United Ethiopian Muslims Movement (UEMM)

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት (ኢሙንሕ)

4324 Georgia Avenue NW – Washington, DC 20011     uemm2017@gmail.com

 

October 25, 2017

መድፍ ጠምዶ ሣንጃ ወድሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ፍርሃት፣ የሰቀቀንና የሽብር ከበሮ ለ26 ዓመታት ሲያስጎስም የነበረው የወያኔ አምባ ገነን ሥርዓት ፀሓይ እየጠለቀበት መሆኑን የሚያበስሩ ብዙ ተጨባጭ ምልክቶች እየታዩ ነው። ከአገሪቱ ንዋይ ጀምሮ እስከ ግለሰቦች በሕይወት መኖር አለመኖር የመወሰን ሥልጣን የነበራቸው እነበረከት ስሞዖንና አባዱላ ገመዳ በፓርላማው የጓዳ በር እየሾለኩ ነው። የጠቅላይ ሚንስትሩም የልፊኝ አስከልካይም የአልባሳቱን ቁልፍ ማስረከቡንና ወደ ሃይለማርያም ቤተ መንግሥት እንደማይመለስ ነግሮናል። ለመሆኑ ትናንት ወጣትና ሽማግሌ ሳይለዩ ወገኖቻቸውን በአጋዓዚና በፈዴራል ጥይትና ጨፈቃ ሲያስቀጠቅጡ የነበሩ ሥልጣን አስረከብን ሲሉን በቀላሉ የሚታመኑ ወይም የሚተው ይመስላቸው ይሆን?!

ከዚህ ሥራዓት ግፍ ለመገላገል ሕዝቡ ከፍተኛ የሞትና የሽረት ትንቅንቅ እያደረገ ከግድግዳ ጥግ አሲዟቸው ባለበት ወቅት እንኳ የተካኑበትን ሰይጣናዊ ተልእኮ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ለማሳካት የንፁህ ዜጎች ደም በእርስ በርስ ግጭት እንዲፈስ እያደረጉ ነው። በኦሮሞና በሱማሌ፣ በአፋርና በኦሮሞ እና እንዲሁም  ባለፉት ሁለት ቀናት በኤሊባቡር በአማራና በኦሮሞ ወገኖቻችን መካከል በአካባቢው ካድሬዎቻቸው አማካይነት ከባድ ደም መፋሰስ  እያስከተሉ ነው። ተጋብቶና ተዋልዶ ለረዥም ዘመናት “አንተ ትብስ አንተ” በመባባል ተዛዝኖ፣   በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶና ተከባብሮ አብሮ የኖረው ሕዝብ በወያኔ ካድሬዎችና የሌሎች ሆድ አደሮች የሸምቅ ሥራ ካደገበትና ብዙ ካየበት ቀየው ነቅሎ እንዲፈናቀልና አለመረጋጋት በአካባቢው እንዲሰፍን እየተደረገ ነው።የወያኔ ሥራዓት ጉሮሮውን ካነቀው ሕዝባዊ አመፅ ለመተንፈስ በማሰብ በእንዳንድ አካባቢዎች በሕዝቡ መሃል በጫረው እሳት ምክንያት በለበሱት ልብስ ብቻ ሕፃናት ልጆቻቸውን አንጠልጥለው ጫካ ውስጥ ያለምግብና መጠለያ የተደበቁ ወላጆች ትቂቶች አይደሉም።

በሌላ በኩል ወያኔ በካድሬ በሞላው መጅሊስ አማካይነት በሙስሊሙ ላይ ሰሞኑን ሌላ ግንባር ከፍቷል።   የአዲስ አበባው መጅሊስ የወያኔ መሳሪያ እንጂ የኢትዮጵያን ሙስሊም ሊወክል እንደማይችል የኢትዮጵያ መስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት በተደጋጋሚ መግለጫዎች ማውጣቱ ይታወሳል። መጅሊሱ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ ባለድርሻ ነው ብላችሁ የምታምኑና ደፍራችሁ በሚድያ የተናገራችሁ ሁሉ ሰሞኑን ይኸው መጅሊሳችሁ ኢስላማዊ መፃሕፍትን በጆንያ ቀርቅቦ ለማቃጠል እንደተዘጋጀ እጅከፍንጅ ተይዞላችኋል። ዛሬ የናንተ መልስ ከቶ ምን ይሆን?

እኛ የምናውቀው አንድ አሜሪካዊ ቄስ ነኝ ባይ አንድ ሰሞን ቁርዓንን አቃጥላለሁ ብሎ ሲፎክር እንደነበር እንጂ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ነኝ የሚል ድርጅት ይህን መሰል ኢሃይማኖታዊና ሊሰሙት የሚዘገንን ተግባር ይወጥናል ተብሎ ማነው የሚጠረጠረው? በእርግጥም ይህን የመሰለ ዘግናኝ ተግባር በወያኔ ትእዛዝ በእምነታችን ላይ እየተፈፀመ ከወያኔ ጋር መጠጋት ለሙስሊሙ ይበጃል፣ “ከማያውቁት መልዓክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል” የሚል ሃሳብ የሚያሽከረክሩ ከመካከላችን መገኘታቸው በሙስሊሙ ታሪክ ላይ ጠባሳ ትቶ የሚያልፍ መሆኑ አይቀሬ ነው። የወያኔን ሥራዓት በተገቢው ስሙ ወያኔ ብሎ መጥራት የሚያስፈራችሁ ሁሉ ሃቅን ተቀብላችሁ “አካፋን አካፋ “ ብላችሁ በመጥራት  ራስን ከፍርሃት ነፃ በማድረግ ከወገናችሁ ጎን መቆሚያው ወቅቱ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። አለያ በወያኔ ላይ የተነሳው የሕዝብ የቁጣ ማእበል እናንተንም አብሮ ያሰምጣችኋል፣ ያጥረገርጋችኋል። እየዘመመ አሥራአንደኛው ሰዓት ላይ ባለው የወያኔ ዙፋን ሥር መኮልኮል የወያኔን ያህል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል መገንዘብ ይኖርባችኋል።

ለኢትዮጵያ ሙስሊሞችም ሆነ ለመላው የአገራችን  ሕዝብ መፍትሄው የወያኔ ሥራዓት ያለቅድመሁኔታ ሥልጣኑን ለሕዝብ ማስረከብ ነው። ይህም ሊሆን የሚችለው አሁን ሕዝቡ የተጠመደበት መራራ ትግል ሲገፋ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ብቸኛው አዋጭ ጎዳና ይህን ግፈኛ ሥርዓት ከሚታገሉት ሌሎች ወገኖቹ ጋር ተቀናጅቶ መታገል ብቻ ነው። በዚህ ሂደት “እኛም በሚመስለን መንገድ እንታገላለን” በሚል ብልጠት በወያኔ ላይ ነፍስ የመዝራት ሥራ የሚሠሩትን ከወያኔ ለይቶ አለማየት አማራጭ የለውም።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ባልወከልናቸው ሹመኞች ፊት ቀርበን የመስጊድ ቦታ ለመለመን ማመልከቻ አመላላሽ ላለመሆን መሰረቱን መጣልና ተገቢ ቦታችንን መያዝ መጀመር ያለብን በሕዝባዊው አመፅ ተሳትፎአችን ከሌላው ወገናቸን ጎን ቆመን እስከመጨረሻ ስንገፋበት ብቻ ነው ። የሃገራችንና የወገናችንን የወደፊት እጣ ፋንታ ከሚወስኑት ውስጥ መገኘት የምንችለው ዛሬ ወያኔን ለመገርሰስ በሚደርገው ትግል ሙሉ ተሳታፊ ስንሆን ብቻ ነው። በትግላችን ውሳኔ ከሚሰጡት መካከል እንሆናለን። መርሳት የለለብን የሙስለሙ ሰላማዊ ትግል ዛሬ ከዳር እስከዳር እንደቋያ እሳት የተያያዘው ሕዝባዊ አመፅ መሰረት መሆኑን ነው። እኛ ብቻችንን የጀመርነውን ትግል ከሌሎች ወግኖቻችን ጋር ሆነን የመጨረስ ታሪካዊ ግዴታ አለብን። ላለፉት ሥድስት ዓመታት ባደረግነው ትግልና በከፈልነው ምስዋዕትነት ምክንያት በወርቅ ቀለም የተፃፈ ስማችንን ለምንምና ለማንም ስንል ማጉደፍ የለብንም።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት ለሙስሊሙ ሕብረተስብና ለሌላ እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ሁሉ አምባ ገነኑ የወያኔ ሥርዓት ተገዝግዞ ተገዝግዞ መውደቂያው ስለደረሰ የተቀጣጠለውን የሕዝባዊ አመፅ ይበልጥ በማጧጧፍ ከሥሩ ነቅለን በአንድነት እንድንጥለው ጥሪውን ያቀርባል። እንደገና ባገረሸው ሕዝባዊ አመፅ ሕዝቡ የጭቆና መሳሪያ የሆኑትን የወያኔ ንብረቶች እያወደመ ነው። ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለም ነው። ሕዝቡ የወያኔን መቶ በመቶ መወገድ ግቡ እንዳደረገ የሚያጠያይቅ አይደለም። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረትም ሕዝቡ የመረጠውን አቅጣጫ እንዲገፉበት ለሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ያቀርባል። “ብሔራዊ ጭቆናን” መጣል የሚቻለው በብሔራዊ ትግል ብቻ ነው።

 

በአላህ ፈቃድ ሕዝቡ ድል ይቀዳጃል!

አላሁ አክበር!

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት