Email
Share

 

አማን ነህ ወይ ዓባይ? ጣናስ አማን ነወይ?

ይኸ ከይሲ ዘመን በናንተም መጣ ወይ?

ጨለማው ሳይነጋ የሰፈር መንደርህ፣

ለሱዳኖች ሸጡህ ፉል ሊያስቀቅሉብህ፡፡

ግርማ ሞገስ እያልን ቅኔ ብንዘርፍልህ፣

ቅናት ፈጥፍጧቸው ሸረቡ ሊያደርቁህ፣

ሰርቀው ተመስኖ ውስጥ ሸንኮራ አስመጠጡህ፣

እምቦጭን ቻዝ ብለው በውሻ አስነከሱህ፡፡

ግንድ ይዞ ይዞራል እያልን ብንስቅብህ፣

የቤት ጨዋታ እንጅ እውነት እንዳይመስልህ፣

እሙት ዓባይዋ ተሲሳይ በላይነህ፣

ታጥንታችን ፈልቀህ በሥራችን የዞርክ፣

አየር ተሸካሚ የደም ሴላችን ነህ፡፡

ተራስጌ ጠልፈው ተግርጌ ቢያፍኑህ፣

ቄስ ጨስ የሆነ እለት በቀን ትፈታለህ!

 

አማን ነወይ አገር? ቅዬው አማን ነው ወይ?

ማሳውና ጓሮው እህል ያበቅላል ወይ?

አረሙ ታርሞ እሾህ ተነቅሏል ወይ?

አማን ነወይ አጥሩ? ካቡስ አማን ነወይ?

ተባብ ተእንሽላሊት ተጊንጥ ፀድቷል ወይ?

አማን ነወይ ጋራው? ገደሉ አማን ነወይ?

ተራራው ድንበሩ በቦታው አለ ወይ?

አማን ነወይ ዋሻው? ገዳሙ አማን ነወይ፣

ሸንኮራ መትከያ መሆኑ ቀርቷል ወይ?

አማን ነወይ ደብሩ? ታቦቱ አማን ነወይ?

ወጣቶችን መቅበር አልሰለቸውም ወይ?

አማን ነወይ አቡን? ጳጳስ አማን ነወይ?

ሕዝብን ለመስዋዕት ማቅረብ አልተወም ወይ?

አማን ነወይ ቄሱ? ካህን አማን ነወይ?

ተዝካር መዘክዘኩ አልሰለቸውም ወይ?

“አትግደሉ!” ብሎ ገዝቶ ያውቃል ወይ?

አማን ነወይ መስጊድ? መርካቶ አማን ነወይ፣

አላህ ክበር ያለ ድምጡ ተሰምቷል ወይ?

አማን ናት ወይ ጦቢያ? ሕዝቡስ አማን ነወይ?

መጨፍጨፍ መረገጥ በቃኝ አላለም ወይ?

አማን ነወይ ዱሩ? ጫካው አማን ነወይ፣

አንበሳና ነበር ይኖርበታል ወይ?

አማን ነህ ወይ ዓባይ አንተስ አማን ነህ ነወይ?

ውሀውን አጪሰህ ፍም ታጋሰላህ ወይ?

ዓለምን ሲፈጥር ይበል ይሁን ያለህ፣

እጁን እጥብ አርጎ ተጨንቆ የሰራህ፣

የእግዜር ዕደ-ጥበብ ረድኤት የቀባህ፣

እንዴት ባጀህ ግዮን እንዴት ነው ጣናነህ?

ሁለተኛው ወንዜ ሲል ያቆላመጠህ፣

ግዮን ዘኢትዮጵያ ብሎ የሰየመህ፣

ኤደንን አጠጣ ብሎ ያፈሰሰህ፣

ሥጋ መንፈሳችን የተላቆጠብህ፣

የቋጉሜ ሩፋኤል የተጠመቅንብህ፣

ዓባይ ግዮን እያልን ዘፍነን የማንጠግብህ፣

እንዴት ውለህ አደርክ እንደምን ሰነበትክ?

አንተ ስታጎርሰው እርሱም እሚያጎርስህ፣

የተጠላለፈው እትብቱ ተትብትህ፣

እንዴት ሰነበተ መንትያህ ጣናነህ?

ዘፍጥረት በምዕራፍ በአንቀጥ ያስቀመጠህ፣

ታሪክ ሥሎ ጥፎ ከትቦ የማይጠግብህ፣

ስንቱ ሲመራመር ሰምጦ የቀረብህ፣

ዓለም ረጅሙ ብሎ የሚጠራህ፣

ተከፍቶ ተገልጦ የማያልቅ ምስጢርህ፣

ተምዘግዝገህ ስትዘል እሳት እሚወጣህ፣

ሙቀት ህዋሳችን እንዴት ነህ ዓባይነህ?

የኦሪትን ምስጢር በገዳም የያዘው፣

የሙሴን ጥላጦች በእምነት የጠበቀው፣

የሀዲስን ታምር እሚመስክረው፣

የኖህን ፍጥረታት አትርፎ እሚኖረው፣

የኢቶጵን ታሪክ ጠርዞ የያዘው፣

ብራናና ቅርሱ ጭንቅንቅ ያረገው፣

ያሬድ በወረቡ አንስቶ እማይጠግበው፣

እረኛ በዋሽንት እሚያንቆረቁረው፣

ጥበብ አመንጪቶ ባለም እሚያዘንበው፣

የጠበብቶች ባህር ጣናስ እንደምን ነው?

ጣና ታሟል ሲባል በቅርቡ ሰምቼ፣

መኖር ጀምሬአለሁ እንቅልፌን አጥቼ፡፡

ጣሊያን በማፍያው ሊያጠቃ ያልቻለው፣

እምቦጭ በማን ተንኮል አጥምዶ ደፈረው?

እንግሊዝ ባስዋን ቀድቶ ያልጨረሰው፣

ፋሽሽትም በቦቴ ጭኖ ያልበጠቀው፣

ሰይጣን በምን መስኖ አፍስሶ አጎደለው?

ጣናን እምቦጭ ወሮ መጦ ሲጨርሰው፣

ሰይጣን በመስኖ ውስጥ አፍሶ ሲደፋው፣

አንተሳ ዓባይዋ እንዴት ልተርፍ ነው?

እንደተረዳሁት አንተ እንደምትለው፣

እምቦጭና መስኖ ጣናን ታደረቀው፣

መቀሌና ካርቱም ጨለማ ሊሆን ነው፡፡

እየሰማውህ ነው ሌላም መዘዝ አለው!

ዘፋኙ ሸላዩ ስንኝ ሊያጥረው ነው?

ገጣሚው ጠሐፊው ሳይንቲስት ፍላስፋው፣

እርሳሱ ዶልዱሞ ኮቢው ሊደርቅ ነው፡፡

ዘፍጥረት ለዳርዊን ቦታ ሊለቅ ነው፣

ኤደንም በርሃ ሰሃራን ሊሆን ነው፡፡

ጣና ኩልን ሆኖ ውበትን ታልቀባው፣

አንተ አዋዜ ሆነህ ጣምና ታልካንከው፣

ወረቡ ዘፈኑ እንጨት እንጨት ሊል ነው፡፡

ምንድነው መፍትሔው ብለህ ለጠየከው፣

የኢቶጵ ልጅ ጀብዱ ዳግም ማገርሸት ነው፡፡

ሰርቶም አጭበርብሮም ገንዘብ ያካበተው፣

ጣና ዳር ቤት ሰርቶ እሚንደላቀቀው፣

ሽርሽር ጉብኝት ሻንጣ አዝሎ እሚሮጠው፣

ተገዳም ተቱሪስት ገንዘብን እሚያልበው፣

የሰው ልጅ ተሆነ ህሊናውን ይንካው፡፡

ጣና ዓባይን ዘፍኖ እንጀራ እሚጎርሰው፣

ታሪክ እያነሳ ደረት እሚነፋው፣

በዓባይና ጣና ፍቅረኛ ያዝናናው፣

ባልቴት አዛውንቱ ወጣቱ ጎልማሳው

እርመ በላ ፍጡር ተመሆን ያድነው፡፡

ዘፋኝ እስክስታ አውራጅ አታሞ ደላቂው፣

መሰንቆና ክራር በገና ደርዳሪው፣

ጽናጽል አፋጪው ዋሽንት አንቆርቋሪው

ብራና አገላባጪ ተራኪ ፈላስፋው፣

በፍጥረታት ታሪክ በጥበብ እሚያምነው፣

ኢትዮጵያ አፍሪቃ ዓለም በጠቅላላው፣

ልክ እንደ ጣና ልጅ ማተብ እንዳሰረው፣

እምቦጭን በማጭድ እንደተጋተረው፣

ዛሬ ነገ ሳይል ጣናን ይታደገው፡፡

ይታደገው!!! ይታደገው!! ይታደገው!

 

ሐምሌ ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓ.ም.