Skip to content

በተቃውሞ መፈክሮች ታጅቦ በሰላም የተጠናቀቀው የኢሬቻ በዓል

በተቃውሞ መፈክሮች ታጅቦ በሰላም የተጠናቀቀው የኢሬቻ በዓል

በተቃውሞ መፈክሮች ታጅቦ በሰላም የተጠናቀቀው የኢሬቻ በዓል

October 4 2017

ዘመኑ ተናኘ

ሙሉነህ ገላን (የአባቱ ስም ተቀይሯል) የሰላሳ አራት ዓመት ወጣት ነው፡፡ ተወልዶ ያደገው ቢሾፍቱ ከተማ ነው፡፡ ከአንደኛ እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱንም የጨረሰው በዚች ከተማ ነው፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመማር ሐሮሚያ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ለሦስት ዓመት ያህል ቢሾፍቱን ለቆ ቆይቷል፡፡ ከተመረቀ በኋላ ደግሞ ለአንድ ዓመት ያህል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ካሉ ስሙን መጥቀስ በማይፈልገው ወረዳ፣ በአንዱ ተቀጥሮ በመንግሥት ትምህርት ቤት ሠርቷል፡፡ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ ተመልሶ ወደ ትውልድ አካባቢው ቢሾፍቱ በመሄድ በግል ትምህርት ቤት ተቀጥሮ እየሠራ ነው፡፡በየዓመቱ መስከረም ወር መጨረሻ ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ሲመጣ ልዩ ስሜት እንደሚሰጠው ይናገራል፡፡

የኢሬቻ በዓል ወደ ሆራ አርሰዴ ሐይቅ በመሄድ ከአሥር ዓመታት በላይ እንዳከበረ ይገልጻል፡፡ በዓሉ በመጣ ቁጥር ለምለም ቄጤማ ይዞ ወደ ሐይቁ በመሄድ ፈጣሪን ከማመስገን ባሻገር፣ ከኦሮሚያ ክልል ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጣው ሕዝብ የሚፈጥረው ድባብ የተለየ ስሜት እንደሚሰጠው ያስታውሳል፡፡ ‹‹ኢሬቻ የምሥጋና በዓል ነው፡፡ ሰው ለምለም ቄጤማ ይዞ ወደ ሆራ አርሰዴ ሐይቅ በመሄድ ክረምቱ በሰላም በማለፉ ለፈጣሪ ምሥጋና የሚያቀርብበት ቀን ነው፡፡ ዓመቱንም የሰላም እንዲያርግለት የሚጸልይበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ በዓል ደግሞ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚመጣ ይነገራል፤›› ሲል ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡ ‹‹በዓሉ በየዓመቱ መስከረም ወር መጨረሻ ላይ በጉጉት የሚጠብቅ ቢሆንም፣ ካለፈው ዓመት ወዲህ ግን ነገሮች ተቀይረዋል፤›› ሲልም አክሏል፡፡

ወጣት ሙሉነህ ባለፈው ዓመት በበዓሉ ላይ ያጋጠመውን አሳዛኝ ክስተት ማስታወስ አይፈልግም፡፡ ‹‹የስንት ወንድሞቻችን ሕይወት ነው ያለፈው፡፡ ያ ቀን በከተማችን ዳግመኛ እንዳይመጣ የዘወትር ፀሎቴ ነው፤›› ሲል በሐዘኔታ ይናገራል፡፡ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ካለፉት ዓመታት ልዩ እንደነበር ታዳሚዎች ይገልጻሉ፡፡ በቅድመ ዝግጅቱም ሆነ በበዓሉ ዕለት የነበረው የበዓል ድባብ የተለየ እንደነበርም ያክላሉ፡፡ ከዚህ በፊት በዓሉ የፖለቲካ ይመስል የመንግሥት ባለሥልጣናት የተለመዱ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳዎችን ለማሰማት ስለልማቱ፣ ህዳሴው፣ ትራንስፎርሜሽኑ፣ ወዘተ ይገልጹ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በዘንድሮው በዓል ላይ ባለሥልጣናትና የታጠቁ የፀጥታ አካላት ባለመገኘታቸው የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡የቢሾፍቱ ከተማ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ለማክበር ቀደም ሲል ስትዘገጃጅ እንደነበር ሪፖርተር ከዋዜማው ጀምሮ በቦታው ተገኝቶ ለማረገገጥ ችሏል፡፡ ቅዳሜ መስከረም 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከተማዋ በእንግዶችና በባህላዊ ልብሶች በተዋቡ ወጣቶች አመሽታለች፡፡ በሆቴሎችና በሬስቶራንቶች ተከፍተው የነበሩ ሙዚቃዎች፣ ሴቶች በአንገታቸው፣ በእጃቸውና በእግራቸው የተዋቡባቸው ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች የበዓሉን ድባብ ከዋዜማው ጀምሮ ሞቅ አድርገውት እንደነበር ለማየት ተችሏል፡፡ በየቦታው የሚሸጡ የእጅና የአንገት ጌጣጌጦች ዋዜማውን ዋነኛ የገበያ ቀን አስመስለውት ነበር፡፡ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ክብ ሠርተው በባህላዊ ጭፈራ ታጅበው በከተማዋ ላይ ታች ሲሉ የዋዜማው ድምቀት ሆኖ ነበር፡፡

 ሪፖርተር ተዟዙሮ ከተመለከታቸው ቦታዎች ውስጥ ባለፈው ዓመት በዓሉ ሲከበር ተፈጥሮ በነበረው ድርጊት የበርካቶች ሕይወት ያለፈበት ሥፍራ አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ለሞቱ ሰዎች ምክንያቱ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በሐይቁ ዙሪያ የነበረው ገደላማ የመሬት አቀማመጥ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡ አካባቢውን ተዟዙሮ ለማየት እንደተቻለው ገደላማ የነበረውና የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈው አካባቢ በአሁኑ ወቅት ተስተካክሏል፡፡ መሬቱ ተስተካክሎ ለአደጋ ምክንያት እንዳይሆን ተደርጓል፡፡ በዋዜማው ይህን አካባቢ የፌዴራል ፖሊስ በመሣሪያና በአነፍናፊ ውሾች አማካይነት ከፈንጂና ሌሎች ጉዳት ከሚያደርሱ ነገሮች ነፃ መሆኑንና አለመሆኑን ሲፈተሽና ሲያረጋግጥ ነበር፡፡ በዚህ አካባቢ የነበረው የዋዜማ ድባብም ጥሩ እንደነበር አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡  

የኢሬቻ በዓል ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ወጣት ሴቶችና ወንዶች በኅብረት ሆነው በጋራ በመጨፈር ወደ ሐይቁ የሚሄዱበት ዕለት መሆኑ ነው፡፡ አንድ ቡድን ከአንድ እስከ ሁለት መቶ የሚሆን ሰው በመያዝ በባህላዊና በዘመናዊ ጭፈራ በመታገዝ ወደ ሐይቁ የሚደርገው ጉዞ የሚያምር፣ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ አንድነትንና ኀብረትን የሚያሳይ እንደሆነ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡እሑድ መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእኩለ ሌሊት በኋላ የኦሮሞ ወጣቶች ወደ ሆራ አርሰዴ ሐይቅ ሲተሙ አድረዋል፡፡ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ የኦሮሞ ወጣቶች ባህላዊ ዜማ እያሰሙና እየጨፈሩ ወደ ሐይቁ የሚሄዱም ነበሩ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ወደ ሐይቁ ሲደረግ የነበረው ጉዞ የተጠናቀቀው ረፋዱ ላይ ነው፡፡ አባ ገዳዎች ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ በሆራ አርሰዴ ሐይቅ ተገኝተው በመፀለይና ለፈጣሪ ምሥጋና በማድረስ በቶሎ ተመልሰዋል፡፡ እንደ ወትሮው ሕዝቡ በሚሰበሰብበት ቦታ ተገኝተው ንግግር አላደረጉም፡፡

የዘንደሮውን የኢሬቻ በዓል ልዩ ከሚያደርገው ጉዳይ አንዱ ይኼ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በክልሉ ፖሊስ ታጅበው የመጡት አባ ገዳዎች በሰዓታት ልዩነት ተመልሰው ሄደዋል፡፡ከዚህ ቀደም በዓሉ የሚከበረው ታዳሚዎች በሙሉ ወደ ሐይቁ ሄደው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ወደ መሰብሰቢያ ቦታው በመሄድ አባ ገዳዎች የተለያዩ ምሥጋናዎችንና ምርቃቶችን እያሰሙ እንደነበር ታዳሚዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ዘንድሮ ግን ይህ ሲሆን አልታየም፡፡ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ጀምሮ የተሰበሰቡ ወጣቶች በዕለቱ የሃይማኖት ትምህርቶችንና ምርቃቶችን፣ እንዲሁም ምሥጋናዎችን ከመስማት ይልቅ በመፈክሮችና በተቃውሞች በመታጀብ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ውለዋል፡፡ ዕለቱ የሃይማኖታዊ በዓል የሚከበርበት ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ የሚተላለፍበት መስሎ ነበር፡፡በዕለቱ በርካቶች በአንድ ድምፅ መንግሥትን ሲቃወሙና መፈክሮች ሲያሰሙ ነበር፡፡ በዚህ የተቃውሞ ድምፅ ላይ ከወጣት እስከ ሽማግሌ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በሙሉ ተካፋይ ነበር፡፡  የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንደተከበረ ሲገለጽ ቢሰማም፣ ያለው እውነታ ግን የተገላቢጦሽ እንደነበር በሥፍራው ተገኝቶ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከዚህ በፊት አባ ገዳዎች ንግግር ያደርጉበት የነበረው ቦታ መፈክር በያዙና የተቃውሞ ድምፅ በሚያስተጋቡ ወጣቶች ተተክቶ ውሏል፡፡ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ በሥፍራው የነበሩ ታዳሚዎች እጃቸውን በማጣመርና የ‹‹X›› ምልክት በመሥራት ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ‹‹አማራ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ ወንድማችን ነው፣ ወያኔ ይውረድ››፣ ‹‹አቶ ለማ መገርሳን እናከብራቸዋለን››፣ ‹‹የታሰሩት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ይፈቱ››፣ ‹‹የኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን የገደሏቸውና ያፈናቀሏቸው የሶማሌ ዜጎች ሳይሆኑ መሪዎች ናቸው፣ እነሱ ለፍርድ ይቅረቡ፣›› ‹‹ኦሮሚያ የሚገባትን ጥቅም ማግኘት አለባት››፣ ወዘተ የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ውለዋል፡፡ በተቃወሞና በመፈክር በታጀበው በዚህ በዓል ላይ በፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ባንዲራ ተሰቅሎ ሲውለበለብ ታይቷል፡፡

ባንዲራው በሁለት ቦታ ላይ ተሰቅሎ ለሰዓታት ቆይቷል፡፡ የክልሉ መንግሥት ባንዲራ በውስን ግለሰቦች እጅ የታየ ቢሆንም፣ እንደ ኦነግ ባንዲራ ተሰቅሎ ሲውለበለብ አልታየም፡፡ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ባንዲራዎችም በዕለቱ በተለያዩ ሰዎች እጅ ተይዘው ታይተዋል፡፡ በዕለቱ ባንዲራዎቹ ሲውለበለቡ ቢውሉም፣ የፌዴራሉንና የክልል መንግሥታትን የሚወክሉ ባንዲራዎች አልታዩም፡፡ድንጋይ ውርወራም ሆነ ረብሻ ያልነበረበት ይህ በመፈክርና በተቃውሞ የታጀበው በዓል ዕለቱን አስፈሪ ድባብ አላብሶት ነበር፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች በአንድ ድምፅ እጃቸውን በማጠላለፍና አንድ ላይ በመቀመጥና በመነሳት ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ውለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በተለይም በቅርብ ጊዜ ወደ ሥልጣን የመጣውና በወጣት ኃይል የተደራጀው የአቶ ለማ መገርሳ ካቢኔ በብዙዎች ዘንድ ምሥጋና እየተቸረው ሲሆን፣ በዚህ ዕለት ወጣቱ በነፃነት በዓሉን እንዲያከብር ማድረጉ ሌላ የታሪክ ድል ባለቤት ያደርገዋል በማለት ታዳሚዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ በዓሉ ሲከበር የክልሉም ሆነ የፌዴራል የፀጥታ አካላት በአካባቢው አልነበሩም፡፡ የክልሉ የፀጥታ አካላት በዓሉ ከሚከበርበት በ500 ሜትር ርቀት አካባቢ የነበሩ ሲሆን፣ የፌዴራል የፀጥታ አካላት ግን ከዋዜማው በስተቀር በከተማዋ እንዳልታዩ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

 ድንጋይ ባይወረወርምና ጥይት ባይተኮስም የበዓሉ ሥነ ሥርዓት በተቃውሞ ማዕበል ሲናጥ ውሏል፡፡ ተቃውሞው ባለፈው ዓመት የሞቱ ሰዎችን ለማስታወስ በኅሊና ፀሎት ከመጀመሩም በላይ፣ የአንድን ወጣት እጅና እግር በመያዝ ወደ ገደል የመወርወር ትርዒት ታይቷል፡፡ከጠዋቱ ጀምሮ ወደ ሆራ አርሰዴ ሐይቅ ሲተሙ የነበሩ ወጣቶች በቡድን በቡድን በመሆንና ወደ ሐይቁ በመሄድ ሥርዓቱን ከፈጸሙ በኋላ፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ ተቃውሞው በሚካሄድበት ቦታ ተገኝተዋል፡፡ ቀኑን ሙሉ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ውለዋል፡፡ ከመድረክ ሆነው የሚመሩ ሰዎችን ድምፅ በመከተል ከፍተኛ የሆነ የተቃውሞ ድምፅና መፈክር ሲስተጋባ ውሏል፡፡ አቶ ለማ መገርሳን የሚያሞግሱ ድምፆች ከያቅጣጫው ተሰምተዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች አቶ ለማ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ከሆኑ ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ተጨባጭ ሥራዎችን ሲያከናውኑ እንደነበር የተለያዩ ሪፖርቶች ያመላክታሉ ይላሉ፡፡ የሚያደርጉት ንግግርም የብዙዎችን ቀልብ መግዛቱን ያስረዳሉ፡፡ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ በፊንፊኔ የኦሮሞ ባህል ማዕከል ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ካደረጉት ንግግርና በብዙዎች ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ከሰነበተው ጉዳይ መካከል፣ ‹‹እውነት ለመናገር በአሁኑ ወቅት ሕዝባችን የሚፈልገውን ከመሥራት ውጪ ምንም ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ለሁላችንም ግልጽ መልዕክት እያስተላለፈልን ነው፡፡ እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር አመራር ላይ ያለን ሰዎች የሕዝቡን ቃልና ፍላጎት ቸል ብለን ለመሄድ የምንሞክር ከሆነ አንድም ቀን ማደር እንደማንችል ሕዝባችን በግልጽ እየነገረን ነው፤›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ከመናገር ባሻገርም የተግባር ሰው ናቸው ሲሉ ብዙዎች ሲያሞካሿቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ በዓልም ታዳሚዎች ይህን እንዳስመሰከሩ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ አንድ የበዓሉ ታዳሚ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡‹‹አቶ ለማ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ባይሆኑ ኖሮ እንዳለፈው ዓመት የበርካቶች ሕይወት ይጠፋ ነበር፡፡ ድንጋይ ይወረወር ነበር፡፡ ከተማዋ በተኩስ ትሸበር ነበር፤›› ሲል ገልጿል፡፡ 

በዚህ በዓል ላይ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች በተለይም ፈረንጆች ይመጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ አለመምጣታቸውን ተዟዙሮ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም በዚህ በዓል ላይ ለመገኘት የመጣ የውጭ አገር ዜጋ እንዳላዩ ገልጸዋል፡፡ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ጀምሮ በሆራ አርሰዴ ሐይቅ የደረሱ የበዓሉ ታዳሚዎች እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ በተቃውሞና በመፈክር ታጅበው፣ በሰላም ወደ መጡበት ተመልሰዋል፡፡በዓሉ ከተከበረበት ቦታ በቅርብ ርቀት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የጣለው ድንኳን፣ የማኅበሩ መኪኖችና ዕርዳታ ሰጪዎች ይታዩ ነበር፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ የፀጥታ አካላት ግን በዙሪያው አልነበሩም፡፡ የፀጥታ አካላት በዓሉ ከተከበረበት ቦታ በአምስት መቶ ሜትር ርቀት ቢኖሩም ለታዳሚዎች ግን አይታዩም ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት በዚህ በዓል የበርካቶች ሕይወት እንደጠፋ የሚታወስ ሲሆን፣ የዘንድሮው በዓል ግን ያለምንም የፀጥታ ችግር ተጠናቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ለዚህ ሥራውም ምሥጋና እንደሚገባው በርካቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን በዓሉ ከተለመደው ወጣ ብሎ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመጃ እየሆነ መምጣቱ ብዙዎችን እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ በዓሉ ፈጣሪ የሚመሠገንበትና አባ ገዳዎች መርቀው የሚሸኙበት ቢሆንም፣ አሁን አሁን መልኩን እየቀየረ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመጃ እየሆነ ነው ይላሉ፡፡በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር መከበሩ ግን ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣንም፣ ‹‹በዓሉ በሰላም ተጠናቋል፡፡ በዚህ ሁኔታ መጠናቀቁ ደግሞ ለክልላችን ብሎም ለአገራችን ትልቅ ስኬት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዕለቱ የተገኙ የተቃውሞው ተሳታፊዎች በኦሮሞና በሶማሌ ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚሆን ገቢ ሲያሰባስቡ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል፡፡ የተፈናቀሉ የኦሮሞም ሆነ የሶማሌ ክልል ዜጎችን መንግሥት በአፋጣኝ እንዲያቋቋም ጠይቀዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ከ70 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ይታወሳል፡፡ እስካሁን ድረስም ከሶማሌ ክልልና ከሶማሌላንድ እየተፈናቀሉ የሚመጡ ዜጎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባለፈው ዓመት የኢሬቻ በዓል ሲከበር ከ50 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የሚታወስ ሲሆን፣ ለእነሱ መታሰቢያ የሚሆን ሐውልትም ከሆራ አርሰዴ ሐይቅ በቅርብ ርቀት ቆሟል፡፡ በሐውልቱ ላይም ‹‹Memorial Monument for Those Who Lost Their Life on October 02/2016›› የሚል መልዕክት ሠፍሯል፡፡የኢሬቻ በዓል ከተጠናቀቀ በኋላ በተቀውሞው ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች ቢሾፍቱ ከተማ ላገኟቸው የክልሉ የፀጥታ አካላት ምሥጋናና አድናቆት ሲያቀርቡ ተስተውሏል፡፡ የለበሱትን ባህላዊ ልብስና ጌጣጌጥ ለክልሉ ፖሊሶች ሲሸልሙና ሲሰጡም የታዩ ነበሩ፡፡ ታዋቂው ሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ዩኒፎርም ከለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ሲጨፍር የሚያሳየውን ምሥልም በማኅበራዊ ሚዲያ ብዙዎች ተቀባብለውታል፡፡

በዘመኑ ተናኘና

በዳዊት እንደሻው

ሪፖርተር

Share this:

  • Click to share on Telegram (Opens in new window) Telegram
  • Click to share on WhatsApp (Opens in new window) WhatsApp
  • Tweet

Like this:

Like Loading...

Your true media source

All rights reserved

%d