የኢሬቻ በዓል ተቃውሞ ቢሰማበትም በሰላም ተጠናቋል

1 ኦክተውበር 2017

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መንግሥትን የሚያወግዙ ሙዚቃዎች እና መፈክሮች በብዛት ቢሰሙበትም በሰላም ተጠናቋል።

ዛሬ ጠዋት በቢሾፍቱ ከተማ የጣለው ከባድ ዝናብ የበዓሉን ታዳሚ በቦታው ከመሰባሰብ አላገደውም።

ከአንድ ስዓት ተኩል የእግር ጉዞ በኋላ ሆራ አርሰዴ የደረሱት አባገዳዎች በዓሉን በሰላም አክብረው ወደ መጡበት ተመልሰዋል።

በበዓሉ ላይ ከንጋት ጀምሮ መንግሥትን የሚቃወሙ ወጣቶች ድምፃቸውን ሲያሰሙ እንደነበር በስፍራው የነበረው ባልደራባችን ዘግቧል።

አባገዳዎችም ሆኑ የመንግሥት አካል በሥነሥርዓቱ ላይ ንግግር አላደረጉም።

በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ መንግሥት ምንም አይነት ድርሻ አይኖረውም መባሉ ይታወሳል።

በኢሬቻ በዓል ላይ የትኛውም የመንግሥት አካል ድርሻ አይኖረውም ተባለ

ተቃውሞ የሚያሰሙ ወጣቶች

አጭር የምስል መግለጫ

የዘንድሮው በዓል ተቃውሞን አስተናግዷል

የበዓሉን ዝግጅት ሲያስተባብሩ የነበሩት የኦሮሚያ አባ ገዳዎች ምክር ቤት አባላትም ንግግር ሳያደርጉ ወደ መጡበት ተመልሰዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ በዓሉ ከሚከበርበት ሥፍራ በግምት ሁለት ኪ.ሜ ርቀት ላይ የነበረ ሲሆን፤ የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳለው ፖሊስ የጦር መሳሪያ ሳይታጠቅ የፀጥታ ማስከበር ሥራ ሲያከናውን ነበር።

ነገር ግን በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ታይተዋል።

በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ ከሰበታ ከተማ የመጣው ወጣት ዓለሙ አረጋ የዘንድሮ በዓል እጅግ አስደሳች ነውስል ለሪፖርተራችን ተናግሯል።

የዘንድሮ በዓል ከባለፈው ዓመት በተለየ መልኩ አስደሳች እና ሰላማዊ ነውያለቸው ደግሞ ከሻሸመኔ የመጣችው ወጣት ሃምዚያ በሪሶ ናት።

በዘንድሮ በዓል ላይ እሰከ እኩለ ቀን ድረስ በተሳታፊዎች ላይ የደረሰ ጉዳት እንዳልታዘበ እና በአካባቢው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስቸኳይ እርዳታ ለማድረግ በተጠንቀቅ ቆሞ እንደነበርም የባልደረባችን ዘገባ ያመለክታል።