October 9, 2017

ኤርኔስቶ ቼጉቬራ – ዓለማቀፉ ታጋይ

አርጀንቲናዊው ኤርኔስቶ ቼጉቬራ በትምህርቱና በሙያውም ሐኪም ቢሆንም ዓለም በብዙ የሚያወቅው በግራ ክንፈኛ ተዋጊነቱ ነው፡፡

ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ በዓለም ዙሪያ በነፃነት አላሚ ወጣቶች ልቦና ውስጥ እንዳደረ ቦሊቪያ ውስጥ በዓላማ ተፃራሪዎቹ እጅ የገባውና የተማረከው የዛሬ 50 ዓመት በዛሬዋ እለት ነው፡፡
ቼ ተኮትኩቶ ያደገበት የቤተሰብ መሠረቱ ሆኖ በወጣትነቱ ሲበዛ ለድሆች፣ ለተገፉና ለተጨቆኑ ተቆርቋሪ ሆነ፡፡

በወጣትነት ዘመኑ በብዙ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተዘዋውሯል፡፡

ይህም በዘመኑ በየአገሩ መንግስታት ጭቆና የሚፈፀምባቸውን፣ የተገፉትን፣ ፍትህ የራቃቸውንና የተበደሉትን በቅርበት ለማየት እድል ፈጥሮለታል፡፡

ቼ ይሄን አይቶ ሁኔታው መቀየር እንዳለበት የጭቆናው ቀንበር መሠባበር እንዳለበት ማሰብ መብስልሰሉ አልቀረም፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ በሜክሲኮ በሙያው እየሠራና በዩኒቨርስቲ እያስተማረ በነበረበት ወቅት ከኩባውያኑ ወንድማማቾች ራውልና ፊደል ካስትሮ ጋር ተዋወቀ፡፡

እነሱም በአገራቸው የተንሠራፋውን ጭቆና መታገያ መንገዶችን መላ ለማለት በሜክሲኮ እንደሚገኙ ነገሩት፡፡

እውቂያቸው ወደ ዓላማ አጋርነት ተሸጋገረ፡፡

ወደ ኩባ ለመዝመት የወታደራዊና የሸምቅ ውጊያ ልምምድ ውስጥ ገቡ፡፡
በልምምዱ ቼ ከሁሉም ብልጫ ያለውና የላቀ ነበር ይባልለታል፡፡

ጊዜው ደረሰና 82 ሆነው በግራንማ ጀልባ ለታላቁ ተልዕኮ ወደ ኩባ ቀዘፉ፡፡
ጉዞው አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡

ይልቁንም ገና ከማለዳው መስዋዕትነቱ ከበደ፡፡

ከባሕር ጉዞው በኋላ የኩባን መሬት ለመቆናጠጥ ባደረጉት ሙከራ ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ተሠዉ፡፡

ቼጉቬራ መድሐኒትና የሕክምና ቁሳቁስ መያዣ ሳጥኑን ጥሎ ቦምብና ጠመንጃውን ለመታጠቅ ተገደደ፡፡

ከገጠማቸው የተኩስ ውርጅብኝ በኋላ እነ ቼ-ጉቬራ ፊደል ካስትሮና ከ20 ያልበለጡ የሐምሌ 26 ንቅናቄ ተዋጊዎች ነበሩ፡፡

በሴራ ማይስትራ ተራራ ተገን ይዘው በዓላማ ፅናት ተባባሪና ደጋፊዎቻቸውን እያበዙ የጄኔራል ባቲስታን ጨቋኝ አሻንጉሊት አስተዳደር አሸቀነጠሩት፡፡

የኩባ አብዮትም ተባለ፡፡

ቼ-ጉቬራ ከአብዮቱ በኋላ ከስልጣኑም ከሹመቱም ባይቀርበትም ሌሎች ነፃነት የሚሹ ሕዝቦች አሉና ወደዛ ላቅና ብሎ ዴሴቲቱን ተሠናበተ፡፡

 

የቼ ጉቬራ ሃምሳኛ ሙት ዓመት ሲታወስ

Many in Cuba think of Che Guevara as nothing less than a hero
AFP

የኩባዋ ሳንታ ክላራ ከተማ ዕለተ-እሁድ የቼ ጉቬራ ሙት ዓመትን ለመዘከር በተሰባሰቡ በሺህ በሚቆጠሩ ኩባውያን እና የቼ አድናቂዎች ተጨናንቃ ነበር የዋለችው።

ቼ በፈረንጆቹ ጥቅምት 9/1967 ዓ.ም. ነበር ቦሊቪያ ውስጥ ሕይወቱ የጠፋው።

የቼ የልብ ወዳጅ የነበሩት የአሁኑ የኩባ ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ በዓሉን ሊያከብሩ ከተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ነበሩ።

ብዙዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ፕሬዝዳንት ራወል የቼ መታሰቢያ ሃውልት ላይ ነጭ አበባ ሲያስቀምጡ መመልከት ችለዋል።

ለአምስት አሥር ዓመታት የቼ ምስል ከኩባ የመገበያያ ገንዘብ ጀምሮ እስከ ካናቴራ ድረስ መላ ኩባንና ላቲን አሜሪካን ሲያዳርስ ቆይቷል።

ከላቲን አሜሪካ አልፎም ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላ ዓለም ቼ የነፃነት አርማ ተደርጎ ይቆጠራል። ‘ፋኖ ተሠማራ እንደ ሆ ቺ ሚን እንደ ቼ ጉቬራ’ የተሰኘውን ስንኝም ከቀደመው ጊዜ ማስታወስ ይቻላል።

በሳንታ ክላራ የተሳበሰቡ ኩባውያን እንደራሳቸው ሰው የሚቆጥሩትን የአርጀንቲናዊው ቼ ጉቬራን ምስል በካናቴራ እንዲሁም በፎቶ በማውለብለብ ሲያስቡት ውለዋል።

“ቼ ለእኛ ኩባውያን ምን ማለት እንደሆነ እናውቃለን። ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለላቲን አሜሪካውያን እና ለዓለም ብዙ አድርጓል። ለዚህም ነው ምስሉን በደረታችን እርሱን ደሞ በልባችን ይዘን የምንዞረው” በማለት አንድ ኩባዊ ይናገራል።

Che Guevara (L) and Fidel Castro (R)
AFP

አጭር የምስል መግለጫ

ቼ ጉቬራ (ግራ) እና ፊደል ካስትሮ (ቀኝ) ለአራት ዓመታት የኩባን አብዮት መርተዋል።

በፈረንጆቹ 1967 ቼ ሲሞት ሟቹ የኩባ ፕሬዚደንት ፊደል ካስትሮ ያሰሙት ንግግር፤ በተለይ ደግሞ “ኩባውያን ሕፃናት እንደ ቼ ሁኑ” በማለት ያስተላለፉት መልዕክት እንደገና ሲሰማ ውሏል።

በዝክሩ ላይ የተገኙትን ታዳጊ ተማሪዎች ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት የቼ ሌጋሲ በኩባ ለሚመጡት በርካታ አስርት ዓመታት ሰርጾ ሊቆይ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ደጋፊዎቹ እንደ ቆራጥ ጀግና እና መስዋዕት የሚመለከቱት ቼ በነቃፊዎቹ እንደ ጨካኝ አረመኔ መቆጠሩ አልቀረም።

ሆነም ቀረ ቼ ጉቬራ አሁንም እያከተመ ያለው የኩባ የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ትውልድ ትልቅ አካል መሆኑ እሙን ነው።

ባለፈው ዓመት ፊደል ካስትሮ ሕይወታቸው ሲያልፍ ለቀብራቸው የወጡ የእሳቸውና የቼ ደጋፊ ኩባውያን አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው በ80ዎቹ የሚገኝ እንደሆነ ተስተውሏል።

ራውል ካስትሮም በሚቀጥለው ዓመት ሥልጣናቸውን ይለቃሉ።

በኩባም ለመጀመሪያ ጊዜ ከካስትሮ ቤተሰብ ውጭ የሆነ ሰው ከ60 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን እንደሚመጣ ይጠበቃል።

SOURCE     –     BBC .COM /Amharic