October 21, 2017 22:22

በአንድ ቀን ሃያ አምስት ዜጎች አማራ ናችሁ በሚል በገጀራ ተገደሉ     –   ግርማ_ካሳ

ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በሕወሃት እና በኦነግ የተዘረጋው ስርዓት አገሪቷን በዘር ሽንሽኖ ለብዙ ዜጎች መፈናቀል፣ መሞት፣ መጨፍጨፍ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። በተለይም ደግሞ “አማራ ናችሁ” በሚል ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ወገኖች በአርባ ጉጉ አርሲ ቤቶቻቸውን በማቃጠል ከፍተኛ ጭፍጨፋ እንደተደረገባቸው፣ በሃረርጌ በበዶኖ ደግሞ ነፍሰ ጡር ሴቶች ሳይቀሩ በሕይወት ትልቅ ገደል ገደል ውስጥ እንደተወረወሩ የሚታወስ ነው። በቅርብ ጊዜ ደግሞ ወደ ነበሩ አሳዛኝ ክስተቶች ስንመለስ በቤኔሻንጉል ፣ በጉሩፈርዳ፣ በአምቦ አካባቢና በአብዛኛው ኦሮሚያ “ነፍጠኞች፣ አማራ ከመሬታችን ልቀቅ” በሚል ዜጎች በአገራቸው ለሰቆቃ፣ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።
የዘር ፖለቲካው ከአማራው ማህበረሰብ አልፎ በመሄድ ሌሎች ማህበረሰባትን መጉዳት የጀመረበት ሁኔታም እያየን ነው።ከዘር ሽንሸናው የተነሳ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል በተፈጠረው ቀውስ ከሁለት እስከ አምስት መቶ የሚሆኑ ዜጎች ተፈናቅለዋል።
ላለፉት በርካታ ቀናት በኦሮሚያ በተነሱ ተቃዉሞዎች በጣም አሳዛኝ ክስተቶችን እያየን ነው። ገርበጉራቻ ላይ ብዙ ሰው መሞቱን፣ የአማርኛ ታርጋ ያለባቸውን መኪናዎች ታፔላቸው ሲነቀሉ እንደነበረ በስፋት እየተነበበ ነው። ኦሮሞ ባልሆኑ ወገኖች ላይ አደጋ እየደረሰ ነው። በኢሊባቡር ዞን ደግሞ፣ ደጋና ጮራ በሚባሉ ወረዳዎች በአንድ ቀን ብቻ ከሃያ በላይ ዜጎች በገጀራ ተገድለዋል። በተለይም በደጋ ወረዳ ጎሮ፣ ሰፌና ደፎ ቀበሌዎች አማራ ናችሁ በሚል ብዙ ንብረቶች ተቃጥለዋል። በርካታ በአክራሪዎች በአገራቸው የተገደሉ ወገኖቻችን በአሁኑ ወቅት አስክሬኖቻቸው በጮራ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ተከማችቶ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።
ከተገደሉ ወገኖች መካከል አቶ ክንዱ፣ አቶ ምስጋናው፣ አቶ ሙላት፣ አቶ ባቡ፣ አቶ ይማም፣ ሼህ ሁሴን የሚባሉ ይገኙበታል። ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ነዋሪዎች፣ ከሰፈራቸው ለቀው በመውጣት በአሁኑ ወቅት በኢሊባቡር ጫካዎች ሽሽተው ይገኛሉ። የድረሱልኝ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም እነርሱም ለመታደግ የተንቀሳቀሰ አካል እስከአሁን የለም።
በጣም የሚያሳዝነው አማራ በሚባለው ማህበረሰብ ላይ እና በኢትዮጵያ ብሄረተኞች ላይ ሲስተማቲክ የሆነ የዘር ማጽዳት ወንጀል ላለፉት 25 አመታት ሲፈጸም፣ ለነዚህ ወገኖች የሚቆም፣ ለተፈናቃዮች ማቋቋሚያ የሚሆን ድጋፍ የሚሠጥ፣ ይሄን ማህበረሰብ ለመጠበቅ የሚተጋ አንድም የመንግስት አካል አለመኖሩ ነው።
የፌዴራል መንግስቱ በሕወሃት ቁጥጥር ስር መሆኑ የሚታወቅ ነው። በጎንደር ተነስቶ በነበረው ቀዉስ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጆች ከመፍራታቸው የተነሳ ፣ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሲባል፣ ፌዴራል መንግስቱ ቦይንግ አውሮፕላን በማዘዝ ለተወሰኑ ቀናት በሚል ከጎንደር ወደ መቀሌ ማመላለሱ ይታወቃል። ከመተማ አካቢ ጥቃት ይደርስብናል ያሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ ሱዳን በገቡበት ወቅትም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ባጀት ተመድቦላቸው ነበር። በዚህ መልክ ሕወሃት ሆነ የፌዴዴራል መንግስቱ ለዜጎች ለተጎዱ እንክብካቤ ማድረጉ ተገቢ ነው። ሆኖም ግን ይህ አይነት እንክብካቤ ለአንድ ዘር ብቻ መሆኑ አሳዛኝ ነው።
በሶማሌ ክልል ኦሮሞዎች ሲፈናቀሉ ለጉድዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከፍተኛ ገንዝብ እያሰባሰበ ነው። እንደውም ዛሬ ከሼክ አላሙዲን 50 ሚሊዮን ብር አቶ ለማ መገርሳ ተቀብለዋል። ዜጎችን ለመጥቀም በዚህ መልኩ ርብርብ ማድረግ በጣም የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም ግን ለዜጎች የሚደረገው እንክብካቤና ጥበቃ ዘር ለይቶ መሆኑ አሳዛኝ ነው። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለኦሮሞው ብቻ እንጂ ለሌላው ማህበረሰብ እየሰራ አይመስልም።
የክልሉ መንግስት ሆነ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ይሄን ያደረጉት ከሌላ ክልል የመጡ ናቸው በሚል ለተፈጠረው ኢሰብአዊ ወንጀል ሃላፊነት ላለመዉሰድ እየሞከሩ ነው። ይሄ አይሰራም።የነርሱ ክልል፣ እነርሱ እናስተዳድራለን የሚሉት ክልል ነው። እነርሱ ያደራጁት ቄሮ የሚሉዋቸው ናቸው ይሄን ያደረጉት። ያኔም በበደኖና የኦነግ በአርባ ጉጉ የኦህዴድ የኦሮሞ አክራሪዎች ናቸው አማርኛ ተናጋሪዎችን ጨፍጭፈው ፣ በሕወሃት ላይ ለማሳበብ የሞከሩት። አሁን በሌሎች ላይ ጣት መቀሰር አይሰራም። ይልቅ ሃላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ የክልሉ መንግስት በመዉሰድ በክልሉ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎችን ሕይወት መጠበቅ መጀመር አለበት።የገደሉትን ለፍርድ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ይሄ አይነት ዘረኛ የጭካኔ ወንጀል እንዲፈጸም ምክንያት የሆኑ በሽታዎችና የበሰበሰ የዘርና የጥላቻ ፖለቲካ ከአገሪቱ እንዲነቀሉ መስራት ያስፈልጋል። የተፈናቀሉ ወደ ቦታቸው እንደገና መመለስ አለባቸው። ጉዳት ለደረሰባቸው ካሳ መከፈል አለበት።
በነገራችን ላይ በኦሮሚያ አማራ የሚባለው ራሱ አማራ ብሎ የሚጠራው ብቻ አይደለም። ከተለያዩ ብሄረሰብ የሆነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አክራሪ ኦሮሞዎች “አማራ” ነው የሚሉት።በመሆኑ አሁን ባለችዋ ኦሮሚያ ከኦሮሞ ውጭ ያለው ሌላው ማህበረሰብ የመኖር ዋስትና የለውም። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሕግ መንግስት እንደሚለው ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ ናት። እንደ አክራሪ ኦሮሞዎች ስሌት ምን እንኳን ወላጆቻችን፣ አያቶቻችን፣ ቅድመ አያቶቻችን የተወለዱበት ቦታ ቢሆንም፣ ኦሮሞ እስካልሆን ድረስ ለነርሱ መጤ ነን። አባታችን ወይ እናታችን ኦሮሞ ቢሆኑም፣ እኛ ግን ኦሮሞ አይደለንም ካልን፣ አፋን ኦሮሞ ካላወቅን መጤ ነን።
ወገኖች፣ አሁን ያለችዋ ኦሮሚያ እስካለች ድረስ ፣ የኦሮሞ ብሄረተኝነት የወጣቱን አይምሮ እስካሰከረ ድረስ፣ ኦሮሚያ ውስጥ የሕይወት ዋስትና የለም። የክልሉ መንግስት ነገሮችን የመቆጣጠር አቅም ያለው አይመስልም።