አለነ ስብሃት በኬንያ መዲና ናይሮቢ በንግድ ሥራ ከተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ነው። አለነ ወደ ኬንያ በስደት ከመጣ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል።

በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያዊያን በብዛት በሚኖሩባት ኢስሊ አካባቢ በንግድ ሥራ ተሰማርቶ ይገኛል።

በጫማ ንግድ ላይ ለተሰማራው አለነ፤ እስካለፉት ጥቂት ወራት ድረስ ሥራው ጥሩ እንደነበር ይገልጻል። ባለፈው ነሐሴ የተደረገው የኬንያ ምርጫ ግን ፈታኝ ጊዜን ይዞ ብቅ ብሏል።

አለነ ስብሃቱ
አጭር የምስል መግለጫ አለነ ስብሃቱ

“ምርጫው በንግድና የአገልግሎት ዘርፉ ላይ ተጽእኖ አለው። እንደምግብ ያሉ ገበያዎች ሊደሩ ይችላሉ። ከተለመደው ከ50 በመቶ በታች እየሰራን ነው። ሠው ለምግብነት የሚያገለግሉ ነገሮችን ነው መግዛት የሚፈልገው” ሲል ይገልጻል።

ከሁለት ዓመት በፊት መኖሪያውን ናይሮቢ ያደረገው አቡሻ ዘሪሁንም በዚህ ሃሳብ ይስማማል። “ከነሐሴው ምርጫ በፊት እንቅስቃሴው በጣም ጥሩ ነበር። አሁን ሥራ የለም። ከምርጫው ጋር ተያይዞ ሥራ እየቀዘቀዘ ነው” ይላል።

ኬንያዊያን በተወለዱበት አካባቢ ተመልሰው መምረጥን ቀዳሚ ምርጫው ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ በምርጫ ወቅት ሰዎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል።

“መራጮች በየአካባቢያቸው ነው የሚመርጡት። ስለዚህ ናይሮቢ ላይ ብዙ ሰው አይኖርም። መታወቂያ እዚህ የወሰዱ ብቻ ናቸው ከተማ ውስጥ የሚኖሩት” ሲል ችግሩን ይገልጻል።

ነሐሴ 2/2009 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ 54 በመቶ በሆነ ድምጽ ማሸነፋቸውን የሃገሪቱ የምርጫ እና የድንበር ኮሚሽን ይፋ አድርጎ ነበር።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄዱ ሁለት ምርጫዎች ላይ የተሳተፈው አለነ ” ‘ምርጫ’ በሚለው ቃል ብቻ ነው የኢትዮጵያና የኬንያ ምርጫ ተመሳሳይ የሆነው” ይላል። “የኬንያዊያን የዴሞክራሲ ባህል ዳብሯል። ህዝቡ ሲቃወም ምን ድረስ እንደሆነ ያውቃል። መንግስትም መብቶችን ምን ያህል እንደሚጠብቅ አይቻለሁ።”

“ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ፓርቲ በኩል ከሆንክ አትሰጋም። ተቃዋሚ ከሆንክ ግን ስጋቱ ይኖራል። እንደውም በዚህ በኩል ኬንያ የተሻለ ነው” ይላል።

የሁለቱ ሃገራት ምርጫ የተለያየ ነው የሚለው አቡሻም፤ “ኢትዮጵያ እያለሁ ምርጫ ላይ አልተሳተፍኩም። ምርጫ ይባላል እንጂ የተለያዩ አማራጮች ያላቸው ተፎካካሪዎች የሉም። ያለኝ አንድ አማራጭ በመሆኑ ነው ያልመረጥኩት” በማለት ምክንያቱን ያቀርባል።

“የኢትዮጵያ ምርጫ እንደ ኬንያው ቢሆን ምርጫ ሁሌም ይናፍቀኝ ነበር” ይላል። ሰው ቢጎዳም ንግዱም ቢቀዘቅዝም ምርጫ ወቅት ላይ የሚያጋጥም ስለሆነ እዚህ ይሻላል” ሲል ይገልጻል።

አቡሻ ዘሪሁን
አጭር የምስል መግለጫ አቡሻ ዘሪሁን

የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ ያደረገውን ውጤት በመቃወም ፍርድ ቤት የደረሱት ራይላ ኦዲንጋ ተሳክቶላቸው የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ወስኗል።

እ.አ.አ ታህሳስ 2007 በኬንያ ከተደረገው ምርጫ በኋላ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

ይህ ደግሞ ምርጫ በመጣ ቁጥር በዜጎች ላይ ስጋት የሚፈጥር ሆኗል።

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ያደረገው የነሐሴው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ጀምሮ ይሄው ስሜት ሲንጸባረቅ መቆየቱን አቡሻ ያስታውሳል።

“ምርጫው በድጋሚ ይደረግ መባሉም ፍራቻው እንዲቀጥል አድርጓል። ‘ዝርፊያ ይኖር ይሆን?’ የሚል ስጋት አለኝ። ባለፈው ምርጫ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ የሞቱ እና የተዘረፉ መኖራቸውን ነው ሰማሁት። ዘንድሮም እንዳይደገም ነው የምፈራው” ይላል።

“የምንሰማውም የምናየውም በጣም ነው የሚያስፈራው። በዚህ ከቀጠለ ምን እንደሚመጣ አናውቅም” ሲል ሃሳቡን ያስቀምጣል።

ኢስሊ ገበያ
አጭር የምስል መግለጫ ኢስሊ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩባቸው የናይሮቢ አካባቢዎች አንዷ ናት
ኢስሊ ገበያ
አጭር የምስል መግለጫ ኢስሊ ውስጥ ብዙ ኢትዮጵኣዊያን በንግድ ስራ ተሰማርተዋል

አለነ ግን ስጋቱ እምብዛም መሆኑን ይገልጻል። “ያለውን ስጋት ራስን በመጠበቅ ልትከላከለው ትችላለህ። ስደተኛ ስትሆን ሰዓት እላፊ ካልሄድክ፤ እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ ተቋማት የሰጡትን ማስጠንቀቂያ በመከተል ምርጫ ቅስቀሳ ላይ አለመግባት እና አብዛኛውን ጊዜ ከቤት አለመውጣት ነው የሚያስፈልገው። ችግሩ ቤት ድረስ ከመጣ፤ እኛን ብቻ ለይቶ አይደለም የሚመጣው” ሲል ችግሩ የጋራ መሆኑን ያስረዳል።

ከደህንነት ስጋቱ በላይ ለአለነ ስጋት የሆነው የገበያው መቀዛቀዝ ነው። በተለይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅንጅት የሆነው ናሳ በነሐሴ የተደረገው ምርጫ የነበሩት ስህተቶች ካልታረሙ በምርጫው እንደማይሳተፍ በመግለጽ ላይ ይገኛል። ድጋሚ ምርጫው ስህተቶች ተስተካክለው በሌላ ጊዜ ሠሌዳ እንዲካሄድ ጭምር ነው ጥያቄውን እያቀረበ የሚገኘው።

“አሁን ያለውን የንግድ ችግር ቀጣዩ የድጋሚ ምርጫ ይፈታዋል የሚል እምነት አለኝ” ይላል አለነ ስለሐሙሱ ምርጫ ሲናገር። ድጋሚ ምርጫው የማይካሄድ ከሆነና ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ እንደማንኛው ኬንያዊ እኛም ተጎጂ እንሆናለን ይላል። “የምርጫው ጉዳይ እልባት እስኪያጘኝ ድረስ ግን ስጋቱ ይኖራል። ምክንያቱም የንግድ አካባቢያችን ለዝርፊያ ይመቻል፤ ፖሊስም በብዛት የለም። በተጨማሪም እስከ 50 በመቶ ድረስ ተቀዛቅዞ ነበረው ስራ ይበልጥ ሊያሽቆለቁል ይችላል” ሲል ስጋቱን ያስቀምጣል።

ከስጋቱ በተቃራኒ ግን ኬንያ የሚደረገው ምርጫ የተለየ ስሜት እንደሚፈጥርበት አለነ ስብሃት ይገልጻል። “የሠው መብት የሚጠበቅበትን ደረጃ፤ ፍርድ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ መሆናቸውን አይቻለሁ። እኛ ሃገር እንደዚህ ቢሆን ብዬ የተመኘሁበት ሁኔታ ነው ያለው” ይላል።

SOURCE    –  BBC/AMHARIC