16 ኦክተውበር 2017
KALKIDAN
የጣና ሐይቅ በእምቦጭ አረም መወረሩን ተከትሎ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አረሙን በእጅ በመንቀል ለማስወገድ ሲረባረቡ ቢስተዋልም ባለሞያዎች የዚህ መሰሉን እንቅስቃሴ ውጤታማነት እንዲሁም በማሽን የመንቀልን ዘመቻ ተግባራዊነት ይጠራጠራሉ፤ ሐይቁ ላይ የተጋረጠው አደጋ ግን ይህ ብቻ አይደለም።
ከአገሪቱ ጨው አልባ የተፈጥሮ ውሃ ውስጥ ሃምሳ በመቶ ያህሉን የያዘው የጣና ሐይቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በእምቦጭ አረም መወረሩ የተስተዋለው እ.አ.አ በ2011 ነው።
አራት ሺህ ሄክታር ያህል የውሃ ክልልን በመሸፈን የጀመረው የአረሙ ወረራ፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 20ሺህ ሄክታርን ወደማካለል አድጓል።
በወቅቱ የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት እምቦጭን “ጣናን የወረረው እጅግ አስከፊው አረም” ሲል የፈረጀው ሲሆን፤ በሐይቁ ዙርያ የሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባብር አረሙን በእጅ በመንቀል ለማስወገድ ተጥሯል።
በዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት እንዲሁም ከመንግሥታዊ ቢሮዎች ጋር በትብብር የተሰናዳው “የጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረም መከላከያ ቁጥጥር ስትራቴጅ” እ.ኤ.አ ከጥቅምት 2011 አንስቶ እስከ ታህሳስ 2013 ድረስ እምቦጭን በእጅ መንቀል ላይ የፈሰሰው ጉልበት በትንሹ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ይገመታል።
ይሁን እንጅ በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አረሙ መጠኑን ከእጥፍ በላይ ጨምሮ በመመለስ ሐይቁን ወሯል።
በአሁኑ ሰዓት 50ሺህ ሄክታር የሐይቁ ክፍል በአረሙ እንደተወረረ የሚገመት ሲሆን፤ ይህም ከአዲስ አበባ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት በአራት ሺህ ሄክታር ብቻ የሚያንስ ነው።
128 ኪሎሜትር ያህል የሐይቁ ዳርቻ በእምቦጭ መሸፈኑም ይገመታል።
በአረሙ እና በሐይቁ ላይ ምርምሮችን ያደረጉት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሥነ–ሕይወት ባለሞያው ዶክተር ሰለሞን ክብረት ለእምቦጭ ዳግም ምፅዓት አንደኛው ምክንያት አረሙን በእጅ ነቅሎ ለማጥፋት በተሞከረበት ወቅት ንቃዩን በአግባቡ ለማስወገድ ትኩረት ባለመሰጠቱ ነው ይላሉ።
“የተነቀለው አረም በሙሉ ለሐይቁ ዳርቻ ቅርብ የሆነ ቦታ ላይ ተትቶ ስለነበር፤ ብዙም ሳይቆይ በዝናብ አማካይነት ከዚያ ቀደም ደርሶባቸው ወደማያውቅባቸው ሰፊ ቦታዎች ሁሉ ሊወሰድ በቅቷል” ሲሉ ዶክተር ሰለሞን ለቢቢሲ ያስረዳሉ።
“መጥፎው ዜና [እምቦጭን] ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እምብዛም የማይቻል መሆኑ ነው” ይላሉ ዶክተር ሰለሞን አክለው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ “ዘሩ እስከሰላሳ ዓመት ድረስ መቆየት የሚችል መሆኑ ነው።“
መጤው አጥፊ
እምቦጭ መነሻውን ላቲን አሜሪካ ያደረገ፤ እንዳሻው በውሃ ላይ የሚንሳፈፍና የሚዋልል ወራሪ አረም ሲሆን በተለያዩ መንገዶች ወደአፍሪካና እስያ እንደተሰራጨ ይነገራል።
ይህ ተክል የተለያዩ ጉዳቶችን የሚያስከትል ሲሆን፤ ጉዳቶቹን የሚያደርስበት መንገድም የውሃ ፍሰትን በመከልከል፣ ውሃው ውስጥ ያሉ ተክሎች እና እንስሳት የፀሐይ ብርሃን እንዳይደርሳቸው በመከልከል፣ አሳን የመሰሉ እንስሳት ኦክስጅን እንዳያገኙ በማፈን ጭምር ነው።
ከዚህም በዘለለ በእርከን ሥራ፣ በኃይል ማመንጨት እንዲሁም በዓሳ ማጥመድ ላይ ተፅዕኖ አለው።
የእምቦጭ አረም ከጠቅላላ አካሉ ውስጥ 90 በመቶ ያህሉ ውሃ እንደመሆኑ ብዙ ውሃን ይመጣል።
እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አጋማሽ የአዋሽ ወንዝን በመገደብ በተሰራው የቆቃ ሐይቅ ላይ ለመታየቱ ማስረጃዎች አሉ። በተለያዩ ጊዜያት የጫሞና የአባያ ሐይቆችን ጨምሮ በሌሎች የአገሪቱ የውሃ አካላት ላይ የእምቦጭ ወረራ ተስተውሏል።
“የጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረም መከላከያ ቁጥጥር ስትራቴጂ” ሐይቁ እንዴት በዚህ መጤ አረም ሊወረር እንደቻለ በትክክል ማወቅ እንዳልተቻለ ይገልፅና ከውጭ ሀገራት የገቡ ያገለገሉ የዓሳ ማጥመጃ መሳሪያዎች፣ ጀልባዎች አሊያም በእርሻ ግብዓቶች አማካይነት ሊሆን እንደሚችል ግምቶች መኖራቸውን ይጠቅሳል።
አረሙ ጣናን ከመውረሩ አስቀድሞ ሱዳን ውስጥ መታየቱንም “ስትራቴጅው” ያስታውሳል።


