8 October 2017

እከሌ ከእከሌ ተወለደ፣ እሱ ደግሞ ከእከሌ እንቶኔን ወለደ፣ በማለት በዝርያ ሰንሰለት የምናየው ሰው ከቤተሰብ አንስቶ ተዛምዶው በጎሳ፣ በነገድ፣ ወዘተ እየሰፋና እየተወሳሰበ በሄደ ማኅበራዊ ዳንቴል የተያያዘ፣ ህልውናውም በዳንቴሉ ቅለትና ውስብስቦሽ የሚመራ ማኅበራዊ ፍጡር (ሶሻል ኦርጋኒዝም) ነው፡፡ የንቦችን ህልውና በግለሰብነት ላይ ልናንጠለጥለው አንችልም፡፡ የሠራተኛና የወታደር ንብን ህልውና ከንግሥቷና ከጠቂዋ ነፃ አድርገን ልናየው አንችልም፡፡ ኑሯቸው የሁሉንም ተራክቦ ይጠይቃል፡፡ የሰው ልጅም ግለሰባዊና ማኅበራዊ ነገረ ሥራዎቹ በደመ ነፍስ ያልታሰሩ ከመሆናቸው በቀር ህልውናው ከቡድንነት ውጪ ሊታሰብ የማይችል ነው፡፡
አሁን ባለንበት ደረጃ የሰው ልጅን ማኅበራዊ ሥሪት ልንገልጸው ብንሞክር፣ ሰባት ቢሊዮንን የዘለሉ የግለሰብነት ህዋሶች ያሉት፣ እነዚህም ህዋሳት በልዩ ልዩ ተቧድኗዊ ሥምሪት፣ ጅማቶችና ተራክቦዎች ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የምናይበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በማሳና በፋብሪካ ውስጥ የተለፋበት የሥራ ፍሬ ከሸክም፣ ከአህያና ከግመል አቅም አንስቶ በተለያየ ዘዴ አገርና አኅጉር እያቆራረጠ በግዥና በሽያጭ የሚያደርገው ቅብብል የተመረኳኮዘ ህልውናችንን ይገልጻል፡፡ ይኼ መመረኳኮዝ ወደ ሆድ ከሚገባ ጉርስ አንስቶ፣ ከሚበጁ እስከሚያጠፉ ዕውቀቶች፣ አስተሳሰቦች፣ ጥበቦችና መሣሪያዎች ድረስ የሰፋ ነው፡፡ የሰዎች የሥራ ፍሬ ላይ፣ የሰዎች ላብና ጥበበኛነት ታዝሎ ሊሸጋገርና ሊነበብ እንደሚችል ሁሉ ግፍም ሊሸጋገር ይችላል፡፡ ጦርነት የሚያስከትለው የእንባና የደም ጎርፍ፣ የጦር መሣሪያ ከመቸብቸብ አንስቶ ከጦርነቱ የሚገኘውን ሀብት ያጨቀያል፡፡ አንዳችን ለሌላችን ጠንቅ ልንሆን እንደምንችል ሁሉ፣ ጠንቅ የመንቀሉም ሆነ መድኅን የመሆኑ ኃላፊነትና ተግባርም በእኛው ውስጥ ነው፡፡
የማኅበራዊ ፍጡርነታችን ህዋሶችና ጅማቶች በዛሬዎቹ ቢሊዮኖች ሰዎችና እንቅስቃሴያቸው ላይ የተቋቋመ ብቻ አይደለም፡፡ ህልውናችን በግለሰብነትም በቡድንነትም የብዙ ብዙ ዕልፍ አዕላፍ ትውልዶች አስተዋጽኦ እየተደራረበ፣ አንዱ ለአንዱ ንጣፍ እየሆነ የተገነባ ስለሆነ፣ ጅማታችን ቁጥር ሥፍር ከሌለው ቅሪተ አካላት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ከእነ ኒውተንና ከእነ ልዊ ፓስተር ጋር፣ ከሌሎቹም  የግኝት፣ የፈጠራና የፍልስፍና ጠቢባን ጋር ሁሉ ተሳስረን ነው የምንኖረው፡፡ ለመረዳት እንዲቀለን እነ ኒውተንን ጠቀስን እንጂ፣ ማኅበራዊ ጅማታችንና ተራክቧችን ከሞላ ጎደል ከደመ ነፍሳዊ አቅም ውጪ ምንም ሰው ሠራሽ ጥበብ ያልነበረው፣ ቅድመ ሰው ፍሬ ለማውረድ ወይም ራሱን ከአደጋ ለማዳን ድንጋይ እስከ ወረወረበት ወይም ዘንግ እስከ ተጠቀመበት የመጀመርያ ጥረት ድረስ የረዘመ ነው፡፡ በዚህ ዝግመታዊ ሒደት ውስጥ መፍጨርጨሪያ ዘዴዎቹን ከማሻሻልም በላይ የሰው ልጅ ሳያውቀው እንደ ማኅበራዊ ፍጡር ራሱን ሊፈጥርም ችሏል፡፡ ይህ ማጠቃለያ አልታየው ያለ ወይም ነገር ማራቀቅ የሚመስለው ቢኖር፣ ነገሩን ከሌላ ጥግ እንመልከተው፡፡ የሰው ልጅ በማኅበራዊ ግለሰባዊ የጥረት ተራክቦዎች እየተባ የተቀዳጀውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ያቀዳጀን በቋንቋ የመነጋገር፣ የማሰብና ችግርን በጥበብ የማሸነፍ፣ ዕውቀትንና ጥበብን በቋንቋና በሥልጠና የማሸጋገርና የማቆየት ማኅበራዊ ባህርያትን ብንነጠቅ፣ ከዚሁ ጋር እስከ ዛሬ የተንኳተቱልን ሰው ሠራሽ ፈጠራዎች፣ ዘዴዎችና ጥበቦች ሁሉ ከጉያችን ቢወገዱ ደመ ነፍሳዊ ችሎታዎችና የመግባቢያ ድምፆች ብቻ ያሉት እንስሳ ከመሆን የማንዘል ደካሞች እንሆናለን፡፡ ወይም የቀድሞው ሰው በልቶ ማደርና ራስን ከጥቃትና ከብርድ መከላከል እንኳ እጅግ ይከብደው የነበረበት (እሳትን እንኳ ባሻው ጊዜ የማቃጠል ክህሎት ያልተቀዳጀበት) ጥንታዊ የህልውና ደረጃ ውስጥ ራሳችንን አስገብተን ምኑን ከምኑ እንደምናደርገው መገመት ነው፡፡
ዛሬ በውስጣዊ ፍጥጫችንና ከከርሰ ምድርና ከገጸ ምድር አልፎ ሰማይ በወጣ ሥልጣኔ አመጣሽ ግሳንግሳችን ለራሳችንና ለምድራችን መጥፊያ እስከ መሆን ደርሰናል፡፡ የጥንታዊው ሰው የመኖርና ያለመኖር ፈተና፣ በያለበት የሁሉንም የትግግዝ እንቅስቃሴ ይጠይቅ የነበረበት፣ ግለሰባዊ ራስ ቻይነት ያልነበረበት፣ ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ የተነሳ ትግግዙም እጅግ ቀላል፣ የቡድን ስብስቡም ቅርብና ጠባብ ነበር፡፡ ዛሬ ከአንዱ የዓለም ጥግ ወደ ሌላው የዓለም ጥግ አሻግረን ለመሸጥ አቅደን እናመርታለን፣ አምርተን እንደመላካችንም ከሌላው እናስመጣለን፡፡ ከአንዱ የዓለም ጥግ ወደ ሌላው የዓለም ጥግ እኛው በሠራነው ጥበብ አማካይነት እንነጋገራለን፣ እንተያያለን፣ ተራርቀን ሳለን በአንድ ቅፅበት አንድ ዓይነት ትዕይንት መከታተል እንችላለን፡፡ አንዱ የዓለም ጥግ ላይ የተከሰተ በሽታ ዛሬ ሥጋቱና መፍትሔ ፍለጋው በዚያው በመከሰቻ ሥፍራው የሚወሰን አይሆንም፡፡
ዛሬ እያንዳንዱ ሰው በድፍኑ በአንዴ ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ ግለሰባዊና ማኅበራዊ፡፡ በዕውቀቱ፣ በአስተሳሰቡ፣ በዘልማዱ፣ በምርጫው፣ በመውደድና በጥላቻው፣ በግላዊ ጥረቱ፣ ወዘተ ሁሉ ውስጥ ግለሰባዊና ማኅበራዊ አላባዎች አሉ፡፡ ግለሰባዊ የሆኑት ዓይነተኛና የብቻ የሆኑት መለያዎቹና የሚያክላቸው ሲሆኑ፣ ማኅበራዊዎቹ ደግሞ ከማኅበራዊ ማህፀኑ የወረሳቸውና የተቀረፀባቸው ናቸው፡፡ የእነዚህም የግንኙነት ሚዛን ከሥልጣኔ (ከማኅበራዊ ባህላዊ የልውጠት ደረጃ) ጋር የሚገናዘብ ነው፡፡ ግለሰባዊነት ደካማ የነበረበት ጊዜ እንደነበር ሁሉ ዛሬ ግለሰቡ የአንድ ማኅበራዊ ፍጡር ህዋስ መሆኑ ልብ የማይባልበት፣ እንዲያውም እውነተኛው ተጨባጭ ሰውነት ግለሰብነት፣ ማኅበራዊ ሰውነት ደግሞ ረቂቅ (ቲዎሪያዊ) ግንዛቤ እስከሚመስል ድረስ የየብቻ ኑሮ ተተክሏል፣ ግለሰብነት ሰፊ መንሸራሸሪያ አግኝቷል፡፡ የወደፊቱም የኅብረተሰብና የግለሰብ ግንኙነት፣ ኅብረተሰብ ይበልጥ የግለሰቦችን ነፃነትንና ፍሬያማነትን እያፋፋ የአጠቃላዩን ምቾትና ግስጋሴ የሚያራምድ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በጠባብ ማኅበር የተቀነበበ ጥንታዊ ኑሮ ማኅበራዊ ጥንቅሩ እየሰፋና የሥራ ክፍፍልንና ማኅበራዊ ዕርከኖችን እየፈጠረ ረዥም ዘመን ተጉዟል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የተለያየ የውስብስብነት ደረጃ ያላቸው ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች እንደተፈጠሩ ሁሉ ነገሥታታዊና መሳፍንታዊ የዘር “ጥራት”፣ መደዴ ሰውነት፣ ባርነት፣ ጭሰኝነት፣ ቡዳነት/ጠይብነት፣ የህንድ ዓይነቱ የካስት ክፍፍል ሁሉ ተከስተዋል፡፡ የገዥነትንና የተገዥነትን ሚና ከማመልከትም ባሻገር በኢኮኖሚያዊ ጥረትም ሆነ በጋብቻ የማይዘለሉ/የማይፋቁ የማንነት መለያዎችም ሆነው ሠርተዋል፡፡ ቀለሞችና ዘሮች በጋብቻ ሊደራረሱ የሚችሉበት፣ የሥራ ሙያና አጥንት የተለያዩበት፣ በኢኮኖሚያዊ ተበላላጭነት ውስጥ ወደ ላይ መውጣትና ወደ ታች መውረድ የሚቻልበት፣ በአጠቃላይ ቀለሞችና ዘሮች የሰው ዥንጉርጉር ገጽታዎች እንጂ የተበላለጡ ተፈጥሮዎች አይደሉም የሚል ይፋ ዓለማዊ ግንዛቤ የተያዘበት የዛሬ ጊዜ ላይ ለመድረስ ብዙ አበሳ ታይቷል፡፡ ዛሬም ቢሆን የአሮጌ አስተሳሰብና የመፀያየፍ አጥሮች ገና ተበጣጥሰው አላለቁም፡፡ አንዳንዶቹ ኋላቀር አመለካከቶች አንጓላይነት (ለምሳሌ በቀለም)፣ በእኩልነት አስተሳሰብ፣ በሳይንስና በጥበብ በተራመዱት አገሮች ውስጥ ደድሮ እናገኘዋለን፡፡ ያውም ቀለምና ዘር (ሬስ) ተፈጥሯዊ የአዕምሮ መበላለጥን እንደማያሳዩ ያረጋገጡ ምርምሮች ዋና ምንጮች እነሱው ሆነው፡፡
ተፈጥሮና ማኅበራዊው ሰው እየተራከቡ ባነፁት የሰዎች ሕይወት ውስጥ መጥተው የሄዱ ማንነቶች እንደነበሩ ሁሉ ገና የሚቆዩ ግን የሚያልፉ ማንነቶች ዛሬም አሉ፡፡ ወንዜነት፣ ጎሳነት፣ ብሔር/ብሔረሰብነትና የአገር ልጅነትም እዚሁ ኃላፊ ማንነት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ እኩልነት ሳይንስና ስሉጥ አኗኗር የሰዎችን አዕምሮና ሕይወት መግራታቸው እየጠለቀና እየሰፋ በሄደ መጠን ቀለምንና ቁመናን፣ እንዲሁም ሃይማኖትንም ሆነ ባህልን የተመረኮዙ ማበላለጫዎች እየመከኑ መሄዳቸው እንደማይቀር ሁሉ፣ የሰዎች ህልውና በየአገሮች የተከፋፈለ መሆኑ እስከ ቀጠለ ድረስም ልዩ ልዩ አገርነት ላይ የተመሠረተ ማንነት ለሰዎች ገዝፎና ቅርብ ሆኖ መታየቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከአገርነት ጋር የተዛመዱ ወይም በአገርነት ውስጥ ያሉ ባህሎችና ማኅበረሰባዊ ቅንብሮችም የየራሳቸው ድርሻና ሚና ይኖራቸዋል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ የማንነት ፈርጆች በሰላም መኗኗርንና በዕድገት ጎዳና መራመድን በሚያስችል ሚዛንና ከበሬታ ካልተያዙ (አንዱ በሌላው የተዋጠበት ዝንፈት ከተፈጠረ) ቀውስ መከተሉ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ እዚህ ፈተና ውስጥ ነበረች፡፡ አሁንም ነች፡፡ ቀድሞ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችንና ማኅበረሰባዊ ማንነቶችን የሌሉ ያህል ጋርዶና ጨቁኖ አንድ አገርነትን ሲደልቅ የኖረ ሥርዓት ለብሔርተኛ ትግሎች መፈልፈያ እንደሆነ ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ እየጦዘ ያለው ብሔር ብሔረሰብነት የአገራዊ ትስስርና የሰብዓዊ መከባበሮችን እስከ መተናነቅ ድረስ ዓይን የለሽ የሆነ የማንነት ቀውስ ፈጥሯል፡፡
እዚህ ቀውስ ላይ እናትኩር፡፡ ደርግ ሄዶ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ስለወጣ ከኤርትራ በቀር የተቀነሰ መሬትና ሕዝብ አልነበረም፡፡ የተወሰነ መታመስ ከመድረሱ በቀር፣ በመሠረቱ የማኅበረሰቦች መኖሪያም አልተቀየረም፡፡ በአመለካከትና በአስተዳደር ዘይቤ የተከተለው ለውጥ ግን ብዙ ነገሮችን ያናጋ ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ግንቦት የኢሕአዴግ ድል ወደዚህ የብሔር ጥያቄና መብት ዋነኛ የጊዜው ማትኮሪያ ሆነና ፖለቲካዊ መብከንከኑ ሁሉ ወደ ብሔረተኝነት ጠቦ ወረደ፡፡ በየብሔር ተወጋግኖ የቀድሞ ታሪክን መፈለግ፣ የደረሰ በደልን ማሰባሰብ የጊዜው ዘይቤ ሆነናም ኅብረ ብሔራዊ ትግልና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለት የነፍጠኞች ጉዳይ መሰለ፡፡ በሰውነት መተሳሰብና መከባበር በአንድ አገር ልጅነት ውስጥ እንኳ ተገቢ ሥፍራ ማግኘት አልቻለም፡፡ ኢትዮጵያ በብሔረሰቦች እግር ብረትነት ብቻ ተሳለችና ከወረራ ግፍ፣ ከግዳጅ አንድነትና ከቁስል በቀር የሚወራ በጎ ነገር ጠፋ፡፡ ግፈኛ አገዛዝን ምኒልክና ነፍጠኞቹ ወደ ደቡብ አውርደው የነሰነሱት አድርጎ ማሰብ የፖለቲካ ንቃትን ከማጣበቡ የተነሳ፣ በስተደቡብና በስተምዕራብ በነበሩ ንጉሣዊ አገዛዞች ዘንድ ሰውን ለባርነት መዳረግን የጨመረ ግፍ እንደነበር፣ እንዲሁም ዝሆንና አንበሳ ገድሎ ጀግና በመባል ዓይነት የሚካሄድ ሰለባ በሰሜንም በስተደቡብም የባህል ሥር እንደነበረው ማገናዘብ ችግር ሆነ፡፡ የሰሜን ሰው ወደ ደቡብና ወደ ምዕራብ (እስከ ሱዳን ድረስ) መሰደድ ከምኒልክ ዘመቻ በፊት እጅግ የቀደመ ታሪክ እንደነበረው፣ ከዘመቻ ጋር ባልተያያዘ ሁኔታ በግል የሚፈጸም ግድያ ያስከትል የነበረውን ደምን በደም የማስመለስ ጭፍን ቅጣት ለማምለጥ፣ የገዳይ አዝማዶች ያለ ኃጢያታቸው ድምፅ እጥፍተው በወሬ ወሬ የማይደረስበት ሩቅ ሩቅ አገር ድረስ ይሰደዱ እንደነበር (ዛሬም የባህል ፍረጃው እንዳልጠፋ) እንኳ የሚያስተውል ጠፋ፡፡ ስለትናንት በደል ለብሔር መቆጨት፣ የዛሬዎቹን የመጤ ዘር-ማንዘሮች በደፈረሰ የበቀል ስሜት እስከ መመልከት አሻቀበና መጤ ግለሰብ ጥፋት ቢሠራ ወይም ከ‹ወገን› ልጅ ጋር ቢደባደብ በነገሩ የሌሉበትን፣ ጭራሽ ወሬውን እንኳ ያልሰሙትን የጥፋት ተጋሪ አድርጎ መበቀል ተደጋግሞ የሚመላለስ የድሮ ሒሳብ ማወራረጃ ሲሆንም ታየ፡፡ የዚህ ዓይነት ጥፋቶች እየተለባበሱ ከተጠያቂነት በተደጋጋሚ ማምለጥ ተችሏል፡፡ በዛቻ አሸብሮና በጥፋት ሰበብ ማፈናቀልም እንግዳ ነገር አይይለም፡፡ ከዚህም ታልፎ በማፈናቀል ሕጋዊነትና ፍትሕ የሚከናወን ይመስል ለተፈጸመ ማፈናቀል በክልል አስተዳዳሪ ደረጃ ምክንያታዊ ማብራሪያ ሲሰጠው ለማየትም በቅተናል፡፡
እስር ቤት ያልሆነች ኢትዮጵያን ‹‹የመፍጠር›› ነገር ሲከተል ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊ የመሆን ጉዳይ ሲፈልጉ የሚይዙት፣ ሳይፈልጉ የሚያቋርጡት (የሚተውት) ነገር ሆኖ ታረመ፡፡ የታረመው የውዴታ ኢትዮጵያዊነት ውልም የብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት እስከ መገንጠል ሆኖ ተቀመጠ፡፡ ይኼው ነገር ቻርተርና የአስተዳደር መዋቅር መሥሪያ ሆነ፡፡ ይኼው ነገር ሕገ መንግሥት ሆኖ ተቀመረ፡፡ ሥልጣን ይዞ ማስተዳደሩም የብሔርተኛ ፓርቲዎች፣ ከብሔርተኛ ፓርቲዎችም (የኢሕአዴግ ቡድኖችና ሸሪኮቻቸው) ይዞታ ሆነ፡፡ ከእነሱ በተቃራኒ ደግሞ እውነተኛ የየብሔር ብሔረሰብ ጥቅም ወካዮች እኛ ነን የሚሉ የተቃውሞ ብሔርተኞች ይፈልቁ ጀመር፡፡ የብቻ ብሔር ብሔረሰባዊ የአስተዳደር ግቢና የብቻ ብሔርተኛ ፓርቲ የሌላቸው ደግሞ በሌላው “በመበለጣቸው” እየቀኑ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በየብሔረሰብነት ለመታወቅና የራስ ይዞታ ለማግኘት ሩጫ ውስጥ ገቡ፡፡ በዚህ ሩጫ ውስጥ በብዙ ነገር የተዛመዱ ማኅበረሰቦችና የአንድ ማኅበረሰብ ቡራቡሬ ሽርፍራፊ የሆኑ ጭምር የተለየ ማንነት አለን እስከ ማለት ነጎዱና “እንለያለን” ባይነትና “አንድ ነን” ባይ ወገኖች ተላተሙ፡፡ ልትሚያው ከቡድኖች አልፎ ሕዝብን እስከ ማነካካት ሲሰፋም ታይቷል፡፡ የክልል መስተዳድር ብሔረሰባዊ ማንነትን አላውቅ ካለ ትግሉ እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ የተፈለገውን ውጤት ካላስገኘ ደግሞ ትግሉ በሌላ መልክ ሊቀጥል ይችላል፡፡
በብሔር ብሔረሰብ ምድር ረገድ ድርሻዬ ወደ ሌላ አለፈ ባይ መብከንከን ደግሞ ሌላ ሁነኛ መናቆሪያ ነው፡፡ ብሔረሰባዊ ማኅበረሰቦች ከአንድ በበለጠ የአስተዳደር አካላት (ጠቅላይ ግዛቶች/ክፍለ አገሮች) ውስጥ ተካተው የነበሩበት የፊት ጊዜ አወቃቀር በየብሔረሰብ የመሬት ድርሻን ለማሰብ የሚመች አልነበረም፡፡ በአዲሱ ዘይቤ ግን አገሪቱ ብሔረሰባዊ አሠፋፈር ላይ ባተኮረና ከብሔር ብሔረሰብነት ጋር በተዛመደ እስከ መነጠል በሚደርስ መብት ላይ የተቋቋመች በመሆኑ፣ “በመፈቃቀድ” ላይ የተንጠለጠለ አገርነት ቢቋረጥ ወይም መነጣጠል ቢካሄድ ቀሪ ሀብት በእጅ ያለ ይዞታ ነውና እዚያ ላይ ያለው ትንንቅ እስከ ደም ጠብታ (የድንበር አካባቢ ሕዝብን የድምፅ ውሳኔ እስከ መጣስ) ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ ቋንቋን በመከተል የየድርሻ ምድርን ለመተሳሰብ መሞከር ደግሞ መቼ እንዲህ ቀላል! የአንዱ ወይ የሌላው ተጎራባች ቋንቋ ተናጋሪዎች የአሠፋፈር መንሸራተት ያደረጉበት ታሪክ ከበስተጀርባ ይኖርና የ“ሀ” ቋንቋ ተናጋሪዎች የሠፈሩበትን ተከታታይ አካባቢ ሁሉ በ“ሀ” ይዞታ ውስጥ እመድባለሁ የሚባል ነገር ይመጣል፡፡ በሌላ በኩል ተዋሳኞች ከጊዜ ብዛት አንዳቸው በሌላቸው ውስጥ በስፋት ዘልቀው፣ ተቀላቅለውና ተጋብተው የሁለትና የሦስት ቋንቋዎች ተናጋሪዎች  ሆነው ሲገኙም ይዞታ መለየቱ ሌላ ራስ ምታት ይሆናል፡፡ ለውጡን እንዳለ ከመቀበል ፈንታ ሥፍራው ቀድሞ የማን ነበር? ማን በኋላ መጣ? ከፍላጎት ጋር የሚስማሙ አፈ ታሪካዊና የጽሑፍ መረጃዎች ቁፈራ! የአንዱ ወገን የቁፈራ ውጤት ከሌላው ጋር የሚፋለስ ሲሆን ደግሞ ጠንቀኛ ቅራኔና ግብግብ! ከዚህ የፈለቁ ፍጥጫዎች ዛሬ ድረስ አሉ፡፡ ደም ያፈሰሱ ግጭቶች በተደጋጋሚ ተከስተው፣ ነገር እንዳይባባስ “በግጦሽና በውኃ መጋጨት ያጋጥማል፤” ምንትስ እየተባለ ተድበስብሰዋል፣ በእርቅ ብጤም ተሸንግለዋል፡፡
ወረት ያላስረጀው የየጎጆ ብሔርተኛነት የሚያመርተው አንጓላይነት፣ ንቁሪያና ግጭት ይህን ያህል መዋቅራዊ መሠረት የያዘ ነው፡፡ ጥፋቶችንና ተጠያቂነትን አድበስብሶ ማሳለፍ ችግር አላቃለለም፡፡ በ“ነፍጠኛ ርዝራዦች” ላይ የተወረወረ ሕገወጥ በትርና መብት ረገጣ እያሳሳቀ ሰፍቶ ለሌላውም ተዳረሰ፡፡ ከዚህም ብሶ ይኼው ዛሬ የሶማሌና የኦሮሚያ ገዥዎች በመካካድና በዋሾነት የተሞላ ግልፍተኛ ወሬ እስከመበተን ኃፍረት ባጡበት አኳኋን፣ የሁለቱም ክልል ሕዝብ ላይ ጭፍን ቅጣትና እስከ ጎረቤት አገር የተሻገረ የሺዎች መፈናቀል ደረሰ፡፡ የተፈጸመው ሰቅጣጭ ድርጊት ቀደምት ገዢዎች ተዳፈረኝ ባሉት ባላጋራ ገዥ ላይ ሲዘምቱ፣ የባላጋራቸው ግዛት ላይ ባገኙት ነዋሪ፣ ማሳና ከብት ላይ ያሳርፉ ከነበረው በቀል ምን ያህል የራቀ/የሠለጠነ ነው? ከዚህ በላይ ምን እስኪሆን ነው የምንጠብቀው? የታጠቀ ኃይል ፖለቲከኛ ከተደረገ እንዲህ ያለ ግፍ ውስጥ ሊዘፈቅ እንደሚችል ለመረዳትና ለመታረም የአሁኑ ልምድ ያንሰናል? የሁላችንም ደኅንነትና መብት ተከባሪነት በፅናት እንዲረጋገጥ አንድ ላይ ለመጮህና ለመታገል ከዚህ በላይ እንዴት ያለ ቁስቆሳ እንፈልጋለን?!
ብሔርተኛ ገዥነትን የማቋቋም መሐንዲሱ ኢሕአዴግ ይህንኑ መዋቅር አቅፎ የብሔርተኛ ጠባብነትንና ትምክህትን ለማሸነፍ እየለፋሁ ነው ሲል እናገኘዋለን፡፡ ትግሉ ግን ጠብ ብሎለት ጠባብነትና ትምክህት ተመናምኖ፣ ጥላቻና  መቃቃር እየታጠበ የሕዝቦች ፍቅር ሲደረጅ እያየን አይደለም፡፡ ለምን? ይህን ጥያቄ እንመርምር፡፡
አዲስ ራዕይ በተሰኘው የኢሕአዴግ የአተያይ መጽሔት (የየካቲት፣ መጋቢት 2009 ዓ.ም. ዕትም) ውስጥ ከምሳሌያዊ አነጋገር የተወሰደ ሥዕላዊ የፖለቲካ አቋም አገላለጽ እናገኛለን፡፡ የጠባቦችን አተያይ “የአገሬ ጅብ ይብላኝ” ከማለት ጋር አያይዞ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቋም ግን የየትኛውንም ብሔር ብሔረሰብ ጅብ የሚቃረን መሆኑን ይነግረናል፡፡ ይህንን ሥዕላዊ የአቋም ማሳያ ስናፍታታው በየብሔር ወገናዊነት ሳልታወር ለተበዳዮች እቆረቆራለሁ፣ በደልን በመከላከል፣ በማጋለጥና ተጋፍጦ በመፋረድ ትግል ላይ አንድ ጋ እገጥማለሁ ማለት ነው፡፡ ይህን የመሰለ አቋም ውስጥ ለመኖር መቻል ከተሳካ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ብዙ ጣጣዎች ይቃለላሉ፡፡ ይኼ እንዲሳካ የምንመኝም ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ኢሕአዴግ ይህን የመሰለ ድንቅ አቋሙን ሕዝብ ውስጥ ሊያሰርፅ የሚሞክረው ግን በስብከት ነው፡፡ ከስብከትም በላይ በርበሬ እየቀነጠሳችሁ አታንጥሱ የማለት ዓይነት ነው፡፡ ብሔርተኝነት ምንም ቢያሽሞነሙኑት በተፈጥሮው የራስን ብሔር ወገን ከሌላው በመለየትና በወገንነት አብልጦ በማየትና በመቆርቆር የጠበበ ነው፡፡ ጥበቱ የሚጀምረውም ራሱን ከሌላው ለይቶ መቧደን ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ አዕምሮ በየብሔርተኛ ወገናዊነት እስከተሟሸና ነጋ ጠባ የሚደለቅ የሚሰለቀው እሱው እስከሆነ ድረስ፣ በፓርቲነት መሰባሰቢያና ሥልጣን መጨበጫው መንገድ እሱው እስከሆነ ድረስ ጥበት የትም ፈቅ አይልም፡፡ ኢሕአዴግ ጥበትንና ከጥበት የሚፈልቅ በደልን እታገላለሁ የሚለውና የሚጥረው እዚያው የጥበት ሙሽትና ፖለቲካዊ አደረጃጀት ውስጥ ተቀርቅሮ ነው፡፡
በፓርቲው መጽሔት ውስጥ የሠፈረውን የየብሔር ብጤኛ ለሆነ በዳይና ሌባ የመወገን አንካሳነትን ለመግለጽ የተጠቀመበትን “የአገሬ ጅብ ይብላኝ” የሚል ምሳሌያዊ አገላለጽ በመገናኛ ብዙኃን እንዲናኝ እንኳ አላደረገውም፡፡ “የአገሬ ጅብ ይብላኝ” ከማለት የተላቀቀ አመለካከት መሬት እንዲቆነጥጥና መኗኗሪያ እንዲሆን የሚያግዝ ምን መዋቅር ላብጅ? የሚለው ጥያቄማ መቼ ተነክቶ! በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ብሔርተኛ ቡድኖችን አዋህዶ ለሌላውም አርዓያ የመሆን ዕርምጃ የለም፡፡ ይህ ቢቀር ብሔርተኛ ቡድኖቹ በየሚገዙበት ክልል ውስጥ ላለው መላ ሕዝብ ቆመናል የሚሉ እንዲሆኑ ማድረግ እንኳ አልተሞከረም፡፡ በዚህ ላይ ብሔርተኛ ጥበት የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ የንግድ ቡድድንንና ደንበኝነትን በብሔር/በክልል እስከ መሸንሸን ሙያውን እያሳየ ነው፡፡
ኢሕአዴግ በአገዛዙ ይህን መሰል ገመና ታቅፎ ብሔርተኛ አድሎኛነትን ለማሸነፍ የሚደረግን ትግል ውጤታማ የማድረግ ሚና እንደምን መጫወት ይችላል? ድክመቱን አጢኖ፣ ግጭትና መታመስ የማይመላለስበት አኗኗር የምናገኘው ምን ዓይነት ማሻሻያ ብናደርግ ነው የሚል ምክክር ከአገሪቱ ሕዝብና ምሁራን ጋር ለማካሄድ አልቻለም፡፡ ቀውሶች ከጊዜ ጊዜ የሚያሳዩት አስተዳደግ ደግሞ ኢሕአዴግ እስኪባንን እንጠብቅ የሚያስብል አይደለም፡፡ ከአንድ ዓይናነት፣ ከጭፍን ውግዘትና ከዝምታ ወጥቶ ያለ ሥጋት ሊያኗኑረን የሚችል መፍትሔ የማፈላለግና እንዲፈለግ የመወትወት ተግባር የሁላችንም ወቅታዊ ኃላፊነት ነው፡፡
የሰው ልጆች ታሪካችን የቱንም ያህል በመከታከት የተሞላ ቢሆን፣ ማኅበራዊ ህልውናችንን በዚህ ምድር ላይ የማዝለቅ ትግል መሠረታዊ ባህርያችን ነው፡፡ ሥልጣኔን በማዳበርና በመቀባበል ወደፊት መራመዳችን አልቀረም፡፡ ማኅበራዊ ህልውናችንን የማራመድ ዘዴና መንገድ ሲስተምና አቅማችንን በመከታከት ስናደቅ ኑሯችን ባለበት ከመርገጥም ብሶ ወደ ኋላ ሊሽቀነጠር ይችላል፡፡ በዚች ምድር ላይ የሰው ዘርን ህልውና በጥቅሉ የማትረፍ ጉዳይ ፈጦ የሁላችንንም ርብርብ እየጠየቀ ባለበት ጊዜ ውስጥ፣ በትንንሽ ብሔርተኝነት ውስጥ ታውሮና በጅምላ (ባርባሪክ) ብቀላ ውስጥ ሲዳፉ መገኘት ሌላ ዘመን ውስጥ ከመኖር ቁጥር ነው፡፡
በብሔርተኝነት መታወር ሁለት ሁነኛ ነገሮች ያጎድልብናል፣ 1ኛ/ በሰው ልጅነት ማኅበራዊ ተፈጥሯችን ውስጥ ያለውን የመተሳሰብና የመከባበር ትርታ ይሰረቅብናል፡፡ 2ኛ/ የየብሔር ዕድገትና ሰላም ከብዙ ማኅበረሰቦች ጋር የተሳሰረ መሆኑን ያስረሳናል፡፡ እነዚህን ማጣት ደግሞ በተግባር እንዳየነው በግፍና በበደል መጨማለቅ፣ በብጥብጥና በግጭት ውስጥ መዳከር ውስጥ ይከታል፡፡ የሰው ልጅ መብቶችን በማክበር ውስጥ ለመኖር መጣጣር ከብዙ ጥፋት ይመልሳል፡፡ እርስ በርስ ለመስማማትና የጥቃት ሥራዎችን ተጋግዞ ለመታገል ያስችላል፡፡
የአንድ አገር ሰላም፣ ደኅንነትና ዕድገት ከጎረቤቶቹ ጋር የተያያዘ መሆኑን ማየትና ክፍለ አኅጉራዊ ዝምድናን ጤናማ አድርጎ መገንባት ለአገሮች በሰላም የመኖር ዋስትና ነው፡፡ የማኅበረሰቦችና የሁሉም እምነቶች እኩልነት መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ተገንብቶ ቢሆን ኖሮ የመን ስትቃወስ ሳዑዲ ዓረቢያና የአካባቢው ሸሪኮቿ ወራሪዎቿ ባልሆኑ ነበር፡፡
በአገር ደረጃ ችግሮችን እየፈቱ ለመኗኗር የሚያስችል ፖለቲካዊ አቅም የማዋቀሩ ነገር ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ውስጥ ያለን ሕዝቦች፣ የምንገኝበት የቀንዱ አካባቢ ማዕበል የሚወደውና ማዕበል ለማሸጋገር የሚያስችል ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ድልድይ ያለበት አካባቢ መሆኑን፣ የውስጣችንም ህልውና አንዱ ከሌላው ጋር በብዙ መልክ የተጠላለፈ መሆኑን በማስተዋል፣ እንደ ዕድገት ደረጃችን ተግባብቶ ከመኖር የተሻለ አማራጭ እንደሌለን መቀበል መሠረታዊ ነው፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ ወረራ የመንን የዕልቂት፣ የችጋርና የኮሌራ ምድር ለማድረግ ዕድል ያገኘው የየመን የፖለቲካ ቡድኖች ያሉበትን በሱኒ ሺዓና በሳዑዲ ኢራን የበላይነት ትንንቅ የተጠመደ አካባቢ መሆኑን አስተውለው፣ እዚያ ወጥመድ ውስጥ የማያስገባ መፍትሔ ለአገራቸው የፖለቲካ ቀውስ ለመስጠት ባለመቻላቸውም ነበር፡፡
በኢራቅ-ሶርያ “እስላማዊ” ነኝ ባይ የአሸባሪ ገዥነት በመዋጋት ትልቅ ሚና የነበራቸው የኢራቅ ኩርዶች ጦርነቱ ገና መደምደሚያ እንኳ ሳያገኝ ከኢራቅ መንግሥት ጋር የጋራ መግባባት እንኳ በሌለበት፣ በየትኞቹም የድንበር ጎረቤቶቹ ዘንድ የኩርዲስታን ነፃ አገር ተፈጥሮ ማየት የማይሻው የኤርዶዋን መንግሥት ተፃራሪነት አፍጦ ባለበት፣ እንዲያውም ዙሪያውን የኩርዶችን መነጠል የሚፀናወት እንጂ፣ የሚያግዝ ሁኔታ በሌለበት ለነፃ አገርነት የሕዝብ ውሳኔ ማካሄዳቸው የሶሪያ፣ የኢራቅና የኢራን ፀረ መነጠል ኃይሎች (በየአገራቸው ያሉ ኩርዶች ወደዚያ እንዳያመሩ ሲሉ) ከቱርክ መንግሥት ጋር ተባብረው እንዲደቁሷቸው ከመጋበዝ አይለይም፡፡ በዚህም ምክንያት የዚያ አካባቢ መጪ ዕጣ ገና ብዙ አስፈሪ ጨለማ ያለበት ሆኗል፡፡
ከዚሁ ሁሉ ትምህርት ሊቀስሙ የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሰላምና በዕድገት ውስጥ የመኖር ፍላጎት፣ ቢያንስ ቢያንስ ሦስት ዝቅተኛ ሁኔታዎችን (በሰው ልጅነት መከባበርንና መተሳሰብን፣ እንደ አንድ አገር ማበርንና በቀጣና ደረጃ ከጎረቤቶች ጋር የሰመረ ተዛምዶ መፍጠርን) ማሟላት ያስፈልጉታል፡፡ በእነዚህ ሦስት የህልውና ውሎች ላይ ያነጣጠረ ሰፊ መግባባት በአገር ውስጥ መፍጠር ከተቻለ የማይገፋና የማይናድ የአፈና ተራራ አይኖርም፡፡ በተባበረ ትግልና በዴሞክራሲ ጎዳና ከክልል እስከ ፌዴራል መንበረ መንግሥት ያሉ ንቁሪያንና ጥላቻን የሚያፈልቁ የአገዛዝ ዝባቶችን፣ “ከ . . .  ሥፍራና ኩባንያ የተመረተ ነገር አልገዛም . . . እንትን የሚባል ቢራ አልጠጣም . . . ” እስከ ማለትና የንግድ ሥራንና ደንበኝነትን በየብሔር እስከ ማድረግ የጠበቡ ክፍፍሎችን ሁሉ ማስተካከል ይቻላል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ሲገኝ ችግሮችን ልንፈታ ይቅርና ተደማምጦ መነጋገርም የተሳነን ሆነን ከተገኘን ከመራራ ስሜት አልወጣንም፣ ተከባብሮ የመኗኗር ዕይታና ጥረቱም ጠፍቶብናል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ጉድለት በቶሎ ለመሙላት ካልቻልን ደግሞ፣ በአምባገነንነት ሥር መቀጥቀጥ ወይም ተንኮታኩቶ መባላት ደመወዛችን ይሆናል፡፡ በመስከረም 2010 ዓ.ም. ውስጥ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ውይይት ተብሎ የሰማናቸው በውጭ የሚኖሩ ሁለት ቅማንቴዎች በስሜት ግለት ከመጯጯህ በቀር ተደማምጦ የመነጋገር፣ ተነጋግሮም የመግባባት ጥረቱም ብልኃቱም አልነበራቸውም (ነጥብ በነጥብ ፈር የሚያሲዝ አወያይነትም አልነበረም)፡፡ እነዚያ ከአንድ ማኅበረሰብ የወጡ ሰዎች እስከ ዛሬ በዘለቀው መንጓለል ላይ እንኳ የተስማማ አቋም አልነበራቸውም፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት ደም ያፈሰሰ መቀናደብ የደረሰውም በእኩልነት ዓይን መከባበር በመጉደሉና ዴሞክራሲያዊ የችግር አፈታት ከስም ያለፈ ሕይወት ስላልነበረው እንደነበር እንኳ ማጤን አልተሳካላቸውም ነበር፡፡ የ‹‹ጎንደር ኅብረት›› ወገን ነኝ ባዩ ሰው ችግሩን ሁሉ በኢሕአዴግ ሴራ መተርጎሙ፣ ኢሕአዴግ መተት ሠርቶ ከፋፈለን ከማለት የማይሻል ነበር፡፡
ቅማንቶች አንቀጽ 39ኝን ሙጥኝ እስከ ማለት የሄዱት የመነጠል መብት አክንፏቸው አልነበረም፡፡ ወደዚያ የመራቸው ዴሞክራሲ የሚያስገኘው የሕዝብ ልዕልና ሕይወት ባለማግኘቱ፣ እንዲሁም ጊዜው የሰጣቸው የመብት መከራከሪያ እሱ መሆኑ ነበር፡፡ በተቀረ አንቀጽ 39ኝን ሙጥኝ ስለተባለ፣ የመሬት ወሰን ስለተበጀ፣ የቅማንት አስተዳደር የሚሉት ነገር ስለተፈጠረ (ከዚህም አልፎ የቅማንት ፓርቲ የሚባል ቢወለድ)፣ እኩልነትና መብቶች እጅ ውስጥ ገቡ ማለት አይደለም፡፡ የመብቶች መረጋገጥ የሚሻው የብቻ ፓርቲንና ድንበር መደንበርን ሳይሆን፣ የእኩልነት አመለካከትንና የዴሞክራሲን በተግባር መቋቋም ነው፡፡ ትናንትም ዛሬም የቅማንቶች የክምችት ሥፍራዎች የት የት እንደሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ከተቋቋመና ከላይ እስከ ታች በየአስተዳደር ዕርከኑ የሕዝብ ልዕልና ከተዘረጋ በየትኛውም ሥፍራ የቡድንና የግል መብቶች ዴሞክራሲያዊ ሕይወት ያገኛሉ፡፡ ቅማንቶች በተከማቹባቸው የአስተዳደር ሥፍራዎች የቅማንቶች የብዙኃንነት ድምፅ ተፈልቅቆ ይወጣል፡፡ በዚያው ውስጥ የተዛቡ ግንኙነቶችን የማስተካከል፣ ነባር የቋንቋና የባህል ቅርስን የማትረፍ፣ ማጥናት ለሚሹም ተንከባክቦ የማቆየት ሥራ ሁሉ ሊከናወን ይችላል፡፡ ቅማንቶች ብዙኃን በሆኑበት ሥፍራ የተከበረ መብትና እኩልነት በሌላ ሥፍራ ንዑሳን ሆነው ወደሚገኙ ቅማንቶችም ይዛመታል፡፡
በአማራ ክልል ውስጥም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች፣ በቅርቡም በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የታዩ የትርምስ፣ የደም መፋሰስና የመፈናቀል ልምዶች በአጠቃላይ ተከባብሮና ተጋግዞ ለመኖር በየብሔረሰብ አዕምሮንና ሕይወትን መሸንሸን ዋስትና እንደማይሆነን ለመገንዘብ አያንሱም፡፡ ዋስትና የሚሆነን፣
አንደኛ፣ ከሁሉ ነገር በላይ በእኩልነትና በመከባበር ከመተቃቀፍ የተሻለ መፍትሔ እንደ ሌለን መገንዘብና ተባብሮ ወደ ዴሞክራሲ መዝለቅና በርጋታ ተደማምጦ፣ መነጋገርንና ለችግሮች መፍትሔ መፈለግን መለማመድ፣
በብሔር መብት ስም እየከፋፈሉ ከሚያባሉም ሆነ በአንድነት ስም መብት ከሚደፈጥጡ አምታቺዎች የተላቀቀና የትኛውንም ሕገወጥነትንና መብት ረገጣን ያለ አድሎአዊነት የሚቃወም የፖለቲካ ዕይታ ማጎልበት፣
በዚህ አማካይነት መንበረ ሥልጣኑን የዝርፊያ ሜዳ ያደረጉ የትኞቹንም ሌቦች ማስተዋል፣ ብሎም በሕዝብ ተመልካችነት፣ ጠያቂነትና ድምፅ ሥር የገባ አስተዳደር ከዳር እስከ ዳር ማቋቋም፣ ከዚሁ ጋር ራስን በራስ ለማስተዳደርና ለብሔረሰቦች መብቶች መረጋገጥ የየብቻ መሬት መለየት ቅድመ ሁኔታም ዋስትናም አለመሆኑን፣ መሬት የብሔረሰባዊ ማንነት ገጽታ አካል አለመሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡
ሁለተኛ፣ የተለየ የአስተዳደር ይዞታ ለመፍጠር የተለየ ማንነት መኖር አለመኖሩ መመዘኛ መሆኑ፣ በዚሁም ምክንያት የራሴ ማንነት አለኝ ይታወቅልኝ ብሎ ወደ ክልል መስተዳድር ማመልከት፣ የማንነት ጥያቄው መልስ ሳያገኝ ሲቀር ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤት ማለት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በሕገ መንግሥቱ መሥፈሪያ መሠረት “ነኝ” እንደምትለው ነህ ወይስ አይደለህም ብሎ በማንነት ላይ ፈራጅ መሆኑ አስገራሚ ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ማንነትን በተመለከተ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራንም ሆነ የምክር ቤት አመለካከት፣ እንዲሁም ሳይንሳዊ ተብሎ የተቀመጠ መመዘኛ ከሕዝብ ልቦና ጋር ላይገጣጠም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ምሁራኑና መመዘኛው የአንድ ብሔር ብሔረሰብ ክፍልፋይ አድርጎ የሠፈሯቸው ማኅበረሰቦች ልዩ ልዩ ነን ብለው የሚያስቡ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ምሁራኑና መመዘኛው የሁለት ሦስት ማንነት ቅይጥ አድርጎ የወሰዳቸውም ሰዎች የጋራ ማንነት አለን ባዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያለው የማንነት ጉዳይ ፈራጅ ሊኖርበት አይገባም፡፡
የአገራችን ፌደራሊዝም የቋንቋ ወይም የብሔር ብሔረሰብ ፌዴራሊዝም ተብሎ ብዙ ጊዜ ይገለጻል፡፡ በእርግጥም የአገሪቱን የክልል አሸናሸን መነሻና አካሄድ በየክልል ውስጥም እየተሠራበት ያለበትን መርህ ስናስተውል ብሔር ብሔረሰባዊ መሥፈሪያ ዋነኛ የዕይታ ማዕዘን መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ብቸኛው መሥፈሪያ ግን አይደለም፡፡ ይህ የታወቀ ቢሆንም፣ የሌሎቹ መሥፈሪያዎች ምንነት ግን ጥርት ብሎ አልተቀመጠም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 እስከ መነጠል የሚሄድ ባለመብትነት በብሔር ብሔረሰብነት ሊፈረጁ የማይችሉ ውጥንቅጥ ማኅበረሰቦችን የሚያካትት ስለመሆንና አለመሆኑ አይነግርም፡፡ “ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ” በተሰኘው አገላለጽ ውስጥ አንዱ ከሌላው ያለው የፍቺ ልዩነትም አልተቀመጠም፡፡ ይሁን እንጂ በአንቀጽ 39(5) ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ በተለይም “ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ”፣ “ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው”፣ “ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው”፣ ወዘተ የሚለው አገላለጽ ከአንድ የበለጠ የብሔር/ብሔረሰቦች ትቅፍቅፍ ውጥንቅጦችንም ጨምሮ ሊኖር ስለመቻሉና የጋራ መግባቢያ ቋንቋም ግድ የማንነት መለያ ላይሆን እንደሚችል ይጠቁማል፡፡ ይህ ግንዛቤ አንቀጽ 46(2) ውስጥ ማንነት ከቋንቋ ተለይቶ እንደ አንድ መሥፈሪያ ከመቀመጡ ጋር ይጣጣማል፡፡ በተግባርም በዋነኛ ማኅበረሰብነት አንድ ብሔር ብሔረሰብነትን ካዘሉት የአፋርና የሶማሌ ዓይነት ክልሎች ባሻገር የደቡብ ሕዝቦች፣ የጋምቤላና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች መደራጀትም ከምንለው ጋር ይስማማል፡፡ ለእነዚህም ብዙ አቀፍ ክልሎች የጋራ የሚሰኝ የማንነት ገጽታም አናጣላቸውም፡፡ ሰፋ ያለ የማንነት መቀራረብን ተንተርሶ በአንድ ክልልነት መቀናበር እንደተቻለ ሁሉ በአንድ ቋንቋ ውስጥ የታዘለ ጎንደሬነትን ወይም ጎጃሜነትን፣ ወዘተ ተንተርሶ ክልል ለመሆን መንገዱ ዝግ አይደለም፡፡ ከአማራነት ትስስር ይበልጥ በጎጃሜነት፣ በጎንደሬነት፣ ወዘተ ያለኝ የማንነት ቁርኝት ይበልጥብኛል ማለት የፈለገ ብዙ ማስረጃ መደርደር አይቸግረውም፡፡
የተለየ ማንነት አለኝ ብሎ መርታት የራስ አስተዳደራዊ ይዞታ ከማበጀት ዕድል ጋር መዛመዱ፣ የተለያየ ጥቅም በማነፍነፍም ሆነ በስስት ግፊት የብቻ አስተዳደር የመፍጠር ፍላጎት ውስጥ ሊያስገባና በዘመዳም የኅብረተሰብ ክፍሎች መሀል መሸካከርያ ሊሆን ሁሉ ስለሚችል በፖለቲካ ረገድ ስህተት ነው፡፡ ለአከላለል ለውጥ ጥያቄ መነሻና መመዘኛ መሆን ያለባቸው አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ መንገዶች ተሞክረው ሊፈቱ ያልቻሉ ውዝግቦችና ጥያቄዎች ሲኖሩ ወይም የአከላል ለውጥ የበለጠ ልማትን የሚጠቅም ሆኖ ሲገኝና በዚህ ላይም የሚመለከታቸው ክፍሎች ሲስማሙ ለውጥ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡
ሦስተኛ በፌዴራል መዋቅሩ ውስጥ የመቆየትና ያለመቆየት ፖለቲካዊ መብትን ከብሔር ብሔረሰብነት ጋር አጣብቆ ሕገ መንግሥት ውስጥ ማስቀመጥም ሆነ ምርጫ በመጣ ቁጥር ይህንን መብት እያነሳሱ መደስኮር ዴሞክራሲያዊነትን አያረጋግጥም፡፡ ዴሞክራሲያዊነት የሚረጋገጠው በዴሞክራሲያዊ መብቶችና መቻቻል ውስጥ መኗኗርን መሠረት በማስያዝ ላይ በመረባረብና ችግሮች ሲመጡ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች ለመፍታትና ውጤቱንም ለመቀበል በመቻል ነው፡፡
እናም በጥቅሉ ድንበር ከመደንበር ይልቅ ሳይናጩ መተዳደር መብለጡን ተማምኖ የንቁሪያና የግጭት መፍለቂያ የሆነ የብሔረተኛ ክፍፍል አዙሪትን ለማሸነፍ የሚያስችል መፍትሔ መሻት ዛሬ የማይታለፍ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ በየትኛውም ዓይነት ብሔርተኝነት አለመታወርን፣ በክልል ደረጃም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ለሥልጣን የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ከአንጓላይ ትልምና ቡድድን የመላቀቃቸውን ነገር፣ ፌዴራላዊ አስተዳደር የሰመረላቸውን አገሮች ልምድ ከእኛ ጋር አገናዝቦ የሰብዓዊ መብት ክትትልንም ሆነ የፌዴራል ምርመራንና የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አሠረጫጨት የማጠናከር ጉዳይ፣ ፌዴራላዊ የአስተዳደር አካላትን ቁጥር ማበራከትም ሆነ ክልሎችንና ክፍላተ ክልሎችን ወደ አራትና አምስት ምድሮች ማቧደን ተረጋግቶ ልማት ላይ ከማተኮር ረገድ የሚኖራቸውን ጥቅምና ጉዳት ጊዜ ወስዶ መመርመር ሁሉ ይመጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ከተከናወነ በኋላ ደግሞ ትልቁ ነገር የቡድንን ፍላጎት በሕዝብ ስም ከመትከል መንገድ በፀዳ አኳኋን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሰፊው የተቀበሉትን የመፍትሔ ማሻሻያ ሥራ ላይ ማዋል ነው፡፡
በታደሰ ሻንቆ

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

SOurce   –      መነሻ ገጽ