ቤተሰብን በልጆቹ ላይ እንዲህ ምን አስጨከነው? አብዛኛው ቤተሰብ እንብላው እንብላው ሆኗል ቅኝቱ እያሉ ሲያማርሩ የሚሰሙት ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም። ኑሮው ይሆን በልጆቻቸው በእህቶቻቸው.. በፍቅረኞቻቸው ያስጨከናቸው?..ወይስ ሴቶቹ አረብ ሀገር ለፍተው..ደም ተፍተው የሚልኩት ሳንቲም ጥሟቸው? የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው አይነት ምንም ስሪ ብቻ ላኪ የሚሉ ቤተሰቦች እንዳሉ እየተሰማ ነው። ምንድነው የተጨካከንበት ምክንያት…እንጃ እስኪ.. ከነገሩኝ ታሪክ አንዱን ላስነብባችሁ….

አንድ ጽሁፌን ያነበበች ልጅ ኮመንት ያደረገችው ገርሞኝ ልጽፍላት ሳስብ በውስጥ ‹‹ቁስሌን ነካኸው። ታሪኬን አውቀህ የጻፍክ መሰለኝ። ይገርማል ሁሉም ቤተሰብ ነው ለካ ልጁን ሊሽጥ የተነሳው።..›› የሚል መልዕክት ትታልኛለች። ሁሉም ቤተሰብ እንኳ አይደለም ጥቂት ቤተሰቦች ናቸው። ለመሆኑ አንቺንም ሊሸጡሽ አስበው ነበር ስንት ተመኑሽ…አይ የኔ ነገር ለወሬ ቸኩዬ ሰላም ሳልልሽም…እያልኩ ቀልጄ ጻፍኩላት። ብዙ ጊዜ ቻት ሲያረጉኝ ነጻ ሆነው በጓደኝነት ስሜት እንዲያወሩት መቀለዴ የተለመደ ነው። ብዙዎቹ ነጻ ሆነው ሲያዎሩኝ አንዳንዶቹ ቀልዴ ፍልጥ ፍልጥ ይላቸዋል መሰለኝ ፍልጥ ስድብ ያስታቅፉኛል። ታዲያ ተሳድበውም ቢሆን እንግባባለን።..

‹‹ውይ እኔም ሰላም አላልኩ ነገር ይዞኝ..›› ብላ ብዙ አወራን። ያወራችኝን አጠር አድርጌ ላስነብባችሁ።

‹‹ሰፈሬ ከቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በላይ ሾሌ ቤት ይባል የነበረውን ታውቀዋለህ?››

“ይቅርታ ሾሌ ነው ሾላ? ያልሽኝ አልገባኝም?..” ሳቋ በሀሳቤ ታየኝ.. ..kkkkk የሚል ብዙ ልካልኛለች። ለጥቃ..‹‹ጥላሁንን ገሰሰ ሾሌያ ነጪ ጠላ ብሎ የዘፈነለት ያ-ሾሌ የተባለ ጠላ ቤት..›› ምልክት ነገረችኝ። አለማወቄን ነግሬያት ብዙ አስረድታኝ ሰነፍ ተማሪ ሆኜባት ወደ ሌላኛው ወጓ ገባች።

‹‹ብቻ ምን አለፋህ ከሰፈር 3 ሆነን በተቀራራቢ ጊዜ ዱባይ ሄድን። እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ከእኛ ቀድመው የሄዱ ልጆችን ስልክ ቁጥር ይዘናል። ሁለቱ ልጆች ከኮንትራት ቤት(ከማዳም ቤት) ጠፍተው (ራን አዌይ) ሆነው ለመስራት ሁለትና ሶስት ወር ነው የፈጀባቸው፡፡ በየጊዜው የላኩት ብር እኔ ከምልከው ጋር አይመጣጠንም።እንድጠፋ ደጋግመው ቢመክሩኝም እኔ አልፈልኩም። የሚከፈለኝ ትንሽ ቢሆንም ሴትዮዬ በጣም ጥሩ ነች። ምንም አትበድለኝም። መዝናኛ ቦታ ሲሄዱ እንኳን እንደሰራተኛ አታየኝም። ከልጆቿ ጋር እንድዋኝ የዋና ልብስ ሁሉ ገዝታልኛለች። ለልጆቿ ልብስ ስትገዛ ለእኔም..ምን አለፋህ እንደ ቤተሰብ ነው የሚያዩኝ።

ሶስት አመት ከስድስት ወር ቆይቼ ወደ ሀገር ቤት ሄድኩኝ። ጊዜዬን አሳልፌ የቆየሁት ግን በገዛ ፍቃዴ ነው። እኔ እናቴ ናፍቃኝ እህት ወንድሜ ናፍቀውኝ ልመጣ ይሄን ያህል ጊዜ ቀረኝ ስላቸው ቆይ ይሉኛል። መጥተሽ ምን ትሰሪያለሽ ገንዘብ ማባከን ነው ይሉኛል።
‹‹በመጨረሻም ስሄድ እከሊት ይህን አረገች፣ ይህን ሰራች አንቺ… እከሊት ለወንድሟ ላዳ ታክሲ ገዝታ…አቤት የማይሉት የለም። በተለይ እህቴ። እነሱ የሚሰሩት እንደ እኔ አይደለም። ጥፍተው የሚሰሩት መጥፎ ስራ ነው…እህቴ አላስጨረሰችኝም።
‹‹…ታዲያ አንቺስ እንደእነሱ አትሰሪም እድሜሽን ጨርሰሽ..ትንሽ ይዘሽ ከመምጣት..?” አለች፡፡ እኔ አልፈልግም ክብሬን ጠብቄ እንደአሁኔ ነው የምቀጥለው፡፡..ተረኛ ሆና ንግግሬን ያቋረጠችኝ እናቴ ነበረች።
“አንቺ እንዳትሰሪ ምን ያዘሽ ክብሬን ምንጥሴ ትያለሽ…ትዳሬ አትይ አልሆነም፡፡ ራስሽን ለውጠሽ እኛንም ትለውጫለሽ…..” አሁን አባባላቸው ገባኝ። ለካ ጠፍተው የሚሰሩት መጥፎ ስራ ነው ስል ሽርሙጥና ነው የሚሰሩት ያልኳቸው መስሏቸው እንድሸረሙጥ እየገፉኝ ነው።
በመካከል እኔም‹‹ሁለቱ ጓደኞችሽ የሚሰሩት ምንድን ነው?›› አልኳት፡፡
‹‹እኔንጃ መደብር ነገር መሰለኝ።ማለቴ ድርጅት ነገር እንጂ ሽርሙጥና አይመስለኝም…እኔ እነሱ የሚሰሩት ጥሩ አይደልም፣ መጥፎ ስራ ነው ያልኩት ህጋዊ ስላልሆኑ ተሸማቆና ተደብቆ የሚሰራ በመሆኑ ነው፡፡ ወደ ሀገር ሲገቡም ገና ለፖሊስ እጅ ሰጥተው ታስረው ነው፡፡ እጅ በመስጠትና በመታሰሩ መካከል ያለውን ከእኔ ጋር በአንድ አውሮፕላን ተሳፍራ የነበረች ልጅ ነግራኛለች፡፡ እርግጥ ኮንትራት ቤት ሆነህ እና ውጭ የሚከፈለው አንድ አይደለም፡፡ በእጥፍ ነው ለውጡ፡፡
እናቷ “..ትዳሬ አትይ አልሆነም..” ያሉትን አስቤ ‹‹አግብተሽ ነበር?›› አልኳት
‹‹ትዳር በእኛ ሰፈር ትላንት አልፎ ነበር..›› አለችና በአጭሩ ዘጋችው። አባባሏ ግን ተመቸኝ። ግን ቁስለትም ጥላሸትም ያለው መሰለኝ።
እስኪ ስለትዳርሽ አውሪኝ..
‹‹ዱባይ ከመምጣቴ በፊት አንድ ፍቅረኛ ነበረኝ። ትንሽ ጊዜ ከእሱ ጋር አንድ ቤት በመኖር አሳልፌያለሁ
‹‹የእሱም የእኔም ቤተሰቦች ውጥር አድርገው ሊያራርቁን ሲሞክሩ ችሎት የሚባለው አካባቢ ትንሽ ቤት ተከራይተን የቀን ስራ እየሰራን አመት ከ7 ወር አብረን ኖርን። ቤተሰብ የገባበት ነገር ውሎ አድሮም ቢሆን ጤና አይኖረውም። ተለያየን።
‹‹ከዛም ዱባይ መጣሁ። አሁን ከዱባይ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ለአንድ ወር ነበር የሄድኩት፡፡ በአምስተኛው ቀን ያን ተናገሩኝ። ወጥቼ መድኃኒዓለም ሄጄ አልቅሼ በማግስቱ ወደ ዱባይ ለመመለስ ትኬቴን 50 ዶላር ጨምሬ ኦኬ አስደረኩና ሻንጣዬን እንኳን ሳልይዝ በዛው ሆቴል አድሬ ዱባይ መጣሁ፡፡ ድጋሚ ከመጣሁ ስልክ እንኳን እልደወልኩም።ገላሽን ሸጠሽ ለውጪን የሚል ቤተሰብን ቤተሰቤ አልልም ብዬ 5 አመቴ አልደውልም።..በሰማሁት ነገር መጥፎ ስሜት ቢሆንም የተሰማኝ ከቤተሰብ መራራቁ ጥሩ አይደለም…እናትሽም ያለማወቅ ነው ብዬ ትንሽ መካክሬያት ተለያንየን…
በርካታ እንዲህ አይነት አስከፊ ጠባሳ ጥለው ያለፉ ታሪኮችን አቅርቤያለሁ፡፡ እንዴት ነው ቤተሰብ የልጁን ደም የሚመጥበት ሁኔታ እየሰፋ መጣ።

እሱም አልበቃ ብሎ ገላሽን ሽጭ በይፋ…ያሳፍራል፡፡