በ-ዮሴፍ ሙለጌታ ባባ, PH.D.

ሀብታሙ አለባቸው በቅርቡ ‹‹ታላቁ ተቃርኖ›› የተሰኘ ቦንብ መጽሀፍ ጀባ ብለውን ነበር። በዝህ መጽሐፉ ውስጥ (ገጽ. 197) እንድህ ሲል በትክክል ይሞግታል፡-

 

 

‹‹በ2009 ዓ.ም ታትሞ ገበያ ላይ የዋለው የፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ‹እነሆ መንገድ…› የሚል መጽሐፍ…የኢትዮጵያን ልማት አንቀው የያዙ ችግሮችን፣ የችግሮቹን ምንጭና አውድ ሳይነግረን፣ መፍትሄውን በምክር መልክ በማዥጎድጎድ ይለግሰናል። ለአገሩ ያለውን ጥሩ ምኞት ብጋራውም ዳንኤል በምሁርነቱ ያበረከተው እስተዋጽኦ ግን እምብዛም እንደሆነ ተሰምቶኛል። የእሱን የመሰሉ ‹የአብረን ተፋቅረን እንኑር› ተምኔታዊ ስብከት የሞላቸው የቡራኬ መጻሕፍት በርካታ ናቸው።››

 ከዝ በፊት Metaphilosophy or Methodological Imperialism? በተሰኘ የምርምር ሥራዬ በኩል፣ የአንድን ችግር ቁልፍ ምንጭ ሳያውቁ መፍትሔ ማፈላለግ ውጤቱ ታጥቦ ጭቃ እንደሆነ በማስረጃ አስደግፈ ለማሳየት መክረዋለሁ። በአንድ ሀገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ የሚቻለው የጋራ ግንዛቤ ሲኖር ብቻ ነው። ኢትዮጵያ በሚትባል ሀገር ውስጥ ደግሞ ይህ የጋራ ግንዛቤ ሊፈጠር የሚችለው ‹የኢትዮጵያ ታሪክ›ን የሚንረዳበት እና የሚንተነትንበት መንገድ/ዘዴ እንደገና በጥልቀት ስንፈትሽ ብቻ ይሆናል። ከምዕራቡ ዓለም የተቀዳ የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ግን በ‹ኢትዮጵያ ታሪክ› አረዳድ ላይ ሥነ-ዕውቀታዊ ጥቃት (epistemological violence) እያስከተለ ይገኛል። ለዝህ ጥቃት ኃላፍነቱን የሚወስዱ ከእኛ የታሪክ አረዳድ በተቃራኒ የተሰለፉና በኩረጃ ፍልስፍና የተካኑ የምዕራባዊያን የአስተሳሰብ ዘይቤ ተከትለው የአውሮፓዊነት መንፈስና ዘረኛ አስተሳሰብ የተላበሱ ኢትዮሮፕያንስ (Westernized Ethiopians) ናቸው። ኢትዮሮፕያንስ የአንድን ግለሰብ ወይም የአንድ ሕዝብ ታሪክ አንድም ፍጹም እርኩስ፣ አልያም ፍጹም ቅዱስ አድርጎ ያቀርባሉ። ይሁን እንጅ የማንኛውም ግለሰብ ወይም ሕዝብ ታሪክ ምልካምና መጥፎ ገጽታ አለው። ስለዝህ፣ አንድም ፍጹም እርኩስ፣ አልያም ፍጹም ቅዱስ አድርጎ ማቅረብ የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ይባላል። ፍልስፍና ከምዕራባዊያን ‹ዓለም› ለተቀዳ ለእንደዝህ ዓይነት የታሪክ አረዳድና ትንተና ፈጽሞ ቦታ የለውም።

 

ስለዝህ፣ ሀብታሙ በትክክል እንዳስቀመጠው ‹‹የአብረን ተፋቅረን እንኑር›› ተምኔታዊ ስብከት የሞላቸው የቡራኬ መጻሕፍት በርካታ ቢሆኑም፣ የአንድን ሀገር ችግር ቁልፍ ምንጭ ሳያውቁ ‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› ቢሎ መዝፈን ግን እንኳን ሞያሌ ሀገር ለሚኖር ሰው እዝ ሸገር ብብት ሥር ላለቸው ሱሉልታ ውስጥ ለሚኖር አንድ ግለሰብ ምንም ዓይነት ስሜት ላይሰጠው ይችላል። ለምሳሌ፡-  ‹‹የአብረን ተፋቅረን እንኑር›› ፍልስፍና ከሚያቀነቅኑ ታዋቅ ሰዎች መካከል አንዱ የሀገራችን ፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቴዲ አፍሮ ነው። ተዲሻ ዲንቅ ችሎታ ያለው ዘፋኝ ከመሆኑም በላይ የተዋጠለት የዜማ እና የግጥም ደራስም ነው! ይህንን ድንቅ ችሎታውን መካድ ቅናት ወይም ድንቁርና ሊሆን ይችላል። ስለዝህ—Respect! ፈጣሪ ረዥም ዕድሜ እና ጤና ይስጠው!

 ይሁን እነጂ፣ ቴዲ አፍሮ ‹‹የኢትየጵያን ታሪክ›› የሚረዳበት መንገድ የሌሎችን ሥነ-ልቦና አቀራረጽ ግምት ውስጥ ያላስገባና ታሪክን ከአንድ ወገን ብቻ በመተረጎም ይታወቃል፤ ስለዝህ ቴዲ ራሱን ትዝብት ላይ ጥሏል። ከዝ በፉት ‹‹የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ›› በተሰኘ ሥራዬ ውስጥ ‹‹ጥቁር ሰው—አፄ ሚኒልክ በቴዲ አፍሮ የታሪክ-መነጽር!›› በሚል ርዕስ ሥር የእሱ ሥራ ‹አንዱን ወገን ብያስከፋና ሌላውን ደግሞ ቢያስፈነጥዝ› መገረም እንደሌለብን ተጨባጭ መረጃ በማቅረብ ሞግቼ ነበር። ዛሬም ቢሆን ቴዲ አፄ ቴዎድሮስን የሳለበት መንገድ ‹አንዱን ወገን ብያስከፋና ሌላውን ደግሞ ቢያስፈነጥዝ› መገረም እንደሌለብን ለማሳሰብ ያህል ነው! እስኪ ወደ ታሪኩ ልመለስ!

ታቦር ዋሚ ‹‹የውገና ድርሰቶች እና የታሪክ እውነቶች›› በተሰኘው ድንቅ ሥራው ውስጥ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሮ ነበር፡-

 

የቴዎድሮስ ጭካኔና የፈጸሙአቸውን ግፎች በሚመለከት ኢንጂነር ታደለ ብጡል ‹‹ቴዎድሮስና አለማዮ›› በሚለው መጽሐፋቸው ከጻፉት ውስጥ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

 

  1. የሸፈተባቸውን ቸኮልን ለመውጋት ወደ ደንበጫ ሄደው ሳለ ቸኮል አመለጣቸው። ከአሽከሮቹም ስድሳ ሰዎች ተማርከው ስለነበረ እነሱን በገበያ ላይ ሰቀሉአቸው። አንደኛው ከቴዎድሮስ አሽከር ጠመንጃ ሲቀማ ተይዞ ነበርና ያንን ሰው ከመድፍ አፍ ላይ አስጠግተው አስቁመው የመድፍ ጥይት እንዲተኩስ አዘዙ። ሲተኮስም ሰውየውን ብትንትኑን አውጥቶ ገደለው በማለት አለቃ ዘነበ ጽፈዋል።
  2. ግራዝማች ዓለሜ የሸፈቱ ጊዜ አንዱ አሽከራቸው ተይዞ መጣ። ከንጉሡ ችሎት በቀረበ ጊዜም ቴዎድሮስ የሞት ፍርድ ካስፈረዱበት በኃላ፣ መቅደላ፣ ወራሂመኖ፣ ደላንታ፤ ዋደሌ ጦርህን ከዚህ ሰው ደም ያላስነካህ ጠላቴ ነህ ብለው በመናገራቸው ያ ሁሉ ሕዝብ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሁሉም በጦር ሲወጋው ብትንትኑ ወጥቶ ለምልክት እንኳ የሚታይ ሥጋው ከመሬት ላይ ጠፋ።
  3. ደጃች ተድላ ጓሉን ለመያዝ አጤ ቴዎድሮስ ገስግሰው በድንገት ደርሰው በተዋጉ ጊዜ ስምንት ሺህ ሰዎችን ማረኩ። ይህን ሁሉ ምርኮኛ እንጅባራ ላይ ሰብስበው ራሱን ሲያስቆርጡ ውለው ጊዜው ሲመሽ የተረፈው ሰው ተቆጥሮ አደረ። ሲነጋጋ ንጉሡ ተነስተው ያደሩትን ሰዎች አምጣ ብለው አስቀርበው ሁሉንም እቆርጠው ፈጁት። ያን ሁሉ ክምር ሬሳ እየተዘዋወሩ ሲያዩ ከሬሳው አንዱ አለሞተ ኖሮ ሲንፈራገጥ አዪት። ቴዎድሮስም ተቆጥተው ‹እንዲሁ ሳትገድሉ ነው የጣላችኋቸው› ብለው ያን የሚንፈራገጠውን ራሳቸው ገድለው ሌላ ሁሉ እታየ ያልሞተው እንዲገደል አዘዙ። ሁሉም ካለቁ በኋላ ይህን ሁሉ ጠላቴን በጄ ጥሎ እንዲህ አስተኝቶ ያሳየኝ እግዝአብሔር ይመስገን፣ ብለው መሬት ይህን ጠላቴን በጄ ጥሎ እንድህ እተኝቶ ያሳየኝ እግዝብሔር ይመስገን፣ ብለው መሬት ስመው ከድንኳናቸው ገቡ።
  4. በ1859 ዓ.ም የአማራ ሣይንት ሰዎች ሊክዱ ነው ብለው ስለነገሩዋቸው ቴዎድሮስ ከአማራ ሣይንተ 400 ሰዎች አስይዘው ሁሉንም በጎራዴ አስደብድበው ፈጁዋቸው። አንድ ሰው ከዋድላ ሰዎች ጋር ቢጣላ ከቴዎድሮስ ዘንድ መጥቶ ዋድሎች ሊከዱዎት ነው ብሎ ነገራቸው። ቴዎድሮስም ለዋድላ ሰዎች ገንዘብ እሰጣለውና ሁሉም ተሰብስበው ይምጣ ብለው አዋጅ አስነገሩ። ይህንንም አዋጅ የሰማው ሕዝብ፣ እረኛ እንኳ ሳይቀር በሙሉ ተሰብስቦ መጣ። አፄ ቴዎድሮስም በራስ አድሉ የሚመራውን የየጁን ጦር ዙሪያውን አስከብበው ስድስት መቶ ሰዎችን በጎራዴ ፈጁአቸው። ይህን የግፍ አገዳደል ያዩት ራስ አድሉ ሌሊቱን አምልጠው መሸፈታቸውን አለቃ ተክለ ኢየሱስ ጽፈዋል።
  5. የመጫና የአገው ሰዎች ሊሸፍቱ ነው ብሎ አሳባቂ ነገራቸው። ቴዎድሮስም አራት መቶ የመጫና የአገው መኳንንት ሰብስበው ዙሪያውን በእሾህ አጥር አጥረው ሱሬ ብቻ እያስታጠቁ ራቁታቸውን እንደ ከብት አጎሩዋቸው። እህልና ውኃም እንዳይሰጣቸው አዘዙ። በረሃብና በውኃ ስም የሚሰቃየው ሕዝብም ከአስር ቀን ቦኃላ መሞት ጀመሩ። በ15ኛው ቀን ግን ሁሉም በረሃብና ውኃ ጥም አለቁ።
  6. ቴዎድሮስ ቃሮዳ ከሚባል አገር ሄዱ። ቃሮዳ በአተክልት አብቃይነቱ በተለይ በወይን ሰብል የታወቀ አገር ነበር። አንድ ማድጋ የወይን ጠጅ በጎንደር ባንድ አሞሌ ይሸጥ ነበር። ፈረንጆች የቃሮዳ የወይን ጠጅ ከሀገራችን ወይን ጠጅ የበልጣል ይላሉ።….ያንን ወይን ሀገር በአዋጅ አስነግረው አስነቀሉት። ይህን የሰማ ሁሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ወይኑን ነቀለ። ከዝህ ወዲህ በኢትዮጵያ ወይን ታጣ። ቴዎድሮስ ቃሮዳ እንደደረሱ ሕዝቡን ሰብስቡልኝ ብለው ሕጻናት ሳይቀሩ 1700 ሰዎች ተሰበሰቡ። ይህንን ሁሉ ሰው ቤት እስከቻለ ድረስ በየቤቱ እያስገቡ ሁሉንም በእሳት እያቃጠሉ መጨረሳቸውን አለቃ ወልደማርያም ጽፏል።
  7. አጼ ቴዎድሮስ ወደ ማህደረ ማርያም በወረዱ ጊዜ ካህናቱ ንጉሡን ለመቀበል ከለቻ ከሚባል ሜዳ ላይ ቆመው በጸናጽልና በከበሮ እያመሰገኑ አቀባበል አደረጉላቸው። ይህን ያዩት ቴዎድሮስ በልልኝ ብለው ወታደሩን አዝዘው 450 ካህናት በጎራዴ ተደብድቦ አለቀ። ከዚያም ተመልሰው ደብረታቦር በወጡ ጊዜ ከርብ ጀምሮ እስከ ፍርቃ በር ወታደራቸውን አሰማረተው ሲቆፍርም፣ በመንገድ ሲሄድም የተገኘውን ሁሉ 7700 ሰዎችን አሰባሰቡ።ይህን ሁሉ ሰብስበው በየቤቱ ውስጥ እያጎሩ የታጎሩበትን ቤት በማቃጠል ሲያስፈጁአቸው ዋሉ። ሰው ተቃጥሎ ስያልቅ ጊዜው ስለመሸ ተራፊውን ከሜዳ ላይ እየተጠበቀ ራቁታቸውን እንዲያድሩ አዘዙ። ሌሊቱን ዝናብ ስለዘነበ ሕጻናትና እመጫት ሣይቀሩ በዝናብ ሲደበደቡ አደሩ። በማግስቱ ቴዎድሮስ ያደረውን ሕዝብ ለማቃጠል መጥተው ሰው ከሚቃጠልበት ቤት እየተከፈለ ሲገባ አንድ የአምስት ዓመት ልጅ እናቱን እየጎተተ ‹‹ነይ እንደትናንቱ ዝናብ እንዳይመታን ቶሎ ከቤት እንግባ›› እያለ ሲያለቅስ ፣ እናቱም ስታለቅስ ቴዎድሮስ አይተው ‹‹ለምን ያለቅሳሉ?›› ብለው ጠየቁ። ልጁ የተናገረውን ቢነግሯቸው ‹‹ፈጣሪዬ ምነው እንዲህ ታደረገኛለህ! ወይ እኔን ቶሎ ግደልና ፍጥረት ይረፍ›› ብለው አልቅሰው ሊቃጠሉ የቀረቡትን ሁሉ ማሩት። ይህ ከሆነ ቦኃላ ደግሞ ጣና ሐይቅ ውስጥ ከምትገኘው ምጽርሐ ወደምትባለው ደሴት በደሴቲቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሙሉ በቤት ውስጥ እያስገቤ ቤቱን በማቃጠል ጨረሱት።
  8. ዶ/ር ብላንክ ስለ ቴዎድሮስ የጭካኔ ተግባር ከጻፉት ውስጥ አቶ ዳኛቸው የተረጎሙትን ብንመለከት፣ እ.አ.አ ህዳር 21 ቀን 1859 ዓ.ም ከሰዓት በኃላ አጼ ቴዎድሮስ የተመረጡ ጥቂት ፈረሰኛና እግረኛ አስከትለው ከጎንደር ግንብ ውስጥ እየተደበቁ የሚያስቸግራቸውን ሽፍቶች ለማጥፋት መገስገስ ጀምረው አስራ ስድስት ሰዓት ባለሞላ ጊዜ ውስጥ ሰማኒያ ማይልስ ርቀው ያለውን ጎዳና አንድ ጊዜ ስንኳ ሣይቆሙ ሲጓዙ አድረው ወገግ ሲል የጊንደር ከተማ ከሚገኝበት ተራራ ስር ደረሱ። ምንም እንኳን በድንገት ለመድረስ አቅደው የመጡ ቢሆንም፣ የጎንደር ነሪ ሕዝብ ወሬውን ሰምቶ ስለነበር በመጨነቅና በመሸበር ሴቶች ወጥተው በእልልታና በደስታ ሲቀበሉዋቸው በፋሲል ግንብ ተሰግስጎ የነበረውም ሽፍታ ሸሽቶ ከጎንደር ወጣ። ወዲያውም ሽፍቶችን ለማግኘት ሠራዊቱ ቤቱንና ቤተክርስቲያኑንም ሣይቀር መበርበርና መዝረፍ ያዙ። ዳሩ ግን ወዲያውም ሽፍቶችን ለማግኘት ሠራዊቱ ቤቱንና ቤተክርስተያኑንም ሣይቀር ባለማግኘታቸው ከአስር ሺ በላይ የነውን የከተማውን ነዋሪ ሕዝብ እንደ ከብት ሰብስበው ነዱት። ከዝህም በኋላ የጥፋት ሥራቸውን ጀምረው ሕዝቡን፣ ቤቱን፣ ቤተክርስጢያኑንና ቤተመንግስቱንም ጭምር በእሳት አቃጠሉት። ከቀሳውስት መካከል አንዳንዶቹ የደፈሩ አጉረምርመው የንጉሥ ነገሥቱን አፈጻጸም በግልጽ ተቃውመው ስላወገዙ ብዙ መቶ ሽማግሌ ቀሳውስት ወደ እሳተ ተወርውረው ተቃጠሉ። የማቃጠሉ ነገር ከዝህ ላይ ሳይቆም እልል እያሉ የተቀበሉት ሴቶችስ የት አሉ? እነርሱ እልል ባይሉ ኖሮ ሽፍቶች መምጣታችንን የት ያውቁ ነበር? በማለት ሴቶች ሁሉ ተይዘው እንዲመጡ አጼ ቴዎድሮስ በማዘዛቸው ሁሉም ከእነሕይወታቸው ወደተቃጠለው ቤት እየተወረወሩ ነደዱ…ብለዋል።
  9. በሸዋ ተሸመው የነበሩት የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ልጅ አቤቶ ሰይፉ በቴዋድሮስ ላይ ስለሸፈቱ ወደ ሸዋ መጥተው ሙቅምድር በሚባል ቦታ 500 ያህል ሰዎችን ማረኩ። ሁሉነም ቀኝ እጃቸውንና ቀኝ እግራቸውን እየቆረጡ ጣሉአቸው። በዝህም የተነሣ የሚከተለው ተገጠመ

አጼ ቴዎድሮስ እጅግ ተዋረዱ

የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነስተው ሄዱ።

10 የጋረድ ጦር የዎድሮስ ወዳጅ የነበረውን እንግልዛዊ ፕላዉዲን ሊቀመኳስ ቤል ደግሞ ጋረድን ገደለ፣ የጋረድ ወንድም ቤልን ገደለ። ቴዎድሮስ በበኩሉ በጦርነት ላይ 1500 የጋረድ ሰዎችን ማርኮ ካስገደላቸው በኋላ ጭንቅላታቸውን ተቆርጦ እንደ ካብ እንደተደረገ አለቃ ወ/ማርያምና አለቃ ተክለየሱስ ጽፈዋል።

ደራሲ ስብሀት ገብረ እግዝአብሔር…ስለካሣ ጭካኔ ሲገልጹ ‹‹አጼ ቴዎድሮስ ሥጋ ደዌኛን እየሰበሰሁ ያቃጥሉ ነበር። ደብረ ታቦር ጎጆ ሲሰራ ያድራል። ቀን ደዌኛቹ እጎጆው ውስጥ ያታጎሩና እሳት ይለቀቅባቸዋል። ካሣ ከሞከራቸው ብዙ ሥራዎች አንዱ ሥጋ ደዌን በሂህ ዓይነት ከምድረ ኢትዮጵያ ማጥፋት ነበር›› ይላሉ።

 አጼ ቴዎድሮስ የፈጸሙአቸው ግፎች ብዙዎች አልተመዘገቡም። ከሽፍትነታቸው ጀምሮ እስከ እለተ ሞታቸው ሰዓት ድረስ ያለቀው ሕዝብ ብዛት ሥፍር ቁጥረ የለውም። ኋይላቸውን ካጠናከሩ በኋላ ከደጃዝማች ወንድራይድና ሌሎች መሣፍንት ጋር በተደረጉት ጦርነቶች ድል በድል ላይ እየተረማመዱ የመጡት ጊዜ ስለነበረ፣ በጦርነቱ ወክትም ሆነ ከጦርነቱ ቦኋላ በምርከኞች ላይ የተፈጸሙትን ግፎች በሙሉ መዘርዘር ያስቸግራል። ከሰባት ጊዜ በላይ ወደ ወሎ ዚዘምቱ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ አልቀዋል፤ የብዙዎቹ ንብረት ወድሞአል፣ አብዛኛው የወሎ ጦር አካለ ጎደሎ ሆኖአል፣ ከአገር ተሰደዋል፣ እንደ እንጨት በእሳት ተማግደዋል። በየሰከንዱ ከሚለዋወጠው ጠባያቸው የተነሳ ሕዝቡን ለምህረት የተባለው ለመዓት፣ ለመዓት የተባለው ደግሞ ለምህረት እተዳረገና ሁሌም መዓትን እየጠበቀ የግፍ ጽዋውን ሲቀበል ኖሮአል።

በተለይም የራስ አሊ ሁለተኛ ወታደሮች በ1853 ዓ.ም በአይሻል ጦርነት ላይ ካሸነፉ በኋላ ሁሉ ከቴዎድሮስ ጭካኔ አንጻር ተጠንተው ቢጻፉ ኖሮ የሳቸውን ማንነት ይበልጥ ግልጽ ያደርግ ነበር። የሚገርመው ግን ቴዎድሮስ በየትኛውም ዘመን ተደርጎ በማይታወቅ ደረጃ፣ በጥይት እየደበደቡ፣ በጎራዴና በሰይፍ ውስጥ በማጎር እያቃጠሉ፣ ያስጨፈጨፏቸውን ሰዎች ጭንቅላት እያስቆረጡ እንደ ድንጋይ ሲያስክቡ የሚውሉና በመጨረሻም እራሳቸው ‹‹እብድ ነኝ›› ፣ መለታቸውና ቀና ብለው ፈጣሪን እየተማጸኑ፣ ‹‹እባክህን ጌታዬ እኔን ግደልና ፍጥረትህ ይረፍ›› ብለው እስከ መጸለይ የደረሱ ጨፍጫፍ መሆናቸውን ለአስራ አራት ዓመታት አገርቷን የጦር አውድማ በማድረግ በኢኮኖሚ አድቀውና በመጨረሻም በታትነው መሞታቸው እየታወቀ ለማመስገን መጣር አሳፈሪ ከመሆኑም በላይ ያለአግባብ ሕይወታቸውን ባጡት ወገኖች ላይ መቀለድ ይሆናል።›› (ታቦር ዋሚ፣ የውገና ድርሰቶች እና የታሪክ እውነቶች፣ ገጽ. 418-424)

 ታሪክን ከአንድ ወገን ብቻ መመልከት የሚያመጣው መዘዝ ብዙ ነው። ቴዲ አፍሮን ማድነቅ እና የኢትዮጵያን ታሪክ ከቅጡ መረዳት ለየቅል ናቸው። የራስ ድንቁርና በአደባባይ ማናጸባረቅ በሳልነት አይደለም። ዶ/ር መረራ ያለውን ነገር ግን ፈጽሞ መርሳት የለብንም ‹‹በነዝህ አመለካከቶች ላይ ስምምነት መፈለግ ሲያንስ አስቸጋሪ ሥራ ነው፣ ሲበዛ ደግሞ የፖሊቲካ የዋህነት ነው!›› እኔም የሚለው የታሪክ አረዳድ ልዩነት ምንጭ፣ የተለያየ የልቡና ውቅር እንድኖረን አድረገዋል። ‹‹የአብረን ተፋቅረን እንኑር›› ቀረርቶ ለሁለም ኢትዮጵያውያን አንድ ዓይነት ትርጉም የለውምና፣ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ መገንዘብ ያስፈልጋል። በቁንጫሳ ፎቶሳ ግጥም ልሰናበታቸው

Baal baasin baasa hin beektuu

Gadheen hasaasa hin beektu

Kan hundee namaa hin beekne

Namarraa goru hin beetu!

 

Yoseph Mulugeta Baba can be reached at kankokunmalimaali@gmail.com