መነሻውን ሰሜን ኮሪያ መዳረሻውን ግብጽ ያደረገ የጦር መሳሪያዎችን የጫነ መርከብ በቁጥጥር ስር ዋለ

የአሜሪካ መንግስት በነሀሴ ወር ውስጥ ከሰሜን ኮሪያ ተነስቶ ግብጽ ሊገባ የነበረ የጦር መሳሪያ የጫነ መርከብ ከነሠራተኞቹ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ከየትኛውም የዓለማችን ሀገራት ውግዘት እየደረሰባት ከምትገኘው ሰሜን ኮሪያ አፍሪካዊቷ ግብጽ የፈጠረችው ወታደራዊ ግንኙነት አሜሪካን አስቆጥቷል፡፡

ግብጽ ምስጢራዊ በሆነ መልኩ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ተቀባይነት የለውም በማለት ዋሽንግተን ለካይሮ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች፡፡

ከሰሜን ኮሪያ ተነስቶ በስዊዝ ካናል በኩል ወደ ግብጽ ሊገባ የነበረው መርከብ የካምቦዲያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ለማደናገር ተጠቅሞበታል ተብሏል፡፡

ከ3 ቀናት በፊት ነገሩን ለዓለም ግልጽ ያደረገው ዋሽንግተን ፖስት ግብጽ ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎችን ከሰሜን ኮሪያ ለማስገባት መሞከርዋ የሁለቱን ሀገራት ፖለቲካዊ ግንኙነት ሊያሻክረው ይችላል ብሏል፡፡

የግብጹ ኢጂፕት ኢንዲፔንደንት እንዳለው ደግሞ ግብጽ አሜሪካ ያዝኩት ያለችው የጦር መሳሪያ ከእኔ ጋር አይገናኝም ከሀገሪቱ ጋርም ግንኙነት የለንም ማለቷን ዘግቧል፡፡
አሜሪካ የግብጽ ወዳጅ ሀገር ነች፡፡ይሁን እንጂ በቅርቡ ወታደራዊ እርዳታዋን መቀነሷ ይታወቃል፡፡

ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ተደጋጋሚ የሚሳይል ሙከራ ማድረጓ ከዓለም ዙሪያ ውግዘትን አስከትሎባታል ፡፡