October 25, 2017 17:42

ረቡዕ፣ ጥቅምት ፲ ፭ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት
“ትንንሽ ጎጆዎች አንድ ትልቅ ጎጆ አይሆኑም!”

የሻለቃ ዳዊት ወልደጊወርጊስ እና የዶክተር ጌታቸው በጋሻው

የሻለቃ ዳዊት ወልደጊወርጊስ እና የዶክተር ጌታቸው በጋሻው

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊወርጊስና ዶክተር ጌታቸው በጋሻው፤ ድርጅቶችን ሰባስበው፤ “አገር ለማዳን!” አንድ ማዕከል ለመፍጥርና ይሄንን ዓላማቸውን ለማሳካት በመሯሯጥ ላይ ናቸው። ይህ የተከበረና ይበል የሚያሰኝ ዓላማ ነው። ዓላማ ሲጠናቀር ለግብ እንዲበቃ፤ ጊዜያዊነትን፣ ሀቀኝነትን፣ ቆራጥነትን እና አፍላቂነትን ይጠይቃል። የታቀደ ሁሉ ይሳካል፤ የተወለደ ሁሉ ይባረካል የሚል የለም። ምኞቱ ግን በሁላችንም ዘንድ አለ። ይህ የሁለቱ ታጋዮች ጥረት፤ ከሀገር ማዳን ፍላጎት የመነጨ ነው ወይንስ የራሳቸውን የግል የፖለቲካ ዓላማቸው ማሳኪያ ነው? የሚለውን እኔ በቀጥታ መመለስ ባልችልም፤ እንደሌሎቻችሁ ሁሉ የራሴ ግንዛቤ ይኖረኛል። ለሁሉም ግለሰቦችን በመተው፤ ሂደቱንና ግቡን በሚመለከት የሚከተለውን አስፍሬያለሁ።


የተለያዩ ራሳቸውን የቻሉና የተሟሉ ትንንሽ ጎጆዎች፤ በያሉበት ተቀምጠው፤ አንድ ትልቅ ጎጆ አይሆኑም። የሕልውናቸው ሁለተና ይዘት፤ ለትንሽ ጎጆነት ብቻ የሚሆን ነው። ትልቅ አምድ፣ ረጃጅም የግድግዳ መቆሚያዎች፣ የጣራ ተዋረዶችና የትልቅ ጎጆ ይዘት የላቸውም። እናም በምንም መንገድ ስለተጠጋጉ ብቻ አንድ ትልቅ ጎጆ አይሆኑም። ይህ ተፈጥሯዊ አይደረጌነት ነው።

ሻለቃ ዳዊት ወልደጊወርጊስና ዶክተር ጌታቸው በጋሻው፤ በኢትዮጵያዊያን የትግል ታሪክ ውስጥ፤ አዲሶች አይደሉም። በደርግም ሆነ በትግሬዎች መንግሥት ዘመን፤ በደርግ ዘመን በመንግሥቱ መዋቅር፤ በትግሬዎች መንግሥት ዘመን ደግሞ፤ በትግሉ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የነበሩና ያሉ ናቸው። እናም እኒህ ግለሰቦች የሚያደርጉት ተግባር፤ የእውቀት ማነስ ወይንም የልምድ እጥረት ያለበት አይደለም። “የሚያደርጉትን ያውቃሉ!” ብሎ ማመን ይቻላል። ወደ ማስተባበር ሩጫቸው ልመለስ።

እኒህ ሁለቱ ግለሰቦች፤ ቀደም ብዬ በግለሰብ ደረጃ ባውቃቸውም፤ ላሁኑ ትንተናዬ፤ በቅርቡ የዐማራውን የተለያዩ ድርጅቶች ወደ አንድ ለማምጣት ሲሯሯጡ ነበር የተገናኘነው። ጥረታቸውን በሚመለከት፤ ዓላማው የተቀደስ እንደሆነ፤ አካሄዱ ግን ትክክል እንዳልሆነ አስረዳኋቸው። በሂደቱ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፤ ቶሎ ብለው፤ የዐማራ ተወካይ አገኘን ብለው፤ ወደ አዘጋጁት አገር አቀፍ ንቅናቄ ለመሮጥ መጣደፋቸውን ነው። በግልጽ፤ “ተው ይሄ አያስኬድም!” አልኳቸው። ሂደቱ ምን መከተል እንዳለበት ገለጽኩላቸው። የነሱ እምነት፤ “ዐማራው ብቻውን ወደ ኋላ ከሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ተገንጥሎ እንዳይቀር፤ በዐማራነታችን ማድረግ ያለብንን እያደረግን ነው!” “ሁኔታው አሁን ገፋፍቶናል። በራሳችን ፈቃድ ነው የምንንቀሳቀሰው።” የሚል ነው። ይህ እንግዲህ፤ ከነሱ ፍላጎት ውጪ፤ የዐማራውን ፍላጎት እያስቀደሙ ነው፤ ማለት ነው። ይሄን ገልጸውልኛል።

በተራዬ፤ እጆቻችሁን ከዚህ አንሱ። በዐማራነት ከተደራጁት ውስጥ ገብታችሁ፤ የዐማራ ድርጅቶችን ወደ አንድ ለማምጣት መጣር ተገቢ ነው። በኢትዮጵያዊነታችሁ በፈጠራችሁት የአገር አቀፍ እንቅስቃሴ፤ በኃላፊነት ቦታ ተቀምጣችሁ፤ (ዶክተር ጌታቸው በጋሻው፤ በአገር አቀፍ ንቅናቄው በኃላፊነት ቦታ እንደተቀመጠ ነግሮኛል) እዚህ የምታደርጉት ትክክል አይደለም አልኳቸው።

ከኔ በኩል ያቀረብኩት፤ ዐማራው አሁን ራሱን ወደ አንድ እያሰባሰበ ያለበት ሁኔታ ላይ ነው። አሁን ዐማራውን እንደ አንድ ሕዝብ የሚወክል አንድ የፖለቲካ ድርጅት የለም። ሂደቱ ግን እየፈጠነ እየመጣ ነው። ዐማራው በያዛችሁት መንገድ መቀጠል አይችልም። ምክንያቱም፤ እኒህ የሰበሰባችኋቸው ድርጅቶች በመካከላቸው ከዐማራነት ውጪ፤ ምንድን የጋራ የሆነ ነገር አላቸው? አደረጃጀታቸውስ ይፈቅድላቸዋል ወይ? የራዕይ አንድነት አላቸው ወይ? የፖለቲካ ግንዛቤያቸው ተመሳሳይ ነው ወይ? እያንዳንዳቸው የፖለቲካ መርኀግብር አላቸው ወይ? ይሄንስ ራሳቸው በመካከላቸው ተሰባስበው ሊፈታተሹና ሊቀራረቡ አይገባም ወይ? እናንተ ከውጪ ሆናችሁ እንዴት ነው ልታሰባስቡ የምትችሉት? ምንስ አመኔታና የመሪነት ወይም የሰብሳቢነት ግዴታ አላችሁ? ብዬ ለጠየቅሁት አጥጋቢ መልስ አላገኘሁም።

ነገሩ እንዲህ ነው። የኒህ ሁለት ታጋዮች ፍላጎት፤ አንድ የሙያ ማህበርን፣ ጥቂት የሲቪክ ድርጅቶችንና የፖለቲካ ድርጅቶችን በአንድ በመጨፍለቅ፤ ተወካይ ልከው፤ የአገር አቀፉን ድርጅት እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ነው። እንዴት ሆኖ? እኒህ ድርጅቶች፤ አደረጃጀታቸው፣ ዓላማቸው፣ ራዕያቸው፣ መርኀግብራቸው – ያውም እያንዳንዳቸው መርኀግብር ካላቸው፣ የማይገናኙ አካላት፤ በምን መንገድ አንድ ስብስብ ሊሆኑ ይችላሉ? ዐማራ ሆኖ መገኘት ብቻ በቂ ነው ወይ? ከኒህ ውጪ ሌሎች ጎጉምቱና ጎላ ያሉ ዐማራዎችና የዐማራ ድርጅቶች የሉም ወይ?

ለዚህ ሁሉ መልሱ የሚጀምረው፤ የዐማራውን ትግል ከሌሎች ጋር ለማቀናጀትና ለመምራት ከሚደረገው ሩጫ በፊት፤ የዐማራው ትግል ምንድን ነው? የሚለውን በመመልከት ነው። የዐማራው ትግል የሕልውና ትግል ነው። ሕልውና ደግሞ የተወሰነ የመሬት ክልልን ማበጀት ማለት አይደለም። ሕልውና፤ “በትግሬዎች መንግሥት ሥር ሆኜ፤ ይሄን ያክል ድርሻ ይወሰንልኝ!” የሚል አይደለም። ሕልውና “ይሄ ቀረብኝ!” “ያ አነሰኝ!” የሚባልበት ትግል አይደለም። ዐማራው፤ “አሁን እንድጠፋ የዘር ማጽዳት ዘመቻ እየተደረገብኝ ስለሆነ፤ ራሴን አደራጅቼ መከላከል አለብኝ!” ነው ያለው። ይህ የማንንም ፈቃድ የሚያስጠይቅ ጉዳይ አይደለም። ዐማራው መኖር አለበት። ዐማራው፤ “በኢትዮጵያ ተበድያለሁና ይሄ ይደረግልኝ!” ወይንም፤ “ያ ይደረግልኝ!” የሚል ጥያቄ አላቀረበም።

ዐማራው የያዘው ትግል ከኢትዮጵያ ወይንም ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይደለም። ምንም እንኳን በመላ ኢትዮጵያ ቢዘመትበትም፤ ዐማራው ትግሉ ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይደለም። የያዘው ትግል፤ በኢትዮጵያ ተበድያለሁና ከኢትዮጵያ ነፃ ልውጣ የሚል አይደለም። ዐማራው የሚታገለው፤ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል አይደለም። በመንግሥትም ደረጃ፤ የዐማራው ትግል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አይደለም፤ አሁን በሀገራችን የኢትዮጵያ መንግሥት የለምና! አሁን በኢትዮጵያ ያለው የትግሬዎች መንግሥት ነው። የዐማራው ትግል፤ ሕልውናውን ሊያጠፋ ከተነሳው፤ ከዚሁ የትግሬዎች መንግሥት ጋር ነው።

በመሠረቱ ዐማራው የያዘው ትግል፤ በማንነት ላይ የተመሠረተ በደልን መቃወም ነው። ዐማራ ሀገሩ ኢትዮጵያ ናት። የዐማራው ዳር ደንበር፤ መላ የኢትዮጵያ ዳር ደንበር ነው። አሁን እኔ ይሄን በምጽፍበት ሰዓት እንኳን፤ የትግሬዎች መንግሥት ቆርሶ ለሱዳን የሠጠውን የጉቦ ዳር መሬት፤ አላስወስድም ብሎ፤ ያገሩን ዳር ደንበር በመጠበቅ፤ በሁለት አጥፊ መንግሥታት፤ በትግሬዎቹና በሱዳን መንግሥታት፤ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው። ይህ በማንነት ላይ የተመሠረተ በደል፤ አኙዋኩን፣ ኦጋዴኑን፣ ኦሮሞውን፣ አፋሩን ሁሉ የሚነካ ጉዳይ ነው። በኦሮሞነቱ የተበደለ ኦሮሞ፤ ከዐማራው ጋር ሆኖ፤ በማንነት ላይ የተመሠረተን በደል አብሮ መቃወም አለበት እላለሁ።

ዐማራው ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ቢታገል ለደስታው ልክ የለውም። የዚህ አብሮነት መሠረቱ ደግሞ፤ ሌሎች አብረውትና አብሯቸው የሚታገሉት፤ የጋራ የሆነ ኢትዮጵያዊነት በመካከላቸው ሲገኝ ነው። ይህ የጋራ ኢትዮጵያዊነት በሌለበት ቦታ፤ የጋራ ትግል ማካሄድ አይቻልም። በርግጥ ሁለት መንገዶች፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይንስ በወገን ተለያቶ ተደራጅቶ መታገል የሚሉት እስካሁን መንታ መንገድ ሆነው ስላስቸገሩ፤ በሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ፤ አተራማሽ ሀቅ ሆነዋል። ነገር ግን፤ የወደፊቷን የሀገራችን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀቅ ለመለወጥና ትክክለኛ አስተዳደር መሥርቶ ወደፊት አብሮ ለመቀጠል፤ የግድ አፍረጥርጠን መነጋገር የሉብን ጉዳዮች አሉ። የትግሬዎች መንግሥት መውደቅ አለበት። ይሄን በጋራ መድረግ አለብን። አሁን ሀገር አቀፍ ድርጅቶች አሉ። በወገንነት ተደራጅተው የሚታገሉ አሉ። ዋናው አሳሳቢ ጉዳይ፤ በተናጠል የምናደርገው ትግል፤ እያንዳንዳችንን እያስበላ፤ የትግሬዎቹን መንግሥት ዕድሜ የሚያስረዝም ስለሆነ፤ በአንድነት ትግሉን ለማቀናጀት፤ አድበስብሶ እኔ ባልኩት መንገድ እንሂድ የሚለውን በመከተል ሳይሆን፤ ያለውን ሀቅ አገናዝቦ፤ በግልጽ ተነጋግሮ፤ መፍትሔ ስናገኝ ብቻ ነው።

መጀመሪያ፤ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመመልከት፤ ዛሬ የምንስማማበት ጉዳይ መኖር አለበት። ዛሬ በመካከላችን ምንም ዓይነት የጋራ የሆነ ጉዳይ ሳይኖር፤ ስለነገ ማሰቡ የዋኅነት ነው። የትግሬዎቹን መንግሥት መጥላት ብቻውን መሰባሰቢያ አይሆንም። የትግሬዎቹን መንግሥት አልሸባብ ይጠላል። አልሸባብ ግን ከትግሬዎቹ መንግሥት የከፋ ጠባብ ድርጅት ነው። የትግሬዎቹን መንግሥት ኢሳያስና የሱው ጥፍጥፍ ሸዓቢያ ይጠሉታል። ኢሳያስና ሸዓቢያ ግን የኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ጠላትነታቸው ከትግሬዎቹ መንግሥት ጋር እኩል ነው። የትግሬዎቹን መንግሥት መንግሥቱ ኃይለማርያም ይጠላል። መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን ሰው በላ አረመኔና ኢትዮጵያን ለዚህ ያበቃ ደርጋማ ነው። በመካከላችን አንድ የሚያደርገን ነገር ሳይኖር፤ ስለ አንድነት ትግል መነጋገር አይቻልም። አንድነት ካለን፤

፩ኛ.     መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ እያንዳንዳችን ማመን አለብን። ይሄን ያልተቀበለ፤ ለነገዋ ኢትዮጵያ እታገላለሁ ሊል አይችልም።

፪ኛ.     የኢትዮጵያን ዳር ደንበር የኔ ነው ብሎ መቀበልና፤ ለዚህ መከበር የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል መነሳት አለብን። ይህ የኢትዮጵያዊነት ግዴታ ነው።

፫ኛ.     የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሰንደቅ ዓላማ የኔ ነውና ከዚህ ሌላ የለኝም ማለት አለብን። ኢትዮጵያዊነትን ከዓርማው ለይቶ ማስቀመጥ አይቻልም።

፬ኛ.     እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊትና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፤ በመላ ሀገሪቱ የመዘዋወር፣ የመስፈር፣ ሀብት የማስፈር፣ በአካባቢው የፖለቲካ ሂደት የመሳተፍ፣ መብት እንዳላቸውና እንዲከበር ማመን።

፭ኛ.    እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ፤ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል የግል መብት እንዳለው መቀበል። በዚህ ሃይማኖቱ ግን ተደራጅቶ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት መሳተፍ፤ ሌሎችን የሚያገልና አንድን ሃይማኖት በሌላው ላይ ለመጫን የሚደረግ ስለሆነ፤ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም፤ የሃይማኖት ድርጅቶችም በመንግሥት መዋቅር ቦታ አይኖራቸውም።

፮ኛ.     እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት ግለሰብ፤ የፈለገውን ርዕዩተ ዓለም ማስተናገድ፣ የግል መብቷ ነው። በዚህም ከመሰል አጋሯ ጋር ተደራጅታ፤ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት በግል ውሳኔዋ የመሳተፍ መብት እንዳላት መቀበል።

፯ኛ.     ከፋም በጄም፤ የሀገሪቱን ታሪክ መቀበልና፤ በመንግሥት ደረጃና በማንኛውም የኅብረተሰቡ ስብስቦች በሩቅም ሆነ በቅርብ የተፈጸሙ በደሎችን፤ ትክክለኛና ሀገር አድን በሆነ መንገድ መፍትሔ ለማስገኘት መጣር።

፰ኛ.    እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊና እያንዳንዷን ኢትዮጵያዊት፤ በእኩልነት ተቀብሎ አንድ ነን በሚል እምነት፤ ሀገር ለመገንባት አብሮ መነሳት።

ለነኚህ ጉዳዮች፤ ከትግሬዎቹ መንግሥት በስተቀር፤ ማንኛችንም ፈቃደኞች ሆነን የምንገኝ ሁሉ፤ አብረን ለመሥራት መነሳት አለብን። ይህ የሚሆነው ደግሞ፤ ሁሉም ያለውን ጥሎ ወደዚህ ይዝመት በሚል አምታች ሂደት ሳይሆን፤ አሁን “ይህን መሠረታዊ መሰባሰቢያ ነጥቦች መቀበሉ የመጀመሪያው ነው!” ብሎ በማመን፤ መቀራረቡን መጀመር ነው።
ትንንሽ ጎጆዎች ወዳልኩት ልመለስ። የሀገሪቱ ታሪክ የኔ ታሪክ አይደለም። የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓለማ የኔ ሰንደቅ ዓላማ አይደለም። በራሴ ክልል ሌላ ማንም እንዲገባ አልፈቅድም። በራሴ ክልል የፖለቲካ ሂደት፤ ሌሎች ሊሳተፉ አይችሉም፣ ኢትዮጵያ ብትፈራርስ ለኔ ጉዳዬ አይደለም! የሚል አንድ ድርጅት፤ በኢትዮጵያዊነት ሊካተት አይችልም። ቢጠየቅም አይጥመውም። እናም ከዚህ ድርጅት ጋር፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ድርጅት አብሮ ሊሰለፍ አይችልም። እንዲህ ያሉ ድርጅቶች በራሳቸው የተሟሉ ስለሆኑ፤ ከሌሎች ጋር ሊኖራቸው የሚችለው የአጭር ጊዜ ትብብር እንጂ፤ ዘለቄታ ያለው አይደለም።
ወደ ዐማራው ትግል ስመለስ፤ ካሉት ታጋይ ድርጅቶች ሁሉ ልዩ የሚያደርገው፤ ከላይ እንዳሰፈርኩት የሕልውና ትግል መሆኑ ነው። የሕልውና ትግል መሬት የማካለል ጉዳይ አይደለም። የሚታገለው ለርዕዩተ ዓለም የበላይነት፣ በትግሬዎች መንግሥት ሥር ሥልጣን ለመጋራት አይደለም። የትግሬዎች መንግሥት፤ ራሱን በብዙ መልክ መድቦና የተቀያየረ ስም ሠጥቶ በመሰለፍ፤ ዐማራውን እያጠፋ ነው። ራሱን ብዐዴን ብሎ፤ “የዐማራ ግዛት!” ገዥ አድርጎ በጠፈጠፈው ክልል፤ ዐማራውን እያጠፋ ነው። ራሱን ኦሕዴድ ብሎ፤ “የኦሮሞ ግዛት!” ብሎ በጠፈጠፈው ክልል ገዥ አድርጎ፤ ዐማራውን እያጠፋ ነው። ራሱን ደኢዴን ብሎ፤ “የደቡን ኢትዮጵያ ግዛት!” ብሎ በጠፈጠፈው ክልል ገዥ አድርጎ፤ ዐማራውን እያጠፋ ነው። በሶማሌ ኢትዮጵያ እና በአፋርም እንዲሁ። በቤንሻንጉልና በጋምቤላም እንዲሁ። በአዲስ አበባም እንዲሁ። ዐማራው በደል እየደረሰበት ያለው በመላ ኢትዮጵያ ነው። ይህ ደግሞ ሀገሩና መኖሪያው ነው። እየተደረገ ያለው የዘር ማጽዳት ሂደት ነው። ይሄን መታገል ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው። እናም የዐማራው መደራጀት ከዚህ የመነጨ ነው።
ይህ የዐማራው በማንነት የተነሳ በደልን መታገል፤ የመላ ኢትዮጵያዊያን ትግል ሊሆን ይገባዋል። አኙዋኩ፣ ኦሮሞው፣ አፋሩ፣ ኦጋዴኑ፣ ይህ እየደረሰበት ነው። ስለሆነም፤ ወደ አንድ ለመምጣት፤ ምክክሩ አሁን መጀመር አለበት። የምክክሩ መነሻ ደግሞ፤ ከላይ ያሰፍርኳቸው ነጥቦች መሆን ይገባቸዋል። ይህ ነው ሀገር አድን ንቅናቄ መሠረቱ። ለአጭር ጉዞና መሰላል ለማድረግ የሚታሰበው ሂደት፤ ሀገርን የከፋ አደጋ ላይ የሚጥልና፤ የነገ ረመጥን በግር ሥር የሚቀብር ነው። በርግጥ ኢትዮጵያን ለማዳን፤ አብሮ መታገልና አብሮ ድል ማድረግ ተገቢ ነው። ነገር ግን፤ የአብሮነቱ መሠረት፤ የጋራ የሆነ አንድ የሚያደርገን ጉዳይ በግልጽ መቀመጥ አለበት። በድጋሜ፤ የትግሬዎቹን መንግሥት መጥላት ብቻውን በቂ አይደለም። ሁሉም የራሱን ሰንደቅ ዓላማ አነግቦ፣ የራሱን ክልል አማክሎ፣ የራሱን አጀንዳ በኪሱ ይዞ የሚደረግ ጉዞ፤ አጋርነት ሳይሆን መፎካከርና አድብቶ ለመመታታት መዘጋጀት ነው።