(ጥቅምት 15, 2010 , ኦስሎ )
ከሁለት ዓመት በፊት በኢህአዴግና በተቃዋሚ ቡድኖች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ክርክሮች ከሞላ ጎደለ በዴሞክራሲ ፍትህና ልማት ዙሪያ ያጠነጠኑ ነበሩ። አሁን አሁን ግን ፖለቲካችን መጀመሪያውም መጨረሻውም የማንነት ፖለቲካ ሆኗል። እንድዚህ ዓይነት የፖለቲካ አካሄድ ከ40 ዓመት በፊት ማርክሲዝምን እንደ ሃይማኖት በተቀበሉ ተማሪዎች የተጀመረና በገዥው ፓርቲም እንደ ብቸኛ ማደራጃና ማታገያ መንገድ የተያዘ ከመሆኑ አንጻር አሁን ያለንበት ቀውስ ብዙዎችን አያስገርምም። ምናልባትም እንደ ትንቢት እያንዳንዱ ነገር ከታቀደለት ጊዜ ሁሉ ቀድሞ እየተደረገ ያለ ነው የሚመስለው። ከዋናው ብሄርን ብቻ ያማከለ ፌደራሊዝም ከማቋቋም እሰክ ግለሰቦችን መኪኖችንና የንግድ ተቋማትን ሳይቀር በብሄር ማንነታቸው እንዲገለጹ በማድረግ በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል። እንዲያውም በህዝቡ መካከል ለብዙ ዘመናት የዳበረ አብሮ የመኖር ባህል ጠብቆን እንጅ እንደ መንግስታችን ስራማ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁንም በሰላም ባልቆየን ነበር። ለሁልም ልክ አለውና ህዝቡም ለ26 ዓመታት በኢህአዴግና በአክራሪ ብሄርተኛ ተቃዋሚዎች ተገፍቶ ተገፍቶ የብሄር ካርዱን በእየ አጋጣሚው እንዲመዝ ተደርጓል። የሰለጠኑ ህብረ ብሄራዊ የሆኑ አገሮች በብሄር የተደራጀ ፖለቲካል በህግ እስከመከልከል የደረሱት መጨረሻው እንደማያምርና በዚህ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንደማይቻል ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው።

እስክ ቅርስብ ጊዜ ድረስ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ስልጣን የያዘ ቡድን ህዝቡን ይጨቁናል ውይንም የሆነ ብሄር በተለየ ተበድሏል የሚል ወቀሳ እንጂ አንዱ በአንዱ ላይ ጥቃት ያደረሰው በኢህአ ዴግ ዘመን የብሄሮችን መብት አስከብረናል እየተባለ በሚደሰኮርበት ጊዜ ነው። ወይንስ እርስ በ እርስ የመናከስ መብትን ነው እንዴ ያጎናጸፉን? በብሄሮች መካከል ከአሁን በፊትም በአንዳንድ አከባቢዎች ግጭት ነበረ አዲስ ነገር አይደለም ምናልባትም አሁን ሁሉንም ነገር መስማት ስለቻልን ነው እንጂ የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡም አልጠፉም። አዎ ግጭቶች ነበሩ ነገር ግን ግጭቶች መሰረት ያደረጉት የብሄርን ማንነት ሳይሆን አጎራባች አከባቢ የሚገኙ ውሃ፤የግጥሽና የእርሻ መሬት አጠቃቀምን ነው። እንደዚህ ዓይነት ግጭት በአንድ ብሄር አባላት መካከልም ተደጋግሞ ይከሰታል። አሁን የሚያሳስበው የእነዚህ ብሄር ተኮር ግጭቶች መደጋገም
እንደተለመደ ነገር ተወስዶ ወደ መፍትሄ የሚኬድበትን መንገድ ጭምር እንዳያጨልመው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የችግሩ መንስኤ (ብሄርን ብቻ ያማከለ ፖለቲካው) መፍትሄ ፍለጋው ለይም ተጽኖ መፍጠሩ ነው። ለምሳሌ አንዱ ቡድን በብሄር ማንነቱ ብቻ ጥቃት ሲደርስበት የሌሎች ዝምታን መምረጥና ነግ በእኔ ብሎ ጠንካራ የተባበረ ተቃውሞ እንዳያሰማ አድርጎታል።

በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ጽንፈኛ ብሄረተኞች የብሄር ፌደራሊዝሙ ምን ያክል ህዝቡንና አገሪቱን አደጋ ላይ እንደከተተ እንኳን እያዩ ሁሉንም ነገር ህወሃት ላይ እያላከኩ የብሄር ፖለቲካው ምንም ችግር እንደሌለበት ለማሳየት መሞከራቸው ነው። አወዳይና ኤሊባቡር በተከሰተው ዘግናኝ ድርጊት የህወሃት እጅ እንዳለበት ብዙ ምልክቶች ቢኖሩም በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ ሰዎችንና እንደዚህ አይነት ድርጊት እንዲፈጸም የጥላቻ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ ቡድኖችም እኩል ተጠያቂዎች ናቸው። እንዲያውም የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሄረተኞች አገሪቱ ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ብሄር ተኮር ቀውስ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ጭምር ቢጎዳ እንኳን የእነሱን የወደፊት ዓላማ ለማሳካት የሚከፈል የአጭር ጊዜ መሰዋትነት እንጂ አሳሳቢ ችግር አይደለም። ኦሮሞው በሌላው ብሄር መጠቃቱ ወይንም ሌላው ብሄር ላይ ጥቃት ማድረሱ ለእነሱ ኦሮሞው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ተከባብሮ የመኖር ተስፋው እስከተዳከመ ድረስ የሚፈለግ አካሄድ ነው። ከዚያ ልክ የሃውዜን ጭፍጨፋ (ማንም ያድርገው ማን) የትግራይ ህዝብን ህወሃት መዳፍ ውስጥ መሉ በ ሙሉ እንዳስገባው ሁሉ እነዚህም አዳኝህ እኛ ብቻ ነን በእንደዚህ ያለ ሁኔታ አብሮ መኖርም አይቻልም ብለው ብቅ ይላሉ። ጽንፈኛ ብሄርተኞች እድሉን ካገኙ ከዚህም የባሰ ማድረጋቸው ስለማይቀር የአገርን ህልውና ማዳኑ በኢትዮጵያዊ እኩልነት በሚያምኑ ላይ ብቻ ወድቋል። የአገራችን ህልውና አደጋ ላይ የወደቀው ህወሃት ስልጣን ላይ የወጣ ቀን ቢሆንም አሁን የደረሰችበት ሁኔታ ግን ወደፊት የሚሆነው በማያሻማ መልኩ ሁሉም አይኑን ገልጦ እንዲያይ አድርጓል። በኢትዮጵያዊ እኩልነት የሚያምን በሙሉ ብላቴናው እንዳለው የ አገር ጉዳይ እንዲ ቢሆን ተብሎ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቦ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ አለበት።

ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ይለምልም።