October 24, 2017 07:58

ኦሮሞና አማራ እሳትና ጭድ ናቸው ሲባል ሰምተናል። የሁለቱ አንድ መሆን የሥርዓቱን ውድቀት ማብሰሪያ ደወል ነውም ተብሏል። የሁለቱ አንድ መሆን መቻል ደግሞ ሥርዓቱ ሥራውን በአግባቡ ካለመሥራቱ የመነጨ መሆኑ ተሰምሮበታል – በነጌታቸው ረዳ።
ስለሆነም ሁለቱን ማህበረሰቦች እርስ በርስ የማባላቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይታመናል። ለዚህ ማሳያዎቹ;
1. አምና ጎንደር ላይ የኦሮሞ ደም የኛም ነው መባሉ የፈጠረው ጫጫታ;
2. ዘንድሮም “ጣና ኬኛ” መባሉ የፈጠረው የቅሬታ ስሜት;
3. እነለማ መገርሳ ስለአንድነት በማቀንቀናቸው ብቻ ጥርስ ውስጥ መግባታቸው;
4. እነደመቀ መኮነን ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን በመጎብኘታቸ የተፈጠረው ቅሬታ;
5. ከሰሞኑ የኦነግን ባንድራ ከወደቀበት በማንሳት የተጀመረው ማስፈራራት;
6. የሚሚ ስብሃቱ “ዛሚ” ሬዲዮ ለግጭቱ የሰጠው ሽፋን;
7. ENN የተባለው የቴ.ቪ. ጣቢያ ያሰማው ሰበር ዜና;
8. EPRDF Official የተባለው ዶ/ር አብይ “ምርጫችን መጠፋፋት ነው” እንዳለ አድርጎ የለጠፈው ነገር;
.. ሌሎችም ማሳያዎች መጨመር ይቻላል።
ከዚህ በቀላሉ ማየትና መረዳት የሚቻለው የሁለቱን ማህበረሰቦች “እሳትና ጭድ”ነት በተግባር ለማሳየት እየተሰራ መሆኑን ነው። በቋፍ ላይ ያለው የኦሮሞና አማራ ግንኙነት ደግሞ ለዚህ የተመቼ ነው። የሰሞኑ ግጭት ከፈጠረው ስሜትና አዝማሚያ የተረዳነውም ይህንኑ ሀቅ ነው።
የችግሩን መንስኤ ውጫዊ አድርጎ ማቅረብ ብቻውን አሳማኝና ዘላቂ መፍትሔ አይደለም። መፍትሔው የብሔር አስተሳሰብና አደረጃጀት አጥሩን መስበር ነው። የኦሮሞና አማራ ዘላቂ ጥቅምና ህልውናቸው የተመሠረተው በአንድነታቸው ላይ መሆኑን ለመናገር የተለዬ የፖለቲካ ዕውቀት ወይም ትንተና አያስፈልገውም። አንድነታቸው ደግሞ እዚያ ማዶና እዚህ ማዶ ቆሞ ሊፈጠር አይችልም። ስለዚህም በመካከላቸው ላለው የብሔርተኝነት ገደል አስተማማኝ የአንድነት ድልድይ መሠራት አለበት።
መኖር ያለበት አስተሳስብና አደረጃጀት ከሁለቱ ማህበረሰቦች ባለፈ ሌሎችንም አሰባሳቢና ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት። የዚህ ዓይነቱ የፖለቲካ ትግል ደግሞ ከግል ስሜትና ፍላጎት ባለፈ ለዘላቂ የህዝብ ጥቅምና ህልውና ማሰብን ይጠይቃል። ከዚህ ውጭ በብሔር አስተሳሰብና አደረጃጀት ታጥሮ ምናልባት ስልታዊ የትግል አጋርነት ከመፍጠር ባለፈ ስትራቴጂያዊ አንድነትና ዘላቂ ጥቅምን ማረጋገጥ አይቻልም።
ይህን ብሔር ተኮር አስተሳሰብና አደረጃጀት ዛሬ ላይ ካልቀጨነው ጦሱ ለሁላችንም; እንዲሁም ለልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችንን የሚተርፍ ነው። ደግሞም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጅ በዚህ አያያዝ የተፈራው መፈጠሩና መሆኑ አይቀርም።
ስለሆነም የጥፋት ናፋቂዎችን ሟርት ፉርሽ ለማድረግ የኦሮሞና አማራ ለሂቃን ታሪካዊ ኃላፊነት አለባችሁ። ከጀርባችሁ ምን ዓይነት ሴራ እየተጎነጎነ ወይም ምን እየተሠራ እንደሆነ አይታወቅም። ስለሆነም እንደ አብራሃም በግ ወደ መሰዊያው አታምሩ። ወደልቦናችሁ ተመለሱና ህዝቡን ከእርስ በርስ መጠፋፋት ታደጉት? ለዚህም በቋፍ ላይ ያለውን የሁለቱን ታላላቅ ማህበረሰቦች ግንኙነት አስተማማኝ መሠረት አስይዙት።
ፈጣሪ አምላክ/አላህ ይርዳን!