October 25, 2017 05:20

ሐራ ዘተዋሕዶ

.በውጭ ካሉ አባቶች ጋራ ለተጀመረው ዕርቀ ሰላም ዓለም አቀፍ ኮሚቴ ተቋቋመ

.ምሥረታውን አስተዋውቋል፤ ዓላማውንና ዕቅዱን ለምልአተ ጉባኤው አብራርቷል

.ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ተነጋጋሪ ልኡካን መመደብ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል

.በጥቅምት መጨረሻ በኮለምበስ ኦሃዮ ከሚደረገው የውጩ ሲኖዶስ ጋራ ይወያያል

.ልዩነቱ ወደ ቀኖናዊነት ሳይከፋ፣ ጥረቱን በቅንነት እንደግፍ፤ ዕድሉን እንጠቀም፤

 

በውጭ ከሚገኙ አባቶች ጋራ ተጀምሮ የተስተጓጎለውን የዕርቀ ሰላም ሒደት በተሻለ አያያዝ ለማስቀጠል ዓለም አቀፍ አስታራቂ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲኾን፤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዓላማውንና ዕቅዱን አቅርቦ ይኹንታ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡

በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ አገልጋዮችና ታዋቂ ምእመናን በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡበት ዓለም አቀፍ አስታራቂ ኮሚቴው፣ ዐሥር አባላትን የያዘ ሲኾን፤ ወደ ኢትዮጵያ በመጡት ሦስት ልኡካኑ አማካይነት ዓላማውንና ዕቅዱን ለምልአተ ጉባኤው በማስረዳት ለወጠነው የዕርቀ ሰላም ጥረት ይኹንታ እንዳገኘ ተገልጿል፡፡

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የአፍሪቃ ቢሮ ሓላፊ የኾኑት ዶ/ር ንጉሡ ለገሰ(ስዊዘርላንድ – ጄኔቭ)፣ መልአከ ሕይወት ሐረገ ወይን(ከካናዳ – ቶሮንቶ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን) እና ቀሲስ ዶክተር መዝገቡ(ከቤልጅየም – ብራስልስ)፥ ትላንት፣ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ፣ በምልአተ ጉባኤው ፊት ቀርበው ተወያይተዋል፡፡

ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ታሪካዊት በኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ የተፈጠረውን አስተዳደራዊ ልዩነት ለመፍታት የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሒደት በየጊዜው ሲስተጓጎል መቆየቱን ልኡካኑ አውስተው፤ በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች አኹን ካለበት ሳይከፋ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ልዩነቱ አስተዳደራዊ መልክ ይዞ ቢከሠትም፣ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሒደት በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱና መዋቅራዊ አንድነቱ ባለመመለሱ ወደ ቀኖናዊ ልዩነት ሊሰፋና ሊከፋ የሚችልባቸው ዕድሎች ከስጋት(ምልክት) በላይ ኾነው እንደሚታዩ ልኡካኑ አስረድተዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የውጩ ሲኖዶስ ብፁዓን አባቶች በዕድሜ እየገፉ መኾናቸውና ልዩነቱን ወደ ቀኖናዊነት የሚያሰፉና ምእመናንን የሚፈትኑ ውስጣዊ ኹኔታዎች በግላጭ እየተስተዋሉ መምጣታቸው፣ የዕርቀ ሰላም ሒደቱን በተሻሻለ አያያዝ በአፋጣኝ በማስቀጠል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማረጋገጥ እንድንነሣሣ አስገድዶናል፤ ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ አስታራቂ ኮሚቴውን፣ በቅንነትና በበጎ ፈቃድ በማቋቋም ስለአካሔዱ ሲመካከሩበት እንደቆዩና በውጩ ሲኖዶስም ጠንካራ ፍላጎት ያላቸው አባቶች እንዳሉ መረዳታቸው እንዳበረታታቸው ጠቅሰዋል፡፡

የዕርቀ ሰላም ሐሳብን በማመንጨትና በማራመድ ከሚጠቀሱት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጀምሮ የምልአተ ጉባኤው አባላት፣ የልኡካን ቡድኑን ጥረት በመደገፍ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባሉ ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቁመዋል፡፡ ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም መፍትሔ አለመገኘቱን የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ኮሚቴው በሚያስቀመጠው አካሔድ መሠረት ጉዳዩ እንደሚታይ ጠቁመው፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለዓለም አቀፍ አስታራቂ ኮሚቴው ጥረት ይኹንታ በመስጠት አስፈላጊውን እገዛና ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

አስታራቂ ኮሚቴው፣ ከጥቅምት መድኃኔዓለም ክብረ በዓል ጋራ ተያይዞ በኮለምበስ ኦሃዮ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንደሚካሔድ በሚጠበቀው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሚመራው የውጩ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ተመሳሳይ ገለጻዎች እንደሚያደርግና በሚያገኘው ግብአት ላይ ተመሥርቶ ቀጣይ የዕርቀ ሰላም አካሔዶቹን እንደሚተልም ተጠቁሟል፡፡

ኹኔታውን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩ ታዛቢዎች፣ የዕርቀ ሰላም ንግግሩ የሚመራበትን የአሐቲ ቤተ ክርስቲያን አስተሳሰብና መርሖ ከወቅታዊው ዓለማዊና ሀገራዊ ኹኔታዎች ጋራ አገናዝቦ ከመቅረፅ ጀምሮ፣ በኹለቱም ወገኖች በኩል፤ ለጉዳዩ ቅርበትና መረጃው ያላቸው፣ ከአሉታዊ ተጽዕኖ የተጠበቁ ጠንካራና ቀና ተነጋጋሪዎች ሊመደቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡