October 24, 2017 07:21

ዶር አብይ አህመድ ከለማ መገርሳ ቀጥሎ ያሉ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከፍተኛ አመራር ናቸው። ኦሮሞው ከማንም ባልተናነሰ የኢትዮጵያ አንድነት ምሰሶ እንደሆነ የገለጹት ዶር አብይ በኦሮሞዉና በሌላው ማህበረሰብ መካከል የተከሰተው መራራቅ፣ አለመተማመንና መፈራራት መስተካከል እንዳለበት ይናገራሉ። ኦሮሞ በባህሉ የፍቅር ህዝብ፣ ሌላው የሚያቅፍ እንደሆነ የገለጹት ዶር አብይ፣ ኦሮሞው እንዲፈራ የተደረገበትን ምክንያቶች ነጥሮ በማውጣት ማስተካከል እንደሚያስፈልግ፣ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ኦሮሞው አንድነቱን፣ መተማመኑ፣ ትስስሩን ፍቅሩን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
” በምድር ላይ እባብን የማይፈራ የለም። እባብን የሚደርስ ሃይለኛ መሬት ላይ የለም። ጭልፊት ደግሞ ማሰብ ትችላለች። መሬት ወርዳ ከእባብ ጋር ግብግብ ከገጠመች ነድፎ ይጥላታል። እርሷ ግን ወደ ሰማይ ይዛው ትወጣለች። ያኔ ማሰብ አይችልም። እያልን ያለነው የውግያውን ሜዳ ቀይሩ ነው። በተጨባጭ ኦሮሞ የዚች ሀገር መሰረት መሆኑን አስመስክሩ።” ሲሉ ነበር ዶር አብይ ኦሮሞው ራሱን ከሌላ ነጥሎ መቀመጥ ሳይሆን ከሌላው ጋር በመቀላቀልና በመያያዝ ወደፊት መሄድ እንዳለበት የገለጹት።
በሶማሌላን በኦሮሚያ ክልል መካከለ በተፈጠረውና ለግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ መፈናቀል ምክንያት በሆነ ቀዉስ ዙሪያ፣ ዶር አብይ ሃረርጌን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ሲናገሩ ፡
“ሐረርጌ የፍቅር ሀገር ናት። ፍቅር ከዚህ ኤክስፖርት ሊደረግ ይገባል።ዓለም እና ኢትዮጵያ በፍቅር እጦት በምትሰቃይበት በዚህ ግዜ እናንተ ፍቅርን እማታካፍሉን ከሆነ እየበላን እንራባለን…” ነበር ያሉት።
ከዶር አብይ ጋር በፓርላማ አብረው የሰሩ የተከበረው አቶ ግርማ ሰይፉ ስለ ዶር አብይ እንዲህ ሲል ነበር የመሰከሩት፡
“አብይ አህመድ (ዶክተር አልነበረም ያኔ) ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እኔን መሸንቆጥ ይወድ ነበር፡፡ ከሸንቆጣው በኋላ ግን የሚሰጠው አስተያየት ሁሌም ይገርመኛል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ቅኝት የለበትም፣ ከስብሰባ ስንወጣ አንተ እኮ የእኛ ፓርቲ አባል ነው መሆን ያለብህ እለው ነበር፡፡ የእኛም ፓርቲ ባይሆን የሚያሰማቸው ንግግሮች አሁን ይፋ እየወጡ ደስ ያሰኘን ጀምሯል፡፡ እኔ በጎ ነገር ከሆነ ከኦህዴድም ይሁን ከሌላ ከጣመኝ ይጥመኛል”
ታዲያ ዶር አብይ ላይ አንድ አይነት ድራማ ሕወሃት መንደር እያየን ነው። ዶር አብይ ተናገሩት በሚል ህወሃት የሚቆጣጠረው የኢሕአዴግ ጽ/ቤት ገጽ ላይ ዶር አብይ ተናጋሩ ብሎ የሚከለተውን ለጥፈው አነበብን። ገረመንም።
“ያለን ምርጫ ሁለት ነው። አንዱ በጋራ ለመኖር መደመር ነው። ሁለተኛው ደግሞ እርስ በርስ መጠፋፋት ነው። የኛ ምርጫ ሁለተኛው መሆን አለበት”
ዶር አብይ ይሄን ይናገራሉ ብሎ የሚያምን ሰው ይኖራል ብለው ሕወሃቶች ይሄን አስቂኝ ፖስት መለጠፋቸው አስገርሞኛል። ህወሃት ከወዲሁ በነ አቶ ለማ መገርሳና በምክትላቸው ዶር አባይ አህመድ ላይ በይፋና በአደባባይ የስም ማጥፋት ዘመቻ መጀመሩን የሚያመላክት ነው።
እርግጥ ነው ሁሉንም ነገር ሕወሃት ላይ ማሳበብ አያስፈለግም። ሕወሃት ነው ከተባለ ህወሃት ሊጠቀምባቸው የቻለ፣ ከሕወሃት የባሱ በጥላቻ የተሞሉ በነ ኦነግና ጃዋሪያን የጥላቻ ፖለቲክ የሰከሩ ፣ ብዙ የኦሮሞ አክራሪዎች አሉ። ኢትዮጵያን የሚጥሉ፣ አማርኛንና አማራ የሚሉትን የሚጠሉ። በኢሊባቡር ያየነውም በኦሮሚያ የከረረ የኦሮሞ ብሄረተኝነት ስላለ፣ ለሌላው ማህበረሰብ በጣም አስጊ እንደሆነ ነው።
ሆኖም አገሪቷ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት፣ በኦሮሚያ ያለው የዘረኝነት በሽታ ለማስወገድ፣ በኦሮሚያ ልክ እንደ ኦሮሞው የሌላዉንም ማህበረሰብ መብት ሊያስከበር የሚችል ቢኖር የነ አቶ ለማ መገርሳ፣ የነ ዶር አብይ አህመድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ነው ሊሆን የሚችለው። የሌላውን ማህበረሰብ ሊያረጋጋ የሚችል ቁልፍና መሰረታዊ፣ ተጨባጭ፣ ከወሬና ከመግለጫ፣ ጣና ሄዶ እምባጭ ከመልቀም ያለፉ ተግባራት መፈጸም አለባቸው። በዚህም ረገድ አዎንታዊ እርምጃ እስካሳዩ ድረስ ሊደገፉም ይገባል። በአንዴ ተአምር እንዲፈጸሙ አልጠብቅም። የ25 የኦነግና የሕወሃት ዘረኛ በሽታ በቀላሉ አይድንም። ሆኖም ግን ደረጃ በደረጃ ቁስሎችን ለመሻር ስራዎች እስከተሰሩ ድረስ
1) በኢሊባቡር በኦሮሞ ስም ሕወሃት ልኳቸው ሆነ ኦነግ ፣ ወይም በራሳቸው የከረረ ዘረኛ ፖለቲካቸው ተነሳስተው ወንጀል የፈጸሙ በሙሉ በትክክል ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ።
2) ዜጎች ላይ ከዘራቸው ወይንም ከሃይማኖታቸው የተነሳ ወንጀል የሚፈጽሙ የሰሩት ወንጀል ሁለት እጥፍ ተደርጎ እንደሚቆጠርም ቅጣቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ማወጅ ያስፈልጋል። አዋጁም ከከተማ እስከ ገጠር ያለው ሁሉ በትክክል እንዲሰማዉና እንዲያወቀው መደረግ አለበት።
3) ለተገደሉ ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል።የተፈናቀሉትን እና በአሁኑ ወቅት ፈርተው በጫካ የተደበቁትን በቶሎ ማቋቋም ያስፈልጋል።
4) ጨፌው በአስቸኳይ ተጠርቶ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ሳይሆን በክልሉ የሚኖሩ ነዋሪዎች ሁሉ መሆኗን መደንገግ አለበት። ኦሮሚያ ethnic region ሳይሆን multi-ethnic region መሆን አለባት። ልክ እንደ ደቡብ እና የአማራው ክልል። የአማራው ክልል በአማራው ክልል ሕግ መንግስት መሰረት በክልሉ የሚኖሩ የሁሉም ብሄረሰቦች ናት። ኦሮሞ፣ አገው፣ ቅምናት፣ ትግሬ፣ አርጎና፣ አማራ ….ኦሮሚያ የኦሮሞ ብቻ መሆን አትችልም።፡
5) ኦሮምኛ የማይናገሩ የክልሉ ነዋሪዎች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በአማርኛ የመንግስት አገልግሎት መሰጠት መጀመር አለበት። አዳማ ናዝሬት ከ85% በላይ አፋን ኦሮሞ የማይናገር ሆኖ በቀበሌዎችና በከንቲባው ጽ/ቤት ፎርሞችን በቁቤ ለአስተርጓሚ ተጨማሪ ገንዘብ እየከፈለ የሚሞላበት ምንም ምክንያት የለም።፡በአጭሩ አነጋገር አማርኛም ከአፋን ኦሮሞ ጋር የስራ ቋንቋ መሆን አለበት።

https://youtu.be/GEr4Ror6i00