ዶ/ር ቴድሮስ እና ሮበርት ሙጋቤ

የዓለም ጤና ድርጅት ሮበርት ሙጋቤን የበጎ ፈቃድ አምሳደር ብሎ ከሾመ በኋላ በተሰነዘረበት ትችት ለሙጋቤ የሰጠውን ሚና ለመሰረዝ ተገዷል።

የድርጅቱ ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ”የተነሱትን ቅሬታዎች በሙሉ ከግምት ውስጥ አስገብቻለሁ” ብለዋል በሰጡት መግለጫ።

ከዚህ በፊት ዶ/ር ቴድሮስ የዙምባብዌን የህብረተሰብ ጤና አገልግሎትን አድንቀው ነበር።

ይሁን እንጂ ባለሙያዎች የዙምባብዌን የህብረተሰብ ጤና ሥርዓት ደካማ ነው ሲሉ ይነቅፋሉ።

ሙጋቤ ስልጣን በያዙ በመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት የጤና አገልግሎቶችን ማስፋፋት ቢችሉም፤ እአአ ከ2000 ጀምሮ የዙምባብዌ ምጣኔ ሃብታዊ አቅሟ በመጎዳቱ የጤና ሥርዓቱም እጅጉን ተዳክሟል።

በዙምባብዌ ለጤና ባለሙያዎች ለወራት ክፍያ ሳይፈፀምላቸው እንደሚቆይ ይነገራል። የመድሃኒት እጥረትም በሃገሪቱ አለ።

ከዜጎቻቸው አማካይ የህይወት ጣሪያ ከ30 ዓመት በላይ የኖሩት ሙጋቤ በተደጋጋሚ ለህክምና ወደ ውጪ ሃገራት ይጓዛሉ።

ዶ/ር ቴድሮስ የሙጋቤን የበጎ ፍቃድ አምባሳደርነት መሰረዝ ”ለዓለም ጤና ድርጅት የሚበጅ ሆኖ ስለተገኝ ነው” ይህንም ከዙምባብዌ መንግሥት ጋር መክረናል ብለዋል።

ለሙጋቤን የተሰጠውን ሚና ከተቃወሙት መካከል የእንግሊዝ መንግሥት፣ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስተር፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የዙምባብዌ የህግ-ባለሙያዎች ማህበር ይገኙበታል።

ይህ የውሳኔ ለውጥ የአዲሱ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርን አመራር ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ተብሏል።

የጤና ሥርዓቷ የተዳከመ በመሆኑ እና በሰብዓዊ መብት አያያዟ የምተወቀሰውን ሃገር መሪ የዓለም ጤና ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆኖ መሾም አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት ስር-ነቀል የሆነ ለውጥ ያመጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ገፅታውን የሚያበላሽ ሁኔታ ተፍጥሮበታል።

SOURCE    –   BBC/AMHARIC