October 15, 2017 19:04 e

ወደ 420 ቀበሌዎች “ከሶማሌ ክልል ጋር እንሁን ? ወይስ ከኦሮሚያ ?” በሚል ሕዝበ ዉሳኔ ሰጥተዋል። በጎንደር ደግሞ ወደ ስምንት ቀበሌዎች “ከጎንደር ዞን ጋር ትሆናላችሁ ወይስ ቅማንት በሚል ዞን ?” የሚይ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
አንዳንድ የኦሮሞ ብሄረተኞች ፊንፊኔ የኦሮሚያ ናት ይላሉ። ናት አይደለችም እያሉ ከመጨቃጨቅ የሸገር ብቻ ሳይሆን እንዳለ በድፍን ሸዋ የሚኖሩ ቀበሌዎች ለምን ሕዝብ ዉሳኔ በቀበሌ ደረጃ አይሰጡም ? “የኦሮሚያ አካል እንሁን ወይም አዲስ አበባን እና ሸዋናን ያካተተ፣ አፋን ኦሮሞና አማርኛ ሁሉቱም የሥራ ቋንቋ የሆነባት ፌዴራል ክፍለ ሃገር ውስጥ እንጠቃለል?” በሚል ?
በኔ እይታ ሸገርን ያካተተ ሸዋ የሚባል ፌዴራል ክፍለሃገር መኖሩ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ነው ባይ ነኝ። ምክንያቱም፡
1) ለአስተዳደር አመች ነው።
2) የሸገር ከተማ ነዋሪን እና በዙሪያዋ ያሉ ገበሬዎችን የሚያስተሳስር ነው። የሸገር ዙሪያ ገበሬ በኢኮኖሚን፣ በንግድም የተሳሰረው ከሸገር ሕዝብ እንጂ እዚያ ማዶ ካሉ፣ አወዳይና ነጆ፣ ያቤሎና ደምቢዶሎ ካሉ ጋር አይደለም።
3) አፋን ኦሮሞ በአዲስ አበባ የበለጠ ስር እንዲሰድ የሚያደርግ ነው። የሸዋ ሰዎች አፋን ኦሮሞም አምርባም ተናጋሪ ይሆናሉ። አሁን በአዲስ አበባ በአፋን ኦሮሞ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ከዘጠኝ ሚሊዪን የሸገር ነዋሪ ምን ያህሉ ሰው እነዚያ ት/ቤቶች ውስጥ እንዳለ እግዜር ይወቀው። ሸዋ የሚባል አስተዳደር ካለ ግን በሁሉም የአዲስ አበባ ት/ቤቶች አፋን ኦሮሞ እንደ ትምህርት ይሰጣል። አስቡት አድማሱን እንዴት እንደሚያሰፋ።
ኦሮሞው አሁን ኦሮሚያ ውስጥ አለኝ የሚለው መብት በሸዋ ውስጥ አይነፈግም።፡የሚቀንስበት ነገር የለም። በአፋን ኦሮሞ አገልግሎት ያገኛል። በአፋን ኦሮሞ ይሰራል። በአፋን ኦሮሞ ይተዳደራል። ግን በሸዋ ያለው አፋን ኦሮሞ መናገር የማይችል ማህበረሰብ ግን ፣ አሁን በኦሮሚያ ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ፣ መብቱ ተረግጦ ነው የሚኖረው። በሸዋ ግን አፋን ኦሮሞ መናገር የማይችለው ማህበረሰብ ከኦሮሞ ማሀረሰብ እኩል ይሆናል። ለምን አገልግሎት በአማርኛ ያገኛልና።
ይሄን አስተያየታችንን የሚቃወም የኦሮሞ ብሄረተኛ ፖለቲከኛ ካለ፣ ያስረዳን። እኩልነት ይኖር ማለታችን ነው ወንጀሉ ? ኦሮሞው ከሌላው እኩል የሆነበት ክልል መጠየቃችን ኦሮሞን መበደል ነዉን ? ኦሮሞ የርሱ መብት ከተከበረለት የሌላውን የሚያከበር ባህል ያለው ሕዝብ እንጂ፣ እኔ ከሌላው በላይ መሆን አለብኝ፣ ለኔ ቅድሚያ መሰጠት አለበት የሚል ሕዝብ ነዉን ?