October 14, 2017

አገራዊ ራእያችንን የሚያናውጡ፤ የህዝባችንን ማንነት የሚመርዙ፣ ስብእናችንን የሚያዘቅጡ አዳዲስ አስተሳሰቦችና መጥፎ ልማዶች በወንጌል እና በስልጣኔ ተሽፍነው ወደ አደባባይ ሲመጡ እንክርዳዱን ከስንዴው ለይቶ ማሳየት ልጆቿን ከጥፋት መታደግ በእቶጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስር ካሉት መዋቅሮች በዋናነት የሊቃውንት ጉባዔ ስልጣንና ተግባር ነበር። ብዙም ሩቅ ሳንሄድ በአስራ ስምንት መቶዎቹ መጨረሻ በግዜው የመጻህፍት ትርጏሜ መንበር በነበረው ከወሎ ደሴ አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል እርቆ በሚገኘው የቦሩ ሥላሴ እነ መምህር አካለ ወልድ በተገኙበት የተደረገው የሮማ ካቶሊኮቹ እንደራሴዎች እነ ዶር አየለ የተረቱበት ዳግማዊ ኒቅያ እና ከዚያ የወጣው ትንታኔ ድንቅ በሆነው ኮካሃ ሃይማኖት ተጽፎ ይገኛል። እነ አስረስ የኔ ሰው፣ አድማሱ ጀንበሬ እንዲሁም አለቃ አያሌውን የመሳሰሉ ልበ ብርሃኖች በየዘመናቸው የተነሱ ቀንዲሎቻችን ነበሩ።
የአቡነ ጳውሎስ አስተዳደር አንድ ብሎ ወደ መንበር ላይ “ሲዎጣ እውር አይመራንም !” ብሎ እነ አለቃ አያሌውን አባሮ ሊቃውንት ጉባዔውን ሽባ ካደረገው ግዜ ጀምሮ ከሳቸው ህልፈት ቦኋላ ዛሬም ድረስ አንደበቱ እንደተለጎመ ነው።
አሁን የመረጃ ዘመን ላይ ነው ያለነው ስንል መረጃ በብርሃን ፍጥነት የምድርን ንፈቀ ከባበት በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ መረጃን ማድርሰ የምንችልበት ወቅት ላይ መገኘታችንን ለማጠየቅ ነው። ይህ የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ነገር በጎ ነገር እንዳለው ሁሉ በአግባቡ ካልተያዘም የሰውን አንጎል በቀላሉ እንዳይመለስ አድርጎ እንደ እርጎ ሊመርዘው እንደሚችል በብዙ አጋጣሚ እየታየ ነው። ሃላፊነት የሚሰማቸው መንግስታት እና ጠንካራ የሲቪክ ተቋማት ባሉበት አገሮች ውስጥ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሰፊ ትኩረት ይሰጣቸዋል።
ከቅርብ አመታት ክስተቶች ጥቂቶቹን ብንመለከት አስደማሚም፣ አስደንጋጭም፣ አደናጋሪም እንዲሁም አሳፋሪም ኩነቶች በሃይማኖት ስም ሲፈጸሙ ታዝበናል።
“ደቂቀ ኤልያስ” እንባላለን ብለው ራሳቸውን የሰየሙ አለን የሚሉትን አዋጅ ለአለም ይነገር ብለን መረጃውን ለተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊና ለአምስት ኪሎው ቅዱስ ሲኖዶስ ሲኖዶስ አስገብተናል ሲሉ ከነበሩት ስብስቦች ጀምሮ በየደረጃው፣በዛው ሰሞን የክረምት ወራት በቃሊቲ ቤተክርስቲያን መስቀል ከሰማይ ወረደ፣ጳጳሳትም ጎበኙት በተባለ ግዜ ወዘተ ምእመኑ ምስጢሩን ለማወቅ ያን ያህል ሲተራመስ ጉዳዩን መርምሮ ሃይማኖታዊ ትንታኔ መስጠት፣ ሃሰትም ከሆነ ድርጊቱን በአግባቡና በወቅቱ መልስ መስጠት ሃላፊነቱ የሊቃውንት ጉባዔ ቢሆንም ቅሉ መልሱ ግን ዝምታ ነበር።
አንድ አጥማቂ ነኝ ብሎ ምእመናኑ እንደከብት ሲነዳ የነበረ መምህር ግርማ ከተባለ ሰው ክህነት ከሌለው ሰው ጀምሮ ከደብረጽዮ በተላለፈው ቀጭን ትእዛዝ እራሱን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ህብረት ብሎ በሚጠራው ድርጅት በኩል ያውም እኮ ሃጢአት; ወንጀልና ነውር ሁሉ ቤተመንግስቱን ካነጸበት የቦኮ ሃራም አገር ናይጀሪያ የየበቀለ ጆሽዋ የተባለ ሃሳዊ ነቢይ ወደ ኢትዮጵያ ተጋብዞ እንዲመጣ ከተደረገ ባለፈው ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ እንደ ስፓኒሽ ቡል ፋይቲንግ ማስታወቂያ ነቢይ እከሌ ነኝ የሚሉ ግዙፍ ቢል ቦርድ በመስቀል ህዝቡን እንደከብት የሚነዱ ጉግማንጉጎች ሲበቅሉ፣ ታቦተ ጽዮንን ወደ አገራችን ከገባች ከሶስት ሽህ አመታት፣ ግማደ መስቀሉን ከተረከብን ከአምስት መቶ አመታት ቦሃላ ወያኔ በቀደደላቸው ቦይ ይፈሱ ዘንድ የዘረኝነት ፖለቲካውን በመለጠጥ ባእድ አምልኮውን ወደ አንድ ህብተሰብ ብሔራዊ ማንነት በማሳደግ በመንግስት ደረጃ የሚዘከር ህዝባዊ በአል በደብረዘይት ሲተከልና ቤተክርስቲያን የስላሴ ልጅነትን ያሰጠቻቸው ልጆቿ ባለማወቅ ለጣኦት የሚሰዋውን መስዋእት ሲዘክሩ፣ በእምነትና የሃሳብ ነጻነት ሽፋን ስንት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ባለበት አገር ውስጥ የህዝቡን ቁስል በጥርኝ ውሃ ለማጠብ ድፍረቱ የሌላቸው ነገር ግን ልዩ ልዩ የቲቪ ቻናሎችን በመክፈት ህዝቡን የሚያደነዝዙ መናፍቃን እንደ አሸን ሲፈሉም ሆነ ቃና በሚባል ወያኔ ሰራሽ ፊልም ወርቃማና ቅዱስ የሆኑት ማህበራዊ እሴቶቻችን እንዲህ ሲናዱ ሁሉ የሊቃውንት ጉባዔ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ እንዳለ ነው። አንድ ነገር ነገር ግልጽ ነው። ዶግማ ሃይማኖት ሲጣስና ምእመናን ሲሰናከሉ ዝም ማለት የሚያስከፍለው ዋጋ አለ፤በምድርም በሰማይም።