October 27, 2017 06:54

የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ አመራር አባላት በሲሳይአጌና ትኩረት ላይ የሰጡትን ቃለምልልስ በጥሞና አደመጥኩት ። እናም ሃዘን ተሰማኝ ። ታዳሚዎቹ ወያኔ የተንገዳገደ መሆኑንና ሥልጣንም እጃቸው ላይ ሊወድቅ እንደሚችል የተገነዘቡ ቢሆንም፣ አሁን የተፈጠረውና በመባባስም ላይ ያለው ፖለቲካዊ ድቀት ምንጩ ምን እንደሆን የተረዱ አይመስሉም ።

ያሬድ ጥበቡ

ያሬድ ጥበቡ

እኔ እስከሚረዳኝ ድረስ የአሁኑን የፖለቲካ ድቀት አይነተኛ የሚያደርገው የሥርአቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሥልጣናቸው መልቀቅ ነው ። ይህን በዱሮ ማርክሳዊ ትንተና አለባብሶ፣ ሥርአቱ ሊወድቅ ስለሆነ፣ መርከቡ ከመስጠሙ በፊት የሚዘሉ የመጨረሻዎቹ አድርባዮች ድርጊት አድርጎ ዶክተር ብርሃኑ መተንተኑ ገርሞኛል። የፖለቲካ ሀሁ ካለማወቅ የሚመነጭ ጀብደኝነት ይመስላል ። አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ ለማ መገርሳና ዶክተር አቢይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት ካለመረዳት የመነጨ ይመስለኛል ። ይህም በፖለቲካ ጥላቻ ከመጨፈን የሚመጣ ችግር ይመስለኛል ። በእኔ እምነት አንድ መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር፣ የብአዴንና ኦህዴድ አመራሮችና አባላት የሚያስተዳድሩትን ልዩ ሃይልና ፖሊስ ከህዝብ ጋር እንዲተባበር ባይፈቅዱ በነዚህ ክልሎች የሚታየው ህዝባዊ ተቃውሞ በእንጭጩ ይቀጭ ነበር ። የኢአን አመራሮች ይህን ሃቅ ቢረዱ ኖሮ ኦህዴድንና ብአዴንን ተላላኪ፣ አድርባይ ወዘተ በሚሉ ቅፅሎች ባልጠሩዋቸው ነበር ። እነዚህ አመራሮች ለራሳቸው ለመዋሸት ፈቃደኛ ካልሆኑ በስተቀር፣ በኦሮሚያና አማራ ክልል የተነሱትንና ያሉትን ህዝባዊ ተቃውሞዎች ራሳቸው እንዳልመሩዋቸውና እንዳላደራጁዋቸው ያውቃሉ። ይህም እውነት ከሆነ፣ ለዚህ አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሃገራዊና ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ሃይሎችንና የማህበራዊ ሚዲያ የጎበዝ አለቆችን እንደማመስገን፣ ማውገዝን የመረጡም ይመስላል ።

በተለይ ብርሃኑ የማህበራዊ ሚዲያ ጎበዛዝትን ለምን ግንቦት 7 ከኦጋዴን ድርጅት ጋር በተናጠል ያደረገውን ስምምነት ተቻችሁ፣ ለምንስ ኦዴግ ከወያኔ ጋር ለመደራደር ካርቱም ሄደ ብላችሁ ፃፋችሁ በማለት፣ የህፃን ፖለቲካ ብሎ እስከማንቋሸሽ ደርሷል። በሚዲያ ነፃነት አይን ሳየው በሁለቱም ጉዳዮች ላይ የተነሱት ትችቶች ተገቢና ብርሃኑ እታገልለታለሁ ከሚለው የዴሞክራሲ መብት ጋር የተቆራኙ ናቸው ። የወያኔ የፖሊትቢሮ አባል የነበረው ሙሉጌታ ጫልቱ የተገኘበት ስብሰባ ላይ አቶ ሌንጮ ሲገኝ ፣ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ድረስ ሄዶ መመለሱ ስለሚታወቅ፣ ያ ለጥርጣሬ በር ቢከፍትና መነጋገሪያ ጉዳይ ቢሆን፣ ይህን በበጎ አይን እንደማየት፣ አገራዊ ንቅናቄውን ለማዳከም እንደተደረገ አድርጎ መተርጎም ከአምባገነናዊ አስተሳሰብ የሚመነጭ ችግር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሊታረምም ይገባል። ከዛሬ እንዲህ ከተባለ ነገ ሥልጣን ሲያዝ፣ ሌላ ዙር የአምባገነንነት አዙሪት እንደማይቀጥል ምን መተማመኛ አለን? ለዚህም ነበር፣ ኢሳትን ካሁኑ የመፃኢቱ ኢትዮጵያ ሚዲያ ተምሳሌት አድርጉት፣ የድርጅት አፈቀላጤ አይሁን ብለን ስንወተውት የከረምነው ።

በተረፈ፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ሲጀምር የጠየቀውን የአማራ ድርጅቶች በአገራዊ ንቅናቄው አለመካተት ጉዳይ መልስ ሳያገኝበትም ሆነ ሳይገፋበት መተው ግር የሚል ነበር ። መሃል ላይ ቪዲዮ ስትሪሙ ሲቋረጥ አምልጦኝ እንደሆን እንጃ፣ ግን የተመለሰ አይመስለኝም ። የአገራዊ ንቅናቄው ጉድለት ሆኖ የሚታየው አንዱ ጉዳይ ሁለቱን ታላለቅ ክልሎች እወክላለሁ የሚሉ የአማራና ትግራይ ታጋዮች የሌሉበት መሆኑ ነው ። እነ ዶክተር አረጋዊ በርሄንና ግደይን የመሰሉ ሰዎች በስደት ላይ ተደራጅተው እየታገሉ ባሉበት ሁኔታ፣ እነሱን ለማካተት ሳይሞከር ስለሽግግር ማውራት ግር የሚል ጉዳይ ነው ። ሁለቱን የኢህአፖ ድርጅቶችና መኢሶንን ሳያካትቱ ስለ ሽግግር ማውራት ባዶነት ነው ። ብዙ መሠራት የሚገባቸው ጉዳዮች ስላሉና ከጊዜ ጋርም ሻሞ ይዞ ሊሰባሰብ የሚችለውን ሁሉ ማሰባሰብ ስለሚገባ፣ ስለሽግግር ከማውራት ተቆጥቦ ስለህብረትና ቅንጅት ማሰላሰሉ ተገቢ ሆኖ ተሰምቶኛል ።

በመጨረሻም ዶክተር ብርሃኑ የዲፕሎማሲ ሥራን አስመልክቶ የተናገረው እጅግ ግር የሚል ነው ። በራሳችን ሥራና አቅም እንጂ በፈረንጆቹ ላይ መመካት የለብንም የሚለው መልእክት መሰጠት የነበረበት፣ ግንቦት ሰባት ሲጀመር ከዛሬ ሰምንት አመት በፊት እንጂ ዛሬ ሥርአቱ ተገዝግዞ የዲፕሎማሲ ሥራው ከፍተኛ ትኩረት በሚጠይቅበት ወቅት መሆን አልነበረበትም። ይህ ሰው አይወደንም፣ ወይም ጥጋበኛ ነው አብረነው ልንሰራ አንችልም ብለው ተስፋ እንዲቆርጡበት ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር ያለ አይመስለኝም ። በኢትዮጵያ ድህነትና አደጋ፣ ምእራባውያኑን ገሸሽ ማድረግ አይቻልም፣ አስገድደው ነው በጉዳያችን ጣልቃ የሚገቡት፣ በጥንቃቄ መያዝም ይኖርባቸው ይመስለኛል። ቪዲዮውን አዳምጬ እንደጨረስኩ የተሰማኝን ስሜት፣ እንደወረደ ነው ያቀረብኩት፣ እመለስበት ይሆናል።