October 24, 2017 15:59

አቶ ማሙሸት አማረ

በ25/11/2009 ዓ.ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ የፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የመሰረተባቸው የመኢአድ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያዎቻቸውን ጉዳዩን ለሚመለከተው ችሎት አቅርበዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ትላንት ጥቅምት 13/2010 ዓ.ም የቀረቡት አቶ ማሙሸት አራት ገጽ የክስ መቃወሚያቸውን በጽሁፍ አስገብተዋል፡

አቶ ማሙሸት አማረ የቀረበባቸው ክስ አርበኞች ግንቦት ሰባት በተባለ በሽብርተኝነት በተፈረጀ ድርጅት ‹‹ተመልምለው›› ተሳትፎ በማድረግ የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር እና መነሳሳት ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል እንደሆነ የክስ ማመልከቻው ያሳያል፡፡

ተከሳሹ በክስ መቃወሚያቸው ‹‹ለ25 አመታት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በኢትዮጵያ እንዲያድግና እንዲጎለብት በሰላማዊ መንገድ ስታገል እንደነበር ችሎቱና መላው የሀገራችን ህዝቦች›› እንዲገነዘቡላቸው በማመልከት መቃወሚያቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

አቶ ማሙሸት የቀረበባቸው የሽብረተኝነት ክስ ግልጽ አለመሆኑን በማስታወስ፣ በክሱ ላይ የወንጀል ድርጊቶቹ የት፣ መቼና በምን ሁኔታ እንደተፈጸሙ የማይገልጹ መሆናቸውን ተቃውመዋል፡፡

ሌላው የክስ መቃወሚያቸው ደግሞ አቃቤ ህግ በማስረጃነት ከክሱ ጋር ያያዘውን የአቃቤ ህግ ማስረጃ የሚመለከት ሲሆን፣ ተከሳሹ ‹‹በሰነድ ማስረጃነት የቀረበባቸው የደህንነት ሪፖርት የሰነድ ማስረጃ ሳይሆን አንድ ግለሰብ ‹አውቃቸዋለሁ› ያላቸውን የተለያዩ መረጃዎች ያሰፈረበት የራሱ የደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኛ ቃል ወይም ሪፖርት በመሆኑ ተቀባይነት የለውም›› በማለት ውድቅ እንዲደረግላቸው የጠየቁበት ነው፡፡

በመሆኑም በብቸኝነት በአቃቤ ህግ ማስረጃነት የቀረበው የደህንት መስሪያ ቤት ሪፖርት በማስረጃነት እንዳይያዝ በማመልከት፣ የቀረበባቸው የአቃቤ ህግ ክስ ውድቅ እንዲደረግላቸው አቶ ማሙሸት በክስ መቃወሚያቸው ላይ ጠይቀዋል፡፡

ፍ/ቤቱ በቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ መልስ አለኝ የሚል ከሆነ በጽ/ቤት በኩል እንዲያስገባ በማሳሰብ በቀረበው መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 24/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሽ አቶ ማሙሸት አማረ ከመጋቢት 20/2009 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡