ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ የእስር ጊዜውን ቢያጠናቅቅም ባላወቅነው ምክንያት የዝዋይ ማረሚያ ቤት አስተዳደር አልፈታውም ብሏል ሲል የተመስገን ወንድም ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የ3 ዓመት የፍርድ ጊዜውን ዓርብ (ጥቅምት 3) ቢያጠናቅቅም የዝዋይ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ግን ያለምንም ምክንያት ተመስገንን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ስላልሆነ ወደ መጣንበት አዲስ አባባ እየተመለስን ነው ሲል ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ በስልክ ገልጾልናል።

ትናንት ሃሙስ የእስረኞች አስተዳደር ክፍል ውስጥ ያገኘሁት ግለሰብ ተመስገን የሚፈታበትን ቀን ጠይቄው መዝገብ አገላብጦ ዛሬ እንደሚፈታ አረጋግጦልኝ ነበር። የእስር ጊዜውም ስለሚጠናቀቅ እንደሚፈታም እርግጠኛ ነበርኩይላል ታሪኩ።

ተመስገን፤ ታሪኩ እና ጓደኞቹን በማረሚያ ቤት ውስጥ ሊያናግራቸው ሲመጣ ባልተለመደ መልኩ በስምንት ወታደሮች ታጅቦ እንደነበር ወንድሙ ይናገራል።

በነበራቸውም ቆይታ መፈታት ነበረብኝ ነገር ግን እንደማይፈቱኝ ነግረውኛል፤ ለምን እንደሆነ አላውቅምሲል ተመስገን ነግሯቸዋል።

የተመስገን እናት፣ የቤተሰብ አባላት እና ጓደኞቹ የእርሱን መፈታት ተስፋ አድርገው በጉጉት እየጠበቁ ነበር።

ይፈታል በሚል ተስፋ በዝዋይ ማረሚያ ቤት ውስጥ እና ከዚህ ቀደም የፃፋቸውን የተለያዩ ፅሑፎች ስብስብ ጊዜ ለኩሉበሚል ርዕስ በመፅሃፍ ታትሞ ገበያ ላይ ውሏል።