስል የስም ማጥፋት ዘማቻ እንደተካሄደና እየተካሄደ ለመሆኑ በደንብ አረጋግጠናል።ስለሆነም ይህን ድርጅታዊ መግለጫ ለማውጣት ተገደናል።

ስለዚህ በድርጅታችን ላይ እየተካሄደ ያለውን የስም ማጥፋት ዘምቻና የስድብ ውርጅብኝ በአማራ ህዝብ ላይ የተካሄደና እየተካሄደ ያለ ማንቋሸሽ አድርገን ስለምንቆጥረው የዚህ ዘመቻ ጠንሳሾችና አስፈጻሚዎች እንዲሁም ፈጻሚዎች ይህን እኩይ ተግባራችሁን በአስቸኳይ እንድታቆሙ በአማራው ህዝብ ስም እንጠይቃለን። ይህ ሳይሆን ቢቀር ህዝባችንን፣ ትግላችንንና ድርጅታችንን የመጠበቅ ግዴታ ስላለብን በሁሉም ዘርፍ የእራሳችንን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን።

በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር የምትኖረው የአማራ ህዝብም እልቂት የተፈረደበትን ወግናችንን ለመከላክል በምናካሄደው መራራ ትግል ከጎናችን ትሰለፍ ዘንድ ጥሪያችንን እያስተላለፍን በአርበኞች ግንቦት ሰባት ውስጥ ያላችሁ የአማራ ልጆችም ትናንት ህወሃትን አዝለው በማስገባት ጸረ አማራ የጥፋት ዘመቻ እንዲታዎጅ እንዳደረጉት ወገኖቻችን ታሪክ ይቀር የማይለው ጥፋት እየደገማችሁት መሆኑን ልታውቁት ይገባል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ
መስከረም 19 ፣ 2010 ዓ.ም