ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖች የእርዳታ አሰጣጥ ሁኔታ አሁንም ችግር እንዳለበት ተጠቆመ፡፡ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የድንበር አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወቃል፡፡ ከሶማሌ ክልል ቁጥራቸው በርካታ የሆነ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ተፈናቃዮቹ በሐረር እየሰፈሩ ቢሆንም፣ ከእርዳታ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ግን ችግሮች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከሶማሌ ክልል ከተፈናቀሉ በኋላ ወደ ሐረር የተጓጓዙ የኦሮሞ ተወላጆች፣ በቂ እርዳታ እያገኙ አለመሆናቸውን መረጃዎችን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ አሁን ላይ ያለው የእርዳታ አሰጣጥ ሁኔታም ብዙም አስደሳች አለመሆኑን የሚናገሩት ተፈናቃይ ወገኖች፣ የተፈናቃዩ ሰው ቁጥር እና የእርዳታው መጠን መሳ ለመሳ እየሔደ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ተፈናቃዮቹን ለማስጠለል በሐረር የተለያዩ አካባቢዎች ድንኳኖች የተጣሉ ሲሆን፣ ተፈናቃዮቹም እዚያ ውስጥ እንዲሰፍሩ እየተደረገ ነው፡፡

ተፈናቃዮቹ እየገጠማቸው ያለው ችግር የምግብ እና የመጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከመጠለያ ጋር የተገናኘ ችግር እንዳለም ይናገራሉ፡፡ የተፈናቃዩ ሰው ቁጥር በርካታ ቢሆንም፣ ለመጠለያነት የተዘጋጁት ድንኳኖች ግን አነስተኛ መሆናቸውን ተፈናቃዮቹ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በተለይ ህጻናት እና እናቶች ከሌላው በተለየ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ተፈናቃዮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድንበር ላይ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሁለቱም ወገን ሲፈናቀሉ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡ (BBN news)