October 24, 2017 06:46

ሐራ ዘተዋሕዶ

• ፓትርያርኩ፣ በማኅበሩ ሥርጭትም ይኹን አገልግሎት ዳግም ዕንቅፋት እንዳይኾኑ አስጠነቀቀ፤
• በአጠቃላይ ጉባኤው ቃለ ጉባኤ፣ በሥርዋጽ የገባው 22ኛ አንቀጽ ሕገ ወጥ በመኾኑ ይታረማል፤
• ሲታዘቡና ሲመክሩ የነበሩ ከ12 በላይ አባቶች፣የተግሣጽ መዓት በማውረድ ልዕልናውን አስከበሩ፤
• በስድብ እና ዘለፋ ሲያሸማቅቁ የነበሩቱ ደግሞ፣ዕድል ተነፍጓቸውና ሐሳብ አጥሯቸው አርፍደዋል፤
• የቀትር በፊቱ ውሎ፣ በጋራ መግለጫው እና የውሳኔ ሐሳቡ ሕገ ወጥ አንቀጽ ላይ ያተኮረው ነበር፤

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን፣ በዓመቱ መባቻ በሦስት ቋንቋዎች ማስተላለፍ የጀመረው የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲታገድ፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ጉባኤ 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ የጋራ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ በጣልቃ እንዲገባ የተደረገው ሕገ ወጥ አንቀጽ እንዲታረም፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወሰነ፡፡
ፓትርያርክ አባ ማትያስ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሰጡትን ትእዛዝ መነሻ ያደረገው ሥርዋጹ፣ በአጠቃላይ ጉባኤው በአጀንዳነት ሳይቀርብና በማንኛውም መልኩ ሳይነሣ በቃለ ጉባኤው 22ኛ አንቀጽ እንዲገባ መደረጉ ሕገ ወጥ ብቻ ሳይኾን፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ለማኅበረ ቅዱሳን ከሰጠው መተዳደርያ ደንብ አንጻርም አግባብነት የሌለው መኾኑን በመተቸት ውድቅ አድርጎታል፡፡
ትላንት፣ ከፓትርያርኩ የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን በኋላ፣ የአጠቃላይ ጉባኤውን የጋራ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ ስለማጽደቅ በኹለተኛነት በተያዘው አጀንዳ የተጀመረው የተጋጋለ ሙግት፤ በዛሬው የቀትር በፊት ውሎ ቀጥሎ የዋለ ሲኾን፤ 14 ያኽል ብፁዓን አባቶች በርእሰ መንበሩና አላግባብ ደጋፊዎቻቸው ላይ የተግሣጽ መዓት አውርደዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ከተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት፣ የዓዲ ግራት ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስንና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ጨምሮ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል እና ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥልጣን ባስከበረው የቀትር በፊቱ ውሎ ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡