ሐራ ዘተዋሕዶ

በ7 አውቶብሶች ተጓጉዘው የደረሱ የምሥራቅ ጎጃም ግፉዓን ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች እንዲሁም የአዲስ አበባ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት በምልአተ ጉባኤው የመክፈቻ ጸሎት መርሐ ግብር ላይ የአቤቱታ ድምፃቸውን ሲያሰሙ፤

  • የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ጸሎት ተካሔደ፤
  • የተሐድሶ ኑፋቄ፣ በጸሎትና በርቱዕ አስተምህሮ ካልተመከተ፤ ከዮዲት ጉዲት ጥፋትና ከግራኝ ወረራ ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና እንደሚያናጋ ብፁዕነታቸው አሳሰቡ፤
  • የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከትን፣ በሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደሎች ያስቸገሩት ብፁዕ አባ ማርቆስ እንዲነሡ፥ ግፉዓን ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ጠየቁ፤
  • ችግሮቹ መፍትሔ ሳይበጅላቸው ከቀጠሉ፣ ለሀገረ ስብከቱና ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች እንደሚያስከትሉ አሳስበዋል፤
  • “ምክር ዝክር የሌላቸው ግራ አጋቢ” ያሏቸውን ብፁዕ አባ ቶማስን አስጠነቀቁ፤ ብፁዕ አባ ማርቆስን እየደገፉ በሚከተሉት፣ ወጣቱን ትውልድ ከቤተ ክርስቲያን የሚያርቅ አካሔዳቸው ወቀሷቸው፤
  • ከደብረ ማርቆስ፣ ብቸና እና ደጀን የተውጣጡትና በ7 አውቶቡሶች ተጓጉዘው የደረሱት ከ500 በላይ ካህናትና ምእመናን፣ የአቤቱታ ድምፃቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አሰምተዋል፤
  • የምልአተ ጉባኤው መክፈቻ ጸሎት መርሐ ግብር በተደረገበት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ አቤቱታቸውን ያሰሙ በርካታ ምእመናን፤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና እና ለሕገ ቤተ ክርስቲያን መከበር ጥብዓት ላሳዩት፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል፤

†††

  • በማዕከል የተቋቋመው፣ የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ጉባኤ፣ በአግባቡ ባለመሥራቱ ዳግም እንዲቋቋም፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ጠየቁ፤
  • የማኅበራት ኅብረቱ፣ ለምልአተ ጉባኤው ባቀረበው ባለ13 ነጥቦች አቤቱታ፤ በመዋቅር የተሰገሰጉ የኑፋቄው ቅጥረኞች ታግደው እንዲመረመሩ፤ ተወግዘው የተለዩት ለሕዝቡ በይፋ እንዲታወቁና ለኑፋቄያቸውም በሊቃውንት ጉባኤው ምላሽ እንዲሰጥ፤
  • ውጉዛኑ፥ በቤተ ክርስቲያን አስማተ ማዕርጋት፣ አልባሳት፣ ንዋያተ ቅድሳትና የትምህርት ማስረጃዎች እንዳይጠቀሙ በሕግ እንዲከለከሉ፤ ባለቤትነትና ባለመብትነት የሕግ ጥበቃ እንዲያገኝ፤
  • ታግደውና ተሰናብተው ጉዳያቸው በተያዘው ውሳኔ እንዲሰጥ፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በመምህራን ላይ የተደረገው“ጅምላ እግድ” እንዲስተካከል፤
  • በኑፋቄ ለተደናገሩ ምእመናን፣ በቤተ ክርስቲያናችን የብዙኃን መገናኛዎች ምላሽ እንዲሰጥና የዐውደ ምሕረት ጉባኤያትም እንዲዘጋጁ፤
  • በተለያዩ ቦታዎች፥ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን በማፍረስ፣ ታቦታትንና ንዋያተ ቅድሳትን በየቦታው በመጣል የሚፈጸመው ድፍረት እንዲቆም፤
  • የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና እንዲከበር፤ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚደረጉ ጫናዎች ተወግደው፣ በቤተ ክህነቱ የቴሌቭዥን ጣቢያ የአየር ሰዓት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፤