ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
ASHRAF SHAZLY

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመንግሥታቸውን አቋም የተመለከተ ማብራሪያ አቅርበዋል፤ ከሕዝብ ተወካዮች ለቀረቡ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ጉዳዮችን ዳስሰዋል። ቀጣዮቹ ነጥቦች በማብራሪያቸው የተነሱ ዐብይ ፍሬ ነገሮችን ይዘረዝራሉ።

1.የባለስልጣናቱ የመልቀቅ ጥያቄ

የአቶ አባዱላ ገመዳ እና የአቶ በረከት ስምዖን የመልቀቂያ ጥያቄዎች መገጣጠም ምንም ግንኙነት የለውም ያሉ ሲሆን፤ አቶ በረከት በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውንና የአሁን ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱን ገልፀዋል።

ከአቶ አባዱላ ገመዳ ጋር ግን ንግግሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን እና ጉዳዩ ያለመቋጨቱን ተናገረዋል።

“መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ እየሰሩ ቢቀጥሉ ደስተኞች ነን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የአቶ አባዱላ የመልቀቂያ ጥያቄ ፓርቲያቸው ስልጣን ላይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ ተከስቶ የማያውቅ ቢሆንም ተጋንኖ ሊታይ አይገባውም ብለዋል።

“እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ሲቀርበቡ ሊገርመን አይገባም፤ መለመድ አለበት” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አቶ አባዱላ ለዓመታት በአፈ ጉባዔነት ከመሩት የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ጉባዔ ሳይገኙ ቀርተዋል።

2.የኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ግጭቶች

በቅርቡ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተፈጠረውና ከመቶ ሺህ በላይ ዜጎችን ያፈናቀለውን ግጭት አስመልክተው ሲናገሩ ግጭቱ ከወሰን ይገባኛል ጥያቄ ይልቅ “በኪራይ ሰብሳቢነት” እንደተሾፈረ እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

“ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲከስቱ የነበሩ ግጭቶች ዋነኛ አመለካከት የተሳሳተ አስተሳሰብ፣ አመለካከት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው” ብለዋል።

የጫት ንግድ፣ የዶላር ጥቁር ገበያ እና የኮንትሮባንድ ንግድ ብሔር ተኮር ቅርፅ መያዙ ለግጭቶቹ ምክንያት ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፀጥታ ኃይሎች ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ሕዝብን ወደ መግደል ያመሩ የልዩ ኃይል አባላት መኖራቸውን አምነው “እነዚህ ሊጠየቁ ይገባል” ብለዋል።

በብዙ የመብት ተከራካሪዎች በርካታ የመብት ጥሰቶችን አድርሷል የሚባለውና የሁለቱን ክልሎች ግጭቶች በመቀስቀስ ወይንም በማማባባስ ሚና እንደነበረው የሚዘገበው ልዩ ፖሊስን በተለየ ከመውቀስ ተቆጥበዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ከምክር ቤቱ አባላት ልዩ ፖሊስ ለምን እንደማይፈርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ፖሊሱ ልዩ ኃይል የሚል ስያሜ ስለተሰጠው ነው የሚለው ስህተት ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም። “መደበኛም ተባለ ልዩ ኃይል በግጭቶቹ ሁለቱም ተሳትፈዋል:: የአመለካከት ችግር ስላለ ነው እንጂ ልዩ ኃይል ስለተባለ አይደለም።”

3.ግጭት አዘጋገብ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል የሚዲያ ተቋማትን እንዲሁም ሌሎች የፌዴራል የብዙሃን መገናኛዎችን የግጭት አዘጋገብ የነቀፉ ሲሆን ዘገባዎች በሚቀርቡበት ጊዜ ቁጥብነት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የማኅበራዊ ሚዲያን ድርሻ መገምገም ቀጣዩ የመንግሥት ኃላፊነት እንደሚሆን ተናግረዋል።

Source    -BBC/AMHARIC