አዎን! እኛ ብዙሀን ነው። ድምጻችንን ስናሰማ የነበረው ብዙሀን ነን። ዛሬም ብዙ ሆነን ነው የምናናግራችሁ። በፎቶው ላይ እንደምታዩት ብዙ ሆነን ነው ስለመብታችን ስንጮኽ የነበረው። ይህ ህዝብ በምንም መመዘኛ ጥቂት የሚባል አይደለም!
ይህ ፎቶግራፍ የቀድሞው መጅሊስ ህዝበ ሙስሊሙን ማዋከብ በጀመረበት ዓመት (2003/2004) በአንዋር መስጂድ ከተደረጉት ተቃውሞዎች አንዱን ያሳያል፡፡ መጅሊሱና ደጋፊዎቹ “እኛን የሚቃወሙት ጥቂት ስርዓት አልባዎች ናቸው” ሲሉ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በመጅሊሱ ላይ ተቃውሞውን ያነሳ ህዝብ በምንም መልኩ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም ይህ ፎቶግራፍ ከበቂ በላይ ምስክር መሆን ይችላል፡፡

አሁን የያኔው ወከባ ቀንሷል። እሰየው!! ይህ ጥሩ ለውጥ ነው፡፡ ነገር ግን ተቃውሞውአቸውን በሰላማዊ ሁኔታ ሲገልፁ የነበሩ በርካታ ዜጎቻችን አሁንም በእስር ቤት ይገኛሉ፡፡ በተለይም በብዙሃኑ ሙስሊሞች ፊርማ ከተወከሉት የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት አባላት መካከል ሁለቱ (አህመዲን ጀበል እና አሕመድ ሙስጠፋ) ለኛ ሊገባን ባልቻለ ሁኔታ ከሌሎች የኮሚቴው አባላት ተነጥለው እስር ቤት ውስጥ ቀርተውብናል። እኛ ለአስራ ስምንቱም የኮሚቴው አባላት ተመሳሳይ ውክልና ነበር የሰጠነው። ሌሎቹን ፈትቶ ሁለቱን ማስቀረቱ ለምን እንደተፈለገ ሊገባን አልቻለም።

እንደሚታወቀው የኮሚቴው አባላት ከመንግሥት እውቅና ተሰጥቶአቸው በድርድር ላይ ነበሩ። ይህ መሆኑ እየታወቀ ነው “አክራሪዎችና አሸባሪዎች” የሚል የክስ ቻርጅ የተከፈተባቸው። በእውነቱ ይህ አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ነው፡፡ ለሀገራችን ገጽታም ጥሩ አይደለም፡፡ ከኮሚቴው አባላት በተጨማሪ በርካታ የሙስሊም ዑለማ፣ ኡስታዞች፣ ዳኢዎች፣ ደረሳዎች የመጅሊሱን ህገ ወጥ እርምጃ በመቃወማቸው ብቻ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ታስረውብናል።
እኔ በድጋሚ ሁለት ነገሮችን አስረግጬ መናገር እፈልጋለሁ፡፡

ተቃውሞውን ያደራጀው ኮሚቴው አይደለም፡፡ ተቃውሞው የተነሳው ከህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ጥያቄዎቹን ለመንግሥት አካላት እንዲያቀርቡለት በሚል ነው ኮሚቴውን የመሰረተው፡፡ ኮሚቴውም ህዝቡ ካዘዘው ውጪ ሌላ ነገር ሰርቶ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ኮሚቴውን የተቃውሞው ጠንሳሽ አድርጎ መመልከቱ ስህተት ብቻ ሳይሆን ስሙንም ማጥፋት ነው፡፡

ኮሚቴው የህዝበ ሙስሊሙ አፈቀላጤ ነበር፡፡ በቃ! ከዚህ ውጪ ሌላ ስልጣን አልተሰጠውም፡፡ ህዝበ ሙስሊሙን ወክሎ ይደራደራል። የህዝቡን አቋም ለመንግስት ያስረዳል። የመንግስትን ምላሽ ደግሞ ወደ ህዝቡ ያደርሳል። ከመንግስት በተሰጠው ምላሽ ላይ ተወያይቶ አቋም የሚይዘው ግን ህዝቡ ነው። ስለዚህ ኮሚቴው የተቃውሞው ጠንሳሽና አመራር ሰጪ ተደርጎ መታየት የለበትም።

ሁለተኛ ህዝቡ ተቃውሞውን የገለጸው ፍጹም ሰላማዊ እና ጨዋነት በተመላበት መልኩ ነው፡፡ ከህጋዊ መስመር የወጣ ተቃውሞ አሳይቶ አያውቅም፡፡ ኮሚቴ ማቋቋሙ ያስፈለገው ከመንግሥት አካላት ጋር ለመነጋገር እንዲቻል ነው፡፡ ህዝቡ ተቃውሞውን በዚያ መንገድ ባይገልጸው ኖሮ አንዳንድ ሃይሎች በዚያ ቀዳዳ በመጠቀም የህዝቡን ጥያቄ በሌላ መስመር ለማስኬድ ይሞክሩ እንደነበረ ሳይታለም የተፈታ ነው።፡ ስለዚህ የኮሚቴው መመስረት በበጎ ጎኑ እንጂ በክፉ መልኩ መታየት የለበትም፡፡

በመሆኑም በተቃውሞው ሳቢያ የታሰሩብን ወገኖች በአስቸኳይ እንዲፈቱልንና ለመንግስት ላቀረብናቸው ሶስት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጠን ዛሬም ደግመን እንጠይቃለን።
ሰላም ለሀገራችንና ለመላው ህዝቦቿ!!