October 27, 2017ቆንጅት ስጦታው

“ቀሪ ንብረታችን ኢትዮጵያችን ናት። ኢትዮጵያችንን እናስብላት አናቁስላት፤ አናድማት፤ አናራቁታት!” ~ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ

አንድ ነገር መጥፎም ጥሩም የሚያደርገው ተጠቃሚው ነው:: እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር፤ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር ኦሪት ዘፍጥረት ስታነብቡ እግዚአብሔር የፈጠረውን በጎ እንደሆነ አየ ይልና ሌላውን ፍጥረት ሲፈጥር ጥሩ ነው ጥሩ ነው እያለ አልፎ ሰውን ሲፈጥር የዛሬውን አያድርገውና እጅግ በጣም ጥሩ አለ ዛሬ መጥቶ ቢያይ ግን እጅግ በጣም መጥፎ የሚል ይመስለኛል በእርግጥ እርሱ እንደኛ አይደለም ተሸካሚ ነውና አይልም።

በእውነት በዚህ ዓለም ላይ መብትና ግዴታ መኖር አለበት ብዬ እላለሁ አሁን የብሔር ብሔረሰቦች መብት የሚለው እሰማለሁ ለመንግስት መጠቆም የምፈልገው ጫፏ ላይ ግዴታ የሚል ቢጨመርና የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ግዴታ ቢባል፤ ሁልግዜ የምናገረው አንድ አባባል አለችኝ “ሰው ምንም መብት ከሌለው ባሪያ ነው፤ ምንም ግዴታ ከሌለው ደግሞ የአእምሮ በሽተኛ ነው!” አሁን የአእምሮ በሽተኛ ታውቃላችሁ ሰርግ የሚጠራው የለም ለቅሶ ቀረህ ብሎ የሚወቅሰውም የለም። ምክንያቱም ግዴታ እንዳንለው ግዴታ የለበትም ባሪያ እንዳንለው መብት የለበትም። እኛ ደግሞ የአእምሮ በሽተኞችም አይደለንም ባሪያዎችም አይደለንም። ስለዚህ መብትና ግዴታ አለ ብዬ አምናለሁ። እንግዲህ በፌስቡካችን ምን እንደሚደረግ ከኔ በላይ እናንተ ታውቁታላችሁ ተጠቃሚ አይደለሁም ተጠቃሚ ያልሆንኩት አያስፈልገኝም ብዬ አይደለም መብራት ስለሌለኝ ነው። እናም መብራት ያላችሁ ተጠቀሙበት ግን እኔ አውሮፓና አሜሪካ ስሔድ ከገንቢነቱ ይልቅ አፍራሽነቱ ነው ብዙ የሚታየው፤ አሁን ለፍቶና ደክሞ ያገኘ ሰውና ለፍቶና ደክሞ ያላገኘ ሰው አወጣጡ እኩል አይደለም። ለፍቶ ያላገኘ ሰው ውስኪ ሊያወርድላችሁ ይችላል እንደውም ውስኪ ቤት ሁሉ ሊከፍትላችሁ ይችላል። ግን ሳያስበው ነውና ያወጣው ነገ ተመልሶ ያለቅሳል ፤ እናም መብትና ግዴታውን የሚያውቅ ትውልድ መፍጠር አለብን። ይቅርታን ብንሰብክ፤ ፍቅርን ብንሰብክ፤ ሕዝቡን ብናግባባው፤ ብናደማምጠው፤ እንደው ረሐቡ ሳያንሰው፤ ጥሙ ሳያንሰው፤ ብርዱ ሳያንሰው፤ ድህነቱ ሳያንሰው፤ የቤት ማጣቱ ሳያንሰው፤ ለዘይት ለስኳር ወረፋ መጠበቁ ሳያንሰው፤ እንደው እውነት ለመናገር ተግባብቶ እንኳን ስቆ እንዳያድር አደረግነው ። ድሮ ቆሎ ቆርጥሞ ቡና ጠጥቶ ጨጓራው እየተላጠ እንኳን እፎይ ብሎ ይተኛ ነበር። ዛሬ ከአውሮፓ ከአሜሪካ የሚፈስሱት መረጃዎች የቡና ስኒ የሚያሰብሩ ናቸው ጀበና የሚያሰብሩ ናቸው። እናም በጣም ከባድ ስራ እየተከናወነ ነው።
የ3000 ዓመት ታሪካችን በሙሉ ገድለን የሚያስፎክሩ ናቸው፡፡ አሁን ሬድዮ ቴሌቪዥን ተመልከቱ በዓል ሲመጣ በተለይም እነዚህ የድልና የአሸናፊነት በዓላት ሲከበሩ ሁልጊዜ ምን ያህል እንደተገደለ ምን ያህል እንደቆሰለ እንለፍፋለን፡፡ እስኪ ደግሞ ምን ያህል እንዳቆሰልን መለፍለፉን አቁመን፤ ገድለን መፎከሩን አቁመን። ሁለተኛውን አማራጭ ደግሞ እንሞክረው እስኪ ቆም ብለን ፍቅርን ሰብከን እንሞክረው፤ ይቅር ተባብለን እንሞክረው።

ባለፈው በየክፍለሐገሩ ትንሽ ግጭት ነበር፤ አሁን ግጭቱ ቆሟል ግን ደግሞ ግጭቱን ከሰዎች ጭንቅላት አጥበው የሚጥሉ የሐይማኖት ሰዎች የታሉ? እውነቱን ለመናገር፤ ሕዝቡ ኪሱ እየተራቆተ፤ እየተራበ መኪና የገዛላቸው ካህናት፤ ጳጳሳት፤ ፓስተሮች ፤ ኡላማዎች ምን ያደርጉለታል? …, በአውሮፓ አንድ ጥያቄ እየተነሳ ነው ይባላል ታውቃላችሁ ፈረንጆቹ የእምነት ተቋሞቻቸውን ላይ ምን ስላደረጉልን ነው ገንዘብ የምናዋጣው? ምን ፈጠሩልን? የሞራል ዝቅጠት፤ የስነ ምግባር ዝቅጠት፤ ባዶነትን ነው ያተረፈልን፤ ታንቀን ብንሞት በጭንቀት ብንታመስ ራሳችንን ስናጠፋ አልደረሱልንም የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው። ስለዚህ አየሩን ተራራውን የሚቋቋም መኪና ከተገዛልን መቀሌ ጎንደር ባህርዳር ቆላ ደጋውን እየወረድን በተለይም እንደየ እምነታችን መስበክ አለብን።

ስለዚህ ጥላቻውን ቆም አድርገን በተለይም ፌስቡክ እጃችን ላይ የወደቀ ሰዎች ጠመንጃውን ያገኛችሁ ሰዎች የት እንደምትቶኩሱ ብታውቁ፤ አንዳንድ ጊዜ ራስ መጠበቂያ የሚሰጠው ራሱን ለሚጠብቅ ሰው ነው። ሰውን እየተኮሰ ለሚገድል የራስ መጠበቂያ አይሰጥም እና ፌስቡክን በትክክል መጠቀም ብንችል? ይቅርታ ብንሰብክበት፤ ብልፅግና ብንሰብክበት፤ እድገትን ብንሰብክበት…..

ዛሬ አይደለም በፓለቲካው መስክ የእምነት ተቋማት ራሱ የጦር ሜዳ ሆኗል ስንት እንባ ይፈሳል፤ ስንት ዋይታ ይሰማል ይሄ እንባ ደግሞ ተጠራቅሞ ተጠራቅሞ አገር ጎርፍ ሆኖ ይወስዳል። የደሐ እንባ ተጠራቅሞ ጎርፍ ይሆናል።

የአክአብ መንግስት የተገለበጠው በአንድ ናቡቴ ደም ነው ሌላ ጥይት ተተኩሶ ቦንብ ፈንድቶበት አይደለም። ኃጢአት አየበዛ፤ ወንጀል እየበዛ፤ ግፍ አየበዛ፤ ጭካኔ አየበዛ፤ አረመኔነት እየበዛ በሔደ ቁጥር ሰዎች ባዷቸውን ይቀራሉ። ይሞታሉ፤ የተሾሙ ይሻራሉ፤ ያገኙ ያጣሉ፤ ጤነኞች ይታመማሉ። እንደው ወገኖቼ በዚህ በፌስቡክ የተሰማራችሁ እንደው ሌላው የበሰለ ነገር ለመናገር አይደለም። እንደው አስበን ብንናገር ብንፅፍ፤ እኛ ሐገር ኔትወርክ ውድ ነው ታውቃላችሁ የኛ አገር ሰው ምን ያህል ዋጋ ከፍሎ ጊዜውን ሰውቶ ገንዘቡን ከስክሶ እንደሚያነብላችሁ ማወቅ አለባችሁ። አንድ ቪድዮ ባዳመጠ ቁጥር ቴሌ ላፍ ያደርገዋል ኪሱን ያራቁትበታል። ይሄን መስዋእትነት ከፍሎ ፤ ሻይ አልጠጣም ብሎ እናንተ እያዳመጠ ያለ ነውና ከሻይ የበለጠ ልብ የሚይዝ ነገር አእምሮን የሚያሯቁት ነገር ባትፅፉለት እንደውም ምርጥ ፅሁፍ ካጣችሁ ዝም ብትሉ፤ እውነቴን ነው የሚፃፍ ሲጠፋ እኮ ዝም ይባላል። አንዳንድ ሰው ይገርማችኋል እጁ ላይ ስላለ ብቻ መፃፍ ስለቻለ ብቻ የሚፅፍ ሰው ያጋጥመናል።

እንደው በእግዚአብሔር ስም፤ በአላህ ስምም ካላችሁ በአላህ እንደው በሁሉም ስም በምታመልኩት አምላክ ስም ይሁንባችሁ ፌስቡክ እጃችሁ ላይ የወደቀ ሰዎች እዘኑለት።

እንደው እባካችሁ ገንቡን፤ አንጹን፤ አፋቅሩን፤ ደሙን አድርቁት፤ ጥላቻውን አድርቁት፤ ይቅርታ ይሰበክ፤ ፍቅር ይሰበክ፤ እንግባባ፤ እንደማመጥ፤ አንተላለቅ ማንም የለ ማንም ሊኖር አይችልም። በእውነት ምናልባት ዛሬ የምንነጋገራቸው ንግግሮች የዛሬ 10 እና 15 ዓመት እንደ ፀበል ይፈለጉ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

በቀደም አንድ ወንድማችን አንድ ነገር እየነገረኝ ነበር አንድ ጭፈራ ቤት ገባን አለ፤ አንድ ጥናት ያደርጋልና ሊቀርፅ ነው። እዛ ጭፈራ ውስጥ የሆነ አካባቢ ዘፈን እንዳይዘፈን ተባለ በእውነት ቤቴ ገብቼ አለቀስኩ። ለምን ዘፈኑ ቀረ ብዬ አይደለም እንኳን ቀረ የቀረበት ምክንያት ግን ያሳስበኛል። የታገደበት ምክንያት ያሳስበኛል።

ስለዚህ ወገኖቼ ይቅርታ ይቅርታ ይቅርታ አስፈላጊ ነው። ከድጃም ወለተማርያምም ከሳውዲ አረቢያ ተባርረው መጥተዋል። እነ ከድጃ እስላም ስለሆኑ ሳውዲ አረቢያ ይቅሩ አልተባለም ቀሪ ንብረታችን ኢትዮጵያችን ናት። ለወልደማርያም ቀሪ ንብረቱ ኢትዮጵያችን ናት ፤ ለመንግስትም፤ ለደጋፊም፤ ለተቃዋሚም ኢትዮጵያችን ናት። ኢትዮጵያችንን እናስብላት አናቁስላት፤ አናድማት፤ አናራቁታት። መሬቷ ድንግል ነው አስተሳሰባችን ድንግል ነው። ግን መሬቱ ሲለማ እኛ ባዶ ሆነን መሬቱ የሚጠቀምበት አጥቶ ጠላቶቻችን እንዳይጠቀሙበት በጣም ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።