October 27, 2017

* በሠላማዊ መንገድ ተቃዉሞ ያሰማ ህዝብ ላይ ግድያ ፈጽሞ ከሕግ ተጠያቂነት ማምለጥ አይቻለም፡፡
* የኢትዮጵያ ህዝብ ሥርዓቱ በሚፈጽመው የማጋጨት ተንኮልና እና ደባ ሳትሰጋ የኦሮሞ እና የአማራ ወንድሞችህ እያደረጉት ካለው የነፃነት ትግል እንድትቀላቀል ጥሪያችን እናቀርብልሀለን::

ከትላንት በስትያ እሮቡ ጥቅምት 15, 2010 ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብ ኦሮሚያ በአምቦ እና በአካባቢው ስኳር ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ተጭኖ ወደ ሌላ አካባቢ መጓዙን በመቃወም በተነሳ ተቃውሞ የፌደራል ፖሊስ እና የአጋዚ ፀጥታ ሀይሎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በወሰዱት የጥቃት እርምጃ 10 ዜጎች ተገድለው ሌሎች 20 ዜጎች መቁሰላቸው ተዘግቧል፡፡

ይህ ተቃውሞ አዲስ ተቃውሞ ሳይሆን የቀድሞው የኦሮሞ ተቃውሞ አካል መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ህዝባችን የመሬት ባለቤትነት መብቱ እንዲከበርለት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ በእውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲተገበርለት፣ በህገ-መንግስቱ የተደነገጉ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች እንድከበሩለት፣ በሠላማዊ ሠልፍ፣ በገበያ አድማ እና በሌሎችም ሠላማዊ የህዝባዊ እምቢተኝነት ዘዴዎችን በመጠቀም ጠይቋል፡፡

እነዚህን ጥያቄዎች ባቀረበባቸው የተቃውሞ ሠልፎች የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱዋቸው እርምጃዎች ሺዎች ተገድለዋል፣ በአስር ሺዎች አካለ ጎደሎ ሆነዋል፡፡ በመቶ ሺዎች ለእሥር ተዳርገዋል፡፡

ይህ መንግስት የወሠደው እርምጃ ህዝቡ ካነሣው መሠረታዊ ጥያቄ በተጨማሪ ሌሎች ጥያቄዎችን በመውለድ ሁኔታውን አወሣስቦታል፡፡ በአሁኑ ግዜ እየተወሰደ ያለው ተጨማሪ ግድያ የህዝቡን በሠላማዊ መንገድ ተቃውሞን የመግለጽ መብት ከማክበር ይልቅ ቀድሞውኑ የነበረውን አሳሳቢ ሁኔታ “ከድጡ ወደ ማጡ” ወይም “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ሆንዋል፡፡

ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ለህዝባችን፣ ለመንግስት አካላት እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚከተለውን ማሳሰብ እንፈልጋለን፡፡

መንግስት ከሕዝቡ ጋር መታረቅ ከፈለገ የመጀመርያው እርምጃ መሆን ያለበት የህዝቡን ጥያቄ በማስተጋባታቸውና የህዝቡን የመብት ትግል በመምራታቸው ብቻ መንግስት እራሱ ለፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ ያደረጋቸውን የፓለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የፖለቲካ እሥረኞች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ መፍታት አለበት፡፡

ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተቃውሞ ሠልፍ በመሣተፋቸው ብቻ ለተገደሉ ዜጎች ፍትህ ይሠጥ፡፡ ሠላማዊ ሠልፈኞችን የገደሉ አካላት በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ፡፡ ለሟች ቤተሰቦች ካሣ ይከፈል፡፡

መሠረታዊ የህዝቡ የመብት፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡

በሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች እና በሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ የሚመሩት ልዩ ሀይል ሚሊሻዎች የድንበር ጥያቄን ሽፋን በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ዜጎች ላይ የሚፈፅሙት ወረራና የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ያዘዙትና የመሩት የህወሀት ጄነራሎች እና የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ፡፡

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈፀሙትን ጭፍጨፋዎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካላት እንዲጣሩ እና ተጠያቂዎች ለፍርድ እንድቀርቡ እንድያደርግ እንጠይቃለን፡፡

የህወሀት ኢህአዴግ መንግስት ሆን ብሎ የሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልል ህዝቦች መካከል ግጭት እንድፈጠር እንዲሁም በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ጠላትነትን ለመፍጠር የጠነሰሰው ሴራ በህዝቦቹ ንቃት ከከሸፈበት በኋላ ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ በተደረጉ ሠልፎች የፀጥታ ጽ/ቤት በርካታ ሠርጎ ገቦችን ያሠማራ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ የእነዚህ ሰርጎች ገቦች ዋና አላማ በኦሮሚያ ከተሞች በሚከናወኑ ሠልፎች በመሣተፍ ሠልፎቹን ወደ ሁከት እንድለወጡ እና ንብረት እንዲወድም ፣ ሠላማዊ ሠልፈኞቹ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር እንዲጋጩ እና የሠልፎቹን አጋጣሚ በመጠቀም በኦሮሚያ የሚኖሩ የሌሎች ብሔሮች ንብረት ላይ ጥቃት በማድረስ የህዝብ ለህዝብ ግጭት ለመቀስቀስ እና የህዝቡን የመብት ጥያቄ ጥላሸት ለመቀባት የታቀደ መሆኑ እውን ነው፡፡

ህወሀት/ኢህአዴግ በ“እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትበተናለች” አባዜ ስለተጠመደ እና የህዝቦች መጋጨትን የሥልጣን ዋስትና አድረጎ ስለወሰደ እጅግ ርካሽ በሆነ ብሔሮች እና ብሔርሰቦች እርስ በእርሳቸው እንዳይተማመኑ፣ እና እንድጋጩ በማድረግ በሥልጣን ለመቆየት ወስኗል፡፡ ይህንንም የማጋጨት ተግባሩን የለት ተለት ተግባሩ በማድረግ የቀጠለበት ስለሆነ አውቃቹ በንቃት እንድትጠባበቁ እና እንድታከሽፉ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በሙሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ እና አገሪቷን በወታደራዊ አገዛዝ ስር ለማስገባት ሆን ብሎ ንብረቶችን ማውደም እና በትላንትናው ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአምቦ ከተማ የፌዴራል ፖሊሶች ተሳቢ መኪናዎችን ያቃጠሉበት ድርጊት ከመንግስት አካላት ያማይጠበቅ ርካሽ ተግባር በመሆኑ በፅኑ እናወግዛለን፡፡

ህወሀት/ኢህአዴግ “ከወደቁ በዋላ መፈራገጥ ለመላላጥ” እንደሚባለው ባለቀ ግዜ አላስፈላጊ ግጭቶችን በመቀስቀስ እና ድራማዎችን በመስራት እድሜውን ለማራዘም ከመጣጣር መራራውን ጽዋ በመጎንጨት የህዝቡን ጥያቄ በመመለስ እና ከተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድኖች ጋር በአስቸኳይ ወደ ንግግር እና ወደ ድርድር እንዲገባ ጥያችንን እናቀርባለን፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ፡ ሥርዓቱ በሚፈጽመው ትንኮሣ፣ እንዲሁም በሚለኩሰው የማጋጨት ተንኮልና ደባ ሳትፈራ እና ሳትሰጋ፣ ሳትሸማቀቅ የኦሮሞ እና የአማራ ወንድሞችህ እያደረጉት ካለው ትግል ጎን እንድትቆም እና የነፃነት ትግሉን እንድትቀላቀል ጥሪያችን እናቀርብልሀለን፡፡