October 15, 2017

Samson Genene

የትኛውም የእድሜ ክልል በተለየ  የወጣትነት የእድሜ ዘመን ነፃነት የሚፈልግበት እና እምቢ ባይነት የሚጠነጠንበት ዘመን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የወጣትነት የእድሜ ዘመን እምቅ ጉልበት ለሀገር ግንባታ የሚውልበትም ዘመን ነው፡፡ የአለም ሀገራት የአብዮት ታሪክ እንደሚነግረን ከሆነ አብዛኛዎቹ አብዮቶች የተመሩት በወጣቶች እንደነበር ነው፡፡ ከጥቁር አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ እስከ ኩባው አብዮት መሪ ፊደል ካስትሮ መሪነት  የተካሄዱትን አብዮቶች ካየን በወቅቱ የአብዮቱ መሪዎችም ሆነ አብዮቱን የሚያቀጣጥሉ የነበሩት ብዙሀኑ በወጣትነት እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ህዝቦች ስለመሆናቸው ለመረዳት እንችላለን፡፡ ይህም የወጣትነት እድሜ ዘመንን እና አብዮት ያላቸውን ቁርኝት ለማየት የሚያስችለን ይመስለኛል፡፡

አንድን ሉአላዊት ሀገር የሚመራ ስርአተ መንግስት አድሎ የሰፈነበት ስርአት ካሰፈነ፣ በህዝቦች መሀል ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ማድረግ ካልቻለ፣የሀይማኖት እኩልነት ማስፋን ካልቻለ… በዛች ሀገር አብዮት የሚነሳበትን እድል ከፍ ያደርገዋል፡፡ በአብዛኛዎቹ በአለማችን የታዩት አብዮቶች መንስኤዎቻቸው በአንድ በኩል ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች የወለዷቸው ሲሆኑ ከፍ ሲልም ፓለቲካዊ ግፍ የወለዷቸው ናቸው፡፡ ከቅርቡ የአረብ አብዮት እስከ ሩቁ የጥቁር አሜሪካኖች አብዮትን መንስኤዎች ስናይ መንስኤዎቻቸው ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ስለመሆኑ መረዳት እንችላለን፡፡

የወጣትነት የእድሜ ዘመን በነበረው ሲስተም ላይ አዲስ ነገር ለመጨመር  ጉጉት የሚያድርበት ዘመን ነው፡፡ አዲስ ነገር ለመሞከር ደግሞ ከየትኛው ነገር በላይ የስራ እና የማሰብ ነፃነትን ይፈልጋል፡፡ የስራም ሆነ የማሰብ  ነፃነት ደግሞ እንደግለሰብም ሆነ እንደ ቡድን እራስህ የምታመጣው እንደመሆኑ በወጣትነት የእድሜ ዘመን ነፃነትን ለማስጠበቅ እስከ መጨረሻው ምህዳር ድረስ የመጓዝ ተነሳሽነትን ይፈጥራል፡፡ ይህ ማለት ግን ከወጣትነት የእድሜ ክልል ውጪ ያለው ህብረተሰብ ለነፃነቱ አይነሳም ማለት አይደለም፡፡ የወጣትነት እድሜ ዘመን ተፈጥሮአዊ ከሆነው የወጣትነት ሀይል ጋር በተያያዘ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በአንፃራዊ መልኩ ሲታይ ለነፃነቱ ዘብ የመቆሙ እውነትነት ያይላል ለማለት እንጂ፡፡

በሀገሩ ባለ የሌብነት አሰራር ተማሮ እራሱን ካቃጠለው ቡአዚዝ እስከ የህወሀት ኢህአዴግን ጠብመንጃ እና ስቃይ ከቁብ ሳይቆጥር በእሬቻ በአል ላይ የህወሀት ኢህአዴግ መንግስት ስልጣን እንዲለቅ በአደባባይ እስከጠየቀው ገመዳ አይነት ያሉ ወጣቶች የጀግንነት ድርጊት ከራሳቸው አልፈው ለብዙሀኑ ወጣት መነሳሳት መንስኤ የመሆናቸው እድል ከፍ ያለ ነው፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን የተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነትን ከፊት ሆነው እየተቃወሙ የሚገኙትም ሆኑ በስርአቱ አፈሙዝ እየተገደሉ ያሉት ህዝቦች በአብዛኛው ወጣቶች እንደመሆናቸው የሀገራችን ወጣትም ለነፃነቱም ሆነ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እስከ ሞት ድረስ እንደሚሄድ እና እየሄደ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

የተንሸዋረረው የህወሀት ኢህአዴግ የፌደራዚም ፓሊሲ ወጣቱን ትውልድ አንድም ከቀየው እና ከአካባቢው ሳይረቅ በዛው ቦታ ብቻ ተወስኖ እንዲኖር እና እንዲሰራ ማገዱ ፣ ከፍ ሲልም እውቀቱን እና ተሞኩሮውን ከቀየ ባለፈ አለምአቀፋዊ እንዳያደርግ መሰናክል መሆኑ ህወሀት ኢሃዴግ የወጣቱን ትውልድ አስተሳሰብ በተወሰነ ምህዳር ስር ብቻ ለመገደብ  እስኬት ድረስ እንደሚሄድ ማሳያ ነው፡፡ህወሀት ኢህአዴግ ላለፉት ሀያአምስት አመታት ሀገራችንን በብቸኛ ፈላጭ ቆራጭነት እየመራ የብዙሀኑን ህዝብ ህይወት ሲኦል የጥቂት ጀሌዎችን ህይወት ግን ገነት ማድረጉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በስርአቱ እየተበደሉ እና ኑሯቸው ሲኦል ከሆነባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ወጣቱ ትውልድ ይገኝበታል፡፡ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የወጣት ትውልድ ስደት የታየው በህወሀት ኢህአዴግ አገዛዝ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ሀገሩን ለቆ ባህር አቋርጦ የሞተው ሞቶ የተረፈው አረብ ሀገራት እና ኢሮፕ እንዲሰደድ ያደረገው የዘረኛው ህወሀት ኢህአዴግ የዘረኝነት እና የአድሎ አገዛዝ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ወጣቱ ትውልድ ከስደት በመለስ በሀገሩ መሬት እምቢኝ ማለት ጀምሯል፡፡ ይህም ወቅታዊውን የሀገራችን የወጣት ትውልድን ጥያቄ ተፈጥሮአዊው ከሆነው የወጣትነት ዘመን ነፃነት ፈላጊነት ጋር ተገናኝ ስናደርገው ወጣቱ ትውልድ ያጣውን እና የተነጠቀውን ነፃነት እስካላመለሰ ድረስ የሚያቆመው ምድረሀይል ላለመኖሩ ለማወቅ የወጣትነት እደሜ ዘመንን እና አብዮትን ድርሳናት ብቻ መመርመሩ በቂ ይመስለኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በብዙሀኑ የሀገራችን ቦታዎች የሚታየው ህዝባዊ እምቢተኝነት በህወሀት ኢህአዴግ አገዛዝ የተንገሸገሹ ወጣቶች የሚከወን እንደመሆኑ በሀገራችን ሰማይ ስር ያንዣበበውን የለውጥ ፍላጎት ተፈጥሮቸዊው ከሆነው የወጣትነት ለውጥ ፈላጊነት ጋር ባስተሳሰረ መልኩ ማየቱን ተገቢ ያደርገዋል፡፡ ከሀገራችን አጠቃላይ ህዝብ ከ65 በመቶ ያህሉ በወጣትነት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኝ እንደሆነ የማእከላዊ እስታትስቲክ አሃዞች ያመላክታሉ፡፡ ይህ ብዙሀኑ የሀገራችን ህዝብ በህወሀት ኢህአዴግ የዘረኝነት፣የሌብነት እና የአድሎ አገዛዝ ተንገሽግሾ አሁን ላይ ለውጥን በመፈለጉ የተነሳ ከአገዛዙ አፈሙዝ ፊት ለፊት ተፋጧል፡፡ የወጣቱን ትውልድ የለውጥ ጥያቄ ስርአቱ እንደለመደው ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር በማያያዝ እና በመፍትሄነትም የማይተገበሩ እቅዶች በማቅረብ በአቋራጭ ለማለፍ እየሞከረ ይገኛል፡፡

ከየትኛውም ዘመነ መንግስት ባልታየ ሁኔታ እስርቤቶችን በወጣቶች የሞላው ህወሀት ኢህአዴግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከሀያ ሺህ በላይ ወጣቶችን ማሰሩን የስርአቱ የፕሮፓጋንዳ ማሽን በሆኑት የራሱ ሚዲያዎች ጭምር የገለጸው ጉዳይ ነው፡፡ ስርአቱ በአንድ በኩል መብቱን የጠየቀውን ወጣቱን ትውልድ እስር ቤት እያስገባ በሌላ በኩል ደግሞ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል የሚፈጥር ፓኬጅ ቀርጫለው እያለ በወጣቱ ትውልድ ወርቃማ ጊዜ ላይ እየቀለደ ይገኛል፡፡ በእኔ እምነት አሁን ላይ ወጣቱ ትውልድ ከየትኛውምጊዜ በተለየ የስርአቱን የማታለያ መንገዶች ተረድቷል፡፡ ለዚህም ማሳያው የሀገሬ ወጣት አሁን ላይ እየጠየቀ ያለው የስርአቱን ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን የስርአቱን ስልጣን መልቀቅ መሆኑ ነው፡፡ ከሀገራችን ሰማይ ስር ወቅታዊ ጥያቄ በማንሳት ከስርአቱ አፈሙዝ ጋር ፊት ለፊት እየተጋፈጡ ያሉት ሞት አይፈሬ ወጣቶች ያነገቡትን ትውልዳዊ ጥያቄ ከግብ ለማድረስ ህዝባዊ አብዮትን እንደመሳሪያ መጠቀማቸው በእኔ እምነት ብዙሀኑ ህዝብ የህወሀት ኢህአዴግን አገዛዝ በተመለከተ ብዙሀኑ ህዝብ አንድ አይነት ጠርዝ እንዲይዝ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡

የወጣቱ የለውጥ ጥያቄ ሲያይልበት ማህበራዊ ሚዲያዎችን እና ኢንተርኔትን ከማቋረጥ ባለፈ  በሀገሪቷ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው ህወሀት ኢህአዴግ ተፈጥሮአዊ የሆነውን የወጣት ትውልድ ለውጥ ፈላጊነት እንደለመደው በጠብመንጃ አፈሙዝ ለመመለስ እየዋተረ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን ወጣቶች መሪነት በሀገራችን የተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት የህወሀት ኢህአዴግ የግፍ አገዛዘዝ የወለደው እንደመሆኑ የብዙሀኑን ህዝብ በተለይም ደግሞ የወጣቱን ትውልድ ማህበራዊ፣ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት እስካላሟላ ድረስ ተፈጥሯዊ የሆነው የወጣት ትውልድ እምቢተኝነት ጥያቄ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡

የሩቁን ትተን የቅርቡን ከግብፅ እስከ ቱንዚያ የተነሳውን ህዝባዊ ቁጣ ስንመለከት ምክንያት አሰሪ በሆነው እድሜያቸው የተነሳ ስራ የደምስራቸው ያህል የመኖራቸው ዋስትና የሆነባቸው ፣ ስራ ለማግኘት ከእውቀታቸ እና ዜግነታቸው ይልቅ ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታ የተበተባቸው እና በሀገራቸው የስራ እድል ያለመኖሩ ያስቆጣቸው እንዲሁም ነፃነትን በሚፈልገው እድሜያቸው ነፃነትን ያጡ ብዙሃን ወጣቶች መሆናቸውን እንረዳለን፡፡

በሀገራችንም የመንግስት ባለስልጣኖች እና ጋሻ ሻግሬዎቻቸው በዘረፉት ሀገራዊ ሀብት ፎቆችን እየሰሩ፣ ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ዘመዶቻቸውን በቅምጥል ከማኖር አልፈው ውሽሞቻቸውን ለግብይት ዱባይ እየላኩ ያለ ተጠያቂነት በሚንጎራደዱበት ብዙሃኑ  ወጣት ስራ ለማግኘት ከዜጋነቱ ፣ተምሮ ካገኘው ዲግሪ፣ማስተርስ፣ዶክትሬት ይልቅ የኢሃዴግ አባልነት መታወቂያ፣ተወልዶ ባደገበት ሀገር ቋንቋ፣ ብሄር  እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡ ከላይ እንደጠቀስኩአቸው ሀገሮች የጀመረውን እና ከተገፊነት ወደ እኩልነት የሚያሸጋግረውን የለውጥ አብዮት ህወሀት ኢህአዴግን ከስልጣን ሳያወርድ የሚገታው  ምንም አይነት ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም፡፡