October 21, 2017 13:43

«ለሀገርና ለከተማ ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ።» ኤር 29፡7
ነቢዩ በስደት አገር  ለሚኖሩት ስደተኞች እሥራኤላውያን ለሀገር ሰላም ፈልጉ የሀገር ሰላም የሕዝብ ሰላም ነውና ይላል ዛሬም ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ለሕዝባችን ለሀገር ሰላም ጸልዩ  የሚል መልእክት ያስተላልፋል
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን! በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ምን እየተከናወነ እንደሆነ የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተል ሁሉ ይረዳዋል ብለን እናምናለን  አሁን አገዛዙ አቅም አጥቶ ነግሮች ሁሉ እየተበላሹ ናቸው የዚህ ወጤት ደግሞ ህዝባችን ወዴት ሊወሰደው እንደሚችል ከወዲሁ እየታየ ነው   ባለፉት ሳምንታት «በተባብሩ ጉባኤ» ላይ ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረብው ሐሳብ የዚህን ስጋት ነበር
እንደ ወቅቱ ሁኔታ አገሪቷ ያልፈረሰቸው ሕዝባችን ፈረሃ እግዚአብሔር ያደረበትና  ጨዋ ሕዝብ ስለሆነ እንጅ መንግስት እንደ መንግሥት  ስለሚያሰተዳድር አይደለም ፤ እርሱ ከቀረ አመታት ተቆጥረዋል።  በዚህ አጋጣሚ ሕዝባቸን በማሳየት ላይ ያለው  ኢትዮጵያዊ  ጨዋነት በቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ ስም  ሳናመሰግን እናልፍም።  መንግሥት ተብየው  እንደሚሰራው ተንኮል ቤሆን ኑሮ  ኢትዮጵያ ሞቃድሾን በሆነች ነበር።  ከጥቂት የፖለቲከኞችን በተለይም የገዢውን ፓርቲ ተንኮል በሚያራምዱ ግለሰቦች አማካይነት  የሚያመጡት መፈናቀል ከልሆነ በቀር  በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ የተለየየ ቋንቋ  የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ፤ ሕዝብ እንደ ሕዝብ አንዱ በአንዱ ላይ ይህን አላደረግም እናም ሕዝባችን ምስጋና ይገባዋል። አንዱ በሌላው ላይ  ሳይነሳ እሰከ አሁን መንግሥት ያሰበው ሳይሳካ ሕዝብ  በሚያደርገው የአስተውሎት ሒደት  አገር እንደ አገር  አለች  ወደፊትም  በጣም አጭር አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች  አይኖሩም  አገርና ሕዝብ ግን ይኖራል።  ውድ ኢትዮጵያውያን! እስከ አሁን የተከተላችሁትን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ይዛችሁ በመቻቻል ይህን የመከራ ቀን  እንድታሳልፉት ከአክብሮት ጋር  ህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል።

የሚከተለው ጥሪ ለአማራጭ ኃይሎች ይሆናል፦ ውድ ወግኖቻችን! የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካና የታሪክ ምሁራን አገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት አጣብቂኝና ሕዝባችን ላይ እያንዣባበ ያለውን አደጋ  ዛሬ አንድ ሆናችሁ  ለሕዝባችሁና ለአገራችሁ ካልሠራችሁ ነገ የዘገየ እርምጃ ነው ፤ ምን አልባትም እድልም ላይኖር ይችላል።  ዛሬ ግን  እግዚአብሔር እድልን ሰጥቷል  ስለሆነም ልዩነታችሁን ወደ ጎን ትታቸሁ አገር በማዳኑ  በወቅቱ ሁኔታ ላይ ትሰለፉ ዘንድ፤እየተራበ በሚገደለው፣ በታሠረው፣ በሚሰደደውና በሚሰቃየው ሕዝባችን ሰም  ጥሪ እንቀርባለን።
በዚህ አጋጣሚ Nov 1st ጀምሮ በኦሃዮ ኮሎምበስ በደብረ መድሐኒት መድኃኔ ዐለም ቤ/ክ በሚካሄደው  የሕጋዊ  ይቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ላይ መንፈሳዊና አገራዊ አጀንዳዎች መካከል በዋነኛነት የሜቀርበው አጀንዳ የሀገራችን የእርቅና የሰላም ጉዳይ ነው።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

የህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሕዝብ ግንኙነት  መምሪያ

አባ ጴጥሮስ የአውስትራሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ዛሬም እንደ ትናንትናው ታሪካዊ ድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ ናት !
ከሁሉ አስቀድመን ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለመወያየት ይህንን ዝግጅት ያደራጁትንና ቤተ ክርስቲያንን በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል የጋበዙትን ሰዎች ልናመሰግን እንወድዳለን ። በዚህ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለን ስንገኝ ፦

አንደኛ ቤተ ክርስቲያናችን ከእግዚአብሔር የተሰጣትን ሰማያዊ አደራና ሐዋርያዊ ተልእኮ መሠረት በማድረግ ፣

ሁለተኛ ኢትዮጵያ ሀገራችንና በታሪኳ የገጠሟትን ተመሳሳይ ሀገራዊ ፈተናዎችን እንዴት እንዳለፈችና ፣ እንዴትስ እኛ ትውልድ ዘንድ በክብር እንደደረሰች የሚያሳየውን አኩሪና መሳጭ ታሪካዊ የተጋድሎ ጉዞ በመመርመርና በዚያም ውስጥ የነበረውን የቤተ ክርስቲያናችንን ታላቅ አስተዋጽኦ መነሻ በማድረግ ፣

ሦስተኛ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ሀገሮችና ሕዝቦች ከገጠማቸው ተመሳሳይ ችግሮች እንዴት በድል አድራጊነት እንደ ወጡና ህልውናቸውን አስቀጥለው የተጓዙበትን ልምድ ግብዓት በማድረግ ሲሆን ፣ ዛሬ ሕዝባችን ከደረሰበት ታሪካዊ ውርደትና ፈተና ፣ ሀገራችንን ካንዣበበባት የመተራመስና  የመፍረስ አደጋ ለመታደግ ይረዳ ዘንድ ፥ ከእናንተ ከልጆቿና ከወዳጆቿ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልታበረክት የምትችለውን አስተዋጽኦና የተጋድሎ ድርሻ በሚመለከት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያምንበትን የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ ነው ።

ክፍል አንድ

የት ነን ?

«እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ። የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች» (ኤር 31 ፥ 15)

የማኅበረሰብ መሪዎች ራሳቸውን የክፉና የደግ መለኪያ ቱንቢ አድርገው “ስገዱልን!” ሲሉ ፣ ጎልማሶች ራስ ወዳድነትን ሙጥኝ ብለው የእርስ በርስ መበላላት መኖርና ሥቃይ አንድ ሲያደርጋቸው ፣ ወጣቶች በመንፈስ ልዕልና ከመኖር ይልቅ በድንገት የሚገነፍሉ  የንዴት ስሜቶቻቸውን እየተከተሉ መልሕቅ እንደሌለው መርከብ በትርጉም አልባነት ማዕበል ሲንገላቱ ፣ በእግዚአብሔር ሕይወት ለዘለዓለም እንዲያብቡ የተፈጠሩት የሰው ልጆች የተፈጠሩበትን ክብር ዘንግተው ለመሞት ተራ የሚጠብቁ እንስሳት ሁነው መመልከት ሕሊናን ያቆስላል ።
ማኅበረሰብ ሲፈርስ ፣ የሰው ልጅ ክብሩ ሲጣል ፣ እረኞች በጎቹን እየቀለጣጠሙ ያለርኅራኄ ሲበሏቸው ማየት ሕሊናን ይጠዘጥዛል ። አልቃሻው ነቢይ ኤርምያስ ቁስሉ ቢያመው ሞት ልጆቿን እንደ ነጠቃት ራሔል ጉንጮቹ የእንባ መፍሰሻ ቦዮች ሆኑ ። መዝሙሩ ልቅሶ ፣ ጸሎቱም እዬዬ ሆነ ። የእስራኤል ስደተኞችም በመዝሙር መጽሐፋቸው ይህንኑ የእንባ መዝሙር በመዘመር ከኤርምያስ ጋር ተባበሩ ፣ እንዲህ ሲሉ
«በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን ፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን ። በአኻያ ዛፎቿ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን ። የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን ፥ የወሰዱንም ፦ የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን ። የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን ? ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ። ባላስብሽ ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ» ። መዝ 136 ፥ 5 ።
እግዚአብሔር የሌለበት ዓለም ቢሆን ኑሮ የራሔል እንባ ፈስሶ በቀረ ፣ የመከረኞቹም ሥቃይ ትርጉም ባጣ ነበር ። ነገር ግን ፣ የድኻ አደግ አባት ፣ የተሰበሩት ምርኩዝ ፣ የተሰደዱት መጠለያ ወደብ ፣ የሕይወት ደራሲዋ የሆነው እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ አለ ። ስላለም የራሔል እንባ ፈስሶ አልቀረም ። የኤርምያስ ጉንጮች በሰቀቀን እንባ ተሸርሽረው አልቀሩም ። ምድር ላይ ጠብ ያለው የራሔል እንባ ምድሩን ብቻ አጨቅይቶ አልቀረም ፣ ሰማያትንም አረስርሷል ፤ ከዘለዓለም የታወጀው የእግዚአብሔር ምሕረት ደምቆ ታውጆበታል ።

ፖለቲካዊ ፈቃድ የተሰጣቸው ሌቦች ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ሥርዓተ አምልኮውን ተውኔት ባደረጉበት ፤ የእምነቱን አቡጊዳ የማያውቁ ሥራ አጦች የመምህራንን ካባ አጥልቀው ፣ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ቃል ከመምራት ይልቅ ፥ ኪሳቸውን ለመሙላት ሲሉ ከንቱነትን እየነገሩ ሰዉን የአእምሮ ድኻ በሚያደርጉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሥነ ምግባር ብርቅ ቢሆን ምን ይገርማል?

እነሆ ! ሁሉም በየፊናው የበላይ ለመሆን ይሮጣል ። በዙሪያው ያሉት ሁሉ በእርሱ ዙሪያ ተሰብስበው እስኪሰግዱለት ድረስ ይቸኩላል ። ራሱን የሁሉ ነገር ማዕከል (አምላክ) አድርጎ ለመገኘት የማይቧጥጠው ገደል ፣ የማይፈነቅለው ደንጊያ ፣ የማይቆርጠው ዛፍ የለም ። እየሆነ ያለው ይህ ነው ። እንደ ኤርምያስ ለሰው ልጆች ክብር ፣ ለወገኖቹ ርኅራኄ የተመላ ልብ ያለው ቅን ካለ ፣ ምንም እንኳ አስተሳሰቡ እንደ ዕብድ ቢያስቆጥረውም ያለቅሳል ። ስለ ወገኖቹ ስሕተትና ዕብደታቸው ስለ ወለደው ሥቃይ ያለቅሳል ። የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ፍቅር የልቡን በር ካልከፈተና ወንድሙን እንደ ራሱ ሊራራለት ካልቻለ ፣ የወንድሙን ሥቃይ የራሱ ሥቃይ አድርጎ ማሰብ ካልቻለ ፥ የትኛውም ፖለቲካዊ ዲስኩርና አደረጃጀት ከመበላላት አያድንም ።

አንድ የ20ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓዊ ፈላስፋ ማኅበረሰብንና የሥልጣን ጥምን በተነተነበት ድርሳኑ እንዲህ ይላል፡-

“Every man would like to be God, if it were possible. Some few find it difficult to admit the impossibility. These are the men framed after Milton’s Satan, combining like him nobility with impiety.” [1]

ፈላስፋው እንዲህ ዓይነት ሰዎች ክቡርነትን ከክፉነት ጋር ቀላቅለዋልና ሰይጣንን ይመስላሉ ይላል ። ሰይጣንን በሚመስል ኑሮ እየኖርን የእግዚአብሔርን ዕረፍት ከወዴት ልናገኝ እንችላለን ?

ሕዝባችን አሁን ያለበት ሁኔታ በየትኛውም አቅጣጫ ተስፋ ያለው ሁኖ አይታይም ። በሀገሪቱ ያሉ ዐበይት ቤተ እምነቶች በየክፍላቸው አንዳቸውም የተስማሙ አይደሉም ። አንድ ቤተ እምነት ነው ተብሎ የሚጠራ ቡድን አምስት ስድስት ዓይነት ዶክትሪን ያስተምራል ። የእርሱን ዶክትሪናዊ ትንተና ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ እርሱን የማይቀበሉትን ለማስጠላት በፍቅር ፈንታ ጥላቻን ይሰብካል ። ይህ ደግሞ ተከታዮቹን በጥላቻ ይመርዛቸዋል ። ከጥላቻ የተረፉትንም ተስፋ መቁረጥ ይጫናቸዋል ። በሥልጣን ላይ ያለው ሴኪዩላሪስት ቡድን እንዲህ ባለው ሃይማኖታዊ ውዥንብር ተጠቃሚ ነው ። የሃይማኖት ተቋማት የተጠናከረ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዳይኖራቸው አበክሮ ይሠራል ። መንግሥቱ የቆመው ማኅበረሰቡን ከፋፍሎ እርስ በርሱ እንዲፈራራ በማድረግ ስለ ሆነ ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የአብሮነትና የደኅንነት ስሜት (sense of security) እንዲኖረው የሚያስችል ፣ እርሱ የማይቆጣጠረው ምንም ዓይነት ተቋም እንዲኖር አይፈቅድም ። ቡድኑ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ ነጻነት ማሳጣት የመጀመሪያ ሥራው ያደረገበት ምክንያትም ማኅበረሰቡን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል ነበር ።

የሀገራችን ሕዝብ ንቅሐተ ሕሊና በተረዳው መጠን እግዚአብሔርን በመፍራት ላይ የተመሠረተ ስለ ነበር አኗኗሩ ሰብአዊ ርኅራኄ የተመላበት ነበር ። ማኅበረ ሰባዊ ልዩነቶች ተቻችለው የኖሩት ፣ ጎሣዎች ሲፋቀሩ ተጋርተው ፣ ሲጣሉ ዕርቅ አውርደው የኖሩበት ምክንያት ሕይወትን የሰው ልጆችን ሁሉ እኩል አድርጎ ከፈጠረው ከእግዚአብሔር አኳያ የመመልከቻ ነጥብ ስለ ነበራቸው ነው ። የሀገር ሽማግሌዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ታላቅ ስፍራ ይዘው የኖሩበት ምክንያት በሰከነ መንፈስ ያንን ነጥብ ጠብቀው ጊዜያዊ ስሜቶችንና ግጭቶችን ማርገብ ይችሉ ስለ ነበር ነው ። ዛሬ ያ ሁሉ አለ ለማለት ያስቸግራል ።

ማኅበረሰቡ አሉኝ የሚላቸውን ማኅበረሰባዊ ተቋማቱንና ተቋማቱ ተገንብተውባቸው የነበሩበትን ማኅበረሰባዊ ዕሤቶች (social values) ሙሉ በሙሉ ማለት እንኳ ባንችል በአብዛኛው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ፈርሰዋል ። ዕድርና ዕቁብ ሳይቀሩ በካድሬዎች እይታ ሥር ናቸው ። “Big Brother is watching you!” እንዲሉ ። [2] የኢትዮጵያውያን መከራ ዛሬም አላቆመም ። የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ቡድን በሀገሪቱ ውስጥ ላለው ወጣት ትውልድ ሥራ መፍጠር አቅቶታል ። የወጣቶች ተስፋ ማጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ከመኖር እንጀራ ፍለጋ በሊብያና በግብፅ በረሀዎች ሞትን እየተጋፈጠ ነው ። ጎሣዊ ቁርሾዎች የሚያስታግሣቸውና የሚያስታርቃቸው ማኅበረሰባዊ ሥርዓት አጥተዋል ። ትናንት በሀገር በቀል የዕርቅ ሥርዓቶች ይፈቱ የነበሩ ግጭቶች ዛሬ የአንድ አካባቢ ሕዝብ ከኖረበት ቀዬ እንዲፈናቀል እስከማድረግ እየደረሱ ነው ። የጎሣ ግጭቶች አሁን ፍጹም መንግሥታዊ መልክ ይዘዋል ። እንደ ድሮው በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ ያሉ ሱማሌዎችና ኦሮሞዎች ሲጋጩ ግጭቱ በሽማግሌዎች የሚፈታ የጥቂት ወጣቶች ጠብ ሳይኾን የጎሣ ክልሎቹ መንግሥታት የድንበር ግጭት ይሆናል ። በቅርብ ጊዜ የተፈጠረው ከምሥራቅ ኢትዮጵያ የተሰማው ክፉ ዜና በዚህ ዓይነት ሀገሪቱ እንደ አንድ ሉዓላዊ ሀገር መቀጠሏን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው ።

ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ወደ ዘመነ መሳፍንት እየተመለሰ ይመስላል ። ልዩነቱ ምናልባት የአሁኑ ዘመን መሳፍንት የታጠቁት መሣሪያ የመግደል ፍጥነቱ በጣም የተሻሻለ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን አይቀርም ። የምድሪቱ ድኾች አሁንም ይራባሉ ፣ አሁንም ይሰደዳሉ ፣ አሁንም በግፍ ይታሠራሉ ፣ አሁንም ይገደላሉ ። የተረፉትም በፍርሃትና በጭንቀት ተወጥረው ይኖራሉ ። ውኃ ፥ መብራት ፥ የመኖሪያ ቤት ፥ የተመጣጠነ ምግብ ለኢትዮጵያውያን ዛሬም ብርቅ ናቸው ። በዜና ማሠራጫዎች ዜና የሚሆነው ኢትዮጵያውያን ውኃ የማጣታቸው ሳይሆን የእንትን ቀበሌ ነዋሪዎች “ንጹሕ የመጠጥ ውኃ” ማግኘታቸው ነው ። ይዘረጋሉ የሚባሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ፥ ዐዋጅ ከተነገረላቸው ከዓመታት በኋላ እንኳ የት እንደደረሱ መጠየቅ አይቻልም ።

ቅዱስ ሲኖዶስ በሥልጣን ላይ ያለው ሴኪዩላሪስት ቡድን ላለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰውን መከራ እየተመለከት ሲያዝን ፣ ግፉ እንዲያቆምም ሲያሳስብ ቆይቷል ። እኛ በስደት የምንገኝ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በምንሰበሰብበት ጊዜ ሁሉ ስለ ወገናችን ያልጸለይንበት ጊዜ የለም ። የኤርምያስ እንባ ዛሬም ይፈስሳል ። ቅዱስነታቸው ከሰው መወያየቱን ትተው በዝምታና በእንባ ከእግዚአብሔር ጋር መወያየቱን መርጠዋል ።

ባለፉት ከሃያ በላይ ለሚቆጠሩ ዓመታት ቅዱስ ሲኖዶስ ከአርባ በላይ የሰላምና የአንድነት ጥሪዎችን አድርጓል ። ጥሪዎቹ በአብዛኛው በመንግሥት ስም ለተቀመጠው ቡድን ብቻ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ እንቆረቆራለን ለሚሉ ፖለቲካዊ ቡድኖችም ነበር ። እንደ አለመታደል ሁኖ ለዚህ የቤተ ክርስቲያን ጥሪ በጎ አጸፋ የሰጠ ተቋምም ሆነ ግለ ሰብ ታይቶ አይታወቅም ። ይህ ከምን መጣ ? የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ነጻነት ለሀገሪቱ ነጻነትና ማኅበረሰባዊ ዕድገት ያለውን ትእምርታዊና ተግባራዊ (symbolic and practical) አስፈላጊነት ካለመገንዘብ ? ወይስ የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ ታሪክም ሆነ የአስተሳሰብ ሥሪት ለመረዳት የቤተ ክርስቲያን ሚና ምን ያህል ጕልሕ እንደ ሆነ ካለማስተዋል ? በስደት የሚገኘው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ግን አሁንም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ነጻነት እስከሚረጋገጥ ድረስ ጥሪውን አያቆምም ።

ብዙ ሰዎች “ይህ ፖለቲካ ነው ። ቤተ ክርስቲያን እዚህ ውስጥ ምን አገባት?” ይላሉ ። እርግጥ ነው ቤተ ክርስቲያን የእኔ የምትለው የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ቡድን ሊኖራት አይችልም ። ነገር ግን የትኛውም የፖለቲካ ቡድን የሰው ልጆችን ክብር ሲደፈጥጥ ስታይ ፥ “ስለ ምን ታሳድደኛለህ!” የሚለውን የሰው ልጆችን ስቃይ የራሱ ያደረገውን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን የምታመልክ ቤተ ክርስቲያን ግፍና በደልን እያየች ዝም ልትል አትችልም ። ዝም ካለችማ የተጠራችበትን ለሚገፉት ጠበቃ የመሆን ዓላማዋን አሽቀንጥራ ጥላዋለች ማለት ነው ።
ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ነጻነቷን ከኢትዮጵያውያን ነጻነት ለይታ አታየውም ። የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻነት የማያከብር ማናቸውም ፖለቲካዊ ሥርዓት ፥ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ነጻነቷን ሊያከብርላት አይችልም ።

ክፍል ሁለት

የታሪክ ምስክርነት

የዚህ ጉባኤ አዘጋጆችና ታዳሚዎች ወገኖቻችን !! የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ታሪክ ውስጥ በመውደቁም በመነሣቱም ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበረች ። እንዲሁ አሁንም ከፊት መሥመር ላይ ትገኛለች ።

ኢትዮጵያን በመገንባት ፣ በማሳደግ ፣ ድንበሯን በማስከበርና አንድነቷን በማጽናት ወዛቸውን ከደማቸው በመቀላቀል ደማቅ ታሪክ ፣ አኩሪ ሀገርና ፣ ኩሩ ሕዝብ ትተውልን ያለፉ ቀደምቶቻችን በጉዟቸው ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችንና ታቦታቱን ከፊት በማስቀደም እንደ ነበር ታሪክ ያዘክረዋል ። የሀገራችን ታሪክ ሲጠና ከፊት ለፊት የሚታይ የሚጨበጥ የሚዳሰሰ ታሪክ ያለው ወይ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ፤ አልያም በቤተ ክርስቲያን የተሠራ ሁኖ ይገኛል ። ይህ ሊያስተባብሉት የሚችሉት ነገር አይደለም ። የኢትዮጵያን ማንነት ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመለየት መሞከር የአውሮፓን ሥልጣኔ ከአውሮፓ ቤተ ክርስቲያን ወይም የመካከለኛው ምሥራቅን ባህል ከእስልምና ውጪ ለማቅረብ የመሞከር ዓይነት ከንቱ ልፋት ነው ። ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ሕዝብ ማንነት ከተሸመነባቸው ዋና ድሮችና ማጎች አንዷና ዋነኛዋ ናት ። ይህ በጎው ነው ።

በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ብሎም ለማፍረስ ፣ ሉዓላዊነቷን በመድፈር ፣ ሕዝቧን በማሰቃየትና በመግደል ፣ ታሪኳንና ባህሏን በማጥፋት ፣ በአጠቃላይ ሀገራዊ ህልውናዋንና የሕዝቧን አንድነት ፣ ሰላምና ነጻነት አደጋ ላይ የጣሉ ኃይሎች በሙሉ ማለት ይቻላል ተቀዳሚ የጥቃት ዒላማቸው የሚያደርጉት ይህቺኑ ቤተ ክርስቲያን ነው ።

ይህን ለመረዳት ብዙ የምርምር ሥራ መሥራት አስፈላጊያችን አይደለም ። ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ጥብቅ ውሕደት መቀበል የማይፈልጉ ወገኖች በምርምርና በእኵልነት ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ኢትዮጵያ የሚል ስም እንኳ ሳይቀር ለእነርሱ አጀንዳ እንዲመቻቸው ቀይረው አንዴ ሱዳን ሌላ ጊዜ ኩሽ ሲሉ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ታዝበናል ።

ይህ ሥራ ሲካሄድ በኢትዮጵያ ያለው በመንግሥት የተወከለው አካል አንድም ቃል ሲተነፍስ አልታየም ። በዚያ ፈንታ ሕጋዊውን ቅዱስ ሲኖዶስ ሲያጥላላ ፥ ስም ሲስጥ ፣ በስደት ያለውን ማኅበረ ሰብ እንኳ እንዳያገለግልና የእነርሱን ጥፋት እንዳያጋልጥ ዘመቻ ሲያቀናብር ሃያ አራት ሰዓት ዕረፍት የለውም ። ሕዝቡም ጠላት የሰጠውን ስድብና የስም ማጥፋት ዘመቻ ተቀብሎ የገዛ ቤተ ክርስቲያኑን የሚያገለግሉትን አባቶቹን እየሰደበ ፣ ማኅበረሰባዊ ራስን የማጥፋት ትንቅንቅ ላይ ይገኛል ።

ቆም ብሎ ማስተዋል ይገባል ! ዐውደ ምሕረት ላይ ሰው በሽጉጥ የተገደለው በማን የፕትርክና ዘመን ነበር ? በ1993 ለተቃውሞ ሰልፍ ወጥተው ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው የነበሩ ተማሪዎችን አሳልፎ እንደ እባብ ለቀጠቀጣቸው የመንግሥት ኃይል የሰጠው ማን ነበር ? በ1997 ያ ሁሉ ደም ሲፈስስ ሕዝቡን ጥፋተኛ አድርጎ ወንጅሎ መግለጫ ያወጣው ማን ነበር ? ከዚያም በኋላ በተደጋጋሚ ሕዝብና መንግሥት ሲጋጩ በቤተ ክርስቲያን ስም ሕዝቡን ጥፋተኛ እያደረገ በአደባባይ የወነጀለ ማን ነበር ? እልፍ አእላፍ በግፍ ሲታሠሩና ሲገደሉ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ በቤተ ክርስቲያን ስም ስለ ልማትና ዕድገት የደሰኮረልን ማን ነበር ? ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ !

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን ምንነት ስለ መለየት ባስተማረበት ክፍል “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” እንዳለው ሁሉ የማንኛውም ግለ ሰብ ሆነ ስብስብ መታወቂያው ዕለት በዕለት የሚሠራው ሥራ ነው ። የቋንቋ ልዩነትን መሠረት ያደረገው በአንድ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሰለጠነው መንግሥት እንደ ቀደሙት ፀረ-ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰሜኑን የሀገራችን ክፍለ ሀገር ኤርትራን አስገንጥዬ ፣ ትግራይን እገነጥላለሁ ብሎ ሲነሣ ቀጥተኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ማለት ነው ።

አላማዬን ለማሳካት እንቅፋት ይሆናሉ በሚል በቅድሚያ እንዲጠፉ ከተፈረደባቸውና በግንባር ቀደምትነት የጥቃት ኢላማ ከተደረጉት ሁለት ዋነኛ አካላት መካከል ይህቺው ቤተ ክርስቲያናችን አንዷ ናት። የዚህ ማሳያ ሁኖ የሚቀርበው ለራሱ ሥራ አስፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ የመደባቸው ሟቹ አባ ጳውሎስ የሥራ ቀናቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያን መልክአ ምድር ቅርጽ ይዞ የነበረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዓርማ በመቀየር ነው ።
ይሁን እንጂ ፣ ኢትዮጵያ በቀላሉ የምትፈራርስ ሁና አትታይም ! የሕዝቧን አንድነት ፣ ሰላምና ነጻነት እናስከብራለን ብላችሁ የምትደክሙ ወገኖቻችን ! እንደ ቀደሙት የሀገራችንና የሕዝባችን ባለውለታ አባቶቻችን በመንገዳችሁ ያስቀደማችሁት ፣ በጉባኤዎቻችሁ የምትጋብዙትና ፣ የትግላችሁ አጋር ያደረጋችሁት ይህቺኑ ቤተ ክርስቲያን ነው ። በዚህም ቅዱስ ሲኖዶሱ እጅግ በጣም ደስተኛ ነው ።

ውድ ወገኖቻችን !! ዛሬ በዚህ ቦታ ከእናንተ ጋር በዚህ ጉባኤ በመገኘት ስለምንወዳት ሀገራችንና ስለምንሳሳለት ሕዝባችን አንድነት ፣ ሰላምና ህልውና ስንመክር በቀደሙት ደጋግና እውነተኛ አባቶቻችን እግር ሥር ስለ መተካታችንና የነሱንም ፈለግ ተከትለን እየተጓዝን ስለ መሆናችን ማረጋገጫ ይሰጠናል ። በዚህም አባቶቻችን የሰጡንን የነጻነት ዓርማ ይዘን አሁን ያለብንን ብዙ ዓይነት ችግር በድል እንደምንወጣው ተስፋችን ብሩህ ፥ እምነታችንም ጽኑ ነው ። ይኽ ችግራችን እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ከአለው መለኮታዊ አላማና ከእኛ እነድነት በላይ አይደለም

በአንጻሩ ደግሞ ከእናንተ ጋር በመሆናችን የተደሰትነውን ያህል በዘር ላይ ብቻ ተመሥርቶ በመንግሥት ስም የተቀመጠው  በመንግሥት ስም በተቀመጠውና በግብረ አበሮቹ በመገፋታችንና በመሳደዳችን እንዲሁ እጅግ ደስተኞች ነን ። ምክንያቱም የእኛ ስደት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማፍረስ አቅደውና አልመው በተነሡ ፣ የሕዝብን ሰላምና ነጻነት በጠመንጃ ኃይል በቀሙ ፀረ-ሰላም ኃይሎች አሳዳጅነት በመሆኑ ነው ።

በዚህም የእውነተኞቹ አባቶቻችን የእነ አቡነ ጴጥሮስና የእነ አቡነ ሚካኤል ልጆች የመሆን ዕድልን አግኝተናል ። በአንጻሩም አሳዳጆቻችን በምግባራቸው የእነማን ልጆች ስለመሆናቸው ነጋሪ አያሻውም ። ለዚህም ታሪክ ሕያው ምስክር ነው ።

ክፍል 3፡

የቤተክርስቲያን የመፍትሔ ሐሳብ

ይቅርታና ዕርቅ

አማኙ ማኅበረሰብና ሌላውም ዜጋ በጠቅላላው ምን ቢያደርግ አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ውስጥ መውጣት ይችላል ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስቀድሞ መጠየቅ ግድ ነው ።

ሀ/ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ዛሬ ከምትገኝበት ችግር ላይ እንዳትደርስ መደረግ የነበረበት ፣ ነገር ግን ሳይደረግ የቀረ ያልተሞከረ መፍትሔ ምንድን ነው ?

ለ/ የተሞከረውና ያልተሳካውስ ምንድን ነው ?

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ከተቻለ ችግሩን ለመፍታት የምንሄድበትን አቅጣጫ በግልጽ እናየዋለን ። ከዚህ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቋቋምና ያሉትንም ለማስተባበር ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል ።

በኢትዮጵያ ከመቶ በላይ ፓርቲዎች ተቋቁመው እንደ ነበር መረጃዎች ያሳያሉ ። አሁንም እንኳ የተለየያዩ በቋንቋና በዘር የተቋቋሙ ፓርቲዎች አንድ ልንሆን ነው እያሉ በየጊዜው መግለጫ ይሰጣሉ ። ለየብቻ ያሉትንና በውል የታወቁትን ከቆጠርን ከሃምሳ በላይ ፓርቲዎች አሉ ። ነገር ግን እነዚህ ፓርቲዎች በልዩ ልዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተነሣ ለሕዝቡ ማበርከት የሚገባቸውን አገልግሎት መስጠት ተስኗቸው እዚህ ደርሰናል ። ስለዚህ ዛሬ አዲስ ፓርቲ መመሥረት ለችግራችን መፍትሔ ሊሆን አይችልም ።

ፓርቲዎችን የሚያስተባብር ኮሚቴ ለማቋቋም መሞከርም ከዚህ ቀደም ከታየው ተሞክሮ በመነሣት ዛሬ ላለው ችግር መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም ። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ፓርቲዎችን ለማስተባበር ተሞክሯል ። ሙከራዎቹ ሁሉ ግን ከማስተባበር ይልቅ በማለያየት ፣ ከማቀራረብ ይልቅ በማራራቅ ሲጠናቀቁ ተመልክተናል ። አንዳንድ የአስተባባሪ ኮሚቴዎችም ፓርቲዎችን ይበልጥ ከማራራቅም አልፈው የራሳቸውን ፓርቲ ወደ ማቋቋም ደርሰዋል ።

የፓርቲዎች ውሕደትስ ? በዚህ ውጥረት በተሞላ ጊዜ ውስጥ ለማካኼድ መሞከር በራሱ ችግር ፈጣሪ ሊሆን ይችላል ። ከዚህ በፊት ፓርቲዎች ተባበሩ ተብሎ የተመሠረቱት እንደ ኢድሀቅ ቅንጅት ፥ ኅብረት ፥ መድረክ ፥ ኢሕአዴግ ፥ ወዘተ ችግር ፈቺ ከመሆን ይልቅ የሀገሪቱ ችግር አካል ሁነው ታይተዋል። በመሆኑም ፣ ዛሬ የፓርቲዎች ኅብረት ወይም ውሕደት ለመመሥረት መሞከሩ ለኢትዮጵያ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ የማምጣት ዐቅሙ ሚዛን የሚደፋ አይደለም ።

*ፖለቲከኞችን አስተባብሮ አሁን ያለውን ሥርዓት ለውጦ የሽግግር መንግሥት ቢቋቋምስ ? ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ታሪኳ ሦስት የሽግግር መንግሥታትን አይታለች-

= የልዑል አልጋ ወራሽ የሽግግር መንግሥት ፣

= የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መንግሥት ፣

= የኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥት” ።

እነዚህ ሦስቱም የሽግግር መንግሥት እየተባሉ ቢቋቋሙም ሀገሪቱን ከጭንቅ ወደ እፎይታ ፣ ከጭቆና አገዛዝ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት የወሰዱ አልነበሩም ። ይልቁንም ሁሉም የአገዛዝን ቀንበር በሕዝቡ ጫንቃ ላይ በመጫን ዛሬ ካለንበት የጥፋት አፋፍ አድርሰውናል ።

ታዲያ ምን ይሻላል ? ቤተ ክርስቲያን ምን ብታደርግ ከዚህ ሀገራዊ አጣብቂኝ መውጣት እንችላለን ? ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት መንግሥት አፍርሶ መንግሥት በመተካት የመገዳደልና የበቀል መንፈስ ተጠምደን እዚህ ግባ የሚባል የሕዝቡን ሕይወት የሚለውጥ የልማት ሥራ ሳንሠራ ይኸውና አራት ትውልድ አለፈ ። እነሆ አሁን የህልውናችን ጉዳይም ጥያቄ ውስጥ ከገባበት ዘመን ላይ ደረስን ።

በግፍ የሚፈስ የንጹሐን ደም መዘዙ ብዙ እንደ ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስም ከታሪክም እንማራለን ። ትናንት በግፍ የፈሰሰ ደም ለዛሬ መከራ ከዳረገን ፣ ዛሬ የሚፈስሰው ደም ምን እንደሚያመጣ ለምን ማስተዋል ተሳነን ? የትናንት ፖለቲከኞች እርስ በርስ መበላላት ለዛሬው መከራ ዳርጎናል ። ዛሬ ካለፈው ተምረን እርስ በርሳቸው የማይበላሉ ፖለቲከኞች ማየት ያልቻልነው ለምንድነው ? አንድን ስሕተት ደግመን ደጋግመን እየሠራን ከቅድሙ መጥፎ ውጤት የተለየ ውጤት የምንጠብቀውስ ስለ ምን ይሆን? አልበርት አንስታይን “Insanity is doing something over and over again and expecting something different.” ይላል ።
ክፉውን ያርቅልንና ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሕዝብ ዕልቂት በሦስት መንገዶች ሊፈጠር ይችላል ።

ሀ/ በገዢው አካል በሚቀነባበር ሤራ ምክንያት ።

ገዢው አካል አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ እንደምናስተውለው ሁለት አማራጮች ብቻ ያሉት ይመስላል ።
አንደኛው ሀገር ማስተዳደር እንደ ተሳነው በማመን ለራሱ የመውጫ መንገድ አበጅቶ የአደራ መንግሥት በመመሥረት ገለል ማለት ነው ።

ሁለተኛው ደግሞ ፣ አሁን እየሆነ እንዳለው በአምባ ገነንነቱ ቀጥሎበት የቻለውን ያህል ሕዝቡን ፈጅቶና አፋጅቶ በመጨረሻ ራሱ መጥፋት ነው ። ዛሬ አገዛዙ የያዘው መንገድ በዚህኛው ትልም ላይ ያለ ስለ ሆነ ከዚህ የጥፋት መንገድ ለማምለጥ የሚደረገው ጥረት በይደር የሚተው አይደለም ።

ለ/ ልዩ ልዩ ፍላጎቶች ባሏቸው የፖለቲካ ቡድኖች ምክንያት ።

በሀገሪቱ ያለው ማዕከላዊ አስተዳደር መዳከም በልዩ ልዩ ቦታ የሚገኙ ቡድኖች ኃይል እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል ። የእነዚህ ቡድኖች መጎልበት በራሱ መጥፎ ባይሆንም ቡድኖቹ ከሀገራዊ ራእይ ይልቅ ጥቃቅን አካባቢያዊ ጥቅሞች ላይ ብቻ በማተኮር ጠላቶቻችን ያሏቸውን ወደ መፍጀት ሊያመሩ ይችላሉ ።

ይህ አሁን በዓይናችን የምናየው የሶማሌና የኦሮሞ ግጭት ፣ አንዱን አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ “ሁለት ነህ ! የአንተ ስም ቅማንት ነው !” “የአንተ ደግሞ አማራ ነው !” “አንተ በእርሱ ስትጨቆን ኑረሃል ፤ ለዚህ ጭቆና እኔ መፍትሔ ይዣለሁ ። የያዝኩት መፍትሔ እርስ በርስህ ስትጋደል ብቻ ነው” በማለት መሣሪያ ወድሮ ሳንጃ መዞ ለማጋደል የተጠነሰሰው የጥፋት መጠጥ ውሱን ጥቅመኞች ለመጠጣት ተዘጋጅተዋል ። ይህ ለእነርሱ የሚጠቅም ይምሰላቸው እንጂ መጨረሻው መላው ምሥራቅ አፍሪካን ለውድመትና ለቀውስ ሊዳርግ የሚችል አደጋ ነው ።

በሦስተኛው ዓለም ውስጥ ያለች የ100 ሚሊየን ሕዝብ ሀገር ስትፈራርስ የአካባቢው ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ሕይወት በነበረበት ይቀጥላል ብሎ ማሰብ ትልቅ ጭፍንነት ነው ።

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ አቀንቃኞች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በጥበብና በሀገራዊ ተስፋ ላይ መመሥረት እንዳለበት አበክሮ ማሳሰብ ያስፈልጋል ። ሀገራዊ ተስፋን ችላ በማለት ጊዜያዊ ቀበሌያዊ ሥልጣንና የቢሆን ዓለም ምኞታቸውን (utopia) ብቻ እንከተላለን ቢሉ የሚሠሩት ስሕተት የኢትዮጵያን ሕዝብ እጅግ በጣም ከባድ የደም ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል መገንዘብ አለባቸው ። ሕዝቡ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ በመሆን በጎሪጥ እንዳይተያይ ሀገራዊ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ ሕዝብን የማንቃትና ተስፋን የማስጨበጥ ሥራ የመሥራት ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል ። በዚህ ረገድ እነርሱ ላይ ከፍ ያለና የማያቋርጥ የውትውታና የማሳሰብ ሥራ መሠራት አለበት ።

ሐ/ የተበዳይነት ስሜት ባዘሉ ሰዎች ቂም ምክንያት ።

ሌላው አስፈሪውና የእልቂት ደመና ያንዣበበው በሀገሪቱ ውስጥ ላለፉት 26 ዓመታት በኢሕአዴግ ጎሠኛና ጨቋኝ አገዛዝ የተፈጸመው ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍ በብዙ ሰዎች ላይ ያልሻረ ቁስልና የግንባር ጠባሳ ማሳረፉ ነው ። የአገዛዙ ዐቅም ማጣት እነዚህ ግለሰቦች አጠቁን በሚሏቸው ሰዎች ላይ ቂማቸውን የሚወጡበት አጋጣሚ ሊፈጥርላቸው ይችላል ። አቶ መለስ ሞት ቀደማቸው እንጂ ደግሰውልን የነበረውን የሩዋንዳ እልቂት በሰው አእምሮ አስቀምጠው አልፈዋል ። ዛሬም ቢሆን አሉ ከሚባሉ የመለስ ራእዮች አንዱ ይህ መሆኑን አሁን በዓየናችን እያየነው ነው ። ይህ ግን ማኅበረሰቡን ወደማያልቅ የመገዳደል አዙሪት ከመድፈቅ ውጪ የሚፈውሰው አንድም ማኅበረሰባዊም ሆነ ግለሰባዊ ነቀርሳ እንደሌለ የማሳመን ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅብናል ። በተለይ የሃይማኖት ተቋማት በዚህ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለብን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጽኑዕ ታምናለች ።

ሕዝብን ከእልቂት ለማዳን የሚያስፈልጉ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች
ለእንዲህ ያለ ድርጅት የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ተሳታፊ መሆን አለባቸው ። ከዚህም ጋር ፓርቲዎች ሕዝብን በሚያደራጁበት ወቅት ሀገራዊ ተስፋን እንጂ ማኅበረሰባዊ ቂምና ጠባሳ ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የሚያቅብ የሥነ ምግባር ሕግ ማውጣት ፣ የምክርና የማስተባበር ሥራ መሥራት ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን የሚቀጥሉት ሥራዎች ደግሞ የሚከተሉት ሲሆኑ መተግበር ያለባቸውም በፖለቲከኞች ፥ በሀገር ሽማግሌዎችና በምሁራን ይሆናል ።

1/ ጊዜያዊ የአደራ መንግሥት ማቋቋም ።

2/ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ።

3/ የይቅርታና የእርቅ  ኮሚሽን ማቋቋም

ቤተ ክርስቲያን እነዚህን  መፍትሔዎች መጠቆም እንጂ  እነዚህን ሁሉንም ራሷ   በኃላፊነት ተረክባ መሥራት አትችልም ። የይቅርታና የእርቁን ጉዳይ ግን ፥ ፈቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያንንና ሌሎችንም ሰላም ወዳድ ወገኖችን ይዛ መሥራት እንዳለባት ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ያምናል ።

የሚያስፍለጉንና የምናደርጋቸው ጉዳዮች

1/ እውነተኝነትና ግልጽነት፡–

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እውነትም አርነት ያወጣችኋል» ብሏል ። በኅብረተሰባችን ዘንድ አሁን የጠፋው መተማመን የሚለው ቃል ነው ። ቀድሞ ሲባል የምንሰማው “የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ነበር ። አሁን ግን የችግራችን ምንጭ የሆነው ድብቅ አጀንዳ የሚባለው ነገር ነው ። በአንድ ወቅት አንድ ስለ እውነት ፍልስፍና ያጠና ወንድም ስለ ኢትዮጵያውያን አብሮ የመሥራት ጅግር ሲናገር “ለእውነት ቦታ ያለ መስጠት ጅግር ነው” ይል ነበር ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዚህ በእጅጉ ተጎድቷል ። አንዱ የፖለቲካ ድርጅት ሌላውን ማመን አይችልም ። በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ እንኳ ካለው አለመተማመን የተነሣ ብዙው ነገር ለገዛ አባላት ሳይቀር ምሥጢር ነው ።

አንድ ምሥጢር ያልሆነ ነገር አለ- እርሱም የኢትዮጵያውያን ተቆጥሮ የማያልቅ ችግር ነው ። ይህ ፈላስፋ ይህንኑ ጉዳይ ሲያብራራው ለእውነት ቦታ ስለማንሰጥ በቦታው እውነት ያልሆነ ነገር ይተካበታል ። ያ በእውነት ቦታ የተተካ እውነት ያልሆነ ነገር በግልጽ ሲቀመጥ ውሸት ይሆናል ። እያንዳንዱ ሰው ከዚህ እውነት ካልሆነ ነገር ላይ ልቡን ካሳረፈ በውሸት ላይ ቁሟል ማለት ነው ። ይህ ሰው ራሱ እውነት ስለሌለው ሌሎችን እያምንም ማለት ነው ። እርሱንም ሌሎች ሰዎች ባያምኑት አይደንቀውም ምክንያቱም እርሱም ያው ስለ ሆነ ።

ብዙዎች እንደሚያስቡት ሐሳብ የማመንጨትና መርሐ ግብር የመንደፍ ችግር የለም ። ችግሩ ያለው ሐሳብና ራእይን በአንድ ላይ አድርጎ መሄድ ላይ ነው ። ከዚህ የተሰበሰብን ሁላችን ለሕዝብ ዕድገት ለሀገር ብልጽግና እውነተኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል ። መቼም ራስን ከማቃጠል የበለጠ ሌላ ሊታይ የሚችል የችግር መግለጫ ቋንቋ የለም ። ለሕዝብ ፍትሕ ቁሙ ። ደግሞም አጽናኑ ። እውነተኛ ሁኑ ። በአመክንዮ ላይ የተመሠረተ ውይይት ተወያዩ ። አንዱ ሲሠራ ሌላው አይቀልድ ። አንዱ ሲሞት ሌላው አይሳቅ ። ግትር አቋም በፖለቲካ የሚሠራ አይደለም ። ባለፉት አርባ ዓመታት ይደረግ የነበረ የሽኩቻና ያለመተማመን ፖለቲካ አካሄድ እስካሁን ድረስ ለፖለቲከኞቹ አልበጀም ። ለሕዝቡም መከራን እንጂ በረከትን አልሰፈረለትም ። ታዲያ ይህ ገና በውጥኑ የከሸፈ አካሄድ ስለ ምን በመተማመን ፣ በመደማመጥ መንገድ አይቀየርም ? የየትኛውም የሠለጠነ ሀገር ፖለቲካ በግትርነት ሲራመድ ታይቷልን ? መደማመጥን ፥ መቻቻልን ፥ በዚህ ጉዳይ ላይ ወንድሜ ከእኔ ይሻላል እርሱን ማድመጥ ይገባኛል ብሎ ማሰብን እንደ እሾህ የሚፈራ ትውልድ ቢሆንም መነገር ግን አለበት ። በአንድ ጉዳይ ላይ ልዩ ልዩ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ሲነሡ አንጃ ተብለው ድምጥማጣቸው ይጠፋል ። ትግሉ  ሥልጣን መያዝን ሳይሆን ሀገራዊ ተስፋን ማዕከል ባደረገ መልኩ የጋራ ወደ ሆነ አስማሚ ነጥብ መጓዝ ግድ ይላል ። ለዚህ ደግሞ የሚጀመረው ከይቅርታና ከእርቅ ላይ ነው ።

2/ የይቅርታና የሰላም ሂደት ማካሄድ

የደቡብ አፍሪካው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱም የማኅበረሰባዊ ይቅርታን አስፈላጊነት ሲያሳስቡ “ያለ ይቅርታ የወደ ፊት መልካም ዕድል የሚባል ነገር የለም” ብለዋል ። “There is no future without forgiveness”

እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በዚህም ረገድ እንደሌላው ሁሉ እንዋሻለን ። እኔ ከማንም ጋር አልተጣላሁም እንላለን ። ግን ሁላችንም በበቀል መንፈስ የሰጠመ ልብ እንደያዝን አጋጣሚዎች ሁሉ ይመሰክሩብናል ። ለዚህም ዋነኛው ማሳያ ለበጎ ነገር አብረን መሥራት አለመቻላችን ነው ። ብዙዎቻችን ሳናውቀው በልባችን ያጠራቀምነው ቀን ጠብቆ የሚፈነዳ የቂም መግል በቀል አለብን ። ይህ መርዝ በይቅርታ ፈርጦ ካልተፈወሰ ቀን የሚጠብቅ ፈንጂ ነው ። ስለዚህም ይህን ማኅበራዊ ነቀርሳ መንግሎ ለማውጣት ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰባዊ ይቅርታን በኃላፊነት መምራት ይገባታል ብሎ ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ያምናል ።

ፖለቲከኞች ኅብረት የሚሉት የፖለቲካ ስምምነት ብቻውን ፣ ለኢትዮጵያ ጥቅም አይሰጥም ። ይህ ዓይነት ስምምነት ፣ ከአሁን ቀደም ተሞክሮ ያልተሳካ ውጤት አምጥቶ ዛሬ ለሚዘንብብን የመከራ ዶፍ ዳርጎናል ።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፣ ከስደት ተመልሶ ሕጋዊ መስተዳድር ሲያቋቁም ፣ ሦስቱን ቡድን አቀራርቦ በይቅርታና በዕርቅ ፣ ችግሩን በማቃለል ፈንታ በዐዋጅ አንድ ሁኑ በሚል ማስተዋል የጎደለው መንግሥታዊ ትእዛዝ ደም የተቃቡ ዐርበኛና ባንዳን ፣ በጎሪጥ የሚተያዩ ዐርበኛና ስደተኛን ፣ የሚጠላሉ ባንዳንና ስደተኛን በጉልበት አንድ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር ።

ይህ ውሳኔ የንጉሡን ሥልጣን ለማቆየት ቢጠቅምም ማኅበረሰቡን ግን አንድ ከማድረግ ይልቅ በቂምና በጥላቻ ልቡ እየሻከረ እንዲሄድ አድርጎታል ። የደም አብዮት ወልዶ ፣ የደም ጦርነት አሳድጎ ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት አናግቶ ፣ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ንዶ ፣ እጅግ ክፉ የአገዛዝ ቀንበሮችን በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ተክሎ ኼደ ። አሁንም መንፈሳዊ የይቅርታና የዕርቅ ሂደት ካልተከናወነና የማኅበረሰቡ መንፈስ በይቅርታ ካልታደሰ ፣ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ብቻውን ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ሀገሪቱን ወደሚፈለገው የሰላምና የአንድነት ጉዞ ማድረስ አይችልም ።

በአሁኑ ጊዜ የሚጻፉ መጻሕፍት ፣ የሚያሳዩት ይህን ያለ ይቅርታና ዕርቅ የተደረገ በሰው ልጅነት መተዛዘንንና መደጋገፍን ሳይሆን እከክልኝ ልከክልህ የሚል ጊዜያዊ መጠቃቀምን ብቻ መሠረት ያደረጉ ስምምነቶችን ውጤቶች ነው ። ቀደም ሲል የተቋቋሙትን ኢድሀቅ ከተባለው የፖለቲካ አንድነት አንሥቶ አሁን አገራዊ ንቅናቄ እስከ ተባለው ድረስ ያሉትን ስምምነቶችና እነርሱንም ተንተረስው የሚጻፉትን ከ“ያ ትውልድ እስክ ባለቤት አልባ ከተማ” ድረስ ስንመለከት ፣ ውስጣዊ በቀልና ፉክክር የተሞሉ ናቸው ። በኅብረተ ሰባችን ያለውን የበቀል ጥርቅም በሚያሳዝን ሁኔታ ያስነብቡናል ። ለምሳሌ ያህል እነዚህን፣ ጥቂቶቹን ገለጽን እንጂ ፣ በየትኛውም በማኅበረ ሰባችን ውስጥ በየአቅጣጫው ያለው የበቀል ጥርቅም እንዲህ በቀላሉ ተገልጦ የሚያልቅ አይደለም ፤ ባጤኑት ቁጥር ልብ የሚያስበርግግ ይዘት አለው ።

በዚህ በቀል ውስጥ እንዳሉ ፣ አንድነት መመሥረት ማለት ፈንጅ በተጠመደበት ድልድይ ላይ እያወቀ መኪና እየነዳ በመሄድ ሞትን የመረጠ ሰው መሆን ነው ። ለዚህ መድኃኒቱ ዕርቅ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ይህን ዕድል ተጠቅማ በአማራጭ ኃይሎች ወገን በኩል የሚከናወን የዕርቅና የሰላም ሂደት ማድረግ ያስፈልጋታል ብለን እናምናለን ። ምክንያቱም የቅዱስ ሲኖዶስ የስደቱ መነሻ በሀገሪቱ  የፖለቲካ ነጻነት አለመኖር  የሃይማኖት ነጻነትም እንዳይኖር ስለ አደረገው ነው ። በሌላ አባባል ቤተ ክርስቲያንም የዚሁ የመንግሥት ፖለቲካ ተጠቂ ስለ ሆነች ይመለከታታል ማለት ነው ።

በወያኔ ዘመነ መንግሥት ፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ ይካሄድ የነበረውና አሁንም እየተካሄደ ያለውን የሃይማኖት ተጽዕኖ ስንመለከት ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ግን ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ጀምሮ የሃይማኖት ተጽዕኖ በመካሄድ ላይ ነው ። በዚያ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስደት ፣ እንደ ግለሰቦች ጉዳይ ተደርጎ ነበር የተወሰደው ። ግን አሁንም የገዳማት መደፈር ፣ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል ፣ እንደ ቀጠለ ነው ። አሁን እኛ ክዚህ እየተወያየን የኢየሩሳሌሙ ገዳማችን  በመፍረስ ላይ ነው አሁን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን የሚክል አካል ስለሌለ ምንም ነገ እንዳልተፈተረ ዝም ብለዋል ምንስ ሊሉ ይችላሉ የሚፈልጉት ከተሳካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  መዳከም በዚህ ምክንያት ፣ በኢትዮጵያ የሕዝብንና የሃይማኖትን ነጻነት የሚያከብር መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ጥረቷን ትቀጥላለች ። ከሥራዋም አንዱ ፣ ይህንን የሰላምና የዕርቅ ጉዞ በመሪነት ማከናወን ነው ።

ዛሬ በራሳችን ላይ ውሳኔ መወሰን ይኖርብናል ። አሁን ከስምምነት ያለፈ አንድነት ያስፈልጋል ። ከመቀናጀት ያለፈ አንድነት ያስፈልጋል ። አሁን ይቅርታን ለሀገራችንና ለሕዝባችን እንደ ሰጠነው ስጦታ አድርገን ልባችንን መክፈት ያስፈልጋል ። አሁን መጀመሪያ ራሳችን ከአምላካችን ይቅርታ መጠየቅና የተዘረጋችውን የይቅርታ እጁን በፍቅር መቀበል ያስፈልጋል ። ያን ባደረግን ጊዜ እኛ የይቅርታ ሰዎች እንሆናለን ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንብቤ ሐሳቤን ልደምድም

«ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና ፥ እርሱም ፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው ። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ» ። ገላ 5 ፥ 14-15 ።
እርስ በርስ ከመበላላት እርስ በራሳችን እንከባበር ፤ እንነጋገር ፥ ከሽፍታ ትክክለኛ ፍትሕ አንጠብቅም ።

እኛ የፍትሕ ሰዎች ብንሆን ግን ፍትሕ ራሱ ከመካከላችን ይገኛል ። ከፍትሕም ሰላም ይመነጫል ። የሮም ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ እንዳሉት “ያለ ፍትሕ ሰላም ፣ ያለ ይቅርታ ደግሞ ፍትሕ የለም”

(There is no peace without justice and there is no justice without forgiveness) ።
[1] Russel, Bertrand. 1948. Power: A New Social Analysis.
[2] George Orwell. 1949. 1984.