South Sudan
Unicef
አጭር የምስል መግለጫ ደቡብ ሱዳን ለሴቶች ትምህርት ምቹ ካልሆኑ ሃገሮች አንዷ ሆናለች

ባደጉት ሃገራት ውስጥ ትምህርት ተጨማሪ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ያስፈልገዋል አያስፈልገውም የሚለው የፖለቲካ መከራከሪያ ጉዳይ ሆኗል።

በብዙ ታዳጊ ሃገራት ለሚገኙ ቤተሰቦች ግን ‘የመማር እድል ይኖረኝ ይሆን?’ የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ ይቀመጣል።

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚገልጸው ባለፉት አስር ዓመታት የትምህርት ተደራሽነት ያሳየው ለውጥ “ወደ ዜሮ” የቀረበባቸው ድሃ ሃገራት አሉ።

የትምህርትን ጥራት በተመለከተ የተደረገ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ ከ600 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ትምህርት ቤት ቢገቡም እውቀት እየቀሰሙ አይደለም ማለቱን ድርጅቱ “አስደንጋጭ” ብሎታል።

Niger
Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በኒጀር ከ15 እስከ 17 ዓመት ከሆናቸው ሴቶች መካከል 17 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው የተማሩት

በምዕራባውያን ሀገራት የሚገኙ ሴቶች በትምህርት ውጤታቸው ከወንዶች እየበለጡ በሚገኙበት ወቅት፤ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በተለይም ደግሞ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል።

በተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የልጃገረዶች ቀን ሲከበር፤ ሴቶች ትምህርታቸውን ለመከታተል በጣም አስቸጋሪ የሆባቸውን ቦታዎች ለይቷል።

የግጭት ቀጠናዎች

በእነዚህ 10 ሃገራት ትምህርት ከሚያቋርጡት መካከል በቀዳሚነት የሚቀመጡት ልጃገረዶች ናቸው።

በእነዚህ በመፈረካከስ አደጋ ላይ በሚገኙ ሃገራት የሚገኙ ብዙ ወላጆች የድህነት፣ ጤና ማጣት፣የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘትና በጦርነት እና ግጭት ምከንያት ከመኖሪያቸው የመፈናቀል አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

refugees
Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች

ብዙ ወጣት ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ ሥራ እንዲሰሩ ይጠበቅባቸዋል። ብዙዎቹም ትምህርት ዕድል ሳያገኙ ትዳር ይመሰርታሉ።

ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሴቶች ትምህርት የማቆማቸው ዕድል ከሁለት እጥፍ ይልቃል።

የቻድ ስደተኞች
Unicef
አጭር የምስል መግለጫ በቻድ ያሉ ግጭቶች በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሴት ተማሪዎችን ትምህርት አጨናግፈዋል

ደረጃው የተሰጠው በሚከተሉት መስፈርቶች ነው፡

  • የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ቦታ ባላገኙ ልጃገረዶች ቁጥር ጋር ሲመጣጠን
  • የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ቦታ ባላገኙ ልጃገረዶች ቁጥር ጋር ሲመጣጠን
  • የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ባጠናቀቁ ልጃገረዶች ቁጥር ጋር ሲመጣጠን
  • የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባጠናቀቁ ልጃገረዶች ቁጥር ጋር ሲመጣጠን
  • ልጃገረዶች ትምህርት ቤት የሚማሩባቸውን አማካኝ ዓመታት ከግምት ውስጥ በማስገባት
  • መፃፍ እና ማንበብ የማይችሉ ሴቶች ቁጥር ከግምት ውስት በማስገባት
  • የመምህራንን የትምህርት ደረጃ በመመዘን
  • የመምህር-ተማሪ ምጣኔ
  • ለትምህርት ተብሎ በሚወጣ የገንዘብ መጠን

እንደሶሪያ በጦርነት ውስጥ ከሚገኙ ሃገራት ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ከባድ ነው።

ሴቶች ትምህርት ለማግኘት ከባድ የሚሆንባቸው 10 ሃገራት የሚከተሉት ናቸው፤

  1. ደቡብ ሱዳን: የዓለማችን አዲሷ ሃገር በግጭትና በጦርነት በተደጋጋሚ ተጠቅታለች። በዚህ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ከመውደማቸውም በላይ ሰዎች መኖሪያ ቀዬአቸውን ለቀው እየሸሹ ነው። ሶስት አራተኛ የሚሆኑ ሴቶች ወደ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም።
  2. ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ: አንድ መምህር ለ80 ተማሪዎች ይደርሳል።
  3. ኒጀር: ከ15 እስከ 17 ዓመት ከሆናቸው ሴቶች መካከል 17 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው የተማሩት።
  4. አፍጋኒስታን: ትምህርት ቤት በሚሄዱ ወንዶችና ሴቶች መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ሰፊ ነው።
  5. ቻድ: ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚያደርጓቸው ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅፋቶች አሉ።
  6. ማሊ: 38 በመቶ ሴቶች ብቻ ናቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁት።
  7. ጊኒ: ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች በትምህርት ቤት ያላቸው አማካይ ቆይታ ከአንድ ዓመት በታች ነው።
  8. ቡርኪናፋሶ: አንድ በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ ናቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህራታቸውን የሚያጠናቅቁት
  9. ላይቤሪያ: ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ።
  10. ኢትዮጵያ: ከአምስት ሴቶች ሁለቱ 18 ዓመት ሳይሞላቸው ያገባሉ።

በብዙ የደሃ ሃገራት የመምህራን እጥረት አለ።

ለትምህርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገባው ቃል እንዲተገበር እ.አ.አ በ2030 69 ሚሊዮን መምህራን ሊቀጠሩ ይገባል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ዓመት አስታውቆ ነበር።

Florence Cheptoo
አጭር የምስል መግለጫ በኬንያ ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩትና በ60 ዓመታቸው ማንበብ ቻሉት ፍሎረንስ ቼፕቶ

ልጃገረዶችን በትምህርት ቤት ውስጥ ማቆየት ከተቻለ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ትርፍ ይገኛል ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል።

በኬንያ ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩትና በ60 ዓመታቸው ማንበብ የቻሉት ፍሎረንስ ቼፕቶ ትምህርት በግልም ትልቅ ጥቅም እንዳለው ማሳያ ናቸው።

የዋን ዘመቻ ፕሬዝዳንት የሆኑት ጋል ስሚዝ፤ ልጃገረዶች በትምህርታቸው ስኬታማ አለመሆናቸው “በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚኖረው ዘላቂ ድህነት” መክንያት ይሆናል ብለዋል።

“አሁንም ከ130 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች ከትምህርት ቤት ውጭ በመሆናቸው መሃንዲስ፣ የሥራ ፈጣሪ፣ መምህራን እና ፖለቲከኛ ሊሆኑ የሚችሉ 130 ሚሊዮን ሰዎችን እያጣን ነው” ይላሉ።