ተፈናቃዮችወንድማገኝ አሰፋበተፈጠረው ግጭት 14 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋልወ

በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞን ውስጥ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረውን ግጭት በመሸሽ ከቤታቸው ተፈናቅለው በፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው ከሚገኙት መካከል አቶ አቢ አዝመራው ይገኙበታል።

አቶ አቢ እንደነገሩን በስልክ እና በቃል የሚደርስባቸውን ማስፈራሪያን ተከትሎ ነበር ሀሙስ ዕለት ከነቤተሰባቸው ወደ ጫካ ሸሽተው የገቡት። እሳቸው እንደሚሉት በአካል የሚያውቁት ግለሰብ ተገድሏል፤ ሌላኛው ደግሞ ጉዳት ደርሶበት ህክምና ላይ ይገኛል ሲሉ ነግረውናል።

ከኮቼ ኩሳዬ ቀበሌ የተፈናቅልን 91 ሰዎች በፖሊስ ድጋፍ ከጫካ ወጥተን አሁን በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ውሰጥ እንገኛለን ብለውናል። /ሮ ፋጤ እንድሪስም በዛው ፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ችግሩን መቋቋም የማይችሉ ህፃናት፣ እናቶች እና አቅመ ደካሞች አሉ። ምግብ፣ አልባሳት እና መጠለያ ያስፈልገናል መንግሥት ደግሞ ምንም አይነት ድጋፍ እያደረገልን አይደለም ይላሉ። እስከ አሁን ድረስም በርካታ ሰዎች ጫካ ውስጥ እንደሚገኙ ያነጋገርናቸው ሰዎች አረጋግጠውልናል።

ጥቃት ያደረሱት እነማን ናቸው?

የአካባቢው ወጣቶች እና ሌሎች የማናውቃቸው ሰዎች ናቸው ቤቶቻችንን እየለዩ ያቃጠሉት እንዲሁም ንብረት ያወደሙት። ውጡልን ይሉን ነበርይላሉ አቶ አቢ። 1977 ድርቅን ተከትሎ ከአማራ ክልል ወደ አካባቢው በሰፈራ እንደመጡ የሚናገሩት አቶ አቢ፤ እንደዚህ አይነት ችግር እየተፈጠረ ያለው ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ መሆኑን ያስረዳሉ።

በአንድ በኩል የአካባቢው ወጣቶች ማንም አይነካችሁም እያሉ ጥበቃ ያደርጉልናል በሌላ በኩል ደግሞ ጥቃት ይፈፀምብናል። ማንንም ማመን አይቻልም። እኛ እየተሳቀቅን መኖር ስለማንሻ መንግሥት ከዚህ ቦታ እንዲያነሳን እንፈልጋለንሲሉ በምሬት ይናገራሉ።

በመንግስት መሰሪያ ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችወንድማገኝ አሰፋበመንግስት መሰሪያ ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች

የክልሉና እና የአካባቢው ባለስልጣናት ምን ይላሉ?

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋን እና የቡኖ በደሌ ዞን የገጠር ግንባታ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑትን አቶ ሞሲሳ ለሜሳን በስልክ አነጋግረናል።

አቶ አዲሱ አረጋ፤ በቡኖ በደሌ ዞን የሟቾች ቁጥር 14 መድረሱን እና ከነዚህም መካከል 9 የክልሉ ተወላጆች መሆናቸውን ገልፀው በርካታ የሌላ ብሔር ተወላጆች በሚደርስባቸው ዛቻ እና ማስፈራሪያ ሳቢያ ቤት ንብረታቸውን ጥለው እየሸሹ እንደሆነ ተናግረዋል። ከአሁን በኋላ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይከሰት ኦሮሚያ ፖሊስ አስፈላጊ ጥበቃ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

አቶ አዲሱ አክለውም ከኦሮሚያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን ምግብ እና አልባሳት የጫኑ መኪኖች ወደ ቦታ እየተጓዙ እንደሆኑ ነግረውናል። አቶ ሞሲሳ ደግሞ እውነት ነው የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የተቃጠሉ ቤቶች እና እርሻዎች አሉ። ይህ አይነት ጥቃት ደግሞ በአማራ እና በትግራይ ተወላጆች ላይ ብቻ ሳይሆን በኦሮሞ ላይም ጥቃት ተፈፅሟልይላሉ።

ችግሩን ለመፍታት እየሰራን ነው ያሉት አቶ ሞሲሳ እሳቸው የሚመሩት በዞን ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም መንግሥት፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና ፖሊስ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኮሚቴው ተፈናቃዮቹ የምግብ፣ የህክምና እና የአልባሳት ድጋፍ እንዲያገኙ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ጥቃት ፈፃሚዎቹ እነማን ናቸው?

አዲሱ የኦሮሚያ ክልል አመራር እርምጃ የወሰደባቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው ድራማ እየሰሩ የሚገኙት። የመጀመሪያው ክፍል የድንበር ጦርነት መቀስቀስ ነበር ሁለተኛው ክፍል ደግሞ የብሔር ግጭት መፍጠር ነውይላሉ አቶ አዲሱ።

በአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን አንድነት ለመናድ ፍላጎት ያላቸው ናቸው ይላሉ አቶ አዲሱ። የእነዚህን ግለሰቦች ማንነት አስፈላጊውን ማጣራት ካደረግን በኋላ ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል። ለአቶ ሞሲሳም ይህን ድርጊት የፈፀሙት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ እና ከሃገር ሸሽተው የወጡም እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።