ዩንቨርሰቲው ዛሬ ባወጣው ጽሑፍ ሁሉንም የ4ኛ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪዎች (ቴክስታይልን ሳይጨምር) አባርሪያለሁ የሚል መልክት አስተላልፏል፡፡ ቁጥራቸው 2000 (በተማዎች መሠረት) የሚሆኑት እነዚህ ተማሪዎች ከአርብ ምሽት በኋላ ምግብ ተከልክለው ቆይተው ዛሬ በፖሊስ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

መንስኤው ሆልስቲክ የሚባለውን ፈተና ዩንቨርሲቲው ተፈተኑ ሲል እነርሱ ደግሞ አንፈተንም ማለታቸው ነው፡፡ የዩንቨርሲቲው አካላትና ተማሪዎቹ የሚያቀርቡት ምክንያት የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዩንቨርሰቲው በርካታ ተማሪዎችን ባነጋገርኩት መሠረት ‹‹ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት ፈተናውን ተፈተኑ ነው የተባልነው፤ በዚያ ላይ ውጤት ዝቅተኛ ያመጣ ተማሪ የሥራ ልምምድ አይመደብም፡፡ ይህ በእኛ ዩንቨርሲቲ ብቻ ነው እየሆነ ያለው›› ሲሉ ሁለት የሚሆኑ የምህንድስና አስተማሪዎችን አነጋግሬ ተመሳሳይ መልስ ሰጥተውኛል፡፡

ዩንቨርሲቲው የሚለው ደግሞ ለባለፉት በርካታ ዓመታት ፈተናው ሲሰጥ እንደቆየና የተለየ እንዳልሆነ ነው የገለጸው፡፡ አንድ መምህር ደግሞ የማለፊያ ነጥቡ ከ50 ወደ 37ም ዝቅ ተደርጎ ተማሪዎች ሊፈተኑ ፈቃደኛ አይደሉም ብሏል፡፡

በዚህ መካከል ዩንቨርሲቲው ተማሪዎቹን በጅምላ አባሯል፤ ባለፈው ሳምንት በነበረው የሴኔት ስብሰባ ላይ የነበረው ውይይት ተማሪዎችን ከማስረዳት ይልቅ የፌደራል ፖሊስን አስገብቶ ማስፈራራት የሚል መንፈስ የነበረው ነው፤ ከዚያ ተሳትፈናል ያሉን ሰዎች የተናገሩት፡፡ ያም ሆነ ይህ ተማሪዎች ወጥተው በየቦታው ሻንጣቸውን ተሸክመው ሲገኙ አሁንም በፖሊስ እየተደበደቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የዩንቨርሲቲው አመራሮች ሁኔታውን ሳሳውቅ መፈተናቸውን ለምንድን ነው የምትቃወም የሚሉ መልእክቶች ልከውልኛል፡፡ እኔ ፈተና ይፈተኑ ወይም አይፈተኑ የሚል መልእክት አላስተላለፍኩም፤ መብቱም የለኝም፡፡ ሆኖም ግን አካዳሚያዊ ነጻነትን መጋፋት ነው የሚሉትን ያክል ተማሪዎች መባረር አለባቸው የሚል እምነትም የለኝም፤ በተለይ ደግሞ ድብደባው የሰብአዊ መብት ረገጣ ነው፡፡ አንድ ትልቅ ነኝ ብሎ የሚያምን ዩንቨርሲቲ ሁሉንም ተማሪዎች አባርሬያለሁ ብሎ እንደጀብድ ሲያወራ ግን ያሳፍራል፡፡ ተማሪዎቹ ፈተናውን ቢፈሩ ድክመቱ የዩንቨርሰቲው የማስተማር ጥራት ጉድለት ነው የሚመስለኝ፡፡

Source – Muluken Tesfaw