October 21, 2017

 

 

 

 

 

ታዳምና ሄዋን ቢስተካከል እድሜህ፣

ለኔ ጦቢያ እናትህ ሁሌም ጨቅላዬ ነህ፣
በጀርባዬ አዝዬ ቅኔ እማዜምልህ፣
እሹሩሩ ጣና እሹሩሩ ዓባይነህ፡፡
ለቅርጫ ቢያቀርቡኝ የሞትኩ እንዳይመስልህ፣
ስታክ ይሰማኛል ተጀርባዬ ሆነህ፣
የገላና የራስ ቅማል እያስበሉህ፣
እሹሩሩ ጣና እሽሩሩ ዓባይነህ፡፡
ዓለምን ሲሰራ ቀድሶ ቢፈጥርህ፣
ሁለተኛው ልጄ ግዮንዋ ቢልህ፣
ኤደንን መግባት ብሎ ቢባርክህ፣
ቅናት ፈጥፍጧቸው በጀርባዬ ሲያዩህ፣
የሳጥናኤል ሰዎች ዶለቱ ሊያጠፉህ፣
ልክ እንደ ማርያም ልጅ የናዝሬቱ መሲህ፣
እምቦጭን ጠምጥመው ራስክን አደሙህ፣
ጎንህንም ወግተው ሸንኮራ አስመጠጡህ፡፡
እሹሩሩ ጣና እሹሩሩ ዓባይነህ፣
እንኳንስ ተመጠህ እንደ ድንጋይ ደርቀህ፣
አንተ ርቦህ ከስተህ ደክመህም ተማይህ፣
ጡቴን የነከሱኝ እኔው ልሙትልህ፡፡
እጆቼን ወደ ላይ ዛሬም ዘርግቻለሁ፣
ዓባይና ጣናን ጠብቅልኝ እያልኩ፣
ላዳኞችህ ብርታት ፅናት እየፀለይኩ፡፡
እሹሩሩ ጣና እሹሩሩ ዓባይነህ፣
እንጉርጉሮ አቁመህ አዳምጠኝ ከልብህ፣
አጥንት ከስክሰው በክብር እንዳቆዩህ፣
ልክ እንደ ጥንቶቹ አንበሳ ጀግኖችህ፣
ወጣቶች ልጆቼ እስተሚደርሱልህ፣
ከጀርባዬ እንዳትወርድ ጠጉሬን ያዝ ነግንገህ፡፡
እሹሩሩ ጣና እሹሩሩ ዓባይነህ፣
ሥጋቱን ተውና እንቅልፍ ሽልብ ያርግህ፣
ምክክር ይዘዋል ዘብ ጠባቂቆችህ፣
በደም ባጥንታቸው ከጥፋት ሊያድኑህ፡፡
እሹሩሩ ጣና እሹሩሩ ዓባይነህ፣
ልብህ አይከፋ እንባ አይቋጥሩ ዓይኖችህ፣
የአስቆርቱ ይሁዶች እንቦጭ ቢተክሉብህ፣
ቆርጠዋል ሰማእት ነቅለው ሊጥሉልህ፡፡
እሹሩሩ ጣና እሹሩሩ ዓባይነህ፣
ከንፈርህ አይድረቅ አይጠውልግ ወዘናህ፣
ጎንህን ቆፍረው ሸንኮራ ቢያጠጡህ፣
ወጣቱ ተነስቷል ቦዩን ሊደፍንልህ፡፡
እሹሩሩ ጣና እሹሩሩ ዓባይነህ፣
በደንገል ተንሳፎ የተረፈው ልጅህ፣
የሙሴ በረከት ዛሬም ይከተልህ፡፡
እሹሩሩ ጣና እሹሩሩ ዓባይነህ፡
የእናትህ ምርቃት ሁልጊዜ አይለይህ፣
ከጥፋት የሚያድን ጎበዝ አያሳጣህ፡፡
እግዜር በዘፍጥረት በአካሌ እንዳኖረህ፣
እስከ ዘላለሙ ተኔ እንዳይነጥልህ፣
ሰሙን እያቀለጥኩ ወርቅ እንዳሰራልህ፣
እሹሩሩ እያዜምኩ በጀርባዬ እንዳዝልህ፣

እሹሩሩ… ጣና እሹሩሩ… ዓባይነህ፡፡