October 26, 2017 05:09

 

 

አቶ ዘርአይ አስገዶም የብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው። የሕወሃት ሰው። ዶር ነጋሪ ሌንጮ ደግሞ፣ የኦህዴድ ሰው ሲሆኑ፣ በአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የተሾሙ የፌዴራል ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር/ቃል አቀባይ ናቸው። የሚኒስትሮችን ምክር ቤትና እነ የፌዴርል መንግስትን ወክለው የሚናገሩ ማለት ነው። ማንኛውም ሜዲያ፣ መንግስትን በተመለክተ ደዉሉ የሚያነጋገረዉን መረጃ የሚጠይቀው የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤትን ነው።

በብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ሕግ ፣ አንቀጽ አራት ንኡስ አንቀጽ 2፣ “ባለስልጣኑ ተጠሪነቱ ለሚኒስትሩ (ለፊዴራል የኮሚኒኬሽን ሚኒስተር) ነው ሲል ይደነግጋል። ይህ ማለት በወረቀት ላይ በተቀመጠው ሕግ መሰረት አቶ ዘርአይ አስገዶም ተጠሪነታቸው ለዶ ነጋሪ ሌንጮ ነው መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

በኢሊባቡር በተከሰተው አሳዛኝ ክስተት ዙሪያ የብዙ ወገኖች ሕይወት በግፍና በጭካኔ በአክራሪዎች ጠፍቷል። የሚሚ ስብሃቱ ዛሚ ራዲዮና ኢ.ኤን.ኤን በነበረው እልቂትና በዜጎች መፈናቀል ላይ ሰፋ ያለ ዘገባ አቀረቡ።

በተለይም የዛሚ ራዲዮ አባዱላ ገመዳ ላይ ትልቅ ዱላ ነበር ያሳረፉት። በነዛሚ ዘገባ ደስተኛ ያልሆኑት የኦህዴድ ባለስልጣናት ኪራይ ሰብሳቢዎች በሚል እነ ዛሚን አወገዙ። ዶር ነጋሪም በኢቢሲ በመቅረብ አንዳንድ ሜዲያዎች ያሏቸውን (እነ ዛሚን መሆኑ ነው) ከሰሱ። የዛሚ ራዲዮ ለዶር ነጋሪና ለአቶ አዲሱ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ ምላሽ ሰጡ። እንደዚህ ልብ ልብ ተሰምቷቸው የፌዴራል መንግስት ቃል አቀባይን እንዲህ የሚያዋርዱት የተማመኑበት ነገር ኖሮ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ለዶር ነጋሪ ተጠሪ የሆኑት አቶ ዘርዓይ አስገዶም በአደባባይ ዶር ነጋሪ የተናገሩት በማጣጣል ለነ ሚሚ ስብሃቱ ድጋፋቸውን የሰጡበትን ሁኔታ ነው እየሰማን ያለነው። “የክቡር ሚኒስትሩ ንግግር የራሳቸው የግል አስተያየት ነው” ያሉት ዶር አቶ ዘርሃይ “ የስጡት አስተያየት ትክክል ይሁን አይሁን። አከብረዋለሁ።ይሁን እንጂ ማንኛውም ሜዲያ በሚያጠፋበት ጊዜ፣ መቼ፣ ማን፣ በማን፣ ለምን እንደሚቀጠ ሕግ አለ። በአዋጅ ሃላፊነት የተሰጣቸው አካላት አሉ። አንዱ ብሮድካስት ባለስልጣና (እርሳቸው መሆናቸው ነው) ነው፡፡ሌላው ፍርድ ቤት።ከዚህ ዉጭ ሜዲያ የመቅጣት ስልጣን ያለው ተቋም የለም” ሲሉ ዶር ነጋሪን “አርፈው ይቀመጡ” ነገር ብለዋቸዋል።

ብዙዎቻችን በኢትዮጵያ ሁለት መንግስት እንዳለ ስንጽፍና ስንናገር ቆይተናል። አንደኛው በአቶ ሃይለማሪያም የሚመራው፣ እነ ዶር ነጋሪ ሌንጮ ያሉበት የመንግስት አካል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከበስተጀርባ ሆኖ አገር እየገዛ ያለው፣ እነ ሃይለማሪያን የወሰኑትን እና የሚናገሩትን የሚሽር፣ ለማንም ተጠያቂ ያልሆነ፣ ሕወሃቶች ብቻ ያሉበት የካሳንሺሱ መንግስት ነው። ይኸው የአንደኛው መንግስት ተወካይ ተናገሩ፤ የሁለተኛው መንግስት ተወካይ በአደባባይ ውድቅ አደረጉት !!!!! እንግዲህ የኦህዴድና የሕወሃት ግንኙነት ይሄን ይመስላል። አቶ ዘራይና ዶር ነጋሪ ያላቸው አይነት።፡በወረቀት አንዱ በላይ ነው፤ በተግባር ግን ተገላቢጦሽ !!!!