October 4, 2017 |

(BBN News) ትላንትና በሀሮማያ ከተማ የተካሔደውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰዎች መታሰራቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡ በትላንትናው ዕለት በከተማዋ በርካታ ህዝብ በተገኘበት ህዝባዊ ተቃውሞ መካሔዱ ይታወቃል፡፡ በትላንቱ ዘገባችን ላይ እንደጠቀስነው፣ የከተማዋ ህዝብ አደባባይ በመውጣት የህወሓትን አስተዳደር ያወገዘ ሲሆን፣ ከተማዋም ውጥረት ነግሶባታል፡፡ ዛሬ የወጡ መረጃዎች ደግሞ፣ ለምን ሰልፍ ወጣችሁ ተብለው የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ለእስር የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር አይታወቅም፡፡ ሆኖም ከተለያዩ ቦታዎች ተሰብስበው ፖሊስ ጣብያ ያደሩ ሰዎች መኖራቸውን ግን ምንጮቹ ያረጋግጣሉ፡፡ ከታሰሩት ሰዎች ሰዎች መካከል እስከ አስር ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ አስይዘው ከእስር ቤት እንዲወጡ የተነገራቸው ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ምንጮች፣ ስርዓቱ ሰዎችን እያሰረ ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከል ግን የተጠየቀውን የዋስትና ገንዘብ ከፍሎ የወጣ ሰው አለመኖሩን ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በተለያዩ የሀሮማያ ክፍሎች የታጠቁ ፖሊሶች ሲዘዋወሩ እንደነበር እማኞች ገልጸዋል፡፡ ዛሬም በድጋሚ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በሚል ግምት በከተማዋ የተበተኑት ፖሊሶች፣ በተሰማሩበት አካባቢ ቅኝት ሲያደርጉ እንደነበር የገለጹት እማኞች፣ ዛሬ ከተማዋ በተወሰነ ደረጃ ውጥረት ውስጥ እንደነበረችም እማኞቹ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው አገዛዝ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሳበት ተቃውሞ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡