በኦሞ ኩራዝ 5 ፕሮጀክት ላይ 12.1 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ ኃላፊዎችና ደላሎች ተከሰሱ

(ታምሩ ጽጌ – ሪፖርተር ጋዜጣ)

በብድር ከተገኘ 10.1 ቢሊዮን ብር ላይ 15.9 ሚሊዮን ብር ኮሚሽን መከፈሉ ተገልጿል

የኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክትን በጨረታ አወዳድሮ መስጠት ሲገባቸው፣ በሕገወጥ መንገድ በደላሎች አማካይነት ለቀረበው ጃንዚ ጃንግሊያን ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ በ12,119,913,986 ብር በመስጠት፣ በመንግሥትና ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎችና ደላሎች ላይ ክስ ተመሠረተ።

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ የኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት አምስት የቻይና ኩባንያዎች ፍላጎት አሳይተው ነበር። ፋብሪካውን ለመገንባት የቻይና ላይት ኢንዱስትሪያል ኮርፖሬሽን ፎር ፎሬን ኢኮኖሚክ ቴክኒካል ኮኦፕሬሽንና የቻይና ናሽናል ሄቪ ማሽነሪ ኮርፖሬሽን የቴክኒክና የፋይናንስ ፕሮፖዛል እንዲያቀርቡም ተጠርተው እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል። ነገር ግን ክስ ከተመሠረተባቸው መካከል ይደልላሉ የተባሉት ወ/ሮ ሳሌም ከበደ [የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣን የአቶ አባይ ፀሃየ ሚስት]፣ አቶ ፀጋዬ ገብረ እግዚአብሔርና አቶ ፍሬው ብርሃነ ሀረጎት፣ የጃንዚ ዳንግሊያን ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ ተወካይ ሚስተር ዩአን ጃሊን ጋር ባላቸው ስውር የጥቅም መመሳጠር፣ “JJIEC” የቴክኒክና የፋይናንስ ፕሮፖዛል እንዲያቀርብ የተጠራ በማስመሰል፣ የ647,058,000 ዶላር ወይም 12,119,913,986 ብር ፕሮጀክት ኮንትራት ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል እንዲፈጽሙ ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል።

 

ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት ግዥ መመርያ መሠረት በግልጽ ጨረታ ወይም በውድድር ግንባታውን ቢሰጥ የተሻለ ዋጋና የዕቃ ጥራት ይገኝ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል። የቻይና ናሽናል ሄቪ ማሽነሪ ኮርፖሬሽን የስኳር ፋብሪካውን ለመገንባት ከኤግዚም ባንክ ብድር እንደሚያገኝ መተማመኛ ደብዳቤ ጽፎ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ጠቁሞ፣ ከባንኩ የሚገኘው ብድር ከሌሎች የቻይና ንግድ ባንኮች ከሚገኝ የብድር መክፈያ ጊዜና ወለድ አንፃር ጠቀሜታ እንደነበረው ጠቁሟል። ነገር ግን ደላሎቹና ስኳር ፋብሪካውን ለመገንባት በሕገወጥ መንገድ ውል የተፈራረመው “JJIEC” ተወካይ ሚስተር ዩአን ጃሊን ጋር በመመሳጠር፣ ብድሩን የንግድ ባንክ ከሆነው የቻይና ኢንዱስትሪያል ኮሜርሻል ባንክ እንዲሆን በማድረግ 550 ሚሊዮን ዶላር ወይም 10,301,940,000 ብር የግንባታውን 85 በመቶ የብድር ውል እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል።

ግንባታውን የሚያከናውነው “JJIEC” የቻይና ካምፓኒ በኢሜይል በማፈላለግ ያገኘው ፀጋዬ ገብረ እግዚአብሔር የተባለው ተከሳሽ በመሆኑና ካምፓኒውም ኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በ12,119,913,986 ብር ውል የፈጸመ በመሆኑ፣ ከተገኘው ብድር ላይ ደላላው 20,279,895 ብር ኮሚሽን እንደተከፈለው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል። ሚስተር ዩአን ጃሊን የኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክትን ያለምንም ጨረታ ውል ያዋዋሉት የስኳር ኮርፖሬሽን ማኔጅመንት አባላት ያውቃሉ የተባሉት ወ/ሮ ሳሌም ከበደ በመሆናቸው፣ 15,912,911 ብር ኮሚሽን እንደተከፈላቸው፣ እሳቸው ደግሞ ከሚስተር ዩአን ጋር ላስተዋወቃቸው ፍሬው ብርሃነ ለተባለው ተከሳሽ ስምንት ሚሊዮን ብር ከኮሚሽናቸው ላይ መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል። የብድር ውሉን ስምምነት ለመፈራረም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ኃላፊዎችን የሚያውቅ ደላላ ሲፈለግ የተሳካ በመሆኑ፣ ለስኳር ፋብሪካው ግንባታ ቅድሚያ ከተለቀቀው 20 በመቶ 110 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 1.5 በመቶ ሕገወጥ ኮሚሽን በወ/ሮ ሳሌም ከበደ ድርጅትና በአቶ ፀጋዬ ገብረ መድኅን ድርጀት ስም መከፈሉን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል። ተከሳሾቹ አቶ አበበ ተስፋዬ፣ አቶ ሽመልስ ከበደ (በሌሉበት) እና አቶ ኤፍሬም ዓለማየሁን ጨምሮ የልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆንና የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

ወ/ሮ ሳሌም ከበደ አንድን ግለሰብ በቦሌ ክፍለ ከተማ ካራማራ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ካምፕ ድረስ በማስጠራት፣ “የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ኃላፊዎችንና የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎችን ስም ብቻ ማዕከላዊ ወስደን ዕርምጃ እንወስድብሀለን በማለት ፖሊሶች እንዲያስፈራሩት አድርገዋል፤” ተብለው በከባድ ዛቻ ወንጀል ተከሰዋል። ፍርድ ቤቱ የተመሠረተባቸው ክስ ለተከሳሾች በችሎት በንባብ ካሰማ በኋላ፣ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ ዋስትና እንደሚከለክል በመግለጽ፣ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ከተከሳሾቹ ጋር ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የነበሩት አቶ መስፍን መልካሙንና ብርጋዴር ጀኔራል ኤፍሬም ማጌቦን፣ ዓቃቤ ሕግ ለምስክርነት እንደሚፈልጋቸው በመግለጽ ከእስር እንደፈታቸው አስታውቋል። ነገር ግን ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬም መፈታታቸው ለፍርድ ቤት የተገለጸው መስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ ለፍርድ ቤቱ ሳያሳውቅና ያለምንም ማስረጃ መሆኑ ችሎቱን አስቆጥቷል። “ማን ፈቀደላችሁ? እኔ ዋስትና ከልክዬ እንዲታሰር ያደረግኩትን ተጠርጣሪ ፈታችሁ?” በማለት ችሎቱ ጠይቆ፣ ተጠርጣሪው ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮና አስፈላጊው መብታቸው ተጠብቆላቸው መፈታታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበትም አስታውቋል። በመሆኑም በአዳር ዓርብ መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ እንዲያስረዳ በተሰጠው ቀጠሮ መሠረት፣ ዓቃቤ ሕግ ለምስክርነት ፈልጓቸው እንደፈታቸው ፕሮቶኮሉን በጠበቀ ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

በመጨረሻም ያልተያዙትን ተከሳሽ አቶ ሽመልስ ከበደን ፌዴራል ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብና ተከሳሾቹ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

ምንጭ፡ ሪፖርተር