ትምህርታዊ ቪድዮ ኮንፈረንስ፤ ኦክቶበር 13፤ 2017

ክፍል ሁለት፤ ፌደራላዊ ነፃ ክፍለሀገራት አስተዳደር ለኢትዮጵያ ጠቃሚነት፤ታሪክን በተመለከተ፤

ዳንኤል ክንዴ

አገራችንን በሚመለከቱ አንዳንድ አንገብጋቢ በሆኑ አርስቶች ላይ እንድንወያይ፤ የክፍለ ሀገራት አስተባባሪ ኮሚቴዎች ይህንን መድረክ ስላዘጋጁልን በበኩሌ ከፍ ያለ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ፣ አገሮች በትክክል ተሰርተው ከሰማይ ወደ ምድር ዱብ አላሉም፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያቶች እዚሁ በምድር ላይ ተፈጥረው ያድጋሉ፣ የሚጠፉም ካሉ ይጠፋሉ፡፡

የኢትዮጵያም አፈጣጠር ከሌሎቹ አገሮች አፈጣጠር ጋር ልዩ ባይሆንም፣ በተወሰኑ መሰሪ በሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካኝነት አፍራሽ የሆነ ልዩ ትኩረት እየተሰጠው ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ የሰው ልጆች የተፈጠሩባት አገር መሆኗ ቀርቶ፣ እንዲያውም ‹‹ኢትዩጵያ የምትባል አገር የተፈጠረችው በ19ኛው መቶኛው ዓመት በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ነበር›› ይሉናል፡፡ ከዛ በፊት ግን የአሁኑ የሰሜንና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረውም ባይ ናቸው፡፡ተንኮለኛ የሆነ መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ ሲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ በማለት ፋንታ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይላሉ።

ከ300 ሚሊዮን በላይ የሆነ ህዝብ የሚኖርበትና ከ350 ያለነሱ ቋንቋዎች የሚነገሩበት አሜርካ እንኳን መሪዎቹ የአሜርካ ህዝቦች አይሉም፡፡ አሜርካ አንድና የማትነጣጠል አገር ናት ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ እንደዚህ ያለ ተንኮለኛ ድርጊት የሚፈፅሙት የኢትዮጵያ ጠላቶች ወኪል የሆኑት ቡድኖች የሚያከናውኑት ተግባር በስራችን ላይ ትልቅ ዕንቅፋት ነው፡፡

1. ለዚህ የተሳሳተ አመለካከት መልስ መስጠቱ ተገቢ ሆኖ ስለታየኝ አጠር አድርጌ ትክክለኛ የሆነውን የኢትዩጵያ ታሪክ አቀርባለሁ -፡

2. ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩትን የመንግስታት ስርዓቶች ለሁለት ከፍዬ የነበራቸውን የአስተዳደር ልዩነት ሸምቀቅ አድርጌ አቀርባለሁ፡-

3. አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በተሳሳተ መንገድ ለትግራይ ክፍለ ሀገር ያወጣውን ፕሮግራም በቀሩት የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ላይ ጭኖ ባቋቋመው የማነቆ የክልል ስርአት ምክንያት ከ26 አመት በኋላ ኢትዮጵያ ‹‹ትኖራለች›› ወይስ ‹‹ትጠፋለች›› በሚል ፈተና ላይ እንድንወድቅ አድርጎናል፡፡

የአንድን የታቀደ ስራ ትክክለኛነት ለማወቅ ከተፈለገ ውጤቱን ብቻ መገንዘቡ በቂ ነው፡፡ ውጤቱ ካልሰራ የቀረበው ሀሳብ ከጅምሩ የተሳሳተ ነበር ማለት ነው፡፡ አልሰራም በተባለው ላይ ሙጥኝ ማለት ደግሞ በምንም መንገድ የአዋቂነት ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ይህንን
ከአጀማመሩ የወደቀ ስርአት፣ ህገ-መንግስቱንና የክልል ስርአቱን ጨምሮ በአዋጅ ማፍረስ ይገባል፡፡

በምትኩ በቀዳሚው ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የነበሩትን ክፍለ ሀገራት ማዕከል ያደረገና ኤርትራንም ከነበራት የአስተዳደር ስርዓት ጋር የሚጣጣም የፌደራል ህገ-መንግስት ቢዘጋጅ ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ ይሆናል ብዩ አምናለሁ፡፡

የተባለው ፌደሬሽን ዜግነትን ያዳብራል፣ የህዝቡን አመለካከት ይለውጣል፣ የአገሪቱን ልማት ያፋጥናል፣ ከኤርትራ ጋር ላለው ችግር መፍትሄ ይጠቁማል፡፡ እንዲሁም ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ጋር ያለውን ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ለማዳበር መንገድን ይጠርጋል ብዮ አምናለሁ ፡፡ ኢትዩጵያ በአውሮፓ ኮሎንያሊስቶች የጥቅም ግጭት የተቆረቆረች አገር ሳትሆን፣ በራሷ የታሪክ ሂደት አማካኝነት የተፈጠረች አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያዊነትም ህዝቡን የሚያቅፍ እንጂ የሚያገል አይደለም፡፡ የስልጣን በሩ ደግሞ ከጭቃ ሹምነት እስከ ንጉስነት ድረስ ክፍት የነበረ ነው፡፡ የፖለቲካ ጨዋታውን ለመጫወት ግን ችሎታን ይጠይቃል፡፡

አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ሸዋን፣ ጎንደርንና አንዳንድ የደቡብ ክፍላትን ማዕከል ያደረገውን የኢትዩጵያን ታሪክ ስንመረምር፣ እንዲሁም በቅርብ ዘመናት ውስጥ ብዙ ኦሮሞዎች ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ስንገነዘብ ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ላይ ከፍተኛ የሆነ እምነት እንዲኖረን ያስገድደናል፡፡

ከአክሱማውያን ዘመን ጀምሮ የትግራይ፣ የአገውና የአማራ ነገስታት ግዛታቸውን እያስፋፉ በሄዱ ቁጥር የተለያዩ ነገዶችን በግዛቶቻቸው ውስጥ ያጠቃልሉ ነበር፡፡

ለምሳሌ በአምደፂዮን ዘመነ መንግስት – ማለት ከ700 ዓመት በፊት – አሁን ኤርትራ የሚባለው አገር፣ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ላስታ፣ ሰቆጣ፣ አማራ፣ ጎጃም፣ ዳሞት፣ ሸዋ፣ ኢፋት፣ ከንባታ፣ ጉራጌ፣ ሐረር፣ ፈታጃር፣ ሀዲያ፣ ዳሮድና ባሌ የኢትዩጵያ አካል ነበሩ፡፡ ከጥቂት አመታት በኋላ ደግሞ በንጉስ ይሳሃቅ ዘመን ዘይላ፣ ሲዳሞ፣ ቦሻ፣ ከፋ፣ እናርያና ጃንጀሮ ተጨመሩ፡፡

በአፄ ዘረያዕቆብ ዘመነ መንግስት ደግሞ ትግራይና አሁን ያለው ኤርትራ አንድ ሆነው በባህረ ነጋሽ እንዲተዳደሩ ተደረገ፡፡ የደቡብ ድንበራቸው የተከዜ ወንዝ እንዲሆን ተወስነ፡፡ በ1445 ዓመተ ምህርት የአፄ ዘረያዕቆብ መንግስት አዳልንና ኦጋዴንን ሲጨምር፤ በሞቃዲሾ ወደብም ኢትዮጵያ መጠቀም ጀመረች፡፡

በህዝብ ግንኙነት በኩል ብንሄድ ደግሞ፣ እንኳንስ ተራው ህዝብ፣ ንጉሶቹ እንኳን ሳይቀሩ ጋብቻቸውን ከአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ነገዶች ከሆኑት ጋር ብቻ አልነበረም ፡፡ የአምደፅዩን ባለቤት ከሃማሴን፣ የንጉስ ይስሃቅ ባለቤት ከጎንደር፤ የዘረያዕቆብ ባለቤት ከሃድያ፣ የሠርፀ ድንግል ባለቤት ከፈላሻ፣ የሱሲኒዮስ ባለቤት ከኦሮሞ፣ የአፄ ቴውድሮስ ባለቤት ከኦሮሞ፣ የአፄ ዩሐንስ 4ኛው ባለቤት ከአፋር፣ የአፄ ምኒልክ እናት ወላሞ፣ የአፄ ኃይለስላሴ ትውልድ ከትግሬ፣ጉራጌ፣ አማራ፣ኦሮሞ ሲሆን፣ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማሪያም ደግሞ ኦሮሞና ሌላም ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

የሰሜኑ ክፍለ ሀገር ከደቡቡ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረውም ከተባለ፤ እንዴት ብሎ ነው ሸዋን ማዕከል ያደረጉ የኢትዮጵያ ንጉሶች አገር ሊመሩ የቻሉት? ይህንን በተመለከተ ይኩኖ አምላክ (1270-1285)፣ አምደፂዮን(1314-1344)፣ ዳዊት(1384-1411)፣ ይስሃቅ(1414-1429)፣ ዘረያዕቆብ (1434-1468)፣ ልብነድንግል(1501-1540)፣ ገላውዲዮስ (1540-1559) እና ሚናስ (1559-1563) ሰሜንና ደቡብ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ናቸው፡፡ ንጉስ ላሊበለ ዝቋላን በ1106 ዓመተ ምህረት ጎብኝተው ነበር፡፡
ለመሆኑ እንዴት ብሎ ነው ከላሊበላ 1609 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው ባሌ ጎባ ውስጥ ከድንጋይ የተጠረበ ቤተክርስቲያን አሁን ድረስ ቆሞ የሚታየው? ላሊበላ ካሉት ቤተክርስቲያናት በአሰራሩ አንድ አይነት ነው፡፡ ማን ሰራው?

በ12ኛው መቶኛ አመት የተሰራ ከድንጋይ የተጠረበ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን፤ እንዲሁም ዋሻ ሚካኤልና እንጦጦ መካከል ተቆፍሮ የተገኘውን ከተማ ማን ሰራው? ደብረሊባኖስ፣ መናገሻ፣ ተጉለትና ዝቋላ ላይ የሚገኙትን ገዳማትና ቤተክርስቲያናት ማን ሰራቸው?

በ12ኛው መቶኛ አመት የተሰራውን አሁን ድረስ የሚያገለግለውን በደቡብ አዋሽ የሚገኘውን የአዳዲ ማሪያም ማን ሰራው? ከፋ ውስጥ ባሃ ላይ የሚገኘውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ማን ሰራው?

ይኸ ሁሉ የሆነው ቱርኮች የኢትዮጵያን ወደቦች ለ300 ዓመታት በቁጥጥራቸው ስር ከማድረጋቸው በፊት ነበር፡፡ የግራኝ መሀመድ ጦር በቱርኮችና በአረቦች ዕርዳታ ኢትዮጵያን ወሮ ለ15 ዓመታት እንዳልነበረች አድርጎ ከማጥፋቱ በፊት ሲሆን፣ እንዲሁም ሶማሌዎችና ኦሮሞዎች በግጦሽ መሬት ባለቤትነት ተጣልተው ባካሄዱት ጦርነት የተነሳ፤ ሶማሌዎች ስላሸነፉና ተሸናፊዎችን ወደ ኢትዮጵያ ስለገፏቸው፣ የባሬንቱ እና የቦረና ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን ወረው በጦርነት የተዳከመውን ህዝብ እያጠቁ፣ መሬቱን እየቀሙ ለ200 ዓመታት እያንገላቱ፣ የነበሩትን ቦታዎች ስማቸውን በመቀየር የኦሮሞ ስም በመስጠት በጠቅላላ በኢትዮጵያ ከመስፋፋታቸው በፊት ነበር፡፡

በዚህ ጊዜ የሰሜንና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ግንኙት ተቋርጦ ነበር፡፡ ስለሆነም፣ ቆየት ብሎ ግንኝነቱ ቀጠለ፡፡ ህዝቡ በልዩ ልዩ ምክንያት የተነሳ እየተጋባና እየተዋለደ አብሮ መኖር ሲጀምር፣ ግለሰቦች እራሳቸውን ከተወለዱበት መንደር፣ ወረዳ፣ አውራጃ ወይንም ክፍለ ሀገር ጋር ማቆራኘት ጀመሩ፡፡

ትግራይ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ሲዳሞ፣ ሐረር፣ ባሌ፣ ወለጋ ወ.ዘ.ተ የተባሉት ክፍለ ሀገራት የራሳቸው የሆነ ታሪክ ስላላቸው የዜጎቻቸው ማንነት መገለጫ ሆኑ፡፡ የአገሪቱ ጦር የኢትዮጵያን መልክ እንዲያንፀባርቅ ሆኖ የተደራጀው በአምደፂዮን ዘመነ መንግስት ነበር፡፡ ስለዚህ ወታደሩ ለጦርነት እንኳ ሲሄድ በጦር አለቃው አማካኝነት ተሰልፎ የጎጃም ጦር፣ የሲዳሞ ጦር፣ የሐረር ጦር፣ የወለጋ ጦር፣ የሸዋ ጦር እየተባለ ነበር የሚዘምተው፡፡ ከዚህም ሁናቴ ክፍላተ ሀገራት ቆየት ያለ ታሪክ እንዳላቸው ለመረዳት እንችላለን፡፡

በኢትዮጵያ የነበሩት ሁለት አይነት የመንግስት አስተዳደሮች፤ 1ኛው፣ በአስተዳደር ማዕከላዊነት አጥብቆ የሚያምን ሲሆን፣ 2ተኛው ደግሞ የሀገሪቱን ስፋትና በመገናኛ በኩል የነበረውን እንቅፋት በመገንዘብ አስተዳደሩን ለቀቅ በማድረግ የሚያምን ነበር፡፡ በወታደሩ ላይ የነበረውን ሸክም በመረዳት፣ ኃላፊዎችን ከማዕከሉ በመላክ ፋንታ በአገሬው ሹማምንት እንዲተዳደር ያደርግ ነበር፡፡

በማዕከላዊነት ከሚያምኑት መሪዎች ውስጥ አምደፂዮን፣ ዘረያቆብ፣ አዲያምሰገድ እያሱ፣ አፄ ቴውድሮስ፣ አፄ ምኒልክ፣ አፄ ኃይለስላሴና ደርግ ይገኙበታል፡፡አስተዳደሩ ለቀቅ ይበል ከሚሉት ውስጥ ደግሞ የዘረያዕቆብ ልጅ በዕደማሪያም፤ እንዲሁም ሱስንዮስ እና አፄ ዮሐንስ 4ኛው ይገኙበታል፡፡

በኢትዩጵያ ታሪክ ውስጥ ለብዙ አመታት በስልጣን ላይ የቆየው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ስለነበረና ብዙ የታሪክ አሻራ ጥሎ ስላለፈ ስለዚህ መንግስት አስተዳደር መነጋገሩ ተገቢ ነው፡፡
በቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት የአስተዳደር ማዕከልነት የገነነበት ጊዜ ነበር፡፡ የተለያዩ ህገመንግስታት ወጥተው ነበር፡፡ ሆኖም ስርአቱ ለህዝቡ የሰጠው የመምረጥ መብት ቢኖርም፣ ለህዝቡ የቀረበ ምርጫ ግን አልነበረም፡፡

አስራ ሶስት ክፍለ ሀገራት ቢቋቋሙም የውስጥ አስተዳደራቸው አንድ አይነት ነበር፡፡ ከማዕከሉ የሚተላለፈውን ትዕዛዝ መፈፀም ብቻ ነበር፡፡ የሚሾሙት አስተዳዳሪዎች ከተሰጣቸው መመሪያ ውጪ የሚፈፅሙት ህዝብ ነክ ተግባር አልነበረም፡፡

የኤርትራ ፌደረሼን በዲሞክራቲክ አሰራር ላይ የተመሰረተ ስለነበር፣ ብዙ ኢትዮጵያውያንና የመንግስት ባለስልጣናት ክፍለ ሃገሮቹን፤ ኤርትራን ሞዴል ባደረገ የፌደሬሽን ስርዓት ለማዋቀር ምኞት ነበራቸው፡፡

ከባለስልጣኖቹም መካከል ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ፣ ልጅ ይልማ ደሬሳ፣ ብላታ ግርማቸው ተክለሃዋሪያት፣ ጀኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጀኔራል ከበደ ገብሬ እና ጀኔራል አማን አንዶምን ለመጥቀስ ይቻላል፡፡

ስለሆነም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ስልጣናቸውን በምንም መንገድ ለማካፈል ወይንም ለማጋራት ፍላጎት ያልነበራቸው መሪ ስለነበሩ የኤርትራ ፌደሬሽን ለቀሩት ክፍለ ሀገራት ሞዴል መሆኑ ቀርቶ ከነጭራሹ ኤርትራ የኢትዩጵያ 14ኛ ክፍለ ሀገር እንድትሆን ተወሰነ፡፡

ደርግ የዘውዱን ስርዓት ቢሽርም፣ ያስተዳደር መዋቅሩን ግን ለመጀመሪያ ዐመታት አለወጠም፡፡ የክፍለ ሀገራቱ አስተዳደሪዎች ከማዕከሉ የሚተላለፍላቸውን ትዕዛዛት ማስፈፀም ብቻ ነበር፡፡ በ1987 ዓ.ም የወጣው ህገ-መንግስት ኢትዮጵያን አህዳዊ አገር አድርጎ ክፍለ ሀገሮችን በአውራጃዎች ከፋፍሎ፣ ጥቂት “ራስ ገዥ” የሆኑ አስተዳደሮች ተቋቁመው ነበር፡፡

የትግራይን ክፍለ ሀገርና በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ለያይተን ማየት መቻል አለብን፡፡ ትግራይ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ስልጣኔ የተወለደባት ክፈለ ሀገራችን ናት፡፡ ለኢትዩጵያ ነፃነትና ዕድገት የትግራይ ህዝብ ይህ ነው የማይባል መስዋትነት የከፈለ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ሊያጠፋ የመጡ እንደ ግብፅና ጣሊያን የመሰሉት ወራሪዎችንም በመቋቋም ረገድ የትግራይ መሬት የጦር አውድማ ሆኖ እንደነበር በምንም መንገድ ልንዘነጋ አይገባም፡፡

ባንፃሩ አገር እንመራለን ብለው ስልጣን የያዙት ግለሰቦች ግን የኢትዮጵያን ሕዝብና ታሪክ እንኳ የሚያውቁ አይመስልም፡፡ የሚያነቃንቃቸው ለህዝቡ ያላቸው ንቀትና ጥላቻ ነው፡፡ ያለፉት መንግስታት ከሰሩት ውስጥ ጠቃሚ የሆነውን እንኳ እየመረጡ አገር መገንባት ሲቻል፣ ስራቸው አገር ማፈራረስ ነው፡፡ ህዝቡን አንድ የሚያደርገውን ሁሉ እያጣጣሉ፣ የሚያተኩሩት ሕዝቡን በሚበታትን ስራ ላይ ነው፡፡ አገራዊነትን አጥፍተው በጎሳ ፖለቲካ እንዲተካ ይፈልጋሉ፡፡ ይሄን ሁሉ የሚሰሩት በሕዝብ በኩል ተቀባይነት ስለሌላቸው የስልጣናቸውን ዘመን ለማራዘም ብቻ ነው፡፡

ሶቪየት ህብረትን፣ ይጎዝላቪያንና ቼኮዝሎቫክያን ያጠፋው ስርዓት ለኢትዮጵያ ይሰራል ብለው አሁንም ያምናሉ፡፡ ይሄም የማሰብ ችሎታቸው ምን ደራጃ ላይ እንደደረሰ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ታዋቂ ምሁራን እንደ እነ ፕሮፌሰር እሸቱ ጮሌና፣ ፕሮፌሰር አስመላሽ በየነ የተካፈሉበት በደርግ ተቋቁሞ የነበረው የብሄረሰቦች ኢንስቲቲዩት፤ ብዙ ጥናት ካደረገ በኃላ የደረሰበት መደምደሚያ እንዲህ ይላል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 580 ወረዳዎች ውስጥ አንድ ቋንቋ የሚናገሩት 30 (5 በመቶ )ብቻ ናቸው፡፡ የቀሩት 530ዎቹ ወይም 95 በመቶ የሚሆኑት ግን ልዩ ልዩ የሆኑ ቋንቋዎችን የሚናገሩባቸው ወራዳዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ቋንቋን መነሻ አድርጎ መከለል ትርጉም የለውም፡፡
በስልጣን ላይ ተቀምጦ እስካሁን ድረስ ራሱን የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው ድርጅት ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ድረስ›› መመሪያዬ ነው ይላል፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት እንታገላለን ያሉትን ሁሉ መድረኩን ነፍጎ ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን የሚሉትን ሁሉ አሰባስቦ የክልል ፖለቲካውን ጀመረ፡፡

ስለሆነም የክልሎቹ ስፋትና መጠን የተወሰነው ራሱን የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ነኝ በሚለው ድርጅት ማዕከልነት ነበር፡፡ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንደሚባለው ሁሉ 30 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን መሬት “ኦሮሚያ” ብሎ ለሰየመው ክልል አደለ፡፡

በማናቀው ምክንያት ሰፊ የሚሆነው የደቡብና የምዕራብ ኢትዮጵያ መሬት፣ እንዲሁም የወሎ፣ የጎጃምና የሸዋ መሬት በዚሁ ክልል ውስጥ እንዲጠቃለል ተደረገ፡፡ ከኦሮሞ አመጣጥና ታሪክ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለውን አዲስ አበባን እንኳ ሳይቀር ‹‹ፊንፊኔ›› የሚል ስም ሰጠ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚባሉ ለም መሬቶች፣ የደን ሃብቶች፣ የከብት ዕርባታ፣ የቡና፣ ሻይ፣ ጥጥ፣ የልዩ ልዩ ጥራ ጥሬ የእርሻ መሬቶች፣ ማዕድናትና የመብራት ሃይል ማመንጫ ትላልቅ ግድቦች ሳይቀሩ በዚሁ ክልል ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ አለባብሰው ቢያርሱ በዓረም ይመለሱ ይላል የሀገሬ ሰው፡፡ ጊዜ እያየ የሚፈነዳ ታላቅ ቦንብ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀብሮ ይገኛል፡፡ ይህንን ቦንብ ጊዜ ሳይወስድ ተባብረን ማምከን ይኖርብናል፡፡

በእንደዚህ ያለ በልጅ እና በጡት ልጅ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት ሰላምና ዕድገት ሊገኝ አይቻልም፡፡ ፌደሬሽን የሚሰራው አባሎቹ በመሬት ስፋት፣ በህዝብ ብዛት፣ ባላቸው የተፈጥሮ ሃብት ተመጣጣኝነትና አንዱን ከሌላው አስተሳስሮ በጋራ የሚበለፅጉበት ሁናቴ ሲፈጠር ነው፡፡ የድሮ ክፍላተ ሀገራት ከሞላ ጎደል ይህንን ያሟላሉ፡፡ ወደ ነበሩት ክፍለ ሀገራት መመለሱ የሚያዋጣ ይሆኗል፡፡ ይህንን በሚመለከት ሲዳሞ፣ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃምና ጎንደር ህብረት በመፍጠር ትክክለኛውን ዕርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ አርሲና ሐረር በቅርብ ቀን አባል ይሆናሉ ተብሏል፡፡ ስለዚህ እንደ ትግራይ፣ ወለጋና ሌሎችም ክፍለ ሀገራት ቶሎ ቢደራጁ የተባለውን ህገ-መንግስት የማርቀቁን ስራ መጀመር ይቻላል፡፡ ሌሎች መከናወን ያለባቸው ተግባሮች አሉ፡፡ እነዚህን በተመለከተ በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ ለማቅረብ ስለምፈልግ በዚህ አቆማለው፡፡ በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለው፡

October 25, 2017