15 October 2017
የትኛውንም የብሔር የበላይነት የሻረና እኩልነትን ያረጋገጠ የዴሞክራሲ ሥርዓት እስከተዘረጋ ድረስ አብሮ መኖር ችግር አለመሆኑን፣ እንዲያውም ዴሞክራሲ ቢጎድል እንኳ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ይበልጥ የሚከብደው ከአብሮ መኖር የላቀ መለያየት መሆኑን፣ ትግል ተሳክቶ ዴሞክራሲ ከተገነባም በኋላ የመነጠል ጥያቄ ቢኖር ጦርነትና ብጥብጥ በማይኖርበት ሁኔታ ምላሽ የመስጠትን ዕድል ራሱ የዴሞክራሲ ሥርዓትና ባህል ይዞታ የሚመጣ መሆኑን ያስተዋለ ብልህ ትግል እስከተገመደ ድረስ ጥርጣሬ እየጠፋ ‹‹አንድነት›› ባይና ‹‹ብሔር›› ባይ ድርጅታዊ ልዩነት እየፈረሰ መዋሀድ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ዛሬ የሚያስፈልገውም ይኼን አሻግሮ ማየትና ማሳየት የሚችል በኅብረትና በግንባር መልክ እያደገ የሚሄድ ኅብረተሰባዊ የእንቅስቃሴ አስኳል ነው፡፡ በገነት ዓለሙ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

‹‹ዘላቂ ሰላም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ›› በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሠፈሩት ዓላማዎችና እምነቶች መካከል የመጀመርያዎቹ ናቸው፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረትም ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሕግ ከተቋቋመ 22 ዓመት አልፏል፡፡ በዚህን ያህል ጊዜ ውስጥ ግን እንደተባለውና እንደተመኘነው ነዋሪ የሆነና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ሰላም መጨበጥ አልቻልንም፡፡ ዴሞክራሲያችንም የሰብዓዊ መብቶቻችንና መሠረታዊ ነፃነቶቻችንም በተግባር ኑሮ ውስጥ የሚታዩ፣ ዛሬም ሥልጣን ላይ ከወጣው ፓርቲ የቁርጠኝነት መሀላ ወጪ የሚኖሩ ዋስትና ያላቸው አልሆኑም፡፡

በአገራችን ውስጥ ዛሬም ምርጫና የሕዝብ ድጋፍ በጭራሽ አልተዋደዱም፡፡ ገዢውን ፓርቲ መደገፍና መምረጥ የግብር ግዴታን እንደመወጣት እየሆነ መጥቷል፡፡ ለገዢው ፓርቲ የሚሰጠው ድምፅ በአማራጮች ላይ ከሚደረግ የፍላጎቶች ውድድር የፈለቀ ከመሆኑ ይልቅ፣ የኑሮ ግዴታን (የመንግሥት ፍላጎትን) የማሟላት ግዴታ በመሆኑ ይህ ራሱ ሕጋዊነትን (Legitmacy) ይከለክለዋል:: የሕዝብን የድምፅ መተማመኛ እናጣለን፣ ተጋልጠን እንጠየቃለን የሚል ፍርኃት አላሠጋ ያለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫ ያቋቋመው የአምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣናንና የሥራ ዘመን የመሰከረው ተቃውሞ ከኅዳር ጀምሮ መላው 2008 ዓ.ም. ውስጥ ዘልቋል፡፡ የ2009 ዓ.ም. የአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓይቷል፡፡ ክልሎች ጦር የተማዘዙበትን የ2010 ዓ.ም. ታይቶ የማይታወቅ አደጋ አስመዝግቧል፡፡

የገዢውን ፓርቲ ‹‹በጥልቀት መታደስ›› አስገዳጅ ያደረገው የ2008 ዓ.ም. ቀውስ ቢሆንም፣ ዛሬም ገዥው ፓርቲ ያለቀላቸውንና ሁሉም የፈረደባቸውን ክስረቶቹን ተቀብሎ መሻሻል አላደረገም፡፡ ከራሱ ውጪ ሌሎች ወገኖችን የማድመጥ ለውጥ ማድረግ አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ፣ ሰላምና ዕድገት ከራሱ መስመርና ዕቅድ ጋር አንድ አድርጎ ከማየት ጉድጓዱ አልወጣም፡፡

በተቃዋሚዎች በኩል ያለው ችግር ገዥውን ፓርቲ ከመጣልና ከመተካት ግብና ጥቅም ባሻገር የጋራ ዕይታ ጠፍቷል፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ዒላማ ገዥው ቡድን ሳይሆን ለብቻዬ ልግዛ ብሎ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ በአስተሳሰብና በአሠራር ባህል ላይ ያደረሰው ብልሽት ነው፡፡ መንግሥታዊ አውታሩ ከየትኛውም ቡድን ይዞታነት እንዲላቀቅና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ችሮታነት እንዲያከትም መታገል እንቅፋቶችን በጋራ የማስወገድ ጉዳይ ነው፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን ዴሞክራሲያዊ መሰል አምባገነንነትና የአንድ ፓርቲ የበላይ ገዥነት መግራትም ሆነ መቻል ቀላል አልሆነም፡፡ የአምባገነንነቱን መቀጠል የሚያጠናክሩ፣ የሚደግፉና ነባሩ ቢሄድ ሌላ አምባገነንነትን የሚጠሩ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ የዛሬው ጽሑፌ ዓላማ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶችን ማንሳትና ማሳየት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዕድገት ኋላ ቀር መሆን፣ በተፈጥሮ ሀብት ሥርጭት፣ በሕዝቦች ስብጥር፣ በባህልና በታሪክ ያላቸው ቁርኝት፣ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያላቸው ሥፍራና የጥቅም ግንኙነት ሰላማቸውን አስጠብቀው በዕድገት የመጓዝ ዕድላቸውን አብሮ በመኖራቸው ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህ ላይ የአፍሪካ ቀንድ ጦርነት፣ አለመረጋጋት፣ አክራሪነትና ሽብርተኝነት ሁሉ ያለበት ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያ በቀንዱ ውስጥ የበረሃማነት ግፊት የታከለበት የውኃ፣ የግዛትና የወሰን ውዝግብ፣ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥ የጎረቤት ቂም በቀል (ጠላትነት) ያለባት ነች፡፡ አልፎም የክርስቲያኖችና የመስሊሞች አገር ብትሆንም፣ በጎረቤቶቿ ሙስሊም አገሮች ዘንድ የክርስቲያን አገረ መንግሥት ተደርጋ መቆጠር ገና ያልቀረላት፣ ለአሜሪካና ለእስራኤል ያጋደለች ተደርጋ የምትታይ መሆኗ ሳያንስ ጥንቃቄ የጎደለው አሸባሪ እንቅስቃሴ እንድትጠመድ አድርጓታል፡፡

ይህ ሃይማኖት ለበስ አሸባሪነትም በዛሬው ወቅት፣ ቀውስና ግርግር ብቅ ባለበት በጣም ፈጥኖ በመዝለቅ መጥፊያ የሌለው ሥርዓት አልባነትና መጨፋጨፍን (አንድ ባህልና ሃይማኖት ባላቸው አገሮች ሳይቀር) የማራባት አቅም እንዳለው፣ በሩቅና በቅርብ ጎረቤት አገሮች በማያጠራጥር ሁኔታ የተረጋገጠ ነው፡፡ የአክራሪነትና አሸባሪነት ሙከራዎችም ሊሰረስሩን እየተጣጣሩ መሆኑ ሚስጥር አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት እንቅስቃሴና የጎረቤት ጠላትነት ውስጣዊ የግርግር ቀዳዳ አግኝቶ ቢስፋፋና ከክፋልፋይነትና ከጥላቻ ዝንባሌዎች ጋር ቢገናኝ፣ ሊፈጥረው የሚችለው መተላለቅና መበጣጠስ አርቆ ላስተዋለው ይዘገንናል፡፡ ሰላማዊ ህልውናና ዕድገት ድራሻቸው ጠፍቶ ወደ ህልምነት ከመለወጣቸውም በላይ ከስህተት ለመማር ዳግመኛ ዕድል ስለመገኘቱም እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

ይኼንን የመጥፊያ አዘቅት ማስተዋልና ፈጥኖ አደጋውን ለማምከን የአገሪቱ ሕዝቦች በብሔርም ሆነ በሃይማኖት የመሸካከር ስንጥቃት ሳያሳዩ፣ ወይም በሌላ የፖለቲካ ቁርቁስ ሳይታመሱ፣ በአገራዊ የጋራ ደኅነታቸው ላይ አንድ ልብ ሆነው እንዲቆሙ ማስቻል እንቅፍል የማያስወስድ ተግባር ሆኖ ሳለ፣ የእኛ ፖለቲከኞች ሌላ ዓለም ውስጥ ናቸው፡፡ ገዢው ቡድንና ተቃዋሚዎቹ የሚቀራረቡ አይመስሉም፡፡ ተቃዋሚዎች በተቃውሟቸው ይኼን ተሰባስቦ የማሰባሰብ ኃላፊነት ለመወጣት የሚበቁ አልሆኑም፡፡ በዚህ ረገድ የሚደረገው ሙከራ ሁሉ ከመጠንከርና ከመስፋት ይልቅ ተውሸልሽሎ የሚፈረካከስ ነው፡፡ እጅግ አስገራሚው ምፀት ደግሞ አንዱ የመራራቂያና የመፋረሻ ምክንያት ‹‹የብሔረሰቦች መፈቃቀድ›› እና ‹‹እስከ መገንጠል›› የሚባል መብት መሆኑ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ ይኸው ሰፍሯል፡፡ ብሔረተኛና ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ለመቀራረብ በሞከሩ ቁጥር የመግባባትና የመተማመን መሰናክል የሚሆነው፣ ምርጫ በመጣ ቁጥርም ዋናው መጨቃጨቂያ ሆኖ የሚገኘው ይኸው ነው፡፡ እውነታውን ከጭቅጭቃቸው ፋይዳ ጋር ላገናዘበ ፖለቲከኞቹ ነሁልለዋል ወይ የሚያሰኝ ነው፡፡ አንደኛ የመፈቃቀድ አመለካከት እውነታዊ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ነገር ከመፈቃቀድ በላይ የሆነ የህልውና ጉዳይን ከልሎ የሚያደናግር ነው፡፡ እያንዳንዱ ብሔረሰብ፣ ትንሹም ትልቁም፣ ሰላምና ዕድገት ያለው ሉዓላዊ አገር ለመሆን የመቻሉ ነገር ተጨባጭ ዕድል ሳይሆን ተምኔት ነወ፡፡ የመነጣጠል ፍላጎት ከዓለም የትስስር ጉዞና ከአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ጋር የሚጋጭና ማለቂያ ወደሌለው መጠፋፋት የሚወስድ መሆኑ ማየት ለፈለገ ወለል ብሎ ይታያል፡፡

የተሻለ የተፈጥሮ ሀብት አለኝ ወይም የተሻለ አቅም አደራጅቻለሁ ብሎ ለመነጠል የሚደረግ ሙከራ አምባገነናዊ ቅጥቀጣን ከማራዘም፣ ወይም ጭራሽ በሥርዓት አልባነት መንኮታኮት የሚመጣበትን ቀን ከማቅረብ የተሻላ ውጤት የማያመጣ ሆኖ ሳለ፣ ሰላማችንና ወደ ብልፅግና የመግባት ዕድላችን ግድ የሚለው አማራጭ በመላ አገሪቱ ያለውን የማቴሪያል፣ የዕውቀትና የችሎታ ሀብት በፍትሐዊነት ተጠቅሞና እኩል ተያይዞ ማደግ ሆኖ ሳለ፣ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች ሉዓላዊ ናቸው…›› የማይታጠፍ የመገንጠል መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በመፈቃቀድ ኢትዮጵያን ፈጥረዋል…ቅር ያለው ወይም ተበደልኩ የሚል በሕጋዊ አግባብ መለየት ይችላል›› በሚል አስተሳሰብ ውስጥ መሽከርከርና ዛሬ ያለውን አከላል ከአስተዳደራዊ ይዞታነት ባሸገር የየአገር መለያ ድንበር አድርጎ በመውሰድ ሀብቴ ሀብትህ እያሉ መናቆር ተጨፍኖ በእሳት ከመጫወት አይለይም፡፡ (‹‹መፈቃቀድ››ን ስንተች ‹‹ኢትዮጵያ ግዛቷ አይቆራረስም›› የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ወገኖች የዚህን ጽሑፍ ክርክር ወደ ራሳቸው ፍላጎት ሊወስዱት ይሞክሩ ይሆናል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጭንቀት ግን የግዛት አንድነት ማስከበር ሳይሆን የሕዝቦች ሰላምና ዕድገት ተገኝቶ በህልውና የመቀጠል ነገር ነው፡፡)

የአንድ ብሔረሰብ የመነጠል ጉዳይ የራስን ብሔር ዕድል የመወሰን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ብሔረሰቦችም ዕድልና ህልውና ላይ የመወሰን ጉዳይ ነው፡፡ የሌሎችን አብሮ የመኖር ፍላጎት የማሳጣት ብቻ ሳይሆን፣ በቅንጣትነት ቆርጦ የማስቀረት፣ ትልቅ ሆኖ የማደግና ደኅንነትና ሰላምን የማስጠበቅ አቅም ማሳጣትን የሚያስከትል፣ ይኼንን የህልውናን ጥቅም ላለማጣትም ቅዋሜ የሚነሳበት ነው፡፡

ዛሬ ኢሕአዴጎች ‹‹ሉዓለዊነት ሲባል የሕዝብ ወሳኝነት ማለት ነው፣ ዋናው ሕዝብ ነው፣ ተራራና ወንዝ አይደለም…›› የሚሉት ነገር ተራ ቃላት ናቸው፡፡ የሕዝብ መኖሪያው፣ የሚበላው፣ የሚተነፍሰው፣ ዕድገቱና ልማቱ ሁሉ ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በግድ ቢደረግ እንኳ፣ ሰላም የማይገኝበትና ተባብሮ የማደግ ዕድላቸውን ሁሉም ለመባላት ሒደት የሚያስረክቡበት ይሆናል፡፡

ተራራና ወንዝ የማያስጨንቅ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን የድንበር ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ፣ እነ ባድመንና ዛላንበሳን ለሻዕቢያ ያውልህ ማለት ቀላል በሆነ ነበር፡፡ ከቶውንስ የኢሕአዴግ መሪዎች ‹‹ዋናው ሕዝብ ነው›› ለማለት የሚችሉት በምን አፋቸው? ከሻዕቢያ ጋር ሆነው ሕዝቦችን በቅኝ ግዛት ይዞታ መሠረት የሰነጠቁ እነሱው አልነበሩ! ከጥንት ጀምሮ የኖረ የረዥም ዘመን የሕዝብ ዝምድና ታሪክ ውስጥ ጣልቃ የገባ አጭር የቅኝ ግዛት ምዕራፍ የሠራውን ወሰን፣ ከሕዝቦች ወጥነትና የጋራ ህልውና አብልጦ መቀበል በኤርትራም በኢትዮጵያም ሕዝቦች የጋራ ዕድገትና ሰላም ላይ የመፍረድ ውሳኔ ነበር፡፡ አቀያይሟል፡፡ የኤርትራ የዛሬ ካርታ እንደ ቅኝ ዘመኑ ጊዜ ኢትዮጵያን የወደብ መውጫ ለማሳጣት የተዘረጋ አጥር ሆኖ ከመታየት አላመለጠም፡፡

በፌዴሬሽን መፍረስ የተጀመው ጦርነት ስላሳ ዓመታት ደቁሶ ኢሕአዴግና ነፃ አውጪ ተብዬው ሻዕቢያ ላመጡት ሌላ ጦርነት አስረክቦናል፡፡ የ1991/92 ዓ.ም. የፊት ለፊት ጦርነት ቢቆምም፣ ተቃዋሚ ላይ የተቸከለ የሁለቱ መንግሥታት ጦርነት ቀጥሏል፡፡ ያሁኑ ጦርነት የሻዕቢያና የኢሕአዴግ ገዢነት ሲቀር ይቀራል የሚል ተስፋ እንዳይደረግ እንኳ፣ ‹‹ወደብ ማግኘት ተፈጥሯዊ መብታችን ነው›› የሚልና የሌላ ጦርነት መነሻ ሊሆን የሚችል ጥያቄ ፈትሉን ጀምሯል፡፡ በሌላ በኩል የሁለቱም አገሮች አካባቢያዊ ሰላምና ዕድገታቸው፣ ከጦርነት ከመላቀቅም በላይ ኢኮኖሚያቸውን ማስተሳሰርና ንፋስ የማይገባቸው አጋሮች መሆንን ይጠይቃቸዋል፡፡ ይህን እስካልተገነዘቡ (‹‹ኤርትራ›› ቅኝ በተያዘች ጊዜም ሆነ ቅኝ አገዛዙ ወደታች በሰፋ ጊዜ በጋራ የጥቃት ቁጭታቸው የተንፀባረቀውን፣ በኋላም የሁለት በኩል ተሳትፎ ለታየበት የአርበኝነት ትግልና ድሕረ ድል የውህደት እንቅስቃሴ መሠረት የነበረውን በክፉ ቀን ያልተበገረ ያንድ ቤት ልጆች ዝምድና መልሰው እስካልተገነቡ) እና የወደብ ጉዳይን ለሌሎች ጥቅሞቻቸው ሁሉ መሰናክል እንዳይሆን አድርገው እስካልፈቱ ድረስ፣ ተጣምደው እርስ በርስ መቋሰላቸው አይቀርም፡፡ ሁለቱ አገሮች እጅና ጓንት ሆነው እንኳን ለራሳቸው ለአካባቢያቸውም የሚተርፍ ልማት ሊያመጡ የሚችሉበትን ሰፊ ዕድል ማጤን ከቻሉ ወደብ በጣም ቀላል ነገር መሆኑን ይረዱታል፡፡

ሌሎችም የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እንወክላለን የሚሉ ፖለቲከኞች ከኢትዮ ኤርትራ ጠባሳ ተምረው ‹‹የብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ›› በሚል ምኞታዊ የጠባብ ሥልጣን መፈክር ተሳስተው ከማሳሳት እስካልተወጡ ድረስ፣ እሳት ውስጥ የመግባት አደጋ አይወገድም፡፡ የብሔር የመገንጠል መብት ሳያበላ ሊከናወን የሚችልበት ዕድል ወደፊት ቢገኝ እንኳ፣ ያንን ዕድል የሚያስገኘው የኢኮኖሚ ግስጋሴና የዴሞክራሲ ባህል በሁሉም ቦታ መሳካት ብቻ ነው፡፡ ጥቅሜና ህልውናዬ አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል የእርስ በርስ ትንንቅ የማይኖረው የዚያ ዓይነት ሁኔታ ሲሟላ ነው፡፡ ይኼ በሌለበት በዛሬው እውነታ፣ የራስን ዕድል በራስ መወስን የሚባል ነገር ቢያንስ በጋራ ተባብሮ መቆምና መሥራት አማራጭ የለሽ መሆኑን ማሳየት አለበት፡፡

የመነጠል ትግልና አምባገነንነት የሚጠቃቀሙ መሆናቸው ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ከመነጠል ዴሞክራሲንም፣ ሰላምንም፣ ዕድገትንም መጨበጥ አስቸጋሪ በሆነበት በዛሬው ጊዜ እውነታ፣ ሕዝብን በመነጠል ትግል ውስጥ መጎተት ወይም አብሮ በመኖርም ሆነ በመለየት ላይ ሕዝብ ፍላጎቱን በሪፈረንደም ይግለጽ የሚል እንቅስቃሴ ማካሄደ መድረሻው ጥፋት ነው፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮትን በወታደራዊ ሥልጣን እንዲጠናቀቅ ከዚያ በኋላም ወታደራዊ ደርግ አፈር ልሶ እየተነሳ 17 ዓመታት እንዲገዛ ካስቻሉት ምክንያቶች አንዱ፣ በአገሪቱ ውስጥ በጊዜው የነበረው የመነጠል ትግል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዛሬም የሚካሄድ የመነጠል ትግል የአገሪቱ የዴሞክራሲ ደጋፊ በዚሁ ሥጋት እንዲከፋፈልና ገዢው ቡድን በመተላለቅ እያስፈራራ ዕድሜውን እንዲያራዝም ከመጥቀም አያመልጥም፣ እየጠቀመም ነው፡፡

የሰሜን ሱዳንና የደቡብን ሁኔታ ከአገራችን ጋር አስተያይቶ መከራከርያ ለማድረግ የሚሞክር ካለ ጭፍን ወይም አዎንታዊነት የራቀው መሆን አለበት፡፡ በደቡብ ሱዳን ቁልጭ ካሉ የሃይማኖችና የባህል ልዩነቶች ባሻገር የልማቱ ሁሉ ተጠቃሚ በሆነውና ዓረብነት አለኝ በሚለው የሰሜን ሱዳን የበላይነት ሥር ለድህነት፣ ለድንቁርናና ለችጋር ተትቶ የቆየ፣ የሱዳን ግዛት ተብሎ ከመቆጠር በቀር የአንድ አገር አካል የሚያስብል ሌላ ተዛምዶ የሌለውና በዚህና በሰሜኑ ሃይማኖታዊ ጫና ምክንያት የብረት ትግል ውስጥ የገባ ሕዝብ ነው፡፡ የኤርትራ መነጠል የአንድ ጥንታዊ ሥልጣኔ አካባቢን ለሁለት የቆረጠ ነበር፡፡ ከዚያም በላይ ሻዕቢያ የአሰብ አስተዳደርን ሁሉ ጠቅሎ የእኔ ነው ሲል ‹‹ይችን ይወዳል!›› የሚል ተቀናቃኝ ዘመቻ ያልመጣበት፣ በኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ ተቀምጦ የነበረው መንግሥት የዓላማው ሸሪክ ስለነበረ ነበር፡፡ ሸሪኩም በግልበጣና በተቃውሞ ያልተናጠው ነባሩን ሠራዊት በትኖ በራሱ ሠራዊት የሚሠራ ስለነበር ነው፡፡ ያኔ መቀጣጠል ያልቻለው ጣጣ ግን ይኸው ጊዜውን ጠብቆ ፍሞ፣ ግሞ አሁን የደረሰበት ደረጃ ደርሷል፡፡

አንዳንድ ጊዜና አሁን አሁን ኦነግን በተመለከተ እስከ ዛሬ እገነጠላለሁ ብሎ አያውቅም እስከ ማለት ተደርሷል፡፡ ተብሏል አልተባለም የሚል ክርክር ውስጥ አልገባም፡፡ ግን ሕዝብ ይወስን የሚል ጥያቄ ራሱን ችሎ የቆመ እንዳልሆነ መሳት የለብንም፡፡ አብሮ በመኖር ላይ ወይም በመለየት ላይ ውሳኔ የመስጠት ነገር ዝም ብሎ ከመሬት አይነሳም፡፡ ለዚህ ጥያቄ መምጣት ምክንያት የሚሆነው ከበስተኋላው የመነጠል እንቅስቃሴ መኖሩ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹የሕዝብ ውሳኔ›› ዋና ጥያቄ ሳይሆን የጥያቄ መፍቻ ዘዴ ነው፡፡

ማትኮሪያ መሆን ያለበትም ሕዝብ ይወስን ባይነት ሳይሆን፣1ኛ) ከዚህ ጀርባ ቡድኖች ይበጃል ብለው የሚከራከሩለት አቋም ምንድነው የሚለው ነው፡፡ 2ኛ) በአብሮ መኖር አለመኖር ላይ የመወሰን መብት በራሱ ሰላምን፣ ዴሞክራሲንና ፍትሕን ያቀዳጃል ወይ? ወደ እርስ በርስ ጦርነት የመግባትን ዕድል የሚያስቀረው የቱ መንገድ ነው? ያሉት ገዢዎች ወርደው የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ፣ ተባብሮ  ዴሞክራሲ ዘላቂ መሠረት እንዲይዝ ለማድረግ በመረባረብ ፋንታ በሽግግር ወቅት ቶሎ አዋክቦ ለመነጠል ጥያቄ ውሳኔ ሕዝባዊ መልስ ለማስገኘት ግፊት ቢሞቅ፣ ወይም ውሳኔ ሕዝብ የማስደረግ ክንዋኔ ቢጀመር በመከራ የተገኘች የዴሞክራሲ ጭላንጭል በወታደራዊ ግለበጣ እንድትቀለበስና ሌላ የተራዘመ አምባገነንነትን እንዲዘረጋ፣ ወይም እዚያም እዚያም በሚነሳ ተፃፃሪ አመፅ ተላግቶ ፍጅት እንዲመጣ መንገድ መስጠት አይሆንም ወይ? እነዚህን ለመሳሰሉ ህልውናን የሚወስኑ ጥያቄዎች የማያሻማ መልስ መስጠት የማይዘለል ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚህ ኃላፊነት ውጪ ሆኖ ‹‹ሕዝቡ ይወስን›› በሚል አቋም ውስጥ መድበስበስ የአፈናን ዕድሜ የሚያሳጥር የዴሞክራሲ ትግል ለመገንባት አያስችልም፡፡

ለዴሞክራሲ የሚደረግ የኢትዮጵያን ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ከሚተናነቁትና ምናልባትም አድራጊ ፈጣሪነትን ከሚጠቅሙ ችግሮች መካከል አንዱ፣ በተለያዩ ፓርቲዎች ቡድኖች መካከል ያለውና በመነጠል መብት ላይ የሚካሄደው የባዶ ሜዳ ክርክርና በዚህም ላይ የተመሠረተ አቋም ነው፡፡ የመነጠል ጥያቄን በማያነሱ እንዲያውም የማያዋጣና ከፋፍሎ የሚያስጠቃ መሆኑን አነሰም በዛ እንደ መገንዘብ ባሉ ቡድኖች ዘንድ የሚታይ የባሰ የፖለቲካ ጅልነት ደግሞ አለ፡፡ ባንድ በኩል የብሔረሰቦች እኩልነትና ሙሉ መብት በሕገ መንግሥት የተጻፈና ከጊዜ ጊዜ እየተሰበከ ይሁን እንጂ በተግባር እየሠራ እንዳልሆነ፣ የብሔር የበላይነት ዛሬም እንደ ቀጠለና ፌዴራላዊ የሚባለው አወቃቀር የአንድ ፓርቲ አገዛዝ እንደሆነ እየተናገሩ፣ (ባለው አገዛዝ ሥር አንቀጽ 39ን ተግባራዊ ለማድረግ መከር የትም እንደማያደርስ እያወቁ) አንቀጽ 39ን ሙጥኝ አትንኩብን የሚሉ ብሔረተኞችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ ሰዎች አንቀጽ 39ን በፕሮግራማቸው አስፍረው የአንቀጹ ጠበቃ ስለሆኑ ምንም ጠብ እንደማይል፣ ብሔረሰባዊ አድልኦን አሽቀንጥሮ እኩልነትንና ነፃነትን ማረገገጫው የጭቆናውን ምንጭ ተባብሮ ታግሎ ዴሞክራሲን መዘርጋት እንደሆነ፣ የኩቤክን ሕዝብ ካንድም ሁለቴ ሪፈረንደም ለማካሄድ ያበቃው ‹‹የመነጠል መብት›› አንቀጽ ሳይሆን የዴሞክራሲ መገንባት እንደነበር መረዳትና መቃናት ተራራ እንደ መግፋት ከብዷቸዋል፡፡

የብሔረሰብ እስከ መገንጠል የሚባል መብት በቻርተሩም ጊዜ ሆነ ከዚያ በኋላ ለአንዱ ማስፈራሪያ ለሌላው ማሞኛ ከመሆንና ከመነታረኪያነት ያለፈ እርባና አልነበረውም፡፡ ‹‹መነጠል አይበጀንም፣ ፍላጎቱም የለንም…›› እያሉ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በመፈቃቀድ የተመሠረተች ነች… ቅር ያለው የመነጠል መብት አለው…›› የሚል ቅብጥርጥር ውስጥ መግባት፣ ከዚያም አልፎ የመተባበር ጥያቄ ሲመጣ እስከ መገንጠል ያለ መብትን ትቀበላላችሁ? የሚል ጥያቄና ክርክር ማንሳት፣ ሳንተማመንና ሳንቀራረብ እንረገጥ እያሉ ከመስበክ የማይለይ የመጨረሻ ንዝህላልነት ነው፡፡ ይህ ንዝህላልነት መሰባሰብን ከልክሏል፡፡

በመነጠል መብት ላይ እየተናቆሩ መለያየትን ተሻግሮ በትግል መያያዘ እንደሚያስፈልግ በገባቸውም ላይ ተፅዕኖው በቀላል የሚለቅ አልሆነም፡፡ መነጠል መብት ነው የሚባል ነገር አይበጅም ከሚሉ ወገኖች ጋር ግንባር መግጠም የብሔር መብትን አሳልፎ እንደ መስጠት ሆኖ የሚተናነቃቸው፣ ከዚህም ቢያልፉ (እስከ መገንጠል የሚባል መብት ከብሔር ብሔረሰብነት ጋር የተጣበቀና የማይደፈር ተጨባጭ መብት እስኪመስል ድረስ በመሰበኩና ብሔርንም መወከል በየብሔር እየተቧደኑ ይኼንኑ መብት ማነብነብ በመለመዱ የተነሳ) ብሔራችንን የካድን ተደርገን እንቆጠራለን ወይም ዘመቻ ይከፈትብናል የሚለው ሥጋት ይታገላቸዋል፡፡

ኅብረ ብሔር ነን በሚሉት በኩልም በብሔረሰብ ከተሰባሰበና ‹‹እስከ መገንጠል›› የሚል መብትን በፕሮግራሙ ካሰፈረ ቡድን ጋር ግንባር መግጠም ዓላማን እንደ መሳትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንደ መስማማት የሚቆጥረውና በዚህ አስተሳሰብ የሚምታታው ቁጥሩ ቀላል አይለም፡፡ ‹‹ተፈቃቅደን›› ባይነት ከ70 እስከ 80 ብሔረሰባዊ አገሮች መሆን በተጨባጭ እንችላለን ብሎ የምር የሚያምን አለመሆኑና የሚያምን ካለም ብቻውን የሚቀር ወፈፌ ከመሆን በቀር ምንም ያለማምጣቱ (የተናጠል ትግል የትም ያለማድረሱ)፣ እናም ዛሬ የተፈጠረ መቀራረብ በሒደት ብዙ መልካም ነገሮችን ይዞ የመምጣቱ እውነትነት ጠንካራ ግንዛቤ አልፈጠረም፡፡

የትኛውንም የብሔር የበላይነት የሻረና እኩልነትን ያረጋገጠ የዴሞክራሲ ሥርዓት እስከተዘረጋ ድረስ አብሮ መኖር ችግር አለመሆኑን፣ እንዲያውም ዴሞክራሲ ቢጎድል እንኳ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ይበልጥ የሚከብደው ከአብሮ መኖር የላቀ መለያየት መሆኑን፣ ትግል ተሳክቶ ዴሞክራሲ ከተገነባም በኋላ የመነጠል ጥያቄ ቢኖር ጦርነትና ብጥብጥ በማይኖርበት ሁኔታ ምላሽ የመስጠትን ዕድል ራሱ የዴሞክራሲ ሥርዓትና ባህል ይዞታ የሚመጣ መሆኑን ያስተዋለ ብልህ ትግል እስከተገመደ ድረስ ጥርጣሬ እየጠፋ ‹‹አንድነት›› ባይና ‹‹ብሔር›› ባይ ድርጅታዊ ልዩነት እየፈረሰ መዋሀድ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ዛሬ የሚያስፈልገውም ይኼን አሻግሮ ማየትና ማሳየት የሚችል በኅብረትና በግንባር መልክ እያደገ የሚሄድ ኅብረተሰባዊ የእንቅስቃሴ አስኳል ነው፡፡

በገነት ዓለሙ

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡