ስዩም ተሾመ

ስዩም ተሾመ

በኦሮሚያና ሶማሊ ክልለ አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ የተከሰተው ግጭት እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው። በሰውና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው። እንደ ሀገር በወደፊት አብሮነታችን ላይ ትልቅ ጠባሳ የጣለ ክስተት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ በግጭቱ ምክንያት ከ50 እስከ 60 ሺህ ዜጎች መፈናቀላቸው ተዘግቧል። ከቀናት በፊት የፌደራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ የፌደራሉ መንግስት ገና የተፈናቃዮችን ቁጥር እያጣራ እንደሆነ ገልፀዋል።

እንዲህ ባለ ያልተጠበቀ ክስተት ዜጎች “ጨርቄን-ማቄን” ሳይሉ ሕይወታቸውን ለማትረፍ እንደሚሸሹ እሙን ነው።  ሃብትና ንብረታቸውን ጥለው የሸሹ ዜጎች ደግሞ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። ሰዎች ድጋፍ የሚያደርጉት በሰብዓዊነት፣ በዜግነት ወይም ደግሞ በብሔርተኝነት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም፣ ሁሉም ሰው እንደ ሰው ሰብዓዊነት ይሰማዋል፣ እንደ ዜጋ የዘግነት ግዴታ አለበት፣ እንደ ተወላጅ የብሔርተኝነት (ወገንተኝነት) ስሜት ይኖረዋል። ድጋፉን ማንም፥ በየትም፥ ከየትምና እንዴትም ያምጣው ተፈናቃዮቹ ግን ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
በሌላ በኩል ሁሉም የመንግስት አካላት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ማበረታታት እና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ለእንዲህ ባለ በጎ አድራጎት ሕዝቡን ማስተባበር እና በመልካም እሴቶቻችን ዙሪያ ማስተሳሰር እንደ ሀገር ወደፊት አብሮነታችንን (common future) ያጠናክረዋል። ስለዚህ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲደረግ ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና በማበረታታት የትብብርና አብሮነት ስሜት እንዲሰርፅ ማድረግ የመንግስት ድርሻና ኃላፊነት ነው።
ትላንት አመሻሹ ላይ በሞባይል ስልኬ “700 ላይ 0 በመላክ በ5 ብር ከኢትዮጲያ ሱማሌ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መልሰን እናቋቁም” የሚል የፅሁፍ መልዕክት ሲገባልኝ በጣም ደስ አለኝ። ዜሮን ፅፌ በተጠቀሰው አድራሽ የአምስት ብር ድጋፍ አደረኩኝ። ወዲያው ላደረኩት ድጋፍ በኦሮምኛና አማርኛ የተፃፈ ¨Deggarsa Keessaniif Galatoomaa ስለተደረገ እርዳታ እናመሰግናለን” የሚል የምስጋና መልዕክት ደረሰኝ። ነገር ግን፣ ማታ ወደ ሶስት ሰዓት አከባቢ “የተላከው መልዕክት ያልተሟላ በመሆኑ ይቅርታ እንጠይቃለን” የሚል መልዕክት ደረሰኝ። እንደገና ዜሮን ፅፌ ከላይ በተጠቀሰው አድራሽ የአምስት ብር ድጋፍ አደረኩኝ።

በእርግጥ የአምስት ብር ድጋፍ ማድረግ ከቁብ የሚቆጠር ላይሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ለፅኁፌ አንባቢዎች በተጠቀሰው አድረሻ የአምስት ብር ድጋፍ እንዲያደርጉ በፈጠርኩት መነሳሳት በግማሽ ቀን ውስጥ ብቻ 158 ወዳጆቼ በድምሩ የ790 ብር ድጋፍ አበርክተዋል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ግልፅ ነው። ይሁን እንጂ፣ ዛሬ ጠዋት ወደ 994 የጥሪ ማዕከል በመደወል በትላንትናው ዕለት ከ700 የመልዕክት አድራሻ “የተላከው መልዕክት ያልተሟላ በመሆኑ ይቅርታ እንጠይቃለን” የሚል መልዕክት እንደመጣልኝ በመግለፅ ማብራሪያ ጠይቄ ነበር።

የኦሮሚያ-ሶማሊ ግጭት ተፈናቃዮች

ከማዕከሉ ሰራተኛ የተሰጠኝ ምላሽ “በ700 ላይ የተጀመረው የድጋፍ ማሰባሰቢያ የተሳሳተ ነው” የሚል ፍፁም አስገራሚና ያልተጠበቀ ነበር። ዳግም ወደ 994 በመደወል ምክንያቱን ለማጣራት ስሞክር መልዕክቱ ለሙከራ የተላከ መሆኑን በመጥቀስ የተቆረጠብኝ ሂሳብ ተመላሽ እንደሚደረግ ተገለፀልኝ።  በመጨረሻ ዛሬ አመሻሹ ላይ ከ994 “ውድ ደንበኛችን 10ብር ተመላሽ ተደርጎሎታል” በሚል መልዕክት ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ያደረኩት ድጋፍ ተመላሽ ተደርጓል። በተጠቀሰው የድጋፍ ማሰባሰቢያ አድራሻ ድጋፍ ላደረጉ የኢትዮቴሌኮም ደምበኞች በሙሉ ያደረጉት ድጋፍ በተመሳሳይ ተመላሽ ተድርጓል። ለምን?

የጥሪ ማዕከሉ ሰራተኛ እንዳለችው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መልዕክቱ “ለሙከራ” የተላከ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም፣ አንደኛ እንደ ኢትዮቴሌኮም ያለ የመንግስት ተቋም ከደንበኞቹ ላይ አምስት ብር በመሰብሰብ ሙከራ የሚያደርግበት አግባብ የለም። ሁለተኛ ከዚህ ቀደም በቆሼ የቆሻሻ መናድ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በተመሳሳይ የመልዕክት አድራሻ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል። ከዚሁ ጋር ብዙ የኢትዮቴሌኮም ደንበኞች በ700 የመልዕክት አድራሻ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ የቆሼ አደጋ በደረሰበት ወቅት ያደረጉት ድጋፍ ለተጎጂዎቹ አለመድረሱን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲገልፁ ተስተውለዋል። ይህም በ700 የድጋፍ ማሰባሰቢያ ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሰራር መኖሩን ይጠቁማል።

በ700 የድጋፍ ማሰባሰቢያ የተላከው መልዕክት “የተሳሳተ” ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም፣ በተላከው የፅሁፍ መልዕክት የድጋፉ ዓላማና ግብ በአግባቡ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ድጋፍ ለሚያደርጉት የኢትዮቴሌኮም ደንበኞች በአማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎች በአግባቡ ተዘጋጅቷል። በዚህ መልኩ ዓላማና ግብ ተቀምጦለት በዕቅድ የተሰራ ስራን “ስህተት ነው” ሊባል አይችልም። በስህተት የተፈፀመ ከሆነም ድርጊቱን የፈፀመው አካል በይፋ መታወቅና መጠየቅ ይኖርበታል። ድርጊቱ የተሳሳተ መልዕክት መላክ ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የድርጅቱ ደንበኞች የተሳሳተ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መልዕክት በመላክ ያለ አግባብ (ለግል ጥቅሙ) ከሕዝብ ገንዘብ በመሰብሰብ ሊጠየቅ ይገባል።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮቴሌኮም አመራርና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በ700 የመልዕክት አድራሻ እየተፈፀመ ያለውን “ሕገ-ወጥ” ተግባር ተከታትለው ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። የድርጅቱና የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ለሕዝቡ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም፣ በህዝብ ላይ ወንጀል ተፈፅመዋል።

አንደኛ፡- በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ የኢትዮቴሌኮም ደንበኞች “700 ላይ 0 በመላክ በ5 ብር ከኢትዮጲያ ሱማሌ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መልሰን እናቋቁም” በሚል የተላከው መልዕክት “ስህተት ነው” የሚባል ከሆነ የተሳሳተ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መልዕክት በመላክ ያለ አግባብ ገንዘብ የመሰብሰብ ሙከራ በማድረግ በሕዝብ ላይ ወንጀል ተፈፅሟል። ሁለተኛ፡- መልዕክቱ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እውቅና ተሰጥቶት የተላከና በኢትዮቴሌኮም ወይም በሌላ አካል ያለ አግባብ እንዲቆም ከተደረገ ደግሞ ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ 60 ሺህ ዜጎች ከወገኖቻቸው ድጋፍ እንዳያገኙ እንቅፋት በመሆን በሕዝብ ላይ ወንጀል ተፈፅሟል። ከዚህ በተጨማሪ፣ መላው የኢትዮጲያ ሕዝብ ለተፈናቃዮች ድጋፍ በማደረግ ወገንተኝነቱን እንዳያሳይ እንቅፋት ሆኗል። በዚህም ይህ የመንግስት አካል ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲደረግ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠርና ማበረታታት ይልቅ እንቅፍት በመሆን ድርሻና ኃላፊነቱን ሳይወጣ ቀርቷል። በአጠቃላይ “በ700 የድጋፍ ማሰባሰቢያ” አማካኝነት በሕዝብ ላይ ወንጀል ተፈፅሟል!