Posted by | October 2, 2017

የዐምሐራ ብሔርነት በእነዚህ መለኪያዎች
ክፍል አንድ

(ይህን ጽሑፍ ለማጋራት የቅርብ ምክንያቴ በፍቃዱ ኃይሉ ስለ “የአማራ ሥነ ልቦና” በሚል ርዕስ የፌስቡክ ያጋራን ጽሑፍና ከዚሁ ጋር በተገናኘ የቀረቡት አስተያየቶች ናቸው። ይሁን እንጂ ይህ ጽሑፍ በመግቢያነት ብቻ የሚያገለግል ነው። ዋናው ጽሑፍ በክፍል ሁለት ይቀርባል።)

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት (በሌኒን እና በስታሊንም) መሠረት “ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ” ለመባል አምስት መሥፈርቶች መሟላት አለባቸው፡፡ እነዚህም፡-ተመሳሳይ ባህል ወይም ልምዶች ፣ መግባቢያ ቋንቋ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና፣ የሥነ-ልቦና አንድነት እና በአንድ በተያያዘ አካባቢ መኖር ናቸው፡፡

ለነገሩ ከላይ የተዘረዘሩት መሥፈርቶች በዚህ ዘመን ተቀባይነት የላቸውም፡፡ የተለየ  ቋንቋ መኖር ግድ አይደለም፡፡ አንድ አካባቢ ላይ ሰፍረው ባይገኙም፣ የራሳቸውን አስተዳደር ለመመሥረት ባይችሉምና ባይፈልጉም እንደብሔር ዕውቅና ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በታሪክ ብሔርተኝነትን ድንበር ገድቦት ሲቆም አልታየም፡፡ራስን በራስ ለማስተዳደር የግድ በአንድ አካባቢ መኖር ወሳኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀገር ለመመሥረትም እንደዚሁ፡፡

ሀገር መመሥረት የማይችልን፣ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እንዲችል በአንድ በተለዬ አካባቢ መኖር ካልቻለ ብሔር ወይንም ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ አይደላችሁም ማለት ግን አሳማኝ አይመስልም፡፡ ለነገሩ ዕውቅና ማግኘት የግድ መስተዳድር ለማቋቋም ብቻ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ዕውቅና፣ በአብዝኃኛው ሥነ-ልቦናዊ ይዘት ነው ያለው፡፡ አስተዳደራዊ እርከን ከማቋቋም ውጭም ብዙ መብቶች አሉና፡፡

ሌላው የባህልና የልምዶች ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የተለየ ስም ያለው ሕዝብ፣ የኔ የሚለው የጥንት መኖሪያ ያለው፣ በአንድነት የሚተርከው አፈታሪክና ተረት፣ ትዝታና ተመሳሳይ ባህል ያለው እንዲሁም ከሕዝብ የሚመነጭ የጋራ መብትና ግዴታ ካለው ይህ ብሔር ነው የሚሉም አሉ፡፡  ይሁን እንጂ እነዚህ መለኪያዎች ብዙ ጊዜ ለጎሳና ለነገድ መለያነት ሊያገለግሉም ስለሚችሉ በመጠንና በስፋት ከፍ ላሉት ለብሔርና ለብሔረሰብ በቂ መለያዎች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም በተለይ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች ባህላቸው ላይለያይ ይችላል፡፡

ለአብነት በኦሮሚያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ አማሮች ከአማራ ባህልና ልምዶች ይልቅ የኦሮሞ ባህልና ልምድ የበለጠ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ነባር ሬድ ኢንዲያንስ ከባህል አንጻር ከሌላው አሜሪካዊ የተለየ ባህል ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ተመሳሳይ ጂንስ ለብሰው፣ በተመሳሳይ ቅላጼ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናግረው፣ ማክዶናልድ ዋና ምግባቸው ሆኖ ከማንነት አንጻር ግን ራሳቸውን ሌላ ብሔር/ማኅበረሰብ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ በመሆኑም ባህል ቁርጥ ያለ መለያ ሊሆን አይችልም፤ ነገር ግን በተጨማሪነት ለመለያነት አያገለግለም ማለት አይደለም፤የተለየ ባህል ያላቸው የሉም ማለትም ደግሞ አይደለም፡፡

ሌላው የብሔር ማንነትን የሃይማኖት ተመሳሳይነት ወይንም መለያየት አይወሥነውም፤ሃይማኖትን  መለወጥም ብዙም ከብሔር ማንነት ጋር ቁርኝት የለውም፡፡ ለምሳሌ አንድ ኦሮሞ ዋቀፌታን ትቶ የፕሮቴስታንት እምነት ቢከተል አንዱ የኦሮሞነት የጥንቱ መገለጫ ዋቀፌታ ቢሆንም ሃይማኖታዊ ለውጡ ለብሔሩ የሚኖረውን ታማኝነት አያሳጣውም፡፡  ቋንቋው ተቀይሮም፣ ባህሉ ተዋህዶም፣ ኢኮኖሚያዊ መገለጫዎቹም ቀርተው ብሔርና ብሔርተኝነት ሊኖር ይችላል፡፡

አራተኛው መስፈርት የጋራ ዘር ወይንም ህልውናን የተመለከተ ነው፡፡ አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን ብሔር ማለት የጋራ ዝርያ መጋራቱን የሚያምን በዛ ያለ ሕዝብ የያዘ ስብስብ ወይም ቡድን ነው በማለት ይተረጉሙታል፡፡ የጋራ ዝምድና አለኝ ብሎ ማሰቡ፣ በጋራ “ሆ” ብሎ እንዲነሳና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ያስችለዋልም፡፡ በጥንታዊው የአውሮፓውን የብሔር አረዳድ ብሔር ማለት “አንድ የጋራ የዘር ግንድ አለን በሚል ስህተት፤ እንዲሁም በጋራ የሚጠሏቸው ጎረቤቶች እንዳላቸው በማሰብ በእነዚህ አንድነትን የፈጠሩ ሰዎች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው” የሚል ነው፡፡

የአንድ ብሔር ተወላጆች እውነትም ይሁን ስህተት ከጋራ ዘራችን ከእንቶኔ ነው የመጣነው፤እነ እቶኔ ደግሞ ጠላቶቻችን ናቸው በማለት የጋራ ጠላት በውስጣቸው ካሰረጹ አንድ ጠንካራ ብሔር ለመሆን ይረዳል እንደማለት ነው፡፡የጋራ የዘር ግንድ ባይኖርም የጋራ ጠላትን ግን ልሂቃኖች ሊፈጥሩት ይችላሉ፡፡የጋራ ጠላት እንዳለው በማድረግ ብሔርተኝነትን ማሳደግ ይቻላል፡፡

የመጨረሻው መሥፈርት ሥነ-ልቦናን የተመለከተ ነው፡፡ አንዳንዶች ብሔር ሲሉ በአብዝኃኛው የሥነ-ልቦናና የአመለካከት ጉዳይ በማድረግ ሙግታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ተጨባጭ የሆነ መለያን አይፈልግም፡፡ በምሳሌ ለማብራረት ያህል አንድ አባትና እናቱ ኦሮሞ የሆነ ልጅ አዲስ አበባ ተወልዶ አደገ ብንልና ኦሮምኛ አይችልም ብንል፤ በባህልም ረገድም ባህሉ እንደአዲስ አበቤው ቅልቅል እንጂ ቱባ የሆነውን የኦሮሞ ባህል አያውቅም እንበል፡፡ የብሔር ነገር የሥነ-ልቦናና የአመለካከት ስለሆነ ይሔ ልጅ “ኦሮሞ ነኝ” ማለቱን ወይንም መሆኑን አይተውም፡፡ በእርግጥም የብሔራቸውን ቋንቋ ሳያውቁ፣ ባህላዊ ክንዋኔዎችንም ሳይተገብሩ የብሔር ታማኝነታቸው፣ ማንነታቸው ግን ከወላጆቻቸው በደም ያገኙትን ብሔር የሆኑ እልፍ አእላፍ ግለሰቦች እናገኛለን፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት እንደአሜሪካም ባሉ ሀገራት ምንም የባህልና የቋንቋ ልዩነት ሳይኖራቸው ሂዝፓኒክ፣ ሬድ ኢንዲያንስ ወዘተ መሆናቸው ላይ ግን ፈጽሞ ላይደራደሩ ይችላሉ፡፡ የባህል ውህደት/ተመሳስሎሽም የሥነ-ልቦና ውህደትን ላያመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ የብሔር ጉዳይ በዋናነት የአመለካከትና የሥነ-ልቦና አንድነት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ የዐምሐራ የብሔር ጉዳይም ሲነሳ ሕገ መንግሥቱ ላይ በተገለጸው መለኪያ ይሁን በአሁኑ ወቅት የበላይነት ካገኘው መሥፈርት አንጻር ቢታይ ቅንጣት ታክል የሚጎድለው ነገር የለም፡፡

የዐምሀራ ብሔርተኝነት ሲነሳ፤

 

===============

ክፍል ሁለት

ዐምሀራ ብሔር ስላልሆነ ወይንም የማንነት ጥያቄ ስላነሳ ሳይሆን አንዳንድ ምሁራን ስለዐምሀራ ጉዳይ ሲጽፉ ዐምሀራ የሚባል ብሔር የለም በማለት የብሔርነት ህልውናውን ጭምር ከመጠራጠራቸው የተነሳ ነው። ወይንም በተለዋጭና ሲሻሻል አማራ የሚባል ብሔር ቢኖርም የብሔርተኝነት (የዐምሀራነት) ስሜት የለውም። እንደውም ዐምሀራነትን ከኢትዮጵያዊነት እና አልፎ አልፎም ከክርስቲያንነት ጋር አምሳያ በማድረግ ሲያትቱ ይሰተዋላሉ። በቀላል አገላለጽ ዐምሀራነትና ኢትዮጵያዊነትን ኦርቶዶክስ ክርስቲያንነት አንድ የማድረግ ዝንባሌ አለ። ለመሆኑ ዐምሀራ የሚባል ብሔር የለምን?

የፕሮፌሰር መስፍንን ክርክር ማሳያ እናድርግ። እሳቸው ሊቃውንት ዐምሀራ ለሚለው ቃል፣ ከሥርወ-ቃሉ በመነሳት “ነጻ፣ የተመረጠ፣ መገዛትን የማይወድ” ወዘተ ሕዝብ ነው በማለት የሰጡትን ትርጓሜ መነሻ ያደርጋሉ። ዐምሀራ ማለት ነጻ ሕዝብ ማለት ነው የሚለው ብዙም ትርጉም የማይሰጥ ቢሆንም፣ ነጻነትን የሚወድ ለማለት ነው ከተባለም ነጻነትን የሚጠላ ሕዝብ ያለ ስለማይመስለኝ ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም ብዙም ስለብሔሩ የሚገልጸው ነገር ያለ አይመስልም። በግዕዝ-“ዐም”፣በዕብራይስጥ-“ዐሚ” ማለት ‘ሕዝብ’ ሲሆን፣ “ሀራ” ማለት ደግሞ ሁለት ትርጉም አለው። የመጀመሪያው ‘ነጻ’ ማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‘ሠራዊት፣ወታደር’ እንደማለት ነው።

ፕሮፌሰሩ፣ በአለቃ ታዬ “አማራ ጥሩ የላስቶች ወታደር የነበረ ሕዝብ ነው” የሚለውን ሐሳብም እንደአስረጂ ያቀርባሉ። “ሀራ” የሚለው ቃል ሁለተኛው ትርጉም ‘ሰራዊት፣ወታደር’ ማለት ስለሆነ የአለቃ ታዬና ሌሎች ምሁራንም ዐምሀራ የላስቶች ወታደር የነበረ ሕዝብ ነው ሲሉ ይህንን ወታደርነቱን ለመወከል የተሰጠ ቃልም ይመስላል-ዐምሀራ። ይህ አጠራር ሕዝቡ ከተፈጠረ በኋላ የተሰጠ፣ አመጣጡን አይቶ ስም የወጣለት ከማስመሰል ውጭ ዐምሀራ የሚባል ሕዝብ የለም ለማለት በጭራሽ ሊጠቅም የሚችል አይደለም።

አባ ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር በትግርኛ-አማርኛ መዝገበ-ቃላታቸው ደግሞ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም” ያሉትንና የንቡረ-እድ ኤርምያስን “የኅብረብሔር አጠቃላይ መጠሪያ” የሚሉትን ትርጓሜ እንደማጠናከሪያ በመውሰድ ዐምሀራ የሚባል የተለየ ጎሳ የለም በማለት ይደመድማሉ።

የሁለቱ ሊቃውንት ስያሜ ከፕሮፌሰር መስፍን መደምደሚያ ጋር ይስማማል ማለት ይቻል ይሆናል። ይሁን እንጂ የአባ ዮሐንስ፣ መዝገበ ቃላታዊ ፍቺ በመሆኑ እና ብዙም ማብራሪያ ስለሌለው ለክርክር አይመችም። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ነው ማለት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ “ዐምሀራ ነው” የሚል አንድምታ ስላለውና ይህንን እውነት ለማለት ደግሞ የሌሎች ብሔረሰብ አባላት ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ መፍትሔ የሚሆን ይመስለኛል። ዐምሐራ ነን ካሉ አባ ዮሐንስ ትክክል ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት የአንዱ ሕዝብ ስም ነው የሚል ትርጓሜ ከያዘ የፕሮፌሰርን ክርክር ያፈርሳል።

ፕሮፌሰር መስፍን፣ ቀጥለውም የተለያዩ ሰዎች “ዐምሀራ ነኝ” ሲሉ “ክርስቲያን ነኝ” ማለታቸውም እንደሆነ በመግለጽ ክርስቲያን ከሚለው ጋርም ያመሳስሉታል። እርግጥ ነው ይህን አጠራር ብዙ ሰው ሲጠቀምበት ይስተዋላል።

የዐምሀራነትና የክርስቲያንነትን “ተመሳስሎሽ” በተመለከተ አንድ ክርስቲያን የሆነ ትግራዋይ ወይንም ኦሮሞ “ሃይማኖትህ ምንድን ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ መቼም ቢሆን “ዐምሀራ” ሊል አይችልም። ለነገሩ በዐምሀራ ክልል ውስጥም የሚገኙ ክርስቲያኖች “ሃይማኖታችሁ ምንድን ነው?” ሲባሉ በተለይ አሁን አሁን “ዐምሀራ ነኝ” አይሉም። ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ሙሉወንጌል ወዘተ ይላሉ እንጂ። በመሆኑም እየተቀየረ መሔዱንም መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

ሊቃውንት ከሥርወ-ቃሉ በመነሳት ትርጉም የሰጡት ዐምሀራ የሚባል ቢያንስ ሕዝብ በመኖሩ ነው። የአለቃ ታዬም የዐምሀራን ሕዝብ ከየት መጣነት (ከላስቶች ወታደር እንደተገኘ) አስረዱ ከማለት ውጭ “የለም” አላሉም። ሊቃውንት ዐምሀራ የሚባል ብሔር ወይንም ሕዝብ “የለም” አላሉም።ትርጉምን የሰጡት ቢኖር ይመስለኛል።

ታዲያ አብዝሃኛው ዐምሀራ ስለብሔሩ ሲጠየቅ ‘ዐምሀራ ነኝ’ ማለት ለምን አይቀናውም ለሚለው ጥቂት ምክንያቶችን ላቅርብ።

ለዐምሀራ እንደብዙዎቹ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጥንት አባትና እናት/የጋራ የዘር ግንድ አለኝ ሲል አይሰማም። የጋራ የዘር ግንድ ላይ የተመሠረተ የጋራ አፈታሪክና ተረት ሲትርክ አይስተዋልም። ጎሳ፣ ነገድና የመሳሰሉትም ቅድመ-ብሔር ዝግመተ-ለውጣዊ ዕድገት እንደሌሎቹ በርካታ ብሔሮች በዚህ ቢያንስ በዚህ ዘመን የለም፤በተጨማሪም በሰነዶችም ላይ መገኘቱን አላውቅም።

ይህ ሁነት አለመኖሩ ወይንም አለመከሰቱ፣ወይንም እነዚህን ማኅበራዊ መዋቅሮች መሻገሩ፤ ዐምሀራ እንደ አንድ የተለየ ብሔር የብሔርተኝነት ስሜትና የአንድነት መንፈስ እንዳያሳድግ አልበለዚያም ይዞ እንዳይቆይ አድርጎታል ማለት ይቻላል።

ለብሔርተኝነት ሌላው ምንጩ ጭቆና ነው። እንደሌሎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች፣ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተራዘመ ጭቆና ስላልደረሰበት ይህ ስሜቱ አላደገ ይሆናል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናውኑ ካሉት አድራጎቶች ይህንን ለውጥ መኖሩን ማጤን ይቻላል። በውጤቱም የዐምሀራ ብሔርተኝነትን አሁን ባለው ደረጃ ላይ ያደረሰው መሆኑን መገንዘብ ቀላል ነው።

ሦስተኛው ምክንያት ዐምሀራ ባለፈው መቶ ዓመት በተለይም በባህል ረገድ ጭቆና ስላልነበረበት በሌሎች ሀገራት እንደተስተዋለው ባህላቸውን ወደሌሎች እንደሚያስተላፉ ብሔሮች እራሳቸውን እንደነጠላ የሰው ልጅ (ዜጋ) እንጂ እንደ ቡድን አለማሰባቸው፣ እንደ ዜጋ እንጂ እንደ ብሔር ወይም ነገድ በመሰባሰብ ዘር ባለመምዘዛቸው ምክንያት ነው ። ዐምሀራም ልክ እንደሌሎች በዚህ ሒደት ውስጥ እንዳለፉ ብሔራት ተመሳሳይ ታሪክና እሳቤ አለው ማለት ይቻላል። ዐምሀራ በዘር አይሰባሰብም፤ ዘሩን ሳይሆን ርስቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ሚስቱን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ የክተት ነጋሪት ሲጎሰም ወደኋላ ብሎ የማያውቅ ሕዝብ ነው። ደግሞም የትም ዘምቷል፤የትም ለምዷል።

ሌላው ስለብሔር ስናነሳ የብዙኃኑ ስለብሔሩ ያለውን ንቃት እንጂ የልሂቃኖች መንቃት ብቻ አለመሆኑ ነው። የብዙኃኑን ንቃት ለማምጣት ደግሞ በተለያዩ ኩታገጠም ቦታዎች እያረሱ ከብት እያረቡ በዚያው አካባቢ ባለ የገበያ ቦታ እየተገበያዩ በአንድነት በሚኖሩ፣ ባልተማሩ ኅብረተሰቦች ዘንድ፣ ትራንስፖርትና ሌሎች መገናኛ ዘደዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በቀላሉ የሚፈጠር አይመስልም። የራሱን ማንነት እየተረዳና እያወቀ የሚመጣው ከሌላው ጋር በሚፈጥረው ግንኙነትና መስተጋብር ነው። እርስ በርሱ ብቻ የሚገናኝ ኅብረተሰብ ብሔርተኝነት መሰባሰቢያው አይደለም፤ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ፈረንሳይ ናት።

በ1870ዎቹ ፈረንሳይ ውስጥ የፈረንሳዊነት ስሜት አልነበረም። እራሳቸውን በአካባቢያቸውና በመሳሰሉት ነገሮች ነበር የሚለዩት። ከናፖሊዎን ወታደርም ቢያንስ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የውጪ ቅጥረኞች ነበሩ። ገበሬው የፈረንሳይ ሕዝብ የፈረንሳዊነት ስሜት ስላልነበረው “ለእናት ሀገሬ ፈረንሳይ” ብሎ የሚዋጋበት ደረጃ ላይ እንኳን አልደረሰም ነበር። ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ ነው ፈረንሳዊነት እያደገ የመጣው። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሁኔታ ከፈረንሳዮቹ ጋር ይለያያል። የአድዋን ጦርነት ያስታውሷል።

ሁኔታው ሰፋ ባለ ቦታ/ክልል ለሚኖሩ ለማንኛውም ብሔር የሚሠራ ቢሆንም ከላይ ከ1-4 ተጠቀሱት ምክንያቶች ሲታከሉባቸው ግን ለዐምሀራ የበለጠ ይሰራል ባይ ነኝ።

ብዙ ሰዎች (ከላይ የተገለጹትን ንቡረ-እድ ኤርምያስና ምንአልባትም እንዳገላለጻቸው ከሆነ አባ ዮሐንስም) ዐምሀራነትና ኢትዮጵያዊነትን አንድ የማድረግ አዝማሚያ ይታያል። ዋናው ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው። መጠናትም የሚገባው ይሔው ነው። አብዝኃኛው የዐምሀራ ልሂቃን (በተለይ የገዥው ፓርቲን የሚቃወሙት) መገንጠልን፣ ብሔርና ቋንቋን መሠረት ያደረገ አስተዳደር ለምን ይቃወማሉ? ለምንስ ብሔራቸውን ሲጠየቁ፣ አሁን እንኳን እየቀነሰ እንደመጣ ቢታወቅም፣ “ኢትዮጵያዊ” ማለት ይቀናቸዋል? በሌላ አገላለጽ ለምን “ዐምሀራ ነኝ” ማለት አይፈልጉም?

ሀገር ማቅናት ወይንም አንዲትን ሀገር አሁን የያዘችውን ቅርጽ እንዲኖራት አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብሎ የሚያስብ ብሔር እራሱን የሚጠራው በሀገሪቱ ስም፣ ራሱን የሚቆጥረውም እንደዜጋ እንጂ፣እንደ ብሔር አይደለም። በስፔን የሚኖሩ ካስቲሊያን፣ ስፔን የአሁን ይዘቷን እንድትይዝ ፊታውራሪዎች ስለነበሩ ራሳቸውን እንደካስቲሊያን ከመውሰድ ይልቅ ስፓንያርድ (ስፔናውያን) ማለት የሚቀናቸው ሲሆን ብሔርነታቸው ሳይሆን ዜግነታቸው ይቀድምባቸዋል። ካታሎንያን፣ ባስኮች፣ ቫሌንሽያዎች እራሳቸውን በብሔራቸው ሲጠሩ ካስቲሊያኖች ለፍተን እዚህ ያደረስናትን ስፔንን ሊገነጣጥሉ ነው ብለው ያስባሉ።

የእንግሊዞችም የብሔርተኝነት ስሜት ከዐምሀራ ጋር ተመሳሳይ ነው። ዌልስና ስኮትላንዶች ራሳቸውን ዌልሳዌና ስኮትሽ በማለት ሲጠሩ እንግሊዞች ግን የላላ ብሔርተኝነት ስላላቸው እራሳቸውን ከታላቋ ብሪታኒያ ነጥለው እንግሊዛዊ ማለትን አይፈለጉም ነበር። ይሔንን ንጽጽር ክርስቶፎር ክላፕሃም ጥሩ አድርጎ ጽፎታል። በኢትዮጵያም ብዙዎች “አባቶቻችን ለፍተው ለፍተው መና ቀሩ፤ አንቀጽ 39 የእነሱን ልፋት ከንቱ ማድረጊያ ስልት ነው” ብለው ያስባሉ።

ሲጠቃለል የዐምሀራ ልሂቃንም ይሁኑ (በተወሰነ መልኩ ሕዝቡም) ይህን ዓይነት ስሜት ያንጸባርቃል ማለት ይቻላል። የእነ ንቡረ-ዕድ ኤርምያስ አተረጓጎምም ከዚህ ጋር ይሔዳል።

ከላይ በቀረቡት ምክንያቶች ለማሳየት የሞከርኩት የዐምሀራ ሕዝብ ራሱን ዐምሀራ ነኝ ብሎ ሲጠራ አለመስተዋሉ ዐምሀራ የሚባል ብሔር የለም የሚያሰኝ አለመሆኑን እና ተያያዥ ምክንያቶችን ነው።

የበፍቃዱ ኃይሉ፣ስለማንነት የሰጠው የተሳሳተ ትርጓሜ እንዲሁም ቋንቋው በ13ኛ ክፍለ ዘመን፣ብሔሩ በ7ኛው ወዘተ በማለት ያቀረበውን በሌላ ጊዜ እመለስበት ይሆናል።

በጉዳዩ ላይ የበለጠ ለመረዳት የሚከተሉትን ጽሑፎች ማንበብ ነው፡፡

ማጣቀሻ፡-

Connor, Walker (1972) “Nation-Building or Nation-Destroying?” World Politics, Vol.24,No.3.
Connor, Walker, (2004) “The timelessness of nations” Nation and Nationalism, Vol.10.
Connor, Walker. (1984) The National Question in Marxist-Leninist Theory and Strategy, Princeton, NJ: Princeton University Press.

Connor, Walker.(1980), “Nationalism and Political Illegitimacy”, Canadian Review of Studies in Nationalism. VII (Fall 1980). Eugen. Weber, (1976) Peasants into Frenchmen: The Modernization of Rural France, 1870–1914. Stanford, Calif.
Gellner, Ernest (1987) Nationalism. London, Weidenfeld and Nicholson.
Hayes, H.(1931) The Historical Evolution of Modern Nationalism. New York: Macmillan.
Lenin, I.Viladmir The Right of Nations to Self-determination, Collected Works, Vol.20.
Smith, D. Anthony (1999), Myths and Memories of the Nation, Great Britain, Oxford University Press.
Chirstoper Clapham (1988), Transformation and Continuity in Revolutionary Ethiopia. Cambridge: Cambridge University Press, Pp.23-24.

Walker Connor (2004) “The timelessness of nations” Nation and Nationalism, Vol.10. 35-47, P.40.

Weber, Eugen. (1976) Peasants into Frenchmen: The Modernization of Rural France, 1870–1914. Stanford, Calif.,

Tegegne Teka(1998),”Amhara Ethnicity in the Making”, in M.A.Mohamed Salih and John Markakis (eds) Ethnicity and the State in East Africa,Nordiska:Afrikainsitutet.Uppsala,PP.116-126.

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የአማራ ሕዝብ ባህልና ቋንቋ፣ባሕር ዳር 2001፣ ገጽ VI።

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም፣ (2003)፣ የክህደት ቁልቁለት፣ አዲስ አበባ፣2ኛ እትም፣ ከገጽ 120-124።

Siegfried Pausewang (2009) “Political Conflicts in Ethiopia– in View of the Two-Faced Amhara Identity” In: Svein Ege, Harald Aspen, Birhanu Teferra and Shiferaw Bekele,(eds) Proceedings of the 16th International Conference of Ethiopian Studies, Trondheim ፓስዋንግ የዐምሀራ ሁለት የማንነት ገጽታዎች የሚላቸው ኢትዮጵያዊነትና ዐምሀራነትን ነው።

 

 

 

 

ማጣቀሻ፡-