ኧረ እባካቹህ እባካቹህ! ኧረ ተው ብሰሉ! ወያኔ እኮ የዚህን ያህል ቂል ተላላና የዋህ መሆናችንን አውቆ ንቆን እኮነው እድሜ ዘለዓለማችንን ሲያጃጅለን የሚኖረው፡፡ በተለይ ደግሞ ማን ገረመህ? ብትሉኝ አሁን ከሰንበት ቅዳሴ መልስ ኦ. ኤም. ኤንን ከፍቸ ስመለከት እነ ጃዋር አራት ሆነው ቀርበው እየተቀባበሉ አባ ዱላን እያወዳደሱ፣ እየካቡ፣ ብሔራዊ ጀግና አድርገው ሲያራግቡ ተመልክቸ በጣም ነው የደነቀኝ፡፡

እነኝህ ሰዎች ስውር የወያኔ ቅጥረኞች ሆነው ካልሆነ በስተቀር አባዱላ በዚህ በዚህ ጊዜ እንዲህ እንዲህ አደረገ!” እያሉ ያወሩት ነገር እንዲህ ዓይነቱን ነገር ያለ ወያኔ ትዕዛዝና ሸፍጠኛ ተልዕኮ ማንም የወያኔ አገዛዝ ባለሥልጣን በግል ተነሣሽነቱ ለማድረግ የሚችልበት ቀዳዳና ክፍተት ፈጽሞ የሌለ መሆኑ በሚገባ እየታወቀ አባዱላን በዚህ ዘመን እንዲህ አደረገ!” እያሉ ያወሩት ነገር በራሱ ነጻ ፈቃድና ፍላጎት ለሕዝብ ባለው ተቆርቋሪነት አደረገ!” ብለው ሊያምኑና ለማሳመንም ጥረት ሊያደርጉ ባልቻሉ ነበር፡፡ ወያኔ ማንም ሰው እሱ ከሚፈልገውና ከሚፈቅደው ውጭ ማንም ውልፍት እንዳይል፣ ነጻ ሆኖ እንዳያስብ የሚያደርግ የአፈና አሠራር ከባለሥልጣናቱም አልፎ ተራው ሕዝብ ላይም እንኳ ሳይቀር በአንድ ለአምስት የጥርነፋ አሠራሩ እንዴት አድርጎ ለመቆለፍ የሚጠቀም አገዛዝ ለመሆኑ ሁሉም የሚያውቀው ነገር ነው፡፡

አሁን እስኪ አባ ዱላ በምን ልቡ፣ በየትኛው ተቆርቋሪነቱ፣ በየትኛውስ ነጻነቱ ነው እንዲህ ዓይነቱን ደፋር እርምጃ ሊወስድ የሚችለው? ሰውየውን ስታውቁት ሰብእናው እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለው ይመስላቹሀል? እንኳንና እሱ የኦሮሞ ደም የሌለበት ይቅርና አሮሞ የሆኑት የኦሕዴድ ባለሥልጣናት እንኳ አባዱላ ሰጠው የተባለውን ምክንያት ጠቅሰው ስለ ሕዝባቸው ሲሉ መውሰድ ያለባቸውን እርምጃ ሲወስዱ ወይም ሲያኮርፉ እንኳ አልታዩም፡፡ እኔ አባዱላን እንኳንና እዚህ ተቀምጦ ወያኔ ላይ አኩርፎ ወያኔን ሊያስቀይም የሚችል እርምጃ ይወስዳል ብየ ላምን ይቅርና ከሀገር ውጭ በሔደበት ከዳ!” ቢባል እንኳ ገንዘብ ይዞ ሸሽቶ እንዲቆያቸው እንዳደረጉት ነው እንጅ ላስብ የምችለው ወያኔን ከዳ ብየ ፈጽሞ ላምን አልችልም፡፡

ምንድን ነው ታዲያ ምክንያቱ? ያላቹህኝ እንደሆነ ወያኔ ይሄንን ያደረገበት ሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይታዩኛል፦

1. ወያኔ ሁልጊዜ ደስ የማይለው አስጨናቂና ተጋፊ ተቃውሞ ከሕዝብ በገጠመው ጊዜ የሕዝቡን የቁጣና የተቃውሞ ግለት ለማብረድ የሚወስዳቸው እርምጃዎች አሉ፡፡ እነሱም፦ ሀ, እንዳጠፋ አምኖ ፈጥኖ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ የማይፈጽመውን ቃል ለተቆጣው ሕዝብ በመግባት፡፡ ለ, የሆነ ድራማ (ትውንተ ኩነት) ይሠራና አፈትልኮ የወጣ ምሥጢር አስመስሎ ለተቃውሞው ጎራ እንዲደርስና እንዲነገር እንዲራገብ በማድረግ ሕዝቡ በቃ ወያኔ አልቆለታል!” ብሎ እንዲያስብ በማድረግ፡፡ ሐ, እንዲህ እንደ አሁኑ አባ ዱላ እንዳደረገው ባለሥልጣናቱ አገዛዙን የተቃረነ እርምጃና ተቃውሞ የወሰዱ በማስመሰል ተጋፍቶ የመጣበትን የሕዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ ግለት ለማብረድ ሲጠቀምበት የቆየ ዘዴው በመሆኑ የሚለው አንዱ ምክንያት ሲሆን፡፡

2. በዚህ በሰሞኑ በሱማሌና በኦሮሞ መሀከል የድንበር ግጭትን መንስኤ አድርጎ በሁለቱ መሀከል የተፈጠረው ግጭት የክልል መንግሥታት ሥልጣን አልባ አሻንጉሊት መሆናቸውን፣ ሥልጣኑ ተጠቅልሎ የተያዘው በሕወሀት ብቻ የተያያዘ መሆኑን ለምዕራባውያኑ አጋልጦበታል፡፡ ወያኔ ታዲያ ይሄንን የምዕራባውያኑን ትክክለኛ ግንዛቤ ማስጣል፣ መሻር ስለፈለገ የኦሕዴድ ባለሥልጣናት የሕዝባቸው ትክክለኛ ወኪሎችና ነጻ ባለሥልጣናት አስመስሎ ለማሳየት ሲል ነው አባዱላን ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ቅሬታ የተሰማውና በዚህም ምክንያት የአፈጉባኤነት ሥልጣኑን በፈቃዱ ለቀቀ!” እንዲባል ያደረገበት ምክንያት፡፡

እንጅ እነ ጃዋር አሁን አጩኸው እንዳራገቡት፣ ብዙዎቻችንንም እንደመሰለን አይደለም፡፡ አባዱላ በሙስና ከተዘፈቁ የወያኔ ባለሥልጣናት አንዱ ነው፡፡ ከመቀመጫው ላይ ቁስል ያለበት ውሻ እንደልቡ መጮህ ይችላል ወይ? አባዱላ በሙስና አሳበው ወኅኒ ያበስብሱኝ ብሎ ነው ወይ እንዲህ ሊያደርግ የሚችለው? ኧረ ከዚያም አያደርሱትም እንደእነ ሐየሎም ሴራ ጠንስሰው ባለበት ነው ደፍተው የሚጥሉት፡፡ ይሄንን የወያኔን ሸፍጠኛ ጠባይ አባዱላም ሆነ ሌሎች የየክልሉ አሻንጉሊት የወያኔ ሹመኞች አሳምረው ያውቁታል፡፡ እናም! እናማ የአባዱላ በፈቃዱ ሥልጣኑን መልቀቅ የወያኔ ድራማ (ትውንተ ኩነት) እንጅ እውነት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ወያኔ በየጊዜው የሚፈጥራቸው የማዘናጊያ ድራማዎች ሳትዘናጋ ትግልህን አጠናቅረህ ቀጥል! ነው መልእክቴ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com