Skip to content

ያቀረባቸው የሕግ ማሻሻያዎች በመንግሥት ውድቅ የተደረጉበት ኢሠማኮ አዲስ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አስታወቀ

25 October 2017

ዳዊት ታዬ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የሠራተኞችን መብት ይጋፋሉ፣ ለኢንዱስትሪ ሰላም እንቅፋት ይፈጥራሉ በማለት ቅሬታ ሲያቀርብባቸው የቆዩ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ሰነድ ያካተታቸው አንቀጾች እንዲስተካከሉ ያቀረባቸው ሐሳቦች ውድቅ መደረጋቸው እንዳሳሰበው ገለጸ፡፡ በጉዳዩ ላይ የኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት አቋሙን የሚያሳውቅ ውሳኔ እንደሚያሳልፍም አስታወቀ፡፡

የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ፣ ሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንደተናሩት በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ከተካተቱ አንቀጾች ውስጥ የሠራተኛውን መብት የሚጋፉና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚፃረሩ ሆነው በማግኘታቸው፣ አዋጁ እንዲህ ያሉትን ጉዳች ሳያሻሽል ቢጸድቅ ሥጋት እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት በረቂቁ ሰነዱ ላይ ኢሠማኮ ያሉትን ልዩነቶችና ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን ሐሳቦች በዝርዝር ቢያቀርቡም፣ ‹‹አብዛኛዎቹ ሐሳቦቻችን ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል፤›› ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ቢፀድቅ በርካታ ችግሮች እንደሚያስከትል በማመን ምን ማድረግ እንደሚገባ ከሁሉም የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች ጋር ሲመክርበት ቆይቷል፡፡ የጉዳዩን አሳሳቢነት በማጤን በተለያዩ መንገዶች ለመንግሥት ያቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ የኢሠማኮ  ጠቅላይ ምክር ቤት በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት (ጥቅምት 15 እና 16 ቀን 2010 ዓ.ም.) በሚያካሂደው ስብሰባ መወሰድ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች እንደሚወሰን አቶ ካሣሁን ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ የሚያስተላልፈውን ውሳኔ ተከትሎ ዕርምጃ እንደሚወሰድ፣ ፕሬዚዳንቱ ገልጸው፣ ዕርምጃው ምን ሊሆን እንደሚችል የሚወስነውም ጠቅላይ ምክር ቤቱ በመሆኑ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደሚወሰን ከወዲሁ መናገር እንደማይችሉ አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም ለሠራተኞች ሥጋት ሆኗል የተባለው አዲሱ ረቂቅ ሕግ ከመጽደቁ በፊት በተለያየ ደረጃ ከሠራተኞች መሪዎች ጋር በተደረገ ስብሰባ ረቂቁ አሁን ባለበት ደረጃ መፅደቅ እንደሌለበት በማመን ኢሠማኮ እስከመጨረሻው መታገል እንደሚኖርበት ስምምነት ተደርጓል፡፡ መንግሥትን ዳግመኛ ማነጋገርና ሕጉ ከመፅደቁ በፊትም እንዲመከርበት የሠራተኞች መሪዎች እንደወሰኑ ገልጸዋል፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳትም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጠኑት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለመገኘቱ እንዳሳዘናቸው አቶ ካሣሁን ጠቁመዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንደ ማሻሻያና እንደ አዲስ የቀረቡት አንቀጾች፣ በኢንዱስትሪ ሰላምና በሠራተኞች ላይ የሚያሳርፉት ጫና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በመገንዘባቸው ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው፣ በጥንቃቄ እንዲታይ የተደረጉ ጥረቶች እንዳልተሳኩ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ ለ33 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የሕጉን አሳሳቢነት የሚያስረዳና በረቂቁ ላይ ያለንን ልዩነት እስከነማብራሪያው በደብዳቤ ጭምር አቅርበናል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም ሆኖ እስካሁን ድረስ አንድ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ብቻ ለኢሠማኮ ምላሽ እንደሰጠና ረቂቅ ሕጉን እንደሚደግፍ አስተያየቱን እንደሰጠ ገልጸዋል፡፡

አቶ ካሳሁን በመግለጫቸው ወቅት፣ በረቂቁ ሰነዱ ውስጥ ኢሠማኮ ሊካተቱና ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያላቸው ከ20 በላይ በዝርዝር ካቀረባቸው ነጥቦችን ውስጥ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሀ)፣ ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ስለማቋረጥ በሚለው አንቀጽ ሥር የሰፈረው ይገኝበታል፡፡ በረቂቅ ሕጉ መሠረት ሠራተኛው ከኅብረት ስምምነትና በሥራ ደንብ ወይም በሥራ ውል ከተዘረዘሩት ውጭ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በተሰጠው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጠቅላላው ለሁለት ጊዜ ወይም በጠቅላላው በስድስት ወር ውስጥ ለአምስት ጊዜ የሥራ ሰዓት አለማክበር፣ በአሠሪው በኩል ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ለማቋረጥ እንደሚያበቃ ይጠቅሳል፡፡

ነባሩ አዋጅ ግን በመደዳው አምስቱን ቀን መቅረት ወይም በአንድ ወር ውስጥ በጠቅላው ለአሥር ቀናት ያህል መቅረት፣ ወይም በአንድ ዓመት በጠቅላላ ለ30 ቀናት ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ መቅረት የሥራ ውል እንዲቋረጥ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ኢሠማኮ ሊደረግ ይገባዋል በማለት ያቀረበው ‹‹ሥራ ላይ ያለው አዋጅ የሥራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ከማቋረጥ በመለስ አንድ ወይም ሁለት ቀን ያረፈደ ሠራተኛ ላይ ተመጣጣኝ የዲሲፒሊን ዕርምጃ መውሰድን አልከለከለም፤›› ያሉት አቶ ካሣሁን፣ ሆኖም ሠራተኞች ከሥራ ለማርፈድ የሚያስገድዷቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች እንዲሁም ሌሎች ተደራራቢ ኃላፊነቶች ሊታዩላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የተመቻቸ የትራንስፖርት አገልግሎት በሌለበት ሥርዓት ውስጥ እንዲህ ያለ መብት ነክ አንቀጽ ማስቀመጥ ተገቢ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ገንዘቡንም ከፍሎ በወቅቱ ወደ ሥራ ገበታው ለመጓዝ ሠራተኛው የሚቸገር በመሆኑ፣ ትራንስፖርት ቢያገኝ እንኳ መሠረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ምክንያት እየተስፋፋ የመጣው የትራፊክ መጨናነቅ፣ ሠራተኞች በሥራ ቦታቸው አቅራቢያ መኖሪያ እንዲመቻችላቸው ካልተደረገ በቀር፣ በወር ከሁለት ቀን በላይ አያረፍዱም ማለት እንደማይቻል በመግለጽ  የረቂቅ ሕጉ አንቀጽ መሻሻል እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

የመንግሥት መኪና የመደበላቸው ኃላፊዎች ወይም የግል መኪና ያላቸው ሰዎች በወር ሁለት ቀን አያረፍዱም ብሎ መደምደም ተጨባጭ ሁኔታን መካድ በመሆኑ፣ አገሪቱ ያለችበት የዕድገት ሁኔታና ከሠራተኞች አቅም በላይ የሆኑ አስገዳጅ  ምክንያቶች በመኖራቸው፣ በቂ ምክንያት የተባሉት ወይም በቂ ምክንያት ያልሆኑት ተዘርዝረው ባለመቀመጣቸው ምክንያት መለየት አስቸጋሪ እንደሆነና አንቀጹ በዚህ መልክ መቀመጡ እንደማይደገፍ አብራርተዋል፡፡

ኢሠማኮ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ቅሬታውን የገለጸበት ሌላው አንቀጽ የሠራተኛ ቅጥር የሙከራ ጊዜን የተመለከተው ነው፡፡ በነባሪ ሕግ የሠራተኛ ቅጥር የሙከራ ጊዜ የ45 ቀናት ዕድሜ እንዳለው ያስታወሱት አቶ ካሣሁን፣ አሁን ወደ 90 ቀናት ወይም ወደ ሦስት ወራት መራዘሙ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡

ለሥራ የሚፈለገውን ዕውቀትና ክህሎት ለይቶ ለቅጥር እንደ መሥፈርት አስቀድሞ ማስቀመጥ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ የሚያስችል የሥራ ላይ ሥልጠና የመስጠት ኃላፊነትን መወጣት ሲገባ፣ የሙከራ ጊዜውን አለአግባብ ወደ 90 ቀናት ማራዘም ተገቢ አይደለም በማለት ኢሠማኮ አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡

የሙከራ ጊዜው ወደ 90 ቀናት መጨመሩ የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና ሥጋት ላይ የሚጥልም በመሆኑ የሙከራ ጊዜው አሁን እየተሠራበት ባለው የ45 ቀናት ጊዜ ገደብ ውስጥ ሳይነካ መቀጠል ይገባዋል በማት ኢሠማኮ ቢከራከርም፣ ሐሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

‹‹ረቂቅ አዋጁ የመንግሥት ሠራተኞችን የማይመለከት ሆኖ መቅረቡን ልንቀበለው አንችልም፤›› ያሉት አቶ ካሣሁን፣ የመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀት መብት እንዲከበርና የአዋጁ ተፈጻሚነትም እነሱንም እንዲያካትት ያቀረብነው ሐሳብ  ውድቅ በመደረጉ አልተሳካልንም ብለዋል፡፡ በአዋጁ የሕግ ተፈጻሚነት ወሰን ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀት መብት እንዳይኖራቸው ተደርጓል ያሉት አቶ ካሣሁን፣ የመንግሥት ሠራተኞች በዚህ ረቂቅ አዋጅም ሆነ የመንግሥት ሠራተኞች በመንግሥት አስተዳደር አዋጅ ውስጥ እንዲደራጁ አለመፈቀዱ ስህተት ነው ብለዋል፡፡ በሌሎች አገሮች የመንግሥት ሠራተኞች እንዲደራጁ ይፈቀዳል በማለት በአፍሪካ  ግን የመንግሥት ሠራተኞች እንዳይደራጁ የሚከለክሉት ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲና ኤርትራ ናቸው ብለዋል፡፡ አቶ ካሣሁን እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች የመንግሥት ሠራተኞችን ብቻም ሳይሆን፣ የፖሊስ ኃይል አባላትንም ሳይቀር በሠራተኛ ማኅበራት ውስጥ እንደሚደራጁ በመጠቀስ፣ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኞች እንዳይደራጁ መከልከሉ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ነው ብለዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የመንግሥት ሠራተኞች መደራጀት እንደሚችሉ ቢያሰፍርም እስካሁን ድረስ ሕግ ይወጣል በማለት የመንግሥት ሠራተኞች ሳይደራጁ በመቆየታቸው ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት የመንግሥት ሠራተኞችን ባለማደራጀት በዓለም የሥራ ድርጅት እየታወቀችበት የመጣችበት የመብት ክልከላ መሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡  ‹‹የመንግሥት ሠራተኞችን አይመለከትም የተባለው ነገር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጋፋ ነው፡፡ ይህ መሆን የለበትም ብለን ነበር፤›› በማለት አቶ ካሣሁን የኢሠማኮን ቅሬታዎች አንጸባርቀዋል፡፡

እንዲሻሻል ጠይቀን ተቀባይነት አላገኘም በማለት የጠቀሱት ሌላው አንቀጽ የጉዳት ካሳን የተመለከተው ነው፡፡ አንድ ሠራተኛ ቢሞት ደመወዙ በአምስት ወራት ተባዝቶ ለቤተሰቡ ይሰጣል የሚለው ነው፡፡ እየቀነሰ በመጣው የገንዘብ የመግዛት አቅም፣ የሠራተኛውም የደመወዝ መጠን ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተደማምሮ ከአቅም በላይ እየሆነ በመጣበት ወቅት ሠራተኛው ሲሞት ለቤተሰቡ የሚሰጠው ካሳ በአምስት እጅ ብቻ መታሰቡ እጅግ አነስተኛ ስለመሆነ ኢሠማኮ  አልተቀበለውም ተብሏል፡፡

አቶ ካሣሁን ይህንን ጉዳይ ሲያስረዱም በምሳሌነት የጠቀሱት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚከፍሉትን የደመወዝ መጠን ነው፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሠራተኞች የሚከፈለው ትልቁ ክፍያ 1,100 ብር ነው፡፡ ስለዚህ 1,100 ብር በአምስት ተባዝቶ ሲሰጥ ቤተሰብ የሚደርሰው 5,500 ብር በመሆኑ፣ ብዙ ቤተሰብ ለሚያስተዳድር ሠራተኛ ይህ ገንዘብ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ፣ ይህ አንቀጽ እንዲህ መቀጠል የለበትም፣ ደመወዙ በአሥር ተባዝቶ መሰጠት አለበት ብለናል፡፡ ይህንን ሐሳባችን ግን አንቀበልም ተብለናል፡፡››

በኢሠማኮ ጥያቄ ቀርቦበት ሊስተካከል ያልቻው የሠራተኛው ጥያቄ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲቀመጥ የሚጠይቀው ነው፡፡ ባለው የኑሮ ውድነትና ሠራተኛው የሚከፈለው ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት፣ ኑሮን ያገናዘበ ዝቅተኛው የደመወዝ ዕርከን በሕግ መቀመጥ እንዳለበት ያቀረበው ሐሳብ ከመንግሥት ይሁንታ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ‹‹1,000 ብር በሚከፈልበት ሥራ የሚተዳደር ሠራተኛ ያለው ድሃ ነው፤›› ያሉት አቶ ካሣሁን፣ ኑሮን ያገናዘበና የሥራ ዘርፉን ግምት ውስጥ ያስገባ ዝቅተኛው የደመወዝ መጠን በሕግ መቀመጥ እንዳለበት ኢሠማኮ ያቀረበው ሐሳብ በመንግሥት  አልተደገፈም ብለዋል፡፡

በወሊድ ወቅት ለባሎች የአምስት ቀናት ፈቃድ እንዲሰጥ በመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ውስጥ ቢካተትም፣ ይህ ሕግ ወጥ ይሁን የሚል ጥያቄ በኢሠማኮ ቀርቦም ሊታይ አልቻለም ተብሏል፡፡ በሥራ ሒደት መካከል ለሠራተኞች የሚሰጥ ዕረፍት ይኑር የሚል ሐሳብ በማቅረብ በሕጉ እንዲካተት የተደረገው ሙከራም እንዳልተሳካ ያስረዱት አቶ ካሣሁን፣ አንድ ሠራተኛ ሳይንቀሳቀስ ስምንት ሰዓት ሙሉ እየሠራ እንዲቆይ ማድረግ ከባድ በመሆኑ በሥራ መካከል ዕረፍት ይሰጠው፣ በሕግ የተደገፈ የ15 ወይም የ20 ደቂቃ የዕረፍት ጊዜ ይኑረው የሚለው ሐሳብም እንደሌሎቹ ሁሉ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

በረቂቅ ሕጉ ውስጥ ሊስተካከል ይገባዋል ተብሎ በኢሠማኮ የቀረበው ሌላው አሳሳቢ አንቀጽ፣ ‹‹አንድ ሠራተኛ ሥራ ለመልቀቅ ሲፈልግ ከ90 ቀናት በፊት ማሳወቅ ይኖርበታል፤›› የሚለው ነው፡፡ ሠራተኛው ሥራ ለመልቀቅ የዚህን ያህል ጊዜ መጠበቅ የለበትም የሚል አቋም ያለው ኢሠማኮ፣ እስካሁን ሲሠራበት የቆየው የ30 ቀናት ቆይታ ሳይነካ እንዲቆይ ኮንፌደሬሽኑ ጠይቋል፡፡

ኢሠማኮ በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ሌሎችም በርካታ የማሻሻያ ሐሳቦችን ያቀረበው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በማስመልከት እንደሆነ አስታውቆ፣ መሻሻል አለባቸው ያላቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በማካተት ጉዳዩ በመንግሥት በኩል ትኩረት እንዲሰጠውና ከመፅደቁ በፊትም በጥንቃቄ እንዲታይ አሳስቧል፡፡

ሪፖርተር

Share this:

  • Click to share on Telegram (Opens in new window) Telegram
  • Click to share on WhatsApp (Opens in new window) WhatsApp
  • Tweet

Like this:

Like Loading...

Your true media source

All rights reserved

%d