October 21, 2017 14:56

 

የአማራን ማህበረሰብ በሕወሓት (በወያኔ) ከተቃጣበት ጥፋት የመከላከሉን ንቅናቄ ኢትዮጵያን ከማዳን እቅድ ጋር አዋህዶ በዘዴ ማኪያሄድ የአማራዉን ተጋድሎ አጉል መበረዝ ነዉ? የአማራዉን ልዩ የጥፋት ኢላማነትና የመኖር ወይም ያለመኖር ትግል አስቸኳይነት እሳቤ ዉስጥ አለማስገባት ይሆን? በርግጠኛነት “አዎ” ይላሉ አማራ አክትቪስቶች እና ነዉጠኞች።
አክለዉ እንደሚሉት አጣዳፊዉ የአማራ ህልዉና ትግል ቀደምትነት በሌሎች “ሁለተኛ ደረጃ” የተቃዉሞ ጥረቶች (ለምሳሌ በዲሞክራሲያዊ ለዉጥ ዙሪያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች) እና ጥረቶቹን አጃቢ በሆኑ ሌሎች ፖለቲካዊ “ቅንጦቶች” መስተጓጐል የለበትም። አማራዉ “በመጀመሪያ ዙር” ለብቻዉ ራሱን የማዳን ትግል አድርጐ “ካሸነፈ በኋላ” ነዉ ከሌሎች የአገሪቱ ማህበረሰቦች ጋር በኢትዮጵያዊነት የሚተባበረዉ።
ይህ ነገድ ተኮር አስተሳሰብ  ለአማራዉ ተሟጋች በሆኑ በርካታ ስብስቦች ዘንድ ሰፍኗል። በተጨማሪ፣ ለየት ባለ ቅጅት አስተሳሳሰቡ የአማራዉንና የሌሎች ነገዶችን እንቅስቃሴዎች በብልሃት ለራሳቸዉ ፖለቲካ አላማዎች መከታተያ መሣሪያ ማድረግ በሚጥሩ ወገኖች (በተለይ ሻቢያ በግንቦት ሰባት ድርጅትና ሚዲያ አማካኝነት በሚያደርገዉ ሙከራ) ይዘዋወራል።
ጉዳዩን በአገራዊ አገባቡ ይበልጥ ሰፋ አድርጐ ለማስቀመጥ፣ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያደርገዉ የወያኔ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ተቃዉሞ ዉስጥ የጐሣዊ ማንነትና የኢትዮጵያዊነት ግንኙነት “የዜሮ ድምር ጨዋታ” የሚባል ነዉ? ማለትም፣ የአገራዊ ንቅናቄ ትርፍ ወይም እድገት የግድ የነገዳዊ ትግል ኪሳራ ወይም ኋላ ቀርነት ሆኖ መታየት አለበት ወይ?
ግንኙነቱ የግድ የዜሮ ድምር እንዳልሆነ ምንም ያህል ስዉር አይደለም። አንዱ ወይም ሌላዉ ሳይባል በነገዳዊ/ግዛታዊ አካባቢዎችና በአገር ደረጃ የሚኪያሄዱ ትግሎች እርስ በርስ ተመጋጋቢ፣ ተደጋጋፊና ተጠነካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ። መሆንም አለባቸዉ። የኢትዮጵያ አካባባዊና ባህላዊ ማህበረሰቦች ማንነቶች እንደ ደሴቶች በድፍኑ ለየብቻቸዉ ቁጭ ቁጭ ያሉ ሳይሆኑ በሰፊዉ አገራዊ ድርና ማግም ናቸዉ። በተለይ አማራዉ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምእራብና በምስራቅ፣ እንዲሁም በመሐል አገር አለ። ነገዳዊ ህልዉናዉ ምንጊዜም በኢትዮጵያዊነት የታቀፈና የተደገፈ ነዉ፤ በአገሪቱ ግንባታና እድገት መካከለኛ ሚና ተጫዉቷል። የኦሮሞዎች ማንነትም እንዲሁ።
በተጨማሪ ብዙሃን የኢትዮጵያ ነገዶች ማህበረሰባዊና ባህላዊ ተጽእኖዎች ተለዋዉጠዉም በጋራ አብዮታዊ ልምድ የዘር ሳይሆን የመደብ ትግድ አኪያሂደዉም አገሪቱን በአንድነት እንደለወጡ የምንዘነጋዉ ነገር አይደለም። የዛሬን የወያኔ ሞገደኛ አገር ከፋፋይና አሰናካይ አገዛዝ አያርገዉና በኢትዮጵያ የዘመናት እድገትና ዘመናዊ አብዮታዊ ለዉጥ ትስስራቸዉ፣ አንድነታቸዉ፣ ይበልጥ እየተጠናከረና እየተሻሻለ በመምጣት ላይ እንደነበረ ይታወቃል።
ይህ ታሪካዊና ወቅታዊ እዉነታ በተለይ በአገሪቱ ሁለት ታላላቅ ማህበረሰቦች በከፊል ተደራራቢ የሆነ ህልዉና፣ ማለትም በአማሮችና ኦሮሞዎች ማንነቶች ተወራራሽነትና ትስስር፣ ጐልቶ ይታያል። እዉነታዉ እርግጥ አይኔን ግንባር ያርገዉ ላሉ የጐሣ ፖለቲካ አክራሪ ወገንተኞች ስዉር ይሆን ይሆናል። ብዙዉን ጊዜ እንዲያዉም ጠበዉ ህዝብ አጥባቢ በሆኑ ዘረኞች፣ የኢትዮጵያን ህብረተሰብ በከፋፋይ ክልሎች አጉረዉና አሽገዉ በሚጨቁኑ ወገንተኛ-ጐሠኛ ሊህቃን ህዝባዊ ትስስሩ የይካዳል። ሆኖም በነዚህ ጠባብ ወገንተኞች መካዱ ተጨባጩን ታሪካዊና ወቅታዊ ሁኔታ ፈጽሞ እንዳልነበረና እንደሌለ አያደርገዉም።
እንግዲህ የአማራዉ ማህበረሰብ ህልዉና  በነገዳዊ፣ ባህላዊ፣ አካባባዊ ወይም ግዛታዊ ደሴታዊነት (insularity) የተከለለ አለመሆኑን እንረዳለን። እንደ ማህበረሰብ የአማራዉ መለያ በመሠረቱ በክልል የታጐረ የጐሣ ማንነት የሌለዉና የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ደግሞ ማህበረሰባዊም ግለሰባዊም ነፃነቶች አፋኝ የሆነ የዘር ጉረኖ የማይጭን መሆኑ ነዉ። አማራዉን ከሌሎች የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ክፍሎች በይበልጥ የሚለየዉ እንደ ማህበረሰብ ለመኖርና ለመዳበር፣ ራስነቱንም ለመጠበቅ፣ በጠባቡና በብቸኝነት ጐሣዊ/አካባባዊ “ራስነት” መያዝ ወይም ማራመድ የማያስፈልገዉ መሆኑ ነዉ።
የአማራዉ ሰፊና ተለማጭ ነገዳዊም አገራዊም ህልዉና የጥንካሬዉና የትልቅነቱ መሠረት እንጂ የድክመቱ መገለጫ አልነበረም። ዛሬም አይደለም። ይህ ተክለህላዌዉ ዉጨኛ አገር ወራሪዎች ሲመጡም የኢትዮጵያን ጐሣ ዘለል ብሔራዊ ሃይሎች በማስተባበር በቆራጥነት፣ በጀግንነትና በስልት ተከላክሎ ጠላትን ደጋግሞ ድል ከመንሳት አላገደዉም ወይም አልገታዉም ። እንዲያዉም አማራዉ በዚህ መንገድ ራሱንም አገሩንም ከጥፋት መታደግና በነፃነት መጠበቅ ችሏል።
ይህን የማድረግ ችሎታዉ ከማህበረሰባዊ ባህሪዉ ጋር የተያያዘ ነዉ። የአማራዉ ማንነት የተገነባዉና የዳበረዉ በከፊል ከብዙሃን የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች፣ በተለይ ከኦሮሞዎች ጋር በአገሪቱ ዉስጥ ህዝባዊ ፍልሰት፣ ዝዉዉር፣ መስፋፋትና ሰፈራ በመለዋወጥ ነዉ። ይህ ታሪካዊ ሂደት እርግጥ ሁልጊዜ ሰላማዊና ችግሮች አልባ አልነበረም። በዓለም ዙሪያ በአገሮች ምሥረታና እድገት እንደታየዉ ሁሉ በኢትዮጵያም የማህበረሰቦች ፍልሰቶችና መስፋፋቶች ልዉዉጡ፣ በአገር ማቅናቱ ሂደት፣ ግጭቶችና ዉጊያዎች ነበሩ።
ቢሆንም በኢትዮጵያ አገራዊ ግንባታ አማራዉ “ሌሎችን” በጠላትነት ከማግለልና ከማራቅ ወይም ተለጣፊ ከማድረግ ይልቅ በተግባቢነት፣ በተዛማጅነት፣ በተዋሐጅነትና ከሞላ ጐደል በመንግሥት ሥልጣን ተካፋይነት አቅርቧል። ባህሉን፣ ቋንቋዉን፣ ማንነቱን ሳይቀር ከአገሪቱ ብዙሃን ማህበረሰቦች ጋር በሰፊዉ ተጋርቷል። በዚህ አይነት የሰጥቶ መቀበል ሂደት ባንዴ ማህበረሰባዊና አገራዊ ማንነቱን አበልጽጓል። አመራር መስጠትም ችሏል። በዝርዝርም ባይሆን በመሠረቱ ይህ ይመስለኛል የአማራ ማህበረሰባዊ ህልዉና።
ይህ ማንነቱ ለዛሬዉም ራሱንና አገሩን የማዳን ትግሉ ወሳኝ እንድምታ አለዉ። ሆኖም ያለንበት ወቅት አማራን ከጥፋት እንታደጋለን በሚል ይፋ አላማ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ (በተለይ ዳያስፖራዊ) ድርጂቶች፣ አክቲቭስቶችና ስብስቦች፣ እንዲሁም የፖለቲካ፣ የምሁራንና የሚዲያ ወገኖች እንድምታዉን በቅጡ የማጤን ፍላጐት ወይም አዝማሚያ ምንም ያህል አያሳዩም።
የአማራን ህልዉና አቀራረባቸዉ ባመዛኙ ግልብ ነገዳዊነት ላይ የሚያጠነጥን ነዉ። አገራዊ ተንቀሳቃሽነት ማመንጨት (proactive national agency) ግድ ስይላቸዉ በስልታዊ ትዕግሥት ያልተመዛዘነ ችኩል፣ ታክቲካዊ ተከላካይነት ላይ ያተኮረ የአማራ ተጋድሎ ያጐላሉ። የአማራን ማዳን ጥረት ብዙዉን ጊዜ ኢትዮጵያን ከመታደግ ንቅናቄ አግልለዉና አርቀዉ ያያሉ። ይህ ትኩረት መሠረታዊ ምክንያቶችና ችግሮች አሉት። በችግሮቹ ዙሪያ እዚህ ሰፊ ዉይይት ማቅረቢያ ቦታ ባይኖርም አገባብ ያላቸዉ ጥቂት ነጥቦች ባጭሩ ማስቀመጥ ይቻላል።
እንደ ማንኛዉም የኢትዮጵያ ነገዳዊ ወይም ባህላዊ ማህበረሰብ አማራዉ ለዘለቄዉ በአገሩ በሰላምና ነፃነት የሚኖረዉ ከብዙሃን የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ጋር ከሞላ ጐደል ባሉት አገራዊ ግንኙነቶች ዉስጥ ህልዉናዉንና ደህንነቱን ሲያረጋግጥ ነዉ። አማራነት ከሌሎች የአገሪቱ ማህበረሰቦች መካከል ብቻ የሚገኝ ሳይሆን አነሰም በዛም በየዉስጣቸዉም  ያለ ነዉ። አማራዉ ከአገሪቱ ብዙሃን ማህበረሰቦች ጋር ተጋብቷል፣ ተዋልዷል፣ ተዛምዷል፣ ተዋህዷል። እዚህ ላይ የሚነሳዉ ጥያቄ አማራዉ ህብረተሰባዊና ባህላዊና ብሔራዊ ትስስሮቹ ዉስጥ ሆኖ ደህንነቱንና ሰላሙን ለማግኘት የሚታገለዉ እንዴት ነዉ? የሚል ይሆናል። ራስነቱን የሚያረጋግጠዉ ወይም የሚጠብቀዉ በምን መንገድ ነዉ?
አማራዉን ማህበረሰብ ከጥፋት እንታደግ በሚል አላማ ዙሪያ ለሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ድርጅቶችና ስብስቦች ይህ ጥያቄ ምንም ያህል ችግራቸዉ አይደለም። ጉዳዩን የሚያዩት አቃለዉ በአንድ ጐኑ ነዉ፤ ማለትም ኢትዮጵያን ከማዳን እቅድ ጋር በመርህም ሆነ በስልት ምንም ያህል ሳያይዙ በጐሣዊ ማንነቱ ነዉ። በዚህ አይነት አተያይ የማህበረሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚጥሩት ነገዳዊ ማንነቱን (በተለይ ደግሞ ተጐጅነቱን) አጉልተዉ በመከለልና በመመሸግ ለማጠናከር በመሞከር ይመስላል። የአማራን ህዝብ ከጥፋት ለመከላከል የሚፈልጉት ባመዛኙ በልዩና ብቸኛ ራስነቱ ነዉ። ይህ የአማራ ተሟጋቾችና አክትቪስቶች አስተሳሰብ በቀና መንፈስ የተቀረጸ ሊሆን ቢችልም የተዛባ እንደሆነ ማሳየት አይከብድም።
አንድ ዋና ችግሩ ህብረተሰባዊ፣ ባህላዊና አገራዊ ትስስሮችና አብሮነቶች ዉስጥ ሆኖ የአንድ ማህበረሰብን ህልዉና በብቸኛ፣ ደሴታዊ ራስነት ከልሎና መሽጐ ለመጠበቅ ወይም ለማዳን የሚደረግ ሙከራ በመሠረቱ ተቃርኖ ያለዉ ጥረት ነዉ። አማራዉን ከጥፋት ለመታደግ፣ ማለትም ደህንነቱን ከሚጠናዎቱት ሃይሎችና አገዛዞች ለመጠበቅ፣ ከነዚህ ሃይሎች ብቻ ሳይሆን ከአገሪቱ ብዙሃን ማህበረሰቦች የጋራ ኢትዮጵያዊነትም ራሱን ማግለል አለበት።
ግን በዚህ መልክ ማንነቱን መለየቱ ራሱ አማራዉን ለጥፋት ወይም ለጉዳት ሊያጋልጠዉ ይችላል። ነገዳዊ ልዩነቱንና ብቸኝነቱን አጐልቶ ከሌሎች የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ራሱን ማግለሉ ደህንነቱን ለጥቃት የተመቻቸ ኢላማ ያደርገዉም ይሆናል። ከዚህም አልፎ ለአገር አድን ትግሉ ብቁና ዉጤታማ ተሳትፎዉ እንቅፋት ሊሆንበት የሚችል ነዉ። በአገር ጉዳዮች ዉስጥ መካከለኛ ሚና ተጫዋችነቱን አጥቶ በጥግ ያዢነት እንዲቀጥል የሚያደርገዉ ነዉ።
በዚህ አይነት ራስ አለያይና አተያይ የሚመራ የአማራ አክትቪስትነት ሌላዉ ችግር የአማራዉን ማህበረሰባዊ ራስነትን ወይም ህልዉና በሚመለከት በቂ ግንዛቤ የለዉም። የአማራዉ ህልዉና ሙሉ ወርድና ስፋት በጐሣዊ ወይም አካባባዊ ራስነቱ የተወሰነ እንዳልሆነ ያልተረዳ አክትቪስትነት ነዉ። የአማራዉ ህልዉና ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር በጥልቅ በተያያዘ ታሪካዊ አስታዉሶ፣ ጽኑ መንፈሳዊ እምነትና ሕይወት፣ እንዲሁም ዘር ዘለል በሆነ ብሔራዊ ባህልና ንቃተ ህሊና የታነፀ ነዉ።
በተጨማሪ አማራዉ በዘመናዊ ሃሳቦች መስክ ተንቀሳቅሶ እንደ ማህበረሰብና የኢትዮጵያ ዋና አካል ራስነቱን አዙሮ አይቶ ችግሮቹን መመርመርና መፍትሔዎቻቸዉን ማበጀትም የህልዉናዉ መገለጫዎች ናቸዉ። ከታሪካዊና ባህላዊ ግብአቶች ባሻገር አማራነት ወደፊት ተመልካች ብሔራዊ ራዕይ አፍላቂነትን ያካትታል ወይም ማካተት ይችላል። በአብዮቱ ዘመን ከአገሪቱ ብዙሃን ታጋዮች ጋር አንድ ሆኖ እንዳደረገዉ አማራዉ በዛሬዉ የራስ መታደግና አገር የማዳን ትግሉም ፖለቲካ ሃሳብና ስልትም ጫሪና አነሳሽ መሆን የሚችል ነዉ።
በነዚህ መንገዶች በታነፀ ማህበረሰባዊ-አገራዊ አድራጊ ፈጣሪነት አማራዉ ህልዉናዉን ይበልጥ የማንቀሳቀስና የትግል ስምሪት የመስጠት እምቅ አቅም አለዉ። በዚህ መልክ ተነሳሽነቱን፣ እንቅስቃሴዉንና ስምሪቱን ሃቀኛ ይዘት ሰጥቶ ማራመድ፣ የራሱና የአገሩ ማድረግ፣ ብሎም እንደ ማህበረሰብ የገጠመዉን አስጊና አስከፊ እዉነታ መለወጥ ይችላል።
በተናጠል ነገዳዊ ማንነትን የሚያጐላዉ የአማራ አክቲቭስቶች አስተሳሰብ ያለዉ ሌላ ችግር የአማራዉን ተጋድሎ አመለካከቱ ነዉ።አተያዩ ባመዛኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቃተ ህሊናን ያገለለ፣ ይባስ ብሎም የኢትዮጵያን ብሔርተኝነት የሚያጣጥልና ከትግል እሳቤ ዉስጥ የማያስገባ ነዉ። በይበልጥ ትኩረት ለመናገር፣ የአመለካከቱ ችግር የአማራዉ ንቅናቄ ከኢትዮጵያዊነት የተገለለ ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከልማትና ከሌሎች ጉዳዮችም የጸዳ የህልዉና ትግል ብቻ ተብሎ መታየቱ ነዉ።
በወያኔ ፈላጭ ቆራጭም መሰሪም አገዛዝ አማራዉ እንደ ማህበረሰብ እርግጥ የሞትና የሽረት ተጋድሎ ማድረግ ተገዷል። ሆኖም ተጋድሎዉ በተለይ ፖለቲካን (የሃሳብ፣ የስልት፣ የአደረጃጀት፣ የታክቲክና የእንቅስቃሴ አድራጊ ፈጣሪነትንና ቅንብርን) እንደ “ቅንጦት” በማየት ጥግ የሚያስይዝ “የህልዉና ትግል” ነዉ ማለት ምን ትርጉም አለዉ? ለመሆኑ አማራዉ ራሱንና አገሩን ከጥፋት ለማዳን ከወያኔ አገዛዝ ጋር በተለያዩ መስኮችና ደረጃዎች ከባድ፣ ትዉልድ ተሻጋሪ፣ ተጋድሎ ሲያደርግ እንዴት ነዉ ተጋድሎዉ ከፖለቲካ ዉጪ ነዉ የሚባለዉ? ለአማራዉ ራስና አገር አድን ትግል የሚበጅና የማይበጅ ፖለቲካን መለየት እርግጥ ግድ ይላል። ግን ትግሉ አካቶ ከፖለቲካ የጸዳ ነዉ ማለት ዘበት አይደለም ወይ?
ፊት ለፊት ሲያዩት አባባሉ ቅጥ የለሽ ቢሆንም በተወሰነ ቅጅዉ ከጀርባዉ ያለዉ ሃሳብ ወይም ትርጉም ይገባኛል። ይኸዉም አማራዉ ዛሬ የገጠመዉንና ሳይዉል ሳያድር መክላት ያለበትን የለት ተለት ወይም ተጨባጭ የመኖርና ያለመኖር ሁኔታ ያለምንም ፖለቲካ ስሌት፣ ድርጅታዊ አጀንዳ ወይም ርዕዩተዓለማዊ ወገንተኛነት በቀጥታና ባንዳፍታ መረዳት አስፈላጊነትን ማረጋገጥ ነዉ። ይህ አመለካከት ነጥብ አለዉ፤ በጥቅሉ ምንም ያህል አከራካሪ አይመስለኝም።
ይሁን እንጅ አማራዉ አሁን የገጠመዉን አደገኛ እዉነታ በታሪክ ሂደት ያነፀዉንና ያዳበረዉን ህልዉና ባገለለ “ቀጥተኛነት” ወይም ግልብ ተጨባጭነት የመገንዘቡ ሙከራ ትልቅ ችግር አለዉ። ግንዛቤዉ ሆን ተብሎም ባይሆን በዉጤት የአማራዉን መሉ ራስነት የሚያጓድልና የሚያቀጭጭ ነዉ። ይህ የተዛባ ራስ ግንዛቤ አማራዉ የቆመበትን ህያዉ እዉነታ፣ ማለትም የሚሰማዉንና የሚኖረዉን ማህበረሰባዊ፣ ባህላዊና ብሔራዊ ልምድ ያደበዝዛል፣ ሕይወት ይነሳል።
ይህም የሚያስከትለዉ ዉጤት አማራዉ ህልዉናዉን በሚያመነምን የተራቆተ ተናጠል የነገድ ማንነት ራሱን ለዉጭም ሆነ ለዉስጥ ጠላት ጥቃቶች ይበልጥ ማጋለጡን ነዉ። ማህበረሰቡ ለዘላቂ የመኖር ትግል ከብሔራዊ ባህል መሠረቱ ተነስቶና በስልታዊ ትዕግሥት ተንቀሳቅሶ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መቆጣጠሩ ቀርቶ ራሱ የተለዋዋጭ ሁኔታዎችና በጐዉን የማይመኙለት አድራጊ ፈጣሪዎች ቁጥጥር ተቀባይ በመሆን እንዲቀጥል ይገደዳል። ይህ እንዳይሆን ወይም እንዳይቀጥል የአማራዉን ህልዉና በሙሉ ወርድና ስፋቱ ማረጋገጥ ከመርህም ሆነ ከራስ አድን ትግል ስልት አኳያ አስፈላጊ ነዉ።
አያይዘንም እንደ ማህበረሰብና እንደ አገር ሁላችን አንድ መሠረታዊ ነገር ተረድተን ለለዉጥ መነሳሳት ይገባናል። ይኸዉም እዉኑ አለም፣ በተለይ የሰዉ እና የህብረተሰብ እዉነታ፣ ዝምብሎ በድፍኑ ያለና በአንድ ጐን ወይም አቅጣጫ ተጽእኖ የሚያሳርፍ አይደለም። ፍጹምና ዘላለማዊ ቋሚነት የለዉም። ራዕይ፣ ሃሳብና እምነት የለት ተለት ኑሮን፣ እዉን አለምን፣ ሊለዉጡና ሊያሻሽሉ ይችላሉ። በተጨባጭ ኑሮ ዉስጥና አልፈዉም ያልነበረ አዲስ እዉነታ የመፍጠር እምቅ አቅምም አላቸዉ።
በተለይ አገር ወዳዱ የአማራ (በሰፊዉ ደግሞ የኢትዮጵያ) ወጣት ትዉልድ ይህን በሚገባ ተገንዝቦ በአንድነት ፍቱን ንቅናቄ በመፍጠር ህዝቡንና አገሩን ከጥፋት ለማዳኑ ከባድ ትግል የራሱን አስተዋጽዎ ማድረግ ይጠበቅበታል።

[ይህ አመለካከት ተጨባጭ ማንነትን ግልጽ እዉነታ አድርጐ በቀቶታ ለመጨበጥ የሚሞክር  ግን የዋህ ተግባራዊነት (naïve realism) የሚያንጸባርቅ አመለካከት]